የጀርሞች መድኃኒቶችን መላመድ የእንስሳት ምርትና ምርታማነት በእጅጉ እንደሚቀንስ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፡- የጀርሞች መድኃኒቶችን መላመድ የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን በእጅጉ እንደሚቀንስ የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን አስታወቀ።

ኅብረተሰቡ ያለ ህክምና ባለሙያ ትዕዛዝ መድኃኒቶችን እንዳይጠቀም በስፋት ሊሠራ እንደሚገባም አመልክቷል።

በባለሥልጣኑ የእንስሳት መድኃኒት ምዝገባና ፍቃድ ባለሙያ ዶክተር ኃይሉ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ መድኃኒትን ያለ ባለሙያ ትእዛዝ መጠቀም የጀርሞች መድኃኒቶችን መላመድ ይፈጥራል፤ ይህም የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን በእጅጉ ይቀንሳል።

መድኃኒቶችን ለምን ያህል ጊዜ ለምን አይነት በሽታ መወሰድ አለበት የሚለውን መወሰን ያለበት በባለሙያ ነው ያሉት ዶክተር ኃይሉ፤ በዘፈቀደ መድኃኒቶችን መጠቀም ፤በሽታ አምጪ ጀርሞች መድኃኒቶች እንዲላመዱ እድል ይሰጣቸዋል ብለዋል።

የበሽታ ተህዋሲያን ራሳቸውን ለማኖር ባላቸው ተፈጥሯዊ የመቋቋሚያ መንገዶች ምክንያት በሚከሰት የጀርሞች መድኃኒቶችን መላመድ፤በዓለም አቀፍ ደረጃ የእንስሳት ምርትና ምርታማነት በእጅጉ ሊቀንስ እንደሚችል አመልክተዋል።

በአሁኑ ሰዓት ያለው የጀርሞች መድኃኒቶችን መላመድ በዚህ ፍጥነት ከቀጠለ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የእንስሳት ምርትና ምርታማነት በ11 በመቶ እንደሚቀንስ ጥናቶች መጠቆማቸውንም ዶክተር ኃይሉ ገልጸዋል።

የመድኃኒቶች በጀርሞች የመላመድ ችግርን ለመቅረፍ በችግሩ ዙሪያ የማህበረሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ያመለከቱት ዶክተር ኃይሉ፤ ኅብረተሰቡ ያለ ህክምና ባለሙያ ትዕዛዝ መድኃኒቶችን እንዳይወስድ በስፋት ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

መድኃኒቶችን በአግባቡ መጠቀም ሌላኛው ችግሩን መከላከያ መንገድ መሆኑንም አስታውቀው፤ በሽታን አስቀድሞ መከላከልም የመድኃኒትን መላመድ ለመቀነስ ሌላኛው አማራጭ እንደሆነ አመልክተዋል።

ዳግማዊት ግርማ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You