ሰሎሞን በየነ
በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ያለውና ልጓም ያጣው የዋጋ ንረት በዝቅተኛ ገቢ ከሚተዳደረው የኅብረተሰብ ክፍል አልፎ መካከለኛ ገቢ አለው ተብሎ የሚታሰበውን የአገሪቱን ዜጎች ጭምር ብርቱ ፈተና ውስጥ ከቷቸዋል።
በተለይ ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ የእህል፣ የጥራጥሬና የአትክልት እንዲሁም የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሄዱ በኅብረተሰቡ ኑሮ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ይገኛል።
ይባስ ብሎ በያዝነው ወር በሁሉም ዓይነት ምርትና አገልግሎት በሚባል ደረጃ በአገሪቱ እየተስተዋለ ያለውን የዋጋ ንረት ተከትሎ በቀን አንዴ በልቶ ለማደር የተሳነውን የኅብረተሰብ ክፍል ቤት ይቁጠረው።
ችግሩን «በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ» ያደረገው ደግሞ አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች ያልተገባ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ የተለያዩ ምርቶቹን በመደበቅ አሁን ላይ በአገሪቱ እየተስተዋለ ያለውን የዋጋ ንረት እያባባሱት ይገኛሉ።
ለአብነት ከሰሞኑ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ጀሞ ሚካኤል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ልዩ ስሙ አንበሳ ጋራዥ ጎን በአንድ ግለሰብ መጋዘን ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ ሁለት ሚሊዮን ጀሪካን የፓልም የምግብ ዘይት ተከማችቶ መገኘቱ አገርን ጉድ ያስባለና ያነጋገረ ጉዳይ ነበር።
በመሆኑም በዛሬው የዘመን ችሎት አምዳችን ሰው ሰራሽ የምርት እጥረት በመፍጠር ያልተገባ ትርፍ ለማግበስበስ ሲባል ምርትን በሕገወጥ መንገድ አከማችቶ መያዝ የሚያስከትለው የሕግ ተጠያቂነት ምን ይመስላል? ስንል የሕግ ባለሙያና ጠበቃ የሆኑትን አቶ ተሾመ ወ/ሃዋርያትን እንደሚከተለው አነጋግረናቸዋል።
ምርትና አገልግሎትን መደበቅ ምን የሕግ ተጠያቂነትን ያስከትላል ከሚለው በፊት ምርትን አከማችቶ መያዝ ወይም መደበቅ ፖለቲካ አንድምታው ምንድ ነው የሚለውን ማየት በጣም ጠቃሚ ነው የሚሉት አቶ ተሾመ፤ መንግሥት ከውጭ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ፈሰስ በማድረግ በድጎማ የሚያስገባቸውን ምርቶች ወይም በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን በሕገ ወጥ መንገድ አከማችቶ መያዝ ወይም መደበቅ ኅብረተሰቡ ምርትና አገልግሎት አጥቶ ችግር ላይ ወይም ረሃብ ላይ እንዲወድቅ ያደርጋል፤ ኅብረተሰቡ ችግር ላይ ሲወድቅ ደግሞ በመንግሥት ላይ እንዲነሳሳና በአገሪቱ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እንዳይሰፍን ምክንያት ይሆናል ይላሉ።
በዚህም አገራችን ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አገራት በተከሰተው የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ሳቢያ፤ የአገራቱ ሰላም ሲናጋ ታይቷል። ሕዝብ በመንግሥት ላይ ተነስቶ አያሌ መንግሥታት ከዙፋናቸው ሲወርዱ ተስተውሏል።
ለአብነት በቅርቡ እንኳን በሱዳን በዳቦ ዋጋ ጭማሬ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ መንግሥት ከሦስት አስርተ ዓመታት በላይ ተደላድሎ ከተቀመጠበት ዙፋኑ ወደ ወህኒ ሲወርድ፤ እስካሁን በአገሪቱ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እንዳልሰፈነ የሕግ ባለሙያው ይናገራሉ።
በመሆኑም ካለው የሕግ ተጠያቂነት ባለፈ ምርትን በሕገ ወጥ መንገድ መያዝ ወይም መደበቅ ያለው ፖለቲካዊ አንድምታ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ምክንያቱም የተራበ ሕዝብ ምን ሊያስከትል እንደሚችል አገራችንን ጨምሮ በተለያዩ አገራት ታይቷል።
