አዲስ አበባ፦ በበጋ ወቅት የሚያጋጥመውን የእንስሳት መኖ እጥረት ለመፍታት አንድ ሺህ 605 ሄክታር መሬት ላይ መኖ ለማልማት እንቅስቃሴ መጀመሩን የአፋር ክልል እንስሳት፣ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ኢብራሂም መሃመድ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በተለይ እንደገለጹት፤በበጋ ወቅት በመኖ እጥረት ምክንያት እንስሳት ጉዳት እንዳይደርስባቸው በክልሉ በሚገኙ ሰባት ወረዳዎች ውስጥ አንድ ሺ150 ሄክታር መሬት በመንግሥት ድጋፍ ለማልማት የታቀደ ሲሆን፤ 455 ሄክታር መሬት ደግሞ አርብቶ አደሮች በራሳቸው እያለሙ ይገኛሉ፡፡
እንደ አቶ ኢብራሂም ማብራሪያ፤ በዓመቱ በአጠቃላይ 207 ቶን መኖ ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ መኖው በየአስራ አምስት ቀኑ እየታጨደ ነው፡፡ እስከአሁን ድረስ 109 ሺህ ቶን መኖ ተሰብስቧል፡፡ ለሚያለሙ ወረዳዎች ተገቢው የፋይናንስ እና የግብዓት ድጋፍ እየተደረገ ነው፡፡
ለመኖ ልማቱ ውሃ የማሰባሰብ ሥራ ተሠርቷል ያሉት አቶ ኢብራሂም፤ ዝናብ በሚዘንብበት ወቅት ከአጎራባች ተራራማ አካባቢዎች የሚመጣውን የጎርፍ ውሃ የመሰብሰብ ሥራ አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ መኖ በስፋት በሚለማባቸው አካባቢዎች የሚለማውን መኖ በስፋት ወደ ማይለማባቸው አካባቢዎች የማሰራጨት ሥራ ይሠራል፡፡ በሰባቱ ወረዳዎች ውስጥ የሚለማውን መኖ ማከማቻ ባንኮችን ለማቋቋምም እቅድ ተይዟል፡፡ የሚከማቸው መኖም እንዳይበላሽ እንክብካቤ ይደረጋል፡፡
በአብዛኞቹ ወረዳዎች የሚካሄዱ የመኖ ልማት ሥራዎች በክልሉ መንግሥት ድጋፍ እየለማ ሲሆን፤ ለሰሜን ሸዋ አዋሳኝ በሆነ የአፋር ክልል ዞን ውስጥ የሚካሄደውን 35 ሄክታር መሬት የመኖ ልማት ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ ድጋፍ እየለማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተመሳሳይ ድርቁን ለመቋቋም ከፊል አርብቶ አደር በሆኑ አካባቢዎች ላይ በተጨማሪ የአገዳ ሰብሎችን ተረፈ ምርት ለመኖነት ለመጠቀም የማሰባሰብ ሥራ መሠራቱን አቶ ኢብራሂም አብራርተዋል፡፡
በክልሉ ከሚገኙ ከሁለት የስኳር ፋብሪካዎች ሞላሰስ ወስዶ ለከብት መኖነት ለመጠቀምም እንቅስቃሴ መጀመሩን ያነሱት አቶ ኢብራሂም፤ ለሞላሰስ ማቀነባበሪያ 12 ማሽኖችም መዘጋጀታቸውን አንስተዋል፡፡ በሞላሰስ አጠቃቀም ዙሪያ ስልጠና ለአርብቶ አደሮች እየተሰጠ መሆኑንም በመግለጽ ስልጠናውን እንዳጠናቀቁ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚጀምሩ አብራርተዋል፡፡
በ2010 በጀት ዓመት 928 ሄክታር መሬት የእንስሳት መኖ የተሰበሰበ ሲሆን፤129ሺህ ቶን መኖ መሰብሰብ መቻሉን የክልሉ እንስሳት፣ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 30/2011
መላኩ ኤሮሴ