የሰው ልጅ በዚህች ዓለም መኖር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ አብዛኛውን ኑሮውን ያሳለፈው በህብረትና በጋራ መንፈስ ላይ ተመስርቶ ነው። በዚህም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቹን ፈትቷል። የትስስር ታሪኩ እንደ ወቅቱ የተለያዩ ዓይነት ይዘትና አቀራረብ ሊኖረው ይችላል እንጂ የሰው ልጅና በህብረት ሠርቶ መኖር ተለያይተው አያውቁም።
እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ የህብረት ሥራ እንቅስቃሴ በተደራጀ፤ ዘለቄታ ባለውና ዘመናዊ አሠራሩን በተከተለ መልኩ የሚፈፀም አልነበረም። ምስጋና ለእንግሊዛውያኑ ሮበርት ኦውንና ዊልያም ኪንግ እንዲሁም ለፈረንሳዊው ቻርለስ ፎሪየር ይደርስና ይህ ታሪክ ሊለወጥ ችሏል። እነዚህ የኢኮኖሚ ምሁራን በጽሑፎቻቸው በተለያዩ መድረኮች በሚያደርጓቸው ክርክሮችና ቅስቀሳዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የህብረት ሥራ እንቅስቃሴና አስተሳሳብ እንዲፈጠር አስችለዋል።
በተለይ ከኢንዱስትሪ አብዮት በኋላ በህብረት ሥራ የመደራጀት ፍላጎትና ጥያቄ እየተጠናከረ እ.ኤ.አ በ 1884 የመጀመያው የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበር በእንግሊዝ አገር ሮችዴል በምትባል ከተማ ለመቋቋም በቅቷል። ይህን ፋና ወጊ ማህበርም ህብረት ሥራ ማህበራት በአውሮፓና በአሜሪካ እንዲስፋፉ መንገድ ከፍቷል። የህብረት ሥራ ህግ እኤአ 1852 አውጥቶ ተግባራዊ በማድረግ ረገድም እንግሊዝ ግንባር ቀደም መሆኗን የታሪክ ድርሳናት ያመላክታሉ።
በአፍሪካም ዘመናዊ የህብረት ሥራ እንቅስቃሴ የተጀመረው የቅኝ ግዛት መስፋፋትን ተክትሎ ቢሆንም ከዚያም ቀድሞ የተለያዩ ባህላዊ ህብረቶች እንደነበሩ ይነገራል። ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ደግሞ የህብረት ሥራ ከህብረተሰቡ ባህልና አኗኗር ጋር የተዛመዱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ህብረቶች ያሉት ነው። ለህብረተሰቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በመስጠት ከሚታወቁት ህብረቶች መካከልም እድር፤ እቁብ፤ ወንፈል፤ ጅጌ ፤ ደቦ እና የተለያዩ የቤተሰብና የአካባቢ ማህበራት ይጠቀሳሉ።
ስለ ዘመናዊ የህብረት ሥራ ማህበራት መቋቋም ስንቃኝ ግን በኢትዮጵያ የህብረት ሥራ ማህበር ዕድሜ ግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ማስቆጠሩን እንገነዘባለን። የህብረት ሥራ ማህበራቱ በህግ መቋቋም የጀመሩት በንጉሡ ዘመን ሲሆን፤ መጀመሪያ ጊዜም የገበሬዎች የእርሻ ህብረት ሥራ ድንጋጌ በ 1953 ወጥቶ ሥራ ላይ ውሏል።
በኢትዮጵያ የህብረት ሥራ ማህበራት በስርዓት ተደራጅተው፤ በፖሊሲ ታቅፈው ሥራ ከጀመሩ ወዲህ ማህበራቱ ከራሳቸው ጥረት ባሻገር መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት በመጠቀም ከፍተኛ እምርታ አስመዝግቧል።
በአሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያ 20 ሚሊዮን አባላት፣ ከ23 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያፈሩ፣ ከ85 ሺህ በላይ መሰረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ 388 የኅብረት ሥራ ማህበራት ዩኒየኖችና 3 የኅብረት ሥራ ፌዴሬሽኖች ተደራጅተው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሚገኙ ከፌዴራል ህብረት ሥራ ማህበር የወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በእነዚህ ማህበራትም ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ዜጎቻችን ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል፡፡ በሥራ ዕድሉ በተለይ ተጠቃሚ የሆኑት ሴቶችና ወጣቶች ናቸው፡፡
