ኢትዮጵያ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ጋር የነበራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ረጅም ዘመን ያስቆጠረና ታሪካዊ ነው። ኢትዮጵያን ሲመሩና ሲያስተዳድሩ የነበሩ መሪዎቿ በየዘመናቸው የሀገሪቱን ሀያልነትና ዝና ብሎም ብሔራዊ ጥቅሟን ባስጠበቀ መልኩ ከበርካታ ሀገራት ጋር ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ቆይተዋል።
በመሪዎቿ የአመራር ጥበብና ብልሀት ከሌሎች ሀገራት ጋር የምታደርገው ሁለንተናዊ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በትውልድ ቅብብሎሽ አልፎ የኢትዮጵያን ከፍታና ዓለም አቀፍ ተሰሚነት ይበልጥ በማሳደግ ዛሬ ላይ ደርሷል።
እንዲህ አይነቱ የአመራር ጥበብና ብልሀት ከመሪዎቹ በኩል በመኖሩም ነው ኢትዮጵያ ከተቀረው ዓለም ጋር ያላት የዲፕሎማሲ ግንኙነት በጊዜ ሂደት አድጎና ጎልብቶ የዛሬው ዘመን ላይ የደረሰው። አሁንም ቢሆን የዚህ ዘመን የሀገሪቱ መሪዎች የዚችን ስመ ገናና እና የብዙ ታሪክ ባለቤት የሆነችውን ሀገር አደራ ከአባቶቻቸው ተረክበው ይህንኑ ዝናዋንና ታላቅነቷን ባስጠበቀ መልኩ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን እያስቀጠሉ ይገኛሉ።
በተለይ በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ ከተደረገ ወዲህ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተለያዩ የአፍሪካ፣ እስያ፣ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ ሀገራት ተጉዘው የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በማስረዳትና ከዚህ በፊት ሀገሪቱ የነበራትን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከርና ዳግም እንዲታደስ በማድረግ ትልቅ የዲፕሎማሲ ሥራ ሠርተዋል።
በምላሹም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሄዱባቸው ሀገራት ታላላቅ መሪዎች በተከታታይ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣትና የሀገሪቱን ትክክለኛ ምስልና ገፅታ አይተውና ተረድተው ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በሁለንተናዊ መልኩ አጠናክረው ለማስቀጠል ይሁንታቸውን ገልጸዋል።
የሰሞኑ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝትም የዚሁ ጠንካራ ዲፕሎማሲ ውጤትና ኢትዮጵያ በነዚህ ሀገራት ታላላቅ መሪዎች ያላት የተሰሚነት አቅም እያደገ ስለመምጣቱ ምስክር ነው።
ኢትዮጵያ ከተቀረው የዓለም ሀገራት ጋር አሁን ላይ እያደረገችው ያለው ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከፍ ወዳለ ደረጃ ተሸጋግሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ተሰሚነት ይበልጥ እንዲጎለብትና ከዚህ በላይ እንዲቀጥል ከመንግሥትና ከዚህ ጋር በተያያዘ ከሚጠቀሱ አካላት ተጨማሪ ሥራዎችን መሥራት ይጠይቃል።
አሁን ባለው ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ የዲፕሎማሲው አቅጣጫና አካሄድ እለት በእለት እየተቀያየረ መጥቷል። ለዚህ ተቀያያሪና ተለዋዋጭ ዲፕሎማሲ መስመር ደግሞ ራስን ከወቅቱ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ መሄድ ይጠይቃል። ሀገራት እርስ በርስ የሚያደርጉት ግንኙነት በአብዛኛው ብሔራዊ ጥቅምን፣ የሰጥቶ መቀበልና የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ ነው።
ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ለዚህ ወቅታዊና ተለዋዋጭ የዲፕሎማሲ አቅጣጫ የተለየ ስልት ይዞ መቅረብ ይጠይቃል። በተለይ የታላላቅ ሀገራትን ልብ ለማሸነፍና በእነርሱ ዘንድ ያለንን ተሰሚነትና ተቀባይነት ከፍ ለማድረግ በእነሱ ደረጃ የሚመጥን የዲፕሎማሲ አቅም መገንባት ያስፈልጋል።
ለዚህ የሰላ አንደበትና እውቀት ብሎም የማሳመን ብቃት ያላቸው ዲፕሎማቶችን ማብቃትና መመደብ ያስፈልጋል። በእውቀትና በልምድ የበሰሉ ዲፕሎማቶችን የማፍራቱ ጉዳይ ገና ከታዳጊነት ጀምሮ ሊሠራበት ይገባል። እንዳውም ፖለቲካን ሳይሆን ሙያን ብቻ መሠረት አድርገው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ጥብቅና የሚቆሙና
የሚሟገቱ ዲፕሎማቶችን ነው በብዛት ማፍራት የሚጠበቅብን።
በሌላ በኩል ደግሞ የዲፕሎማቲክ ሥራውን ሊያሳልጡ የሚችሉ ሰዎችን ብቻ በትክክለኛው መስፈርት መርጦ ትክክለኛው ቦታ ላይ መመደብ ይገባል። በምጣኔ ሀብት የበሰለና ቁንጮ የተባለ ምሁር በዲፕሎማሲው ጎራ ይሳካለታል ማለት አይቻልም።
ባይሆን የዲፕሎማሲ እውቀቱን ቢያሰፋ ከምጣኔ ሀብት እውቀቱ ጋር አዛምዶ ኢትዮጵያን ከተቀረው ዓለም ጋር በምታደርገው ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ዙሪያ የራሱን ሙያዊ አብርክቶ ሊያደርግ ይችላል።
የዲፕሎማሲ ሥራ ሁሌም ቢሆን ወጥነት ያለው፣ ተከታታይና ወቅቱን የዋጀ ጠንካራ መሆን ይጠበቅበታል። በዲፕሎማሲ ሥራ እንቅልፍ የለም። መዘናጋት ብዙ ሀገራዊ ጥቅሞችን ያሳጣል። የተሰሚነትን አቅም ያስነጥቃል።
የዲፕሎማሲ ሥራውን ይበልጥ በማዘመንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ አቅም ገንብቶ ተሰሚነትን ለመጨመር መንግሥት ሌት ተቀን መሥራት ይጠበቅበታል። ከዚሁ ጎን ለጎን በዲፕሎማሲው መስክ ቱባ እውቀት ያላቸውን በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ምሁራን እውቀታቸውን በሚገባ መጠቀም ይገባል።
ኢትዮጵያውያን ምሁራኑ ከሀገሪቱ ጎን መቆም ይጠበቅባቸዋል። የመንግሥትን ጥያቄ ተቀብለውና ከጎኑ ቆመው በማገዝ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ አቅም ማሳደግና ተሰሚነቷም እንዲጨምር የማድረግ ሀገራዊ ኃላፊነት አለባቸውና ለዚህ ሊሠሩ ይገባል።
በተመሳሳይ በውጭ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሊህቃንም ያላቸውን እውቀትና ልምድ ተጠቅመው የበኩላቸውን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ይህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የተሰሚነት አቅም ከመጨመር ባለፈ ክብሯንና ዝናዋን ጠብቃ እንድትቀጥል ያስችላታል። የዲፕሎማሲ ሥራውን ከማጠናከር ባለፈ ግን የኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነት ይበልጥ ለማሳደግ በሀገር ውስጥ ተጨማሪ የቤት ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል።
ለአብነትም በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ማምጣት ዋናውና ትኩረት ተደርጎ ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ገበያ አንዱ ራስን ለመሸጥ የሚያስችለው መንገድ በሀገር ውስጥ አስተማማኝ ሰላምና ደህንነት መኖር ነው። ይህ ደግሞ አሁን ላይ እየተሠራበት ያለ ጉዳይ ቢሆንም አሁንም አስተማማኝ ሰላም ለማረጋገጥ ተጨማሪ ሥራዎች መሥራት አለባቸው።
ሀገራት የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የተለያዩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን ይከተላሉ። ከፖሊሲና ስትራቴጂያቸው ባለፈ ግን በውስጣቸው ያለው ሰላምና መረጋጋት ሌሎች ሀገራት በቀላሉ ገብተው በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ተሰማርተው እንዲሰሩ በር ይከፍታል።
በኢትዮጵያም አሁን ላይ አንፃራዊ ሰላም በመኖሩ የተለያዩ ሀገራት በተለያዩ አማራጮች መዋእለ ንዋያቸውን ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እያሳዩ ነው። ሆኖም የተሟላ የሰላም ሁኔታ ማረጋገጥ አሁንም ይቀራል፤ በዚህ ላይም ሊሠራ ይገባል።
ያኔ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተሰሚነት ማሳደግና ማጎልበት ትችላለች። ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ተሰሚነት በጎለበተ ቁጥር ደግሞ የባሕር በር ጥያቄዋን ጨምሮ ሌሎችም ጥቅሞቿ ይከበራሉ። በሌሎችም ሀገራት መሪዎች የመጎብኘት እድሏን ታሰፋለች። ያላትን ታሪካዊ ዝና እና ክብርም አስጠብቃ ትቀጥላለች!!
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19 ቀን 2017 ዓ.ም