ሙሉቀን ታደገ
በአዲስ አበባ ከተማ በየሰፈሩ ተቀምጠው ወራጅ ወጪውን ሲላክፉ እና በሱስ ተጠምደው ድንጋይ ሲያሞቁ የሚውሉ አካላት ቁጥራቸው እየተበራከተ መጥቷል:: እነኝህ አካላት የገቢ ምንጫው ምን እንደሆነ በውል ባይታወቅም ሁልጊዜም በሰፈር ውስጥ ባሉ ድንጋዮች ላይ ተኮልኩለው ይታያሉ። ያውካካሉ፤ ይዘላሉ::
ከዚህም አልፈው የሚወጣውንም የሚገባውንም ይላከፋሉ፣ ከብረ ነክ ስድብም ይሳደባሉ፡፡ አልፎ አልፎም ከስድብም ባለፈ አካላዊ ጥቃት ሲፈፅሙም ይስተዋላል፡፡
በእነኝህ አካላትም በአዲስ አበባ የሚኖሩ ሰዎች ከባድ ዕቃ ገዝተው ወይም ቤት ተከራይተው በራሳቸው መኪና ወይም በተከራዩት መኪና ዕቃ ለመጫን ወይም ለማውረድ ሲፈልጉ እኛ ካልጫነው እና ካላወረድነው ብሎም እኛ ያልነውን ገንዘብ ካልከፈላችሁ ሞተን እንገኛለን በማለት በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎችን አሰላችተዋል፡፡
በዚህም የተማረሩ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሚስተዋለው የጫኝ እና የአውራጅ አለመግባባት ችግር ሆኖ በነዋሪዎቿ መወራት ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡
እነኝህ በጫኝ እና አውራጆች የተማረሩ እና ችግሩ ከአቅም በላይ እየሆነ በመምጣቱ ጉዳዩ ያሳሰባቸው በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ አስኮ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች ስለጉዳዩ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ጠይቁልን ሲሉ ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ጠይቀዋል፡፡
የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም የአስኮ አካባቢ ነዋሪዎችን ብሶት መሠረት አድርጎ ስለጉዳዩ ይመለከተዋል ያለውን አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር የሆኑትን ኮማንደር ፋሲካን ጠይቆ የሚከተለውን መልስ ለአንባቢዎች ይዞ መጥቷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር የሆኑት ኮማንደር ፋሲካ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ያነሱት ቅሬታ እውነት ነው፡፡
እንደተባለው ጫኝ እና አውራጅ አዲስ አበባ ከተማ ላይ በተለያዩ ቦታዎች ከባለንብረቶች ጋር ያለመግባባት እና እንዲሁም እኛ በምንወስነው ገንዘብ ካልሆነ በስተቀር ዕቃችሁን አታወርዱም ወይም አትጭኑም በማለት አንዳንድ ቦታ ላይ ከዕቃው በላይ ገንዘብ የሚጠይቁ አውራጅ ጫኞች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡
በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ተፈቅዶላቸው በጫኝ እና በአውራጅ የሚሰሩ ሰዎች አሉ፡፡ ነገር ግን እነኝህ ተፈቅዶላቸው ጫኝ እና አውራጅ ሆነው የተቀጠሩ ሰዎች ከቤታቸው ቁጭ ብለው ሌሎች ሰዎችን ቀጥረው በማሰራት ያለ አግባብ ገንዘብ በመጠየቅ የከተማዋ ነዋሪዎችን ሲያማርሩ ይስተዋላል ሲሉ ኮማንደር ፋሲካ ይናገራሉ፡፡
እንደኮማንደር ፋሲካ ገለጻ፤ ጫኝ እና አውራጆች ከባለንብረቶች ጋር የሚፈጠሩት አለመግባባቶች በጣም ከፍተኛ የሆነ ችግር እያስከተሉ ስለነበር ይህን በተመለከተ ከየክፍለ ከተማው እና ከየወረዳው የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ እንዲሁም ከጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋም ጋር በጋራ በመሆን ቤታቸው ቁጭ ብለው የሚያዝዙትን እና ትክክለኛ ሥራ የማይሰሩትን በጫኝ እና አውራጅ በስሙ የሚነግዱትን የማስወገድ እና ትክከለኛ ሥራ የሚሰሩ ሰዎችን ብቻ እንዲሰሩ የማድረግ ሥራ ተከናውኗል፡፡
