የከተማዋን የካዳስተር ምዝገባ ሥርዓት ወደ ሙሉ ትግበራ የሚያሸጋግረው የመጨረሻው ምዝገባ

በሀገሪቱ የትኛው አካባቢ ለየትኛው ተግባር መዋል እንዳለበት የሚያሳይ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ እንደሌለ ይገለጻል። በከተሞች ኢንዱስትሪው፣ መኖሪያ መንደሩ፣ የንግድ ማዕከሉ፣ ሆቴሉ ወዘተ. ተቀይጦ ከኖረበት ሁኔታም መረዳት የሚቻለው ይህንኑ ነው። የከተማ ልማት ባለሙያዎች ይህን ዓይነቱ የመሬት አስተዳደር ትክክል እንዳልሆነ ሲያገነዝቡ ኖረዋል፤ የአንድ ከተማ መሬት ለመኖሪያ ቤት፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለንግድ፣ ለአረንጓዴ ስፍራ፣ ወዘተ በሚል ተለይቶ መተዳደር እንዳለበት ያሳስባሉ። ይህ ብቻም አይደለም የከተማ መሬት በሚገባ ተመዝግቦ ባለቤት ኖሮት ሊቀመጥ እንደሚገባም ይገልጻሉ።

በኢትዮጵያ በከተሞች ከመሬት ጋር ተያይዞ የሚታየውን ስር የሰደደ ችግር ለመፍታትም ሆነ ዜጎችም ከተሞችም ሀገሪቱን ከመሬት ተገቢውን ጥቅም ማግኘት እንዲችሉ ለማድረግ የመሬት ምዝገባው ለማዘመን የተለያዩ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።

መረጃዎች አንደሚያመለክቱት፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እስካሁን ከ670 ሺህ በላይ ማኅደሮች ዲጂታላይዝ ተደርገዋል። እነዚህ መረጃዎች በ11 ክፍለ ከተሞች ተለይተው ወደ አንድ ቋት ገብተዋል። በመረጃ ቋት ውስጥ የገባ መረጃ ማንም ሊያጠፋው ሊሰርዘው ሊደልዘው አይችልም።

በመዲናዋ በስፓሻል ዳታም የመሬት ባንክ፣ የካሣና የመሬት ዝግጅት መረጃዎች አንድ ላይ ተደራጅተው እንዲቀመጡ ተደርጓል። ይህም የመዲናዋ ክፍት ቦታዎች ለሚፈለገው ዓላማ እንዲውሉ እያስቻለ ነው። ይህ ሁኔታ የከተማዋ ክፍት ቦታዎች “ለምን ለምን አገልግሎት ይውላሉ?” የሚሉትን መረጃዎች በመጠቀም በቀላሉ ለሚፈለገው ዓላማ እንዲውሉ የጎላ እገዛ ያደርጋል። የትኛውም አካባቢ ያለ መሬት ባለቤት ካለው ለመሬት ወረራ እና መሰል ችግሮች መጋለጡ ይቀራል።

መንግሥት በዋናነት እያደረገ ያለው ቦታውን ማወቅ ባለቤትነትን ማስከበር ነው። ደኖች፣ የወንዝ ዳርቻዎች ወዘተ በሙሉ ለመሬት ወረራ ተጋልጠው ቆይተዋል። ከእነዚህ ቦታዎች መካከል ለልማት የሚሆኑትን በማልማት፣ ለልማት የማይበቁትን የመንግሥት እንደሆኑ ለማድረግ ተለክተው መለያ ቁጥር ተሰጥቷቸው የሚቀመጡበት ሥርዓት መዘርጋቱን መረጃው ያመላክታል።

መሬት ውስንና ውድ የሕዝብ ሀብት ነው። ይህን ሀብት በሚገባ ለማስተዳደርና ከሀብቱ ተጠቃሚ ለመሆን በቅድሚያ ዘመኑን የሚመጥን የመሬት ምዝገባ ማካሄድ/ሕጋዊ የካዳስተር ሥርዓት መዘርጋት/ወሳኝ ነው። በመሬት ማስተዳደር በኩል ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው የታመነበት ይህ የካዳስተር ሥርዓት ምዝገባ በተለያየ ደረጃ ላይ ቢገኝም በተለያዩ ከተሞች ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል፤ እየተደረገም ነው። እንደ አዳማና ቢሾፍቱ ባሉት ከተሞች ይህን ሥርዓት በመዘርጋት ለውጥ ማምጣት እንደተቻለም መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ካዳስተር በከተሞች ከመሬት ይዞታ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል። ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ተቋማት ድረስ ያለውን የመሬት ይዞታ ባለቤትነት የማረጋገጥ ሥራ በመሥራት ከመሬት ጋር ተያይዞ በዜጎች ላይ ሲፈጠሩ የነበሩ ችግሮችን በዘላቂነት ይፈታል። መሬቱ የመንገዶች ባለሥልጣን ከሆነም የመንገድ መሬት የይዞታ ባለቤትነት ማረጋገጫ ለተቋሙ ይሰጠዋል፤ ይህም ከወሰን ማስከበርና ከመሳሰሉት ጋር ያሉ ችግሮችን ይፈታል፤ በዚህ ይዞታ ላይ ምንም አይነት ሌላ ግንባታ እንዳይካሄድ ለማድረግ ይጠቅማል።

