ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷ የተጠበቀ፤ ነጻነቷ የተከበረ ፤ ለቅኝ ገዢዎች ያልተንበረከከች ሀገር ናት። በአልንበረከክም ባይ ኩሩና ጀግና ልጆቿ የሕይወት መስዋዕትነት ዳር ድንበሯ ተከብሮ ኖሯለች።
ይህም በዓለም የነጻነት ተምሳሌት አፍሪካዊት ሀገር ሆና እንድትጠቀስ አስችሏታል።ዛሬ አንገታችንን ቀና፣ ደረታችንን ነፋ አድርገን በኩራት የምንናገረው፤ የምናከብረው ታሪክ የተሰራው ትናንት ጀግኖች በከፈሉት መስዋዕትነት ፤ ነጻነቷን ጠብቀው ባስረከቡን ሀገር ላይ ሆነን ነው።
ይሄ እኛ ለእኛ ብቻ ሳንሆን ዓለም ጭምር የሚመሰክረው ሀቅ ነው ። በተግባር የታየ ፣በታሪክ የተመዘገበ ገድል ጭምር ነው። ይሄ አኩሪ ታሪክ የተገኘው እንዴት ነው? ዛሬ ደረጃ ላይ የተደረሰው ፣ለቅኝ ገዢዎች ያልተንበረከክነው ማን ምን ሰርቶ ነው? ብሎ የአሁኑ ትውልድ ሊጠይቅ ይገባል። ታሪኩን ማወቅ እና መጠበቅ አለበት። ከዚህ ባለፈም ታሪክ ሰሪ ትውልድ መሆኑን በየመስኩ መስራትና ማስመስከር ይጠበቅበታል።
ኢትዮጵያ ማህጸነ ለምለም ሀገር ናት። ሁሌም በየዘመኑ ስሟን ከፍ የሚያደርጉ፣ አንድነቷን የሚያጠነክሩ ፣ አለሁልሽ የሚሉ ልጆች አሏት ። ሁሌም ከጎኗ ይቆማሉ። ከውጪም ሆነ ከውስጥ አንድነቷን የሚያናጋ፣ ሉዓላዊነቷን የሚፈታተን ጠላት ሲገጥማት ደረትና ግንባራቸውን ለጥይት የሚሰጡ ፣ ደማቸውን የሚያፈሱ ጀግኖች ልጆች አሏት። እነሱ እየሞቱ ሀገራችንን አስከብረው የኖሩ እንደነበሩት ሁሉ አሁንም ይሄንኑ ታሪክ የደገሙ ወደፊትም የሚደግሙ ጀግኖች ዛሬም አሉ፤ ወደፊት ይኖራሉ።
መቼም ቢሆን ኢትዮጵያ አትፈርስም ፤አትፈረካከስም፤ በጀግኖቿ ልጆቿ መስዋዕትነት ተከብራ ትኖራለች።
አሁን ያለችው ኢትዮጵያ ከየትም የተገኘች ፤ ማንም የሰራት አይደለችም።ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሎባት እንደ ሀገር ጠንክራ የቆመች የነጻነት ተምሳሌት ናት።
በወራሪው ፋሽስት ኢጣሊያ ወታደሮች የካቲት 12 ቀን 1928 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በሶስት ቀናት ንጹሃን ሴቶችና ህጻናት ሳይቀሩ አንገታቸውን ቀልተዋል፤ በግፍና በጭካኔ ጨፍጭፈዋል። ከ30 ሺህ በላይ ዜጎቻችን ሜዳ ለሜዳ ወድቀዋል። ልጆች ከወላጆቻቸው፣ ባል ከሚስቱ ፤ አዛውንቱ ከጧሪዎቻቸው ዳግም ላይገናኙ የተለያዩበት ከባድ የሀዘን ቀን ነው ።
በአድዋ ጦርነትም የሀገራችን ዳር ድንበር አናስደፍርም ብለው የወደቁ ወገኖቻችን ፤ ደምና አጥንታቸውን የከሰከሱ ብዙ ናቸው ። የሱማሌው ዚያድባሬም የሀገራችንን ዳር ድንበር ጥሶ ሲገባም ዓለምን ያስደነቁ፣ በብቃታቸው የተመሰከረላቸው ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ናቸው የዚያድባሬን ጦር ድባቅ ያስገቡት፤ ሽንፈቱን አከናንበው ወደ መጣበት የመለሱት።
ይሄ ሁሉ ታዲያ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ሆና እንድትቀጥል የተከፈለ መስዋዕትነት መሆኑን ለአንዴም ልንዘነጋው አይገባም። ሁሌም የምንኮራበት ሁሌም የምንዘክረው ሀገርን እንደ ሀገር የማስቀጠል ተጋድሎ ውጤት መሆኑን ሁሉም ሊያውቀውና ሊረዳው ይገባል ።
በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ሕግን ለማስከበር በተደረገው ሂደት ህይወታቸውን የገበሩ ወገኖች ለሀገር አንድነት የተከፈለ ሌላው ማሳያ ነው። ይሄ ሁሉ የሀገርን አንድነት አስጠብቆ ለመሄድ የተደረገ የጀግንነት ውጤት ነው።
በቀጣይም ይሄንኑ አስጠብቆ መሄድ ይጠይቃል ። የዛሬ ዕለትም ለሀገር የተከፈለ መስዋዕትነትን ወደኋላ መለስ ብለን እንድናሰብ ያደርገናል ።ታሪክ አውቀን ታሪክ ሰርተን ታሪክን እንድናስቀምጥ ያስገድደናል።
አሁንም የሀገራችንን ዳር ድንበር ጠብቆ አንድነቷን አስከብሮ ከትውልድ ወደ ትውልድ የማስተላለፍ አደራ ያለብን እኛ የዚህ ዘመን የታሪክ አጋጣሚ ተረካቢ ትውልዶች ነን። ይሄንን ኃላፊነት ተወጥተን ለቀጣዩ ትውልድ አኩሪ ፣ ዘመኑን ያዋጀ ታሪክ ልንሰራ ይገባል።
የዛሬዋ ኢትዮጵያ እዚህ የደረሰችው በብዙ ወገኖቻችን መስዋዕትነት ድምር ውጤት መሆኑን ለአንድም ቀን ልንዘነጋው አይገባም። ይሄንን ሁሉም ዜጋ ተረድቶ፤ ከእሱ የሚጠበቅበትን መስዋዕትነት መክፈል ይገባዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 12/2013