ለሕዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት በሩ ክፍት፤ መንገዱም ሰፊ ነው !

የኢትዮጵያ እና የግብፅ ሕዝቦች ከዓባይ ወንዝ ጋር በተያያዘ ታሪካዊ ትስስር ያላቸው፤ የረጅም ዘመን የሀገረ- መንግሥት እና የተለያዩ ስልጣኔዎች ባለቤቶች ናቸው። እንደ አፍሪካዊም ተመሳሳይ እጣ ፈንታ የሚጋሩ፤ ነገዎቻቸውን መተማመን በሚፈጠር ትብብር ብሩህ ለማድረግ ባለብዙ አማራጮች ናቸው።

ሀገራቱ የዓባይ ወንዝ በመካከላቸው የፈጠረውን ተፈጥሯዊ ትስስር የስትራቴጂክ አጋርነት ምንጭ በማድረግ፤ ለሕዝቦቻቸው የጋራ ተጠቃሚነት አብረው ሊሰሩ የሚችሉባቸው ሰፊ ዕድሎች አሉ። ዕድሎቹን በመጠቀም ለቀጣናው ከዚያም ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ አዲስ የትብብር ምዕራፍ መፍጠር እንደሚቻል ይታመናል።

ይህም ሆኖ ግን በዓባይ ወንዝ ውሃ ዙሪያ በግብጽ በኩል የሚነሱ ፍትሐዊነት የጎደላቸው ፣ በብዙ ውዥንብሮች እና የሀሰት ትርክቶች የተሞሉ ጥያቄዎች ፣ የሀገራቱ ሕዝቦች የዕድሎቹ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ፈተና ሆነዋል። ያለመተማመንን በመፍጠርም በጋራ ተጠቃሚነታቸው ላይ ጋሬጣ ፈጥረዋል።

በየዘመኑ የነበሩ የግብጽ መንግሥታት በዓባይ ወንዝ ዙሪያ ለገዛ ሕዝባቸው ሳይቀር የተዛቡ እና የተሳሳቱ መረጃዎችን በመስጠት፤ በወንዙ ውሃ ጉዳይ ሕዝባቸው ተጨባጭ እውቀት እና ፍትሐዊ አቋም እንዳይኖረው አድርገዋል። የሀገራቱን ሕዝቦች ግንኙነት ስጋት ውስጥ የሚከቱ ትርክቶችን ፈጥረው በስፋት ሲያስተናግዱም ቆይተዋል።

ዘመን ባለፈባቸው አፈ ታሪኮች የግብጽ ሕዝብ መቼም ቢሆን በዓባይ ወንዝ ውሃ ጉዳይ ተኝቶ እንዳያድር አድርገዋል። የዓባይ ውሃን ጉዳይ ዋነኛ የሀገር ውስጥ የፖለቲካ አጀንዳ በማድረግ፤ ወደ ስልጣን መምጫ እና የስልጣን ዘመን መቆያ አድርገውታል። በዚህም ሕዝቡ ባልተገባ መንገድ ሀብቱን፤ ጊዜውን እና ዕውቀቱን እንዲያባክን አድርገውታል።

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አብዛኛው የግብጽ ሕዝብ ስለዓባይ ወንዝ መገኛ ስፍራ ተገቢውን መረጃ ሳያገኝ ቆይቷል። በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ሳይቀር ትውልዶች በተሳሳተ አስተምህሮ ውስጥ ማለፋቸው የአደባባይ ምስጢር ነው። በዚህ ሂደት የሀገሪቱ ምሁራን ተሳታፊ የመሆናቸው እውነታ ደግሞ የችግሩን ግዝፈት ምን ያህል ትልቅ እንደሆነ በተጨባጭ ያመላከተ ነው።

ከዓባይ ወንዝ ውሃ ጋር በተያያዘ ያለው የግብጽ መንግሥታት ኢ ፍትሐዊነት የረጅም ዘመናት ታሪክ ያለው ፣ ከማስፈራራት ጦር አሰልፎ ለወረራ እስከመሰለፍ የደረሰ እና በብዙ አንገት የሚያስደፉ የሽንፈት ታሪኮች ታጅቦ የተጠናቀቀ ስለመሆኑ የታሪክ መዛግብት የሚናገሩት የአደባባይ ምስጢር ነው።