በአዲስ አበባ ከተማም ይህ የምዝገባ ሥርዓት በየዓመቱ ለሰባት ዓመታት ሲካሄድ ቆይቷል። በዚህ ዓመት ስምንተኛው የካዳስተር ምዝገባን ማካሄድ የሚያስችል እወጃ ሰሞኑን በይፋ ተደርጓል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ይዞታ ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ ይህን የመሬት ይዞታ ማረጋገጥ እወጃን አስመልክቶ ባለፈው ሳምንት ለመገናኛ ብዙኃን መገለጫ ሰጥቷል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ግፋወሰን ዴሲሳ በመግለጫው ላይ እንዳስገነዘቡት፤ በከተሞች ከመሬት ይዞታ ጋር ተያይዘው የሚስተዋሉ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት የሕጋዊ ካዳስተር ግንባታ ሥርዓት ዋነኛ መሣሪያ ነው። የከተማ የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ይህንን ዘመናዊ ሁለገብ ካዳስተር ግንባታ ሥርዓት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2022 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ እየሠራ ይገኛል። ኤጀንሲው የይዞታ ማረጋገጥና ምዝገባ ከጀመረበት 2007 በጀት ዓመት ጀምሮ እስከ 2016 በጀት ዓመት ድረስ ሰባት ጊዜ የይዞታ ማረጋገጥ እወጃ በማካሄድ በ337 ቀጣናዎች ላይ የማረጋገጥ ሥራ አካሂዷል።

በዚህም በቁራሽ መሬት 219 ሺህ 722፣ በጋራ መኖሪያ ቤቶች 173 ሺህ 136 መብት በአጠቃላይ 400 ሺህ 84 ይዞታዎች ላይ የይዞታ ማረጋገጥ ሥራ መሠራቱን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፣ በዚህም ሥራ በመብት ደረጃ 80 በመቶውን የሠራ ሲሆን፣ የሚቀረው 20 በመቶ መሆኑን፣ በዚህ ሥራ ከአዲስ አበባ ጠቅላላ የቆዳ ስፋት 54 በመቶውን መሸፈን መቻሉን አስታውቀዋል።

ኤጀንሲው በተያዘው በጀት ዓመት ለመጨረሻ ጊዜ ለስምንተኛ ዙር ቀሪ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ባሉት ባልተረጋገጡ 136 ቀጣናዎች የሚገኙ ቁራሽ መሬቶችን ለመመዝገብ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቀዋል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ ኤጄንሲው በዚህ ላይ ታኅሣሥ 10 ቀን 2017 ዓ.ም እወጃ አካሂዷል። የይዞታ ማረጋገጡ ሥራም በተመረጡ ስድስት ክፍለ ከተሞች የሚከናወን ነው። ከእነዚህ ስድስት ክፍለ ከተማዎች በዝርዝር ሲታይ በየካ ክፍለ ከተማ በወረዳ ሁለት፣ ሦስት፣ ዘጠኝ፣ 10፣ 11 እና 12 በ25 ቀጣናዎች ይከናወናል። በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በወረዳ ሁለት፤ ሶስት፤ አምስት፤ ዘጠኝ 10 እና 13 በ44 ቀጣናዎች የማረጋገጥ ሥራው ይካሄዳል።

