
– ኮሚሽኑ የአስቸኳይ ድጋፎችን ራሱ ለመሸፈን ወደ እርሻ ሥራዎች ገባ
አዲስ አበባ፡- የሰሜን ወሎ ዞን የጸጥታ ሁኔታ መሻሻል ማሳየቱ ለቡግና ወረዳ እና ለአካባቢው ተረጂዎች የአልሚ ምግብ፣ የጤና አገልግሎት እና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስን ተደራሽ ለማድረግ እያስቻለ መሆኑን የአማራ ክልል የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ገለጸ።ለተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እንዲያስችለውም ኮሚሽኑ ወደ እርሻ ሥራዎች መግባቱን አስታውቋል።
በአማራ ክልል የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወይዘሮ ፍቅሬ ሙሉጌታ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የሰሜን ወሎ ዞን የጸጥታ ሁኔታ መሻሻል ማሳየቱ በቡግና ወረዳና አካባቢው የአልሚ ምግብ እጥረት አጋጥሟቸው በችግር ውስጥ ለነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ለማድረግ አስችሏል።
ቡግና ወረዳ በሰቆጣ ዲክላሬሽን ስር ታቅፈው የአልሚ ምግብ ድጋፍ ከሚደረግላቸው ወረዳዎች አንዱ መሆኑን የተናገሩት ወይዘሮ ፍቅሬ፤ በጸጥታ ችግር ምክንያት ለእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች አልሚ ምግቦችን ማድረስ ባለመቻሉ በችግር ውስጥ እያሳለፉ እንደነበር አውስተዋል።
በአሁኑ ጊዜ በአካባቢው አንጻራዊነት የጸጥታው ሁኔታ መሻሻል በማሳየቱ በቡግና ወረዳ 110 ሺህ ለሚሆኑ ተረጂዎች በፌዴራል አደጋ ስጋት ስራ አመራር በኩል 414 ነጥብ 6 ኩንታል አልሚ ምግብ ፣ 4ሺህ 446 ኩንታል ስንዴ ማጓጓዝ እንደተቻለ ጠቅሰዋል።ቀደም ሲልም የተለያዩ ዓለም አቀፍ እና ሀገር በቀል የእርዳታ ድርጅቶች ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
በዘንድሮው የምርት ዘመን የሰሜን ወሎ ዞን ምርታማነቱ የተሻለ ነው ያሉት ወይዘሮ ፍቅሬ፤ ይሁንና በ2015/16 የምርት ዘመን በአካባቢው አጋጥሞ የነበረው ድርቅ የዘንድሮው ምርት እስኪሰበሰብ ድረስ ተጽዕኖ አሳድሯል ብለዋል።በዚህም ምክንያት ከአልሚ የምግብ እጥረት በተጨማሪ አስቸኳይ የምግብ ርዳታ የሚያስፈልጋቸው የማህበረሰብ ክፍሎች እንዳሉ ጠቅሰዋል።
እንደ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዋ ገለጻ፤ የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ኮሚሽኑ የተለያዩ መርሃ-ግብሮችን ቀርጾ እየሠራ ነው፤ ከዚህም አንዱ ኮሚሽኑ ለተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንዲያስችለው እራሱ በእርሻ ሥራዎች ላይ ተሰማርቶ ወደ ማምረት የገባ መሆኑ ነው።በክልሉ ያለው የጸጥታ ሁኔታ ተግዳሮት ቢሆንም በተወሰኑ ቦታዎች ላይ በሰራው ስራ ማምረት መጀመሩን ወይዘሮ ፍቅሬ ተናግረዋል።
በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥም ‹‹ከተረጂነት ወደ ማምረት›› በሚል መሪ ሃሳብ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የመስጠት ስራ መሰጠቱን አስረድተዋል።ከወረዳ እስከ ዞን፣ ከሴፍቲኔት ተረጂዎችና ተፈናቃዮች እስከ አመራር ድረስ ለ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሰዎች ሃሳብን የማስረጽ ስራ ተሰርቷል ነው ያሉት።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19 ቀን 2017 ዓ.ም