ዓይናማ ልቦች…

እንደ መነሻ

በአንድ ሥፍራ ለአንድ ዓይነት ዓላማ በቀጠሮ የተገናኙት እናቶች ዛሬም ስለልጆቻቸው ልዩ ወግ ይዘዋል። እነሱ ሁሌም ቢሆን ስለነዚህ ልጆች ማውጋትና ማሰብን አያቆሙም። ስለ እነርሱ እንርሳ፣ እንተው ቢሉ እንኳን ፈጽሞ አይቻላቸውም። በጀርባቸው፣ ባያዝሏቸው በልባቸው ያኖሯቸዋል። በእጅ ባይዟቸው፣ በሃሳብ ከእነሱ ጋር ናቸው። ለእነዚህ እናቶችና የሌሎቹ ኃላፊነት ተመሳሳይ አይደለም። ልጆቹ እንዳሻቸው የሚሮጡ፣ የሚጫወቱ፣ የሚናገሩ አይደሉምና ልዩ ትኩረትን ይሻሉ።

አብዛኞቹ የጨቅላነት ዕድሜያቸውን በተደጋጋሚ ቀዶ ሕክምና አሳልፈዋል። ይህ ወቅት ለእነዚህ ዕንቦቀቅላዎች አዲስ ዓለምን መተዋወቂያና መግባቢያ ብቻ አይደለም። አብዛኞቹ ይህን ምዕራፍ በታላቅ ስቃይና ህመም ይሻገሩታል። ከልጆቹ እናቶች አብዛኞቹ ሕይወትን በፈታኝ ኑሮ የሚገፉ ብቸኞች ናቸው። አባወራዎቻቸው የጤና ችግር ያለባቸው ልጆች አባት መባልን አይሹም። ይህ እውነታ ገና በጠዋቱ ጥለዋቸው እንዲሸሹ ምክንያት ነው።

ጥቂት የማይባሉት እናቶች ኑሯቸው ጎስቋላና ከእጅ ወደ አፍ የሚባል ነው። ጉልበታቸውን ገብረው፣ በላባቸው ወዝ የሚያድሩ በመሆናቸው ውሏቸው በችግር ይገፋል። እነዚህ ሴቶች በእርግዝና ጊዜያቸው የፎሊክ አሲድን በአግባቡ ባለመውሰዳቸው በወለዷቸው ልጆች ላይ የጤና እክል እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።

የነርቭ ዘንግ ክፍተትና የጭንቅላት ውሃ መቋጠር በሳይንሳዊ አጠራሩ ‹‹ስፓይናቢፊዳና ሀይድሮሴፋለስስ›› በአብዛኛው ችግሩ የሚታወቀው በእርግዝና የመጨረሻ ጊዚያት በመሆኑ ከነችግሩ የሚወለዱ ህጻናት ቁጥር ይጨምራል። እናቶቹ ስሜታቸውን አመሳስሎ ቋንቋቸው አንድ ባደረገው ቆይታ ስለልጆቻቸው ኑሮና ሕይወት እየተወያዩ ነው። ሁሉም በሚባል መልኩ ኑሯቸው በአንድ ይጋመዳል። የአንዳቸው ችግር ግልባጭ ለሌላቸው የሕይወት መስታወት ነው። አብዛኞቹ በችግር ማስነው፣ በመከራ ታግለው ሕይወትን ይገፋሉ። ሙሉ ማንነታቸውን ለልጆቻቸው ሰጥተዋልና ጌጥና ውበት አያምራቸውም።

እነሆ! በ ሆፕ ኤስ ቢ ኤች /Hop SPH/ ቅጥር ግቢ ተገኝተናል። በበርካታ ወላጆች፣ እንግዶችና ህጻናት መሀል። በሥፍራው የመገኘታችን ሚስጥር የአዲሱን ዓመት መግባት ተከትሎ ወቅቱን በታላቅ ተስፋና ብሩህነት ለመቀበል ነው። ይህ አጋጣሚ ደግሞ ወላጆችን አገናኝቶ ልብ ለልብ ያወያያል። ሁሉም ብሶታቸውን፣ ሀዘንና ደስታቸውን ያወጋሉ። ስላለፈው ትናንት ሰላሉበት ዛሬና ስለመጪው ነገ እንዲያወጉ እድል ይፈጥራል።

እያንዳንዱ ጊዜ በሁሉም እናቶች ልቦና በዋዛ የማይፈዝ ዐሻራን አኑሯል። ሁሉም ስለልጆቻቸው ወጥተው የወረዱበት፣ በቤት ኪራይ የተንገላቱበት፣ በቀን ሥራ የደከሙበት፣ በችግር የተፈቱበት እውነትን ሰንቀዋል። አብዛቹ ዛሬም በጉስቁልና ውስጥ ናቸው። ስለ ልጆቻቸው መኖር ታላቅ ዋጋን ከፍለዋል። የእናቶቹ በሕይወት መቆም ለልጆቹ ታላቅ ዋስትና ነው። እነሱ ከሌሉ የእስትንፋቸው መቀጠል አደጋ ውስጥ ይወድቃል። ልጆቹ እንደ እናት ሁሉን ችሎ የሚያሳድግ፣ ነገን የሚሻግር አለኝታ ከጎናቸው የለም።

ይህን ሀቅ ሲያስቡት እናቶች ቅስማቸው ተሰብሮ ከሀዘን ይወድቃሉ፣ ይተክዛሉ። እናም የአብዛኞቹ ስሜት ተመሳስሎ በአንድ ይጋመዳል። ሁሌም የልጆቻቸው ሞት ከእነሱ ህቅታ በአንድ ቀን እንዲቀድም ይመኛሉ። ልጆቻቸውን ቀብረው እነሱ ቢከተሉ እፎይታቸው ነው። ይህ ይፈጸም ዘንድ አብዛኞቹ ለፈጣሪያቸው ይጸልያሉ፣ ይማልዳሉ።

ዕለቱን በእውነታ…

በዚህ ቀን በሥፍራው የተገኙ ወገኖች በድርጅቱ የሚታገዙ እናቶች ብቻ አልነበሩም። ስለህመሙ ግንዛቤ የሚሰጡ ባለሙያዎችና ድርጅቶች፣ አጋር አካላትና ተባባሪ ተቋማት፣ ልበ ቀና በጎ ፈቃደኞችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል። ዕለቱ ወላጆች እርስ በእርስ ለመወያየት ዕድል ያገኙበት ቀን ነው። ጥቂት ቢሆኑም አንዳንድ ጠንካራ አባቶች ከሚስቶቻቸው ጋር በሥፍራው ታድመዋል። እነሱ በልጆቻቸው ላይ የሆነውን እውነት በእኩል ሊጋሩ ልባቸው የቀና አባወራዎች ናቸው።

ጥቂት የማይባሉ እናቶች የሕይወት ተሞክሯቸውን ማጋራት ይዘዋል። አብዛኞቹ ልጆቻቸውን ያለ አባት የሚያሳድጉ፣ በችግርና መከራ ሕይወትን የሚገፉ ናቸው። ብዙ አሳዛኝ፣ አስገራሚ ድምጾች እየተሰሙ ነው። ሁሉም መልከ ብዙ ገጽታን በተላበሱ ሀቆች ተሸፍነዋል። ሽፍናቸውን ሲገለጥ ዓይንን በዕንባ ይሞላሉ። ውስጥን አሸብረው አንገት ያስደፋሉ።

ማህሌት ሽቶ የህጻን ያሬድ ወላጅ እናት ነች። የብቸኝነት ሕይወትን የጀመረችው ባለቤቷ የስድስት ወር ነፍሰጡር ሆና ጥሏት ከሄደ ጊዜ ጀምሮ ነው። በብዙ ችግሮች አልፋ ልጇን ወልዳ ብትስምም ደስታዋ ሙሉ አልሆነም። ትንሹ ያሬድ በዕድሜው ቆሞ ለመሄድ፣ ለመዳህ አልሆነለትም። እግሮቹ እየዛሉ ሰውነቱ ይንቀጠቀጣል። ያለአንዳች ለውጥ ጥቂት ጊዚያት ተቆጠሩ። የአንድ ዓመት ልደቱን ባከበረ ማግስት እናት ቆሞ መሄዱን፣ እንደ እኩዮቹ መሮጥ፣ መንገዳገዱን ጠበቀች። ዓይኖቿ የተመኘችውን አላሳይዋትም። ሁለት ዓመታት ሊሞላው ጥቂት ወራት ሲቀረው ልጇ በሀይድሮሴፋለሰስ መጠቃቱ ታወቀ። ይህ ጊዜ ኑሮን በደባልነት ለምትገፋው ማህሌት እጅግ ከባድ ይሉት ነው። አብረዋት ከሚኖሩ ጓደኞቿ በቀር ‹‹አለሁሽ›› የሚላት ወዳጅ ዘመድ ጎኗ የለም። የልጁን መወለድ እንኳን የማያውቀው ባሏ ድምጹ አይሰማም። ህጻኑ አስቸኳይ ሕክምና ያስፈልገዋል። ይህን ለማድረግ በቂ ዝግጅትና የገንዘብ አቅም ግድ ነው።

ማህሌት ገንዘብም ረዳትም የላትም። ልጇን አዝላ ልብስ አጠባ ብትውልም ገቢዋ ከቤት ኪራይ በላይ አያሻገራትም። እንዲያም ሆኖ ልጇን ካጋጠመው ህመም መታደግ አለባት። እናት በሆነባት ሁሉ ተጨነቀች፣ ግራ ገባት። አሁን ተአምር ከመጠበቅ ውጭ ስለራሷ ርግጠኛ አልሆነችም። በሀዘን ተውጣ ሳለ አንድ ቀን ከልበ መልካሞች ጋር ተገናኘች። እነሱ እውነታውን አይተው ዝም አላሏትም። ትራንስፖርት ሰጥተው ወደ ዘውዲቱ ሆስፒታል አመላከቷት። ማለዳውን ሆስፒታል የደረሰችው ማህሌት ልጇን ሐኪሞች ፊት ለማቅረብ መረጃ ጠየቀች። በእጇ የሪፈራል ወረቀት እንደሚያስፈልግ ተነገራት።

መላ መፍትሔው ቢጠፋት በግራ መጋባት ማልቀስ፣ ማንባት ያዘች። አሁንም ልበ መልካሞች አልጨከኑባትም። ካርድ አውጥታ ወደ ነርቭ ክፍል ተላከች። ህጻኑ ለተመሳሳይ ሕክምና ወደ ሌላ ሆስፒታል መሄድ ነበረበት። ከወራት ቆይታ በኋላ ተራው ደርሶ ሕክምናው ተጀመረ። ለትንሹ ልጅ የቀዶ ሕክምና ማድረግ ግድ ሆኗል። ለዚህ ሕክምና አስፈላጊ ወጪዎች ይጠበቃሉ። ማህሌት እንኳን ለሕክምና ለትራንስፖርት የሚረዷት ሌሎች ናቸው። ሆስፒታል ልጁን ይዛ በቆየች ጊዜ በርካቶች ምሳ እየቋጠሩ ጠየቋት፤ አይዞሽ ሲሉ አበረቷት። አሁንም በሐኪሞች ቀናነት የታሰበው ሁሉ ተከወነ። እንዳያልፉት የለም ልጇ ከአስር ጊዜ በላይ የቀዶ ሕክምና ተደርጎለት ማገገም ያዘ።

ዛሬ ህጻን ያሬድ ለመራመድ፣ ለመሮጥ እየታገለ ነው። የንግግር ችግር የለበትምና ከእናቱና ከሌሎች ጋር ይግባባል። እናት ማህሌት ልጇ ዕድሜው ለትምህርት መድረሱን ስታይ እንደ እኩዮቹ ትምህርት ቤት እንዲሄድ ተመኘች። ግን እሱን ለማስተማር ዛሬም አቅም የላትም።

ሁሉም እንደ አንድ …

ገና በማለዳው እንግዶቻቸውን በክብር መቀበል የጀመሩት የሆፕ ኤስ ቢኤች ግብረሰናይ ድርጅት መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ቤዛ በሻህ ለታዳሚዎቹ የልባቸውን ለማውጋት ወደ መድረኩ ብቅ አሉ። ወይዘሮ ቤዛ ይህን ድርጅት ለመመስረት ምክንያት የሆናቸው የሁለተኛው ልጃቸው እውነታ ነበር። ትንሹ ህዝቅኤል ሲወለድ ጀምሮ አብሮት የዘለቀው ህመም የንግግር፣ የመስማትና የማየት ችሎታውን ነጥቆታል። ዘወትር ከእናቱ የሚግባባው በንግግር አልባው ደማቅ ፈገግታ ብቻ ነው። በፈገግታው ውሎ ያድራል። በፈገግታው ከሁሉም ይኖራል። ይህ ማንነት በእናቱ ቤዛ ዘንድ ትርጉም አላጣም። ውስጣቸው ዘልቆ የማይፈዝ የተስፋ ብርሃን ፈነጠቀ። ይህ ብርሃን ከትናንት አልፎ ነገን ሲያሻግር ምክንያት ነበረው። ዛሬ ለብዙኃን እሱን መሰል ልጆች በድርጅቱ መጠሪያ ተስፋን ሰይሞ ሕይወታቸውን ይጋራ ይዟል። እናት ቤዛ ይህን ድርጅት ሲያቋቁሙ የበርካታ እናቶችን ስሜት በወጉ አውቀውት ነው።

እሳቸው ከማንም በላይ በእነሱ ጫማ እግራቸውን አስገብተው ችግራቸውን ለክተዋል። ህመም ስቃያቸውን ለይተዋል። የእሳቸው ልጅ ህመም የሌሎች መሰሎቹ፣ እኩዮቹ ስሜት ነው። በእሱ ውሰጠት አሻግረው የብዙኃኑን ስቃይና ችግር አስተውለዋል። ቤዛ ካሏቸው ሁለት ልጆች የመጀመሪያዋ ሳሮን ትባላለች። እሷ ከታናሽ ወንድሟ ህዝቅኤል በእጅጉ የተለየች ናት። እንደ ማንኛውም ጤነኛ ልጅ ታወራለች፣ ትሮጣለች። እድሜዋ ለትምህርት ሲደርስም ትምህርት ቤት ገብታ ዕውቀት እየቀሰመች ነው።

ህዝቅኤል ግን ምግብ ከመመገብና ከመሳቅ ውጭ የሚጠበቀው ለውጥ እየታየበት አይደለም። ለእናት ቤዛ ሁለቱም ልጆች የራሳቸው ፍሬዎች ናቸው፤ በእነሱ መኖር በእጅጉ ደስ ይላቸዋል። ሁሌም እንደሚሉት ግን ከሁለቱ የሚጠበቁት የየዕለት ውጤት ፍጹም የተለያየ ነው። እንዲህ መሆኑ ግን ለልጆቻቸው የሚገባውን ዕድል እንዲነፍጉ አላስገደዳቸውም። ለሳሮን ካሰበችው ግብና ዓላማ እንድትደርስ፣ በትምህርቷ፣ በጤናዋ፣ በመንፈሳዊ ሕይወቷ፣ ከሌሎች ጋር በሚኖራት ማህበራዊ ግንኙነትና በሌሎችም እንደ እናት የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። ለህዝቅኤል ደግሞ ምግቡ እንዳይጎድልበት፣ ጤናው እንዳይዛባበት፣ ኢንፌክሽን ተፈጥሮ እንዳይጎዳ፣ እንዳይታመም ደማቅ ፈገግታው እንዳይፈዝ ግዴታቸውን ይወጣሉ። ይህ እውነት የወይዘሮ ቤዛ የእናትነት ግዴታና ድርሻ ሆኖ አብሯቸው ይዘልቃል።

ለምን ?

የሥራ ቦታዋ በዘውዲቱ ሆስፒታል እንደሆነ የገለጸችው ወይዘሮ ሰላም የሁለት ልጆች እናት ነች። ሁለተኛው ልጇ የአብስራ ይባላል። እሱን በማግኘቷ ደስተኛ መሆኗን ደጋግማ ትገልጻለች። የአብስራ ባጋጠመው የሀይድሮሴፋለስስ ችግር ብዙ ተፈትኗል። እናት እሱን ለማስተማር ያልሆነችው የለም። ያለበትን የጤና ችግር የተመለከቱ ትምህርት ቤቶች እንደሌሎች በደስታ ተቀብለው ሊያስተምሩት አልፈቀዱም። ‹‹ልጄን አስተምሩልኝ›› ስትል በርካታ ትምህርት ቤቶችን ጠይቃለች። ከአንዳቸውም ግን በጎ ምላሽ አላገኘችም። እንዲያም ሆኖ ተስፋ አልቆረጠችም።

እግሯ እስኪቀጥን እየዞረች የአስራ ሁለት ትምህርት ቤቶችን ደጃፍ አንኳኳች። ‹‹ግቢ›› ብለው በሩን የከፈቱላት ፈቃደኞች አልነበሩም። የአብስራ ዛሬ 10 ዓመት ሆኖታል። አይናገርም፣ አይሰማም። እይታውም እምብዛም አይደለም። እዚህ ዕድሜው እስከሚደርስ በመውደቅ መነሳት መሀል ተንገላቷል። እናት ሰላም ከልጇ ጋር በርካታ ፈተናዎችን ተሻግራለች። ዛሬም ግን ልጆቿን ግራና ቀኝ ሳትለይ እኩል እያኖረች ነው።

ሰላም የእሷን ሕይወት መነሻ አድርጋ ስለሌሎች እናቶች ኑሮ ታስባለች። እንዲህ ዓይነት ወገኖች ችግራቸው የበዛ ነው። በተለያዩ ጉዳዮች ይፈተናሉ። አብዛኛዎቹ ልጆች የዳይፐር ተጠቃሚዎች ናቸው። ጥቂት የማይባሉትም በዊልቸር እንደሚንቀሳቀሱ ይታወቃል። ለእነዚህ ዜጎች የትምህርትና የሌሎች ጥቅሞች ድጋፍ ማድረግ አልተለመደም። እንዲህ መሆኑ በወጣትነት ዕድሜ የሚገኙ በርካቶች ሳይቀር ደጁን እንዳያዩ ቤት ተዘግቶባቸው እንዲኖሩ ተገደዋል። አንዳንዶች ለእነዚህ ልጆችና ቤተሰቦቻቸው ያለው አመለካከት የተንጋደደ ነው። ችግሩን ከመካፈል ይልቅ አጋጣሚውን ርግማንና ቁጣ አድርጎ ማሳቀቅን ልምድ አድርጓል።

ይህ ዓይነቱ እውነት ሁሌም ለእናት ሰላም የየዕለት ሀዘንና ቁጭትን ፈጥሯል። መልስ ባታገኝም ለምን ስትል ራሷን ትጠይቃለች። ሰላም ሁሌም እነዚህንና ሌሎች ህጻናትን በበጎ ፈቃደኝነት ለማገዝ፣ ለማገልገል ልቧ ይፈቅዳል። ልክ እንደ እሷ ሁሉ የመንግሥት አካላትና፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ህብረተሰቡና የሚመለከታቸው ሁሉ ትኩረት እንዲሰጡት ምኞቷ ነው።

በድርጅቱ ሸክማቸው ከከበዳቸው፣ ኑሮና ሕይወት ከፈተናቸው ቤተሰቦች ጎን ቆመው ‹‹አለናችሁ›› የሚሉ አጋሮች በርካታ ናቸው። እነሱ የብዙኃን እናቶችና ልጆቻቸው ድምጽ ጎልቶ ይሰማቸዋል። ባገኙት ዕድልና አጋጣሚ ሁሉ ቀኝ እጅ ለመሆን ወደ ኋላን አያውቁም። የእነሱ ክፍያና ጥቅም የሰዎችን ዕንባ ማበስ፣ የተቸገሩትን ጎን መዳበስ ነው። ዘወትር በጎደለው ሁሉ ተገኝተው ባዶውን ይሞላሉ። ሸንቁሩን ይደፍናሉ።

ዓይናማ ልቦች …

አቶ እስክንድር ላቀው የሆፕ ኤስ ቢ ኤች /Hop SPH/ የክብር አምባሳደር ናቸው። አቶ እስክንድር በእነዚህ ቤተሰቦችና ልጆቻቸው መካከል መገኘታቸውን እንደ ታላቅ ዕድል ይቆጥሩታል። እንደ እሳቸው እሳቤ ድርጅቱ የተስፋ ማሳያ እንደመሆኑ ሕይወትን አለምልሞ ያቆያል። ትዕግስትና ጥረት ደግሞ ኑሮን ታግሎ የማሸነፊያ መንገዶች ናቸው። የሰው ልጅ ተስፋ በቆረጠ ጊዜ ብዙ ውጥኖቹ ይበላሻሉ። ማሸነፍና መሸነፍ ደግሞ ከማንነት ይመነጫል። አንድ ሰው ውስጡን ካሸነፈ በሁኔታዎች ሁሉ አሸናፊ ነው። በተቃራኒው ውስጡ ለሽንፈና እጅ ለሰጠም ተስፋ፣ ኑሮና ሕይወት ይሏቸው እውነታዎች እንደታሰቡት አይሰምሩም።

አቶ እስክንድር እነዚህን ሀቆች መሠረት ማድረግ የውስጥ ስኬትን ለማስመር እንደሚያግዝ ያምናሉ። ይህ እምነታቸውም ከድርጅቱ ጎን እንዲቆሙና በርካቶችን ‹‹አይዟችሁ›› ብለው እንዲያበረቱ አግዟቸዋል። አንዳንዴ ሰዎች ከፍ ያለ ሀዘን ሲያገኛቸው ክፉኛ ይሰበራሉ የሚሉት እስክንድር እንደ ወይዘሮ ቤዛ ያሉ ጠንካሮች ደግሞ ስብራቱ ሳይብስባቸው ራሳቸውን ጠግነው ለሌሎች ጭምር ወጌሻ መሆናቸው እንደሚያበረታ ርግጠኛ አድርጓቸዋል።

የክብር አምባሳደሩ ድርጅቱን በእግሩ ለማቆም፣ ዕውቀት፤ ጊዚያቸውን ላዋጡ፣ ጉልበት አቅማቸውን ለከፈሉ ሁሉ ምስጋናን ችረዋል። እሳቸውም እንደ ክብር አምባሳደርነታቸው ለልጆቹና ለወላጆቻቸው ጉዳይ በየትኛውም መድረክና አጋጣሚ ሁሉ ድምጽ ለመሆን ቃል ገብተዋል። በዕለቱም አቶ እስክንድር የእናት ማህሌትን ችግር በመረዳት ለልጇ መማሪያ ቁሳቁሶች ለማበርከት መዘጋጀታቸውንና እገዛው ለሌሎችም ጭምር እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ለአንድ ዓላማ ለተመሳሳይ ተግባርና ግብ በአንድ ሥፍራ የታደሙ ወገኖች በሚተያዩ፣ በሚናበቡ ልቦቻቸው በወጉ ይግባባሉ። የትናንቱ የሕይወት መንገዳቸው ለዛሬ አሻግሮ ሲያሳድራቸው በተደላደለ መንገድ አልፈው አይደለም። ነገ የልጆቻቸው ዓለም የተሻለ ይሆን ዘንድ ትግላቸው እንዲህ ቀጥሏል። ብርቱዎቹ፣ ጠንካራዎቹ ወላጆች።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You