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በወረዳ 12፣ ሦስት፣ ስድስት፣ ዘጠኝ፣ እና ወረዳ 13 በሚገኙ 19 ቀጣናዎች ይከናወናል። በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በወረዳ ስድስት፤ ሰባት፤ 10፤ 11 እና 14 የሚገኙ በ22 ቀጣናዎች የሚከናወን ነው። በቦሌ ክፍለ ከተማ በወረዳ ሦስት፣ 12 እና 13 በ15 ቀጣናዎች እንዲሁም በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በወረዳ ሦስት በሚገኙ 11 ቀጣናዎች የሚካሄዱ መሆኑን አስታውቀዋል። በእነዚህ ስድስት ክፍለ ከተሞች በሚገኙ አጠቃላይ በ136 ቀጠናዎች፣ 467 ሰፈሮች ያልተረጋገጡ ይዞታዎችን የማረጋገጡ ሥራ በስልታዊ ዘዴ ወይም በመደዳ የማረጋገጥ ሥራ ይከናወናል ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ሥራውም ከታኅሣሥ 15 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ተከታታይ አምስት ወራት ውስጥ እስከ ሚያዝያ 15 ቀን 2017 ዓ.ም ጠቅሰው፣ ሙሉ ወጪውም በመንግሥት የሚሸፈን መሆኑን በመግለጫው ጠቁመዋል።

ኤጀንሲው ከዚህም ጋር ተያይዞ ለይዞታ ማረጋገጥ በተመረጡ ቀጣናዎችና ሰፈሮች የሚገኙ ባለይዞታዎች የይዞታ ማረጋገጥ እወጃው ከተላለፈ በኋላ የይዞታ ይረጋገጥልኝ ጥያቄያቸውን ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በሚያወጡት ፕሮግራም መሠረት ቀርበው እንዲያመለክቱ ጥሪ አስተላልፏል። አመልካቾች ለይዞታ ማረጋገጥ የተመረጡ ቀጣናዎችንና ሰፈሮችን ዝርዝር መረጃ በየክፍለ ከተማው ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት እንደሚያገኙም አስታውቀዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ ለመሬት ይዞታ ማረጋገጥ በተመረጡ ቀጣናዎችና ሰፈሮች ውስጥ ብቻ ሥራው ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ባለው አምስት ወራት ውስጥ የመረጃ ልዩነት እንዳይፈጠር ሲባል ምንም ዓይነት የስመ-ንብረት ዝውውር እንዲቆም መደረጉንም አሳስበዋል። የይዞታ ማረጋገጥ ሥራው በሚከናወንባቸው ቀጣናዎችና ሰፈሮች ውስጥ ያሉ ባለይዞታዎችም ኤጀንሲው አረጋግጦ ላልመዘገበው ይዞታ ሕጋዊ ዋስትናና ከለላ የማይሰጥ መሆኑን በዚህ ወቅት ተናግረዋል። በመሆኑም አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ከታኅሣሥ 20 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ተከታታይ አሥር የሥራ ቀናት በክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አስፈላጊውን መረጃ በመያዝ የይዞታ ይረጋገጥልኝ ማመልከቻ እንዲያቀርቡም ጥሪ አስተላልፈዋል።

አቶ ግፋወሰን ከመገናኛ ብዙኃን ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችም ምላሸ እንዳብራሩትም፤ ከኮሪደር ልማቱ ጋር ተያይዞ ኤጀንሲው የሚመዘግበው ሕጋዊ ካዳስተር ባለመብቱ ያለውን የመብት ክልከላ እና ኃላፊነት ነው። ባለመብቱ ሲባልም ለምሳሌ መንገዶች ሰፍተው ከሆነ መንገዶች ባለመብት ነው። እያንዳንዱ መንገድ ላይ የሕጋዊ ካዳስተር ምዝገባ ሥራ ይከናወናል። ስለዚህ ከሰፋ የመንገዱ መብት ክልከላ ኃላፊነትን በኤጀንሲው በኩል የመመዝገብ ሥራ ይከናወናል ማለት ነው። አዳዲስ የማዘመን ሥራዎችም ሲመጡ በተመሳሳይ አሠራር ላይ አፕዴት የሚደረጉ መሆኑን ታሳቢ ሊደረግ እንደሚገባ አመላክተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሳተላይት መረጃ /ኢሜጅ/ የሚጠቀመው መቼ ነው በሚል ለቀረበው ጥያቄም ምላሽ ሰጥተዋል፤ የከተማ አስተዳደሩ በ2003 ዓ.ም በጀርመን ኩባንያ አማካይነት በመዲናዋ የአየር በረራ በማድረግ የአየር ፎቶግራፍ ካስነሳ በኋላ የመስመር ካርታዎችን በ2003 ለከተማው መዋቅራዊ ፕላን መሠረታዊ ካርታ ሆኖ እንዲያገለግል መሠራቱን አስታውሰዋል። ከዚያ ወዲህም ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ጠቅሰዋል። የ2014ቱን ወቅታዊ ለማድረግም አሁን እየተሠራበት መሆኑን አመልክተው፣ በአዲስ አበባ ከተማ ከሳተላይት ምስል ጋር ከተያያዘው ይልቅ የበለጠ ግልፅነት ባለው የመሬት ሰርቬይ እየተሠራበት መሆኑን አመላክተዋል።

