አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያውያን በግብፅ ሴራ በብዙ መልኩ መጎዳታቸውን በማስታወስ፤ ለግብፅ ሴራ ነቅተው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ፕሮፌሰር አሕመድ ዘካሪያ አስታወቁ።
ፕሮፌሰር አሕመድ ዘካሪያ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ላይ እንዳስታወቁት፤ ግብፆች በየመን፣ ሊቢያ፣ ሰሞኑን በምሥራቅ አፍሪካ በተለየ ሁኔታ በሶማሊያ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ችግር እየፈጠሩ ነው።
የግብፅ ዲፕሎማቶችም ሆኑ ሌሎች ከግብፅ የሚመጡ ምሁራን እና አጠቃላይ ሠራተኞች ስለ ውሃው መመሪያ ተሰጥቷቸው የሚመጡ ናቸው ያሉት ፕሮፌሰር አሕመድ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ከውሃ ጋር ተያይዞ የሚከወን እያንዳንዱን ድርጊት በተለያየ መንገድ ይከታተላሉ።ኢትዮጵያን ለማደናቀፍ በብዙ መልኩ ይጥራሉ ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን የግብፆችን የተለመደውን የማዋከብ እንቅስቃሴ ስፍራ ባለመስጠት፤ መሥራት ያለባቸውን በደንብ መሥራት ይጠበቅባቸዋል።ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን የቤት ሥራ መሥራት ከቻሉ በሕዳሴው ግድብ ላይ እንደታየው ግብፆች የትም ቢሮጡ ምንም ማምጣት እንደማይችሉ አመልክተዋል፡፡
እንደ አሕመድ(ፕ/ሮ) ገለፃ፤ ኢትዮጵያ ካደገች ግብፅ ድሃ ትሆናለች የሚል የመንፈስ ጭንቀት አለባቸው።በዚህ ምክንያት ከኢትየጵያ የቀረበውን አብረን እንደግ የሚለውን አስተሳሰብ ከመቀበል ይልቅ፤ እናንተ ድሃ ሆናችሁ እኛ ብቻ እንብላ፤ ‹‹እኔ በበላሁት አንተ ተፈወስ›› ከሚል በሽታ መውጣት ስለተሳናቸው አሁንም ሴራ በተሞላበት መልኩ እየተንቀሳቀሱ ነው።
ከናይል ጋር ተያይዞ በሚሠሩ ሥራዎች ዙሪያ፤ የቴክኒክ ድጋፍ በሚል ስም ውሃውን ለመቆጣጠር እንደሚሞክሩ እና ኢትዮጵያ ውስጥም ይህንን ለማድረግ መጣራቸውን ጠቁመው፤ እያንዳንዷን ኢትዮጵያ ውስጥ የዘነበውን የዝናብ ጠብታ የመቆጣጠር ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀዋል።
ይህንን ፍላጎታቸውን በእሳት ላይ ቤንዚል እያርከፈከፉ ኢትዮጵያን በብዙ መልኩ ሲጎዷት መቆየታቸውን አብራርተዋል።አሁንም እየጎዷት እንደሚገኙ ጠቁመዋል።ይህንን መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሕዝቡም ሊረዳው እንደሚገባ አሳስበዋል።
ግብፅ የኢትዮጵያ አንድ ሦስተኛ ውሃ ከኤርትራ ጀምሮ ትግራይን ይዞ እስከ ጋምቤላ እንዲሁም የኦሮሚያን እና የአማራ ክልልን በአጠቃላይ የሚያካትት ሰፊ ተፋሰስ ወደ ሀገሯ እንደሚገባላት አስታውሰው፤ የኢትዮጵያ አፈር ተራቁቶ እየተከላ ለምርት አስቸጋሪ የሆነው ወደ ዓባይ በሚገቡ ወንዞች ምክንያት መሆኑን አብራርተዋል።
ግብፅ ከኢትዮጵያ የተሻለ የውሃ ክምችት እንዳላት ሊዘነጋ አይገባም የሚሉት አህመድ (ፕ/ሮ)፤ የሜዲትራኒያንን ሆነ የቀይ ባሕርን ውሃ በቴክኖሎጂው መጠቀም እንደምትችል አመልክተዋል።
እንደ እስከ አሁኑ 130 ሚሊዮን ሕዝብ ያላትን ሀገር ውሃውን አትንኩ ቢሉም፤ ኢትዮጵያ መንካቷ እንደማይቀር ተናግረዋል። የሚሻለው ተባብሮ በሥነሥርዓት የፈጣሪን ስጦታ መቀበል እና መጠቀም ብቻ ነው ብለዋል።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19 ቀን 2017 ዓ.ም