በታሪክ መገራት ያልቻለው ይህ የግብጽ መንግሥታት ያልተገባ ባህሪ ፤ በዚህ ዘመንም በሀገራቱ ሕዝቦች መካከል ያለመተማመን እና የጠላትነት መንፈስ ምንጭ እየሆነ ይገኛል። በ21ኛው የመረጃ ክፍለ ዘመን የሀገሪቱ መንግሥታት የገዛ ሕዝባቸውን ባልተገባ ትርክት በዓባይ ውሃ ያልተገባ ስጋት ውስጥ እንዲገባ አስበው እየሠሩ ነው ።

የዓባይን ውሃ የሀገር ውስጥ የፖለቲካ አጀንዳ በማድረግ፤ እነሱ ለስልጣናቸው ሲሉ ለሚፈጥሯቸው የተዛቡ ትርክቶች፤ የግብፅ ሕዝብ ገንዘቡን ፣ጊዜውን እና ጉልበቱን ኢንቨስት እንዲያደርግ እያስገደዱት ነው ። ላልተገባ ቅቡልነት ባልተገባ ትርክት ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍል እያደረጉትም ነው።

ለዚህም ባለፉት ስድስት አስርት ዓመታት በምርጫ ሆነ በመፈንቅለ መንግሥት ወደ ስልጣን የመጡ የግብጽ መንግሥታት በስልጣን ዘመናቸው ለሕዝቦቻቸው ባደረጓቸው ዲስኩሮች የዓባይ ወንዝ ውሃን የሀገር ስጋት ምንጭ ለማድረግ ያልሞከረ የለም። ለፈጠሯቸው ስጋቶች መፍትሔ አድርገው የወሰዷቸው አማራጮችም የኃይል እና የሴራ አማራጮች ነበሩ።

ይህ የግብጽ ፖለቲካ የቱን ያህል ቆሞ ቀር እና ዘመንን መዋጀት የተሳነው ስለመሆኑ ተጨባጭ ማሳያ ነው። ዛሬም በስልጣን ላይ ያለው የሀገሪቱ መንግሥት በተመሳሳይ መንገድ የዓባይን ውሃ የሀገር ስጋት ምንጭ አድርጎ ለማሳየት ረጅም ርቀት ሄዷል። በዚህም ከትናንት ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ እንዳልሆነ በተጨባጭ አሳይቷል።

ብዙ ሰላማዊ እና የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረጉ፤ ዘመኑን የሚዋጁ አማራጮች ባሉበት በዚህ ወቅት፤ እንደቀደሙት የሀገሪቱ መንግሥታት ከሴራ እና ግጭቶች ማትረፍ ይቻላል በሚል እየሄደበት ያለው መንገድ ከሁሉም በላይ የሕዝቦችን ፍትሐዊ የጋራ ተጠቃሚነት አደጋ ውስጥ የከተተ ነው። መንገዱ እንደቀደመው ዘመን ለግብጽ ሕዝብ የሚያተርፈው ነገር አይኖርም።

የሴራ እና የግጭት መንገዶች አሁን ባለው ዓለም አቀፍ እሳቤ አትራፊ አይደሉም፤ አትራፊ ይሆናሉ ብሎ አስቦ መንቀሳቀስ ተመሳሳይ ታሪካዊ ስህተቶችን እና ስህተቶቹ የፈጠሩትን የታሪክ ስብራት ከመድገም ባለፈ የሚያስገኘው ትርፍ የለም። ይህን ቆም ብሎ ማሰብ ለሕዝብ ፍላጎት ቆሜያለሁ ለሚል መንግሥት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ሥራ ነው። በአጠቃላይ ለሕዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት አሁንም በሩ ክፍት፤ መንገዱም ሰፊ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል!

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You