እንደ አቶ ግፋወሰን ማብራሪያ፤ የከተማ መሬት በጣም ውስን ከመሆኑ የተነሳ የተረጋገጠ ሥራ ይፈልጋል። የሳተላይት መረጃ /ኢሜጅ/ን በመጠቀም ሲሠራ ሰፊ በሆነ እና የእርሻ መሬት አካባቢ በሚገኝ መሬት ላይ ጥቅም ላይ ይውላል። በመሆኑም እርገጠኛነትን /ፕሪሲሽን/ በማይፈልጉ ቦታዎች የመሬት ሰርቬይ ጥቅም ላይ እንዲል የሚያስችሉ መሣሪያዎች አሉ።

እንደ ዲፈሬንሻል ጂፒኤስ ያሉ መሣሪያዎችም አሉ። አዲስ አበባ ዓለም እየተጠቀመበት ያለውን እንደ “ኮርስ ስቴሽን” ያለውን የቅየሳ መረጃ መሰብሰቢያ መሣሪያ እንደምትጠቀም ገልጸዋል። ይህ መሣሪያ ዘንድሮ እንደሚተከልም ጠቁመዋል። በዚህም ምክንያት በከተማዋ የሳተላይት ኢሜጆችን የመጠቀሙ ዕድል ከፍተኛ ይሆናል ብለዋል።

አቶ ግፋወሰን እንዳስረዱት፤ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ2022 ሁለገብ ካዳስተር ይገነባል። ይህ ሲባል እነዚህ የሚገነቡ ሁለገብ የካዳስተር ሥራዎችን እንደ አነባበሮ በማድረግ ሲወሰዱ ሦስት ንብርብሮች ይኖራሉ። የመጀመሪያው ንብርብር ሕጋዊ ካዳስተር ነው። ከተማው ውስጥ ያለው መብት ክልከላና ኃላፊነትን እንዲሁም ምድረ ገፃዊ ካርታ መረጃው ይሰበሰባል።

ከዚህ በመቀጠልም ፊዚካል ካዳስተር የሚባል አለ፤ ጣራና ግድግዳ፣ ንብረት ግመታ እና የመሬት ግመታን የሚያካትት ሁለተኛ ንብርብር አለ። በሦስተኛ ንብርብርነት የሚያዘው የመሠረተ ልማት ካዳስተር ነው። በመሆኑም ከአምስት ዓመት በኋላ የሚደረስበት ሁለገብ ካዳስተር እንጂ ሕጋዊ ካዳስተር አይደለም። አሁን የተጠናቀቀው ያለው ሕጋዊ ካዳስተር ነው፤ በየደረጃው የሚጠናቀቅ ስለሆነ በዚህ ልክ መያዝ ይገባል።

የዘንድሮው የካዳስተር ምዝገባ ለመጨረሻ ጊዜ ሲባልም የከተማውን መረጃ፣ የመብት መረጃ፣ ፊዚካል መረጃ ሙሉ ለሙሉ ዘንድሮ እንደሚሸፈን አስታውቀዋል። የካዳስተር ምዝገባው ከመሬት ሊዝና ሕገ ወጥነት ጋር ተያይዞ ሕጋዊ ካዳስተር ሀብታችንን ቆጥረን የምናውቅበት ሥርዓት ነው ሲሉ ጠቅሰው፤ ምን መሬት አለ? ማን ምን ያህል ይዟል? መብት ክልከላና ኃላፊነቱ ምንድነው? በሚል የማረጋገጡ ሥራ ከተከናወነ በኋላ ለዜጎች በይዞታቸው ላይ ዋስትና የሚሰጥበት ሥርዓት ነው።

ተቋሙ ከቅድመ ምዝገባ በኋላ በ24 የተለያዩ ርዕሶች አገልግሎት የሚሰጥበት ራሱን የቻለ አሠራር እንዳለው ዋና ዳይሬክተሩ አመላክተዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ በዚያም አገልግሎት ይሰጣል፤ አገልግሎት ከሚሰጥበት አሠራር ውጪ ገቢ ያመነጫል ማለት ነው። በዚህ በጀት ዓመት በዕቅድ የተያዘለትን ወደ 10 ቢሊዮን ብር አካባቢ ከአገልግሎት የሚገኝ ገቢ ይሰበሰባል። የማረጋገጥ ሥራውን በመሥራት፣ ምዝገባ በማከናወን፣ አገልግሎት በመስጠት ገቢ የሚገኝበት ሥርዓት መከናወኑን አስረድተዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You