በእርግጥም የኢኮኖሚ ምሁራን እንደሚስ ማሙበትም በአንድ አገር የህብረት ሥራ ማህበራት በቁጥርም ሆነ በአቅም መጎልበት ከቻሉ በተመሳሳይ መጠን የልማት አንቀሳቃሽ ሞተር በመሆን ኢኮኖሚያዊ አበርክቷቸውም እጅጉን ይልቃል።
የአንድ አገር ኢኮኖሚ እንዲረጋጋና የኢኮኖሚ ዕድገት ቀጣይነት እንዲኖረው፤ ፍትሐዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል እንዲፈጠርና የገቢ ልዩነቶችን እንዲጠቡ ማድረግ ይቻላል። በገጠርም ሆነ በከተማው የሚኖረው ዝቅተኛ ገቢ ያለውን ማህበረሰብ ክፍል የኑሮ ደረጃውን በማሻሻልና ድህነት በማጥፋት ያግዛል።
በአገር ኢኮኖሚ ኡደት ውስጥ በተለይ በገጠር ያሉ የግብርና ህብረት ሥራ ማህበራት ለአርሶና አርብቶ አደሩ የግብርና ምርት ማሳደጊያዎችን ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ፤ በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶች አባላት እንዲያመረቱ በማድረግ፤ የገበያ ማዕከሎችን በመፍጠርና ለተጠቃሚው እንዲደርስ ድልድይ ሆነው ያገለግላሉ።
የአርሶ አደሩን ምርት እሴት ለመጨመር የሚያስችል የተለያዩ ፋብሪካዎችንና የምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎችን በመገንባት፤ ወሳኝ የሆኑ የኢንቨስት መንት ሥራዎችን ያከናውናሉ። ቴክኖሎጂን በማስረፅ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ጥራት ያላቸው ምርቶች አምርተው የውጭ ምንዛሬ ያስገኛሉ።
በከተማ ውስጥም የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት መቋቋማቸውም የንግድ ስርዓቱን በማስተካ ከል ነፃ የገበያ ስርዓትን ያሳድጋሉ። በተለይ በአሁን ወቅት በፍጆታ ዕቃዎችና በግብርና ምርቶች አቅርቦት እየደረሰ ያለውን የመጠን፤ የጥራትና የመለኪያ ችግሮች የዋጋ ንረት በመከላካል ፍትሐዊ የግብይት ስርዓትን እንዲፈጠር ያደርጋሉ።
ማህበራቱ በሥራ ዕድል ፈጠራና የቁጠባ ባህል እንዲጎለብት በማድረግ ረገድም የማይተካ ሚና አላቸው። የአራጣ አበዳሪነት ያጠፋሉ። በተለይ በቁጠባ ረገድ ባንክ አገልግሎት በቅርበት ማግኘት የማይችሉ በገጠር አካባቢና በከተማ ውስጥ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ህብረተሰብ ክፍሎች በገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበራት በማደራጀት የፋይናንስ አገልግሎት እንዲያግኙም ያደርጋሉ።
ማህበራዊ አብርክቷቸውም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። አባላትም ሆኑ አባል ባልሆኑት መካከል የመረዳዳት፤ የመተጋገዝን፣ ለሌሎች ማሰብን ፤የጋራ ተጠቃሚነት እንደ አንድ ተቋማዊ እሴት መከተልና በመተግባር ማህበራዊ ትስስርን ይፈጥራሉ።
በፍትሐዊነት ማመጣጠን ላይ የተመሰረቱ፤ የማያዳሉ ፣ መሰረታቸውም እኩልነት በመሆኑ ፖለቲካዊ ጠቀሜታቸውም የላቀ ነው። ሰፊውን ህዝብ እንደ ዋነኛ የልማት ኃይል በተደራጀ የተሳትፎ እንቅስቃሴ ውስጥ በማስገባት ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ልማት እንዲረጋጋጥ ይግዛሉ።
በተለይ የኪራይ ሰብሳቢነት ተዋጊዎች ናቸው። አባላት፤ የንብረታቸው፤ የሀብታቸውና የምርታቸውና አገልግሎታቸው ተጠቃሚ ባለቤትና ተቆጣጣሪ መሆናቸው መለያ ባህሪያቸው ነው። የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጣር ሊከሰቱ የሚችሉ የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጭን ያደርቃሉ።
አሠራራቸው ግልጽና ተጠያቂነት ያለው በመሆኑ፤ አባላቱ የሚያገኙት ጥቅምና አገልግሎት በሚያደርጉት ተሳትፎ መጠን መሆኑ እንዲሆኑም ሀብትና ንብረታቸውን የመጠበቅና የመቆጣጠር ኃላፊነት ስላለባቸው ኪራይ ሰብሳቢነትን እንዲዋጉ ያስችላቸዋል።
በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ የሚገኙ የህብረት ሥራ ማህበራት ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ አስተዋፅኦአቸው ሲገመገም ስኬታማና የሚያስጨበጭብ ውጤቶች ስለመገኘቱ መረዳት በጣም ቀላል ነው። በተለይ የግብርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ቀጣይነትን አረጋግጠዋል። የጊዜና የጎልበትን ምርትና ምርታማነት የሚያሳድጉ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎትና አቅርቦት እንዲሻሻል፤ የአምራች አርሶና አርብቶ አደሩ የገበያ ዋጋ የመወሰን አቅም እንዲያድግ አስችለዋል።
በከተማ በሸማች ህብረተሰብ የፍጆታ ዕቃዎችን በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ሸማቾችን ካላስፈላጊ ዋጋ ንረት ታድገዋል። የከተሞች የሚፈጠረውን ያልተገባ የኑሮ ውድነትና መልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት በገጠር አግሮ ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ፤ የአምራቹን የቅድመና ድህረ ምርት ቴክኖሎጂ የመጠቀም ባህል እንዲያድግ አስችለዋል። የምርት ብክነት እንዲቀንስና ምርትና ምርታማንት እንዲያድግ የአባልትን የግብርና ምርቶች ወደ ውጭ አገር በመላክ የአገራችንን የውጭ ምንዛሬ ክፍትት ከመሙላት እንፃር ተጨባጭ ስኬቶች አስመዝግበዋል።
ምንም እንኳን የማህበራቱ ስኬት ተቆጥሮ የማያልቅ ቢሆኑም ከዚህ ላይ መጎልበትና ውጤት ማምጣት የሚችሉበትን አቅም አሟጠው አለመጠቀማቸው የሚካድ አይደለም። ለዚህም ጠፍረው የያዟቸው ውስጣዊውም ሆነ ውጫዊ ስንክሳሮች እንዳሉባቸው እርግጥ ነው።
በዚህ ረገድ ሁሌም ከሚጠቀሱ መገለጫዎች አንዱም በየደረጃው የሚገኘው አመራር የማህበራቱን በአገር ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ ያላቸውን አስተዋፅኦ በውል አለመገንዘብ ነው። በርካታ አመራሮች ስለ ማህበራቱ ያላቸው እይታ የተንሸዋረረ መሆኑም የድጋፍና ክትትል ውስንነቶች ምክንያት ሲሆን ይስተዋላል።
የማህበራት አገራዊ ተልዕኮና ሚና ከመንግሥት ጀምሮ ሁሉም አመራር በአግባቡ ያለመገንዘብ ችግር አለ። ለህብረት ሥራ ማህበራት ትልቅ ትኩረት በመስጠት ጠንካራና ታማኝ የሆነ አመራርን ከመመደብ አንፃር ክፍተቶች ይስተዋላሉ። ከጠንካራ ባለሙያ በተጓዳኝ በቂ በጀት ከመመደብና ህብረት ሥራ ማህበራት የሚያቀርቧቸውን ችግሮች በቅርበትና በፍጥነት ከመፍታተ አንፃር ውስንንቶች ይታያሉ። ይህም ማህበራቱ ይበልጥ መጎልበት እንዳይችሉና በተለይም የመስሪያ ካፒታልና የመሰረተ ልማት አቅርቦት እጥረት እንዲገጥማቸው ዋነኛ ምክንያት ሲሆን ይስተዋላል።
ከዚህ በተጓዳኝ ዛሬም ቢሆን ማህበራት ያላቸው አበርከቶ በህብረተሰቡና በባለድርሻ አካላት በሚፈለገው ደረጃ አልታወቀም። አመራሮቹ ጠንካራ አልሆኑም። አባላቱ በሚፈለገው ደረጃ ማደግ አልቻሉም። የግብይት ድርሻቸው በሚፈለገው ደረጃ አላደገም። አንዳንድ ባለድርሻ አካላት የሚያወጧቸው የህግ ማእቀፎች ከኅብረት ሥራ ማህበራት አዋጅ፣ ደንብና ባህሪያት ጋር አዛምዶ አለማየት ይስተዋላል።
ከህብረት ሥራ ማህበራት ትልቁ ስጋትና ማነቆ ኪራይ ሰብሳቢነት ነው። ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትሩፋቶቻቸው ባሻገር በአንድም ሆነ በሌላ መልክ የሚታወቁት በኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ጭምር ነው።
ህብረት ሥራ ማህበር በርካታ ገንዘብ የሚቀንሳቀ ስበት ነው። ይህ ክንውን ጠንካራ ጥበቃ ያስፈልገዋል። ይሁንና ክፍተቶች አሉ። የውስጥ አሠራራቸው የተጠናከረ አይደለም። በዚህም ምክንያት ከፍተኛ የሀብትና ንብረት ብክነት ይስተዋላል። በተለይ የኦዲት፣ኢንስፔክሽን ሰርቴፍኬሽን አገልግሎት በሚፈለገው ደረጃ መስጠትም አልተቻለም።
በተለይ በኦዲት ረገድ ከተካሄዱ የግምገማ ሪፖርቶች መረዳት እንደቻለውም ምንም እንኳን የአንዳንድ ክልሎች አፈፃፀም ጥሩ የሚባል ቢሆንም አብዛኞቹ ግን ስፊ ክፍተት አለባቸው። ለዚህ ዋነኛው ክፍትትም ማህበራት ሥራቸውን የሚሠሩት በሙያተኛ አለመሆኑ ነው።
በኦዲት ሪፖርት ረገድ አቅም ያላቸው ሂሳብ ሠራተኞች ባለመኖራቸው ሂሳብን በወቅቱ የማሳወቅ ችግር አለ። በአግባቡና በተቀመጠው መሠረት ሠርቶ ለኦዲተሮች ያለማቅረብ ችግርም ይታያል። በዚህም ምክንያት ኦዲተሮች ሂሳቦችን ለማስተካከል ረጅም ሰዓት እንደሚወስድባቸው በአንድ መድረክ ላይ አዳምጫለሁ። የኦዲት ግኝቶችም ሆነ የኦዲት አስተያየት ላይ የሚሰጡ ግኝቶችን ታሳቢ በማድረግ ተከታትሎና አርሞ ዳግም ችግሮቹን ለማስወገድ በሚከናወን ሥራ ድጋፍ በመስጠት ረገድ ሰፊ ክፍተት እንዳለም ከአስተያየት ሰጪዎች ተረድቻለሁ።
ይሁንና ህጋዊና ህጋዊነትን ማስጠበቅ የሚቻለው ማህበሩ ምን ያህል ሀብት አለው፤የፋይናንስ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል የሚሉትን ጨምሮ አጠቃላይ ቁመናው በአግባቡ የኦዲት ምርመራ ተደርጎ ሲታወቅ ነው። ምንም እንኳን ችግሩ በአንድ ጀንበር የማይፈታና ሰፊ ትግል የሚጠይቅ ቢሆንም ተግባሩ ግን ከባድ ትግል የሚጠይቅ መሆኑም ሊካድ አይገባውም።
እነዚህ ለአብነት የጠቃቀስናቸው ስንክሳሮች ታዲያ ከህብረት ሥራ ማህበራት ትሩፋቶች ይበልጥ ለመቋደስ እንዳይቻል ዋነኛ ችግር ሆነው የሚጠቀሱ ናቸው። እነዚህን ተግዳሮቶች መሻገር ለነገ የሚባል መሆን የለበትም።
በመሆኑም ጊዜ ሳይስጡ የማህበራቱን አደረጃጀት ማስተካከልና የውስጥ አሠራራቸውን ማጠናከርን ይጠይቃል። የአባላትን ምርት በብዛት፣ በጥራትና በወቅቱ በማሰባሰብ በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር ግብይት ላይ ተጠናክሮ እንዲሠሩ በማድረግ፣ በእሴት መጨመር ተግባራት ላይ ያላቸውን ትኩረት ማጎልበትም ያስፈልጋል። የውጭ ግብይት ድርሻቸውን መጨመርና በዋና ዋና ከተሞች የግብይት መረጃና ታላልቅ የገበያ ማዕከላት ግንባታን መስፋት የግድ ይላል።
የኅብረት ሥራ ማህበራት ቁጥጥር ተግባራትን በማጠናከር በተለይ የኦዲት፣ የኢንስፔክሽንና የሰርቲፍኬሽን ተግባራትን በማከናወን ደህንነታቸውን ማረጋገጥ፣ የግድ ይላል። በኅብረት ሥራ ዩኒየኖችና በአባል መሠረታዊ ኀብረት ሥራ ማኅበራት መካከል ያለው የግብይት ግንኙነት ማጠናክር የግድ ይላል። የኅብረት ሥራ ማህበራት ኤግዚቢሽኖች፣ ባዛሮች እና ሲምፖዚየሞችን በየደረጃው ማጠናከርንም ይጠይቃል።
በአጠቃላይ ከህብረት ሥራ ማህበራት ትሩፋት ይበልጥ ለመቋደስ ሁሉአቀፍ የኅብረት ሥራ ልማት ስትራቴጅ በማዘጋጀት በሚቀጥሉት 15 ዓመታት ውስጥ በማህበራት የሚተገበሩ ዋና ዋና ጉዳዮችን በመለየት፣ ለተግባራዊነቱ እንቅፋት የሆኑ ዋና ዋና ማነቆዎች የሚፈቱበት አቅጣጫ መቀመጡም ለሁሉም ቁልፍ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።
አዲስ ዘመን ጥር 30/2011
ታምራት ተስፋዬ