ስለዚህ ምርትን መደበቅ ጦርነት፣ ሕዝባዊ ነውጥ ሊያስከትል ይችላል። በጥቅሉ ምርትን በሕገ ወጥ መንገድ መያዝ ወይም መደበቅ ፖለቲካዊ አንድምታው ሲታይ የአገርን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው ብለዋል።
አቶ ተሾመ ምርትን በሕገ ወጥ መንገድ መያዝ ወይም መደበቅ ከሚያስከትለው ፖለቲካዊ አንድምታው ባሻገር የሚያስከትለው የሕግ ተጠያቂነት ሲታይ፤ በሕገወጥ መንገድ ምርትን አከማችቶ መገኘት ወይም መያዝ ማለት ሰው ሰራሽ የምርት እጥረት በመፍጠር አንድም ያለአግባብ ለመበልጸግ ሌላም ሕዝብን በመንግሥት ላይ ለማነሳሳት የሚደረግ ሸፍጥ ነው።
ለአብነት ከሰሞኑ በመዲናዋ በአንድ ግለሰብ መጋዘን ውስጥ በሕገወጥ መንገድ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ፓልም የምግብ ዘይት አከማችቶ የተገኘውን ግለሰብ ብናይ መንግሥት አገሪቱ ከሌላት የውጭ ምንዛሬ ላይ ድጎማ በማድረግ ለሕዝብ በተመጣጠነ ዋጋ እንዲቀርብ ያስመጣውን ምርት ለራስ ብልጽግና ቅድሚያ በመስጠት ወይም ያለ አግባብ ለመበልጸግ ካለው ፍላጎት የተሰራ ወንጀል ነው።
እንዲሁም ኅብረተሰቡ በሚፈጠረው የምርት እጥረት ተማሮ በመንግሥት ላይ እንዲያምጽ ለመቀስቀስ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ እነዚህ ግለሰቦች ያላግባብ በልጽገዋል። በመሆኑም በበለጸጉት መጠን በፍትሐብሔርና በወንጀል ሕግ ተጠያቂነት አለባቸው።
የአገሪቷን የውጭ ምንዛሬና አንጡራ ሀብቷን የበሉ በመሆናቸው በበለጸጉበትና እምነት ባጎደሉበት መጠን የሚጠየቁ ይሆናሉ። የንግድ ፈቃዳቸውም እስከ መሰረዝ ደረጃ ሊደርስ እንደሚችል ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ምርትን በሕገ ወጥ መንገድ መያዝ ወይም መደበቅ በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ በኅብረተሰቡ ዘንድ ሰው ሰራሽ የምርት እጥረትን በመፍጠር ሕዝብ በመንግሥት ላይ እንዲነሳ ለማድረግ መሻት በሚል በወንጀል የሚያስጠይቅ ይሆናል።
ስለዚህ አመጽ እንዲነሳ ሕዝብ በመንግሥት ላይ እንዲያመጽ ምክንያት የሆኑ ናቸው ተብሎ በወንጀል ክስ እንደሚመሰረትባቸው ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ሸማቹ ማህበረሰብ ምርትና
አገልግሎት ምክንያታዊ በሆነ ዋጋ እንዲያገኝና መብቱ እንዲጠበቅ እንዲሁም ተገቢ ያልሆነ የንግድ ውድድር በነጋዴዎች መካከል እንዳይከሰትና የምርት አቅርቦቱ የተመጣጠነ እንዲሆን በወጣው የሸማቾች መብት ጥበቃ ሕግ መሠረት ምርትን በሕገ ወጥ መንገድ መያዝ ወይም መደበቅ በወንጀል የሚያስጠይቅና የሚያስቀጣ እንደሆነ ባለሙያው አስረድተዋል።
በአጠቃላይ አንድ ነጋዴ በሕገ ወጥ መንገድ ምርትን ይዞ ወይም ደብቆ ቢገኝ በተለያዩ ወንጀሎች የሚያስጠይቅና የሚያስቀጣው ይሆናል። ማለትም ግለሰቡ ምርቱን በሕገ ወጥ መንገድ የያዘው ያልተገባ ትርፍ ለማግኘት፣ እምነት በማጉደል፣ ያላግባብ በመበልጸግ፣ ሰው ሰራሽ የምርት እጥረት በመፍጠር፣ ሕዝብን ለአመጽ ለመቀስቀስ ወዘተ በሚል የሚከፈትበት የክስ ዓይነቶች ብዙ ይሆናሉ። ስለዚህ በእያንዳንዱ ወንጀል በሚያስቀምጠው የቅጣት ድምር ውጤት መሠረት ቅጣት የሚሰጠው ሲሆን፤ ቅጣቱም ተደማምሮ ከ20 ዓመት በላይ ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ ሊሆን እንደሚችል የሕግ ባለሙያው ተናግረዋል።
ነገር ግን ነጋዴዎች በሕገ ወጥ መንገድ ምርትን በመያዝ የሚፈጽሙት ወንጀል ከባለሥልጣናት ጋር መዋቅራዊ ግንኙነት ያለውና «በእከክኝ ልከክህ» የጥቅም ትስስር የተቆራኘ በመሆኑ ወንጀለኞች ተገቢውን ፍርድ ሲሰጣቸው አይስተዋልም። ስለዚህ የወንጀሉ መነሻ በመንግሥታዊ መዋቅር ያሉ ሌቦች ናቸው። በመሆኑም ይህንን የአገር ሉዓላዊነትን አደጋ ላይ የሚጥል ወንጀል መንግሥት ከውስጡ ያሉትን ሌቦች አጥርቶ ሕግ ፊት ማቅረብ የሚጠበቅበት ሲሆን፤ ኅብረተሰቡም ምርትን በሕገ ወጥ መንገድ የሚደብቁ ወንጀለኞችን በመጠቆም በአገሪቱ የተረጋጋ የገበያ ሥርዓት እንዲሰፍን የበኩሉን ሚና መወጣት እንዳለበት አቶ ተሾመ ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 12/2013