ዳንኤል ዘነበ
የመጋኛ በሽታ በሳይንሳዊ አጠራሩ ‹ቤልስ ፓልሲ› ይባላል። ይህ የፊትን ጡንቻ የሚቆጣጠረው ነርቭ ሲጎዳ ወይም ሙሉ በሙሉ ስራ ሲያቆም የሚመጣ ሲሆን በአንድ በኩል ያለውን የፊታችንን ክፍል የመጣመም ችግር እንዲኖርበት ያደርጋል። ይህ ህመም በአሜሪካ ውስጥ ብቻ 40 ሺህ የሚሆኑ ሰዎችን በየአመቱ የሚያጠቃ መሆኑ ይነገርለታል።
የመጋኛ በሽታ ፆታ፣ ዘር፣ ሃይማኖት ሳይለይ ሰዎችን በእኩል የሚያጠቃ ሲሆን በስኳር ታማሚዎች እና በእርጉዝ እናቶች ላይ የመከሰት እድሉ ከፍ ያለ እንደሆነ የጠቅላላ ሀኪም ባለሙያው ዶ/ር ተመስገን ደጀኔ ይገልፁታል።
እንዴት ይከሰታል?
የመጋኛ በሽታ ፋሺያል ነርቭ ወይም ከጭንቅላታችን የሚወጣው ሰባተኛው ነርቭ በቫይረስ ሲጠቃ እና እሱንም ተከትሎ መቆጣትን ሲያመጣ የሚከሰት ህመም ነው። የነርቩ መቆጣት ደግሞ እብጠትን ከማስከተሉ ባለፈ ነርቩ በአግባቡ ስራውን እንዳይከውን ያደርጋል። በአንድ በኩል ያለውን የፊታችንን ክፍል በትክክል እንዳይሰራ በማድረግ ፊታችን ወደ አንድ በኩል ብቻ እንዲጣመም ያደርጋል፤ አይንን ለመክፈት ስንሞክር የመክበድ ስሜት ይኖራል፤ በተጨማሪም ለመሳቅ ስንፈልግ የቆዳ መለጠጥ ችግርን ያስከትላል።
ምልክቶቹ
የመጋኛ በሽታ ምልክቶች ከምንላቸው ፊታችን ወደ አንድ በኩል ሲጣመም፣ የአይን ቆብ መንጠልