አዲስ አበባ፦ 38ኛውን የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ለመሳተፍ የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ሆቴሎች በበቂ ሁኔታ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማህበር አስታወቀ ።
የማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢና ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አስቴር ሰለሞን በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ ለአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ስብሰባ የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል በሆቴሎች በኩል በቂ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።
በርካታ እንግዶች ወደ ሀገር ቤት ሲመጡ በቀዳሚነት ተጠቃሚ ከሚያደርጓቸው መካከል ሆቴሎች ይጠቀሳሉ ያሉት ወይዘሮ አስቴር፤ የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ በከተማዋ ለሚገኙ ሆቴሎች በዓመቱ ትልቅ ሥራ የሚሰሩበት እና ከፍተኛ ገቢ የሚያገቡበት እንደሆነ አመልክተዋል።
ከዚህ ቀደም የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባዎችም ሆኑ ሌሎች ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ስብሰባዎች ሲካሄዱ የተለየ ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ከሌላው ጊዜ በተለየ በመንግሥት በኩል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራበት ይገኛል ብለዋል።
በቅርቡም ከንቲባ አዳነች አቤቤና የቱሪዝም ሚኒስትሯ በተገኙበት ከባለ ኮኮብ ሆቴሎች ጋር ዝግጅቱን በተመለከተ፤ ከዚህም በኋላ የጸጥታ አካላትን ጨምሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ሊሠሩ በሚገባቸው ሥራዎች ዙሪያ ውይይቶች መደረጋቸውን ጠቁመዋል።
የመብራትና የውሃ አገልግሎቶችን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶች ደረጃውን በጠበቀ መንገድ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች በጋራ የሚከናወኑ ስለመሆናቸውም ገልጸዋል።
አዲስ አበባ እንደ ስሟ አዲስ እየሆነች መምጣቷ ለሆቴሎችም ሆነ ለእንግዶች መልካም እድል ይዞ መምጣቱን ያመለከቱት ፕሬዚዳንቷ፤ ከዚህ ቀደም የመጡ እንግዶች አሁን ቢመጡ ከአየር ማረፊያ ጀምሮ የሚያዩት አዲስ ፣ የተለወጠ እና ያማረ ነገር ነው ብለዋል።
በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎችም በከተማዋ ለምተዋል፤ ይህ ደግሞ የእንግዶቹን የቆይታም ሆነ የመንቀሳቀስ እድላቸውን በማስፋት ሆቴሎች እና ሌሎችንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። ይህም በራሱ እንግዶቹ በተሻለ ሁኔታ እንዲስተናገዱ፤ ስለከተማዋ ጥሩ መረጃ እና የተሻለ ምስክርነት ይዘው ሌሎችን እንዲጋብዙ እድል እንደሚፈጥር አስታውቀዋል።
በተወሰነ ደረጃ በአንዳንድ ሆቴሎች የተጋነነ ክፍያ ስለሚታይ በሆቴሎችና በመንግሥት በኩል ምክክር በማድረግ የሚስተካከልበት ሁኔታ እንዲፈጠር የሚሠራ መሆኑንም ፕሬዚዳንቷ ጠቁመዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 19 ቀን 2017 ዓ.ም