እነዚህ ሰዎች ከተወገዱ እና እውነተኛ የሆኑ ሥራዎችን የሚሰሩ ሰዎች ወደ ቦታው ከገቡ በኋላ በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ የሆነ እርካታ የተፈጠረበት ሁኔታ አለ፡፡ ለምሳሌ ቦሌ ክፍለ ከተማ በአንድ ወቅት አንድ ወረዳ ላይ የሚገኘው በጠቅላላ ሕዝቡ ተነስቶ አውራጅ እና ጫኝ አንፈልግም በማለት ምሬታውን እንደገለጹ አስታውሰው፤ ለዚህም የሕዝብ ምሬት እንደ ዋና ምክንያት የጠቀሱት ኮንዶሚኒየም አካባቢ በተደጋጋሚ በአውራጅ እና ጫኞች የተፈጠረው አለመግባባት እንደሆነ አመላክተው፤ በአንድ ፍሪጅ ላይ እስከ አምስት ሺህ ብር የሚጠይቁ እና የተጠየቀውን አምስት ሺህ ብር የማትከፍሉ ከሆነ እኛ አናወርድም ሌላ ማንም ሰው አያወርድም ብለው ሲያስቸግሩ የነበሩ ሰዎች እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡
እንደዚህ ዓይነት በቅጥፈት የሚሰሩ ሰዎችን አግኝተናቸው ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ ተደርጎ ቢመከሩም አልመለስ ስላሉ ቀጥታ እነዚህን ሕገ ወጥ አካላት ከቦታው በማስወገድ ከመስተዳድሩ ጋር በጋራ በመሆን አዳዲስ የሆኑ መስራት የሚችሉ ሰዎችን ብቻ እንዲቀጠሩ ተደርጓል ሲሉ ኮማንደር ፋሲካ አመላክተዋል፡፡
አዲሶቹ አውራጅ እና ጫኞች ከተቀጠሩ በኋላ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ ማምጣት ተችሏል የሚሉት ኮማንደሩ፤ እንዲያውም ገንዘብ ከሌላችሁ አትቸገሩ እስከማለት የደረሱ ሠራተኞች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
አሁንም ቀደም የነበረው ችግር ሙሉ በሙሉ ስላለተቀረፈ ይህ ሠራተኞችን በመለወጥ የተፈጠረውን ጥሩ ተሞክሮ በሁሉም ቦታ እንዲመጣ እና ቢያንስ ሥራውን የሚሰሩ ሰዎች አሰሪውን እና ሠራተኛው እንደሚገናኙ የማድረጉን ሥራ በየወረዳው የሚገኙ የአስተዳደር አካላት እና ፖሊስ በጋራ እየሰሩ እንደሆነ ኮማንደር ፋሲካ አመላክተዋል፡፡
ይህን ችግር ለማስወገድ የአንድ ጀምበር ሥራ መሆን የለበትም የሚሉት ኮማንደር ፋሲካ፤ ያንድ ጀምበር ሥራ ከሆነ የተወሰነ ጊዜ ብቻ ሆይ ሆይ ይባል እና ችግሩ ሳይፈታ ችግሩ ተፈቷል ተብሎ ችግሩ በስፋት የሚስተዋልበት ሁኔታ ሊኖር ስለሚችል የአዲስ አበባፖሊስ ሥራውን በዘላቂነት ጥረት እያደረገ ነው ፡፡
ትልቁ ነገር ሰዎቹ በሠራተኞቹ በሚፈጥሩት በጫና እና በተፅእኖ ምክንያት ፍጹም የተጋነነ ክፍያ ክፈሉ ሊባሉ አይገባም የሚሉት ከማንደር ፋሲካ፤ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ነዋሪዎችን ባጋጠመ ጊዜ ወዲያውኑ ለጸጥታ አካሉ ጥቆማ በመስጠት ሕጋዊ አሠራር እንዲኖር ሁሉም ሰው መተባበር አለበት፡፡
እንደ ኮማንደር ፋሲካ ገለጻ፤ አንዳንድ ቤተሰቦች ዕቃቸውን ለማውረድ ሁለተናዊ ዝግጁነት ይኖራቸው እና ቤተሰቡ ራሴ አወርዳለሁ በሚልበት ጊዜ ቤተሰቡን ማውረድ አትችሉም የሚሉ አካላት አሉ። እንደዚህ ዓይነት ነገር በሚያጋጥምበት ሁኔታ ለፖሊስ መጠቆም ያስፈልጋል፡፡
በምንም መልኩ ከአውራጅ እና ጫኙ ጋር እንካ ስላቲያ ሳይፈጠር ለአካባቢው ፖሊስ ጣቢያ ጥቆማውን መስጠት ካልሆነም ደግሞ በአዲስ አበባ የፖሊስ ኮሚሽን ስልክ 991 ላይ ጥቆማ በማድረግ እዚያው አካባቢ ያሉ ፖሊሶች ወደ አካባቢው ደርሰው ፍትህ እንዲሰጡ ማድረግ ይቻላል፡፡
ምክንያቱም ንብረቱ ላይ ማዘዝ የሚችለው ባለቤቱ ነው እንጂ ከባለቤቱ ውጭ በንብረቱ ላይ ማንም ሊያዝዝ አይችልም፡፡ በንብረቱ ላይ ባለቤቱ ማዘዝ አይችልም ብሎ የሚመጣ ሰው ካለ ሕገ ወጥ ተግባር ስለሆነ ወንጀል ፈፃሚው በወንጀል እንደሚጠየቅ ኮማንደር ፋሲካ አመላክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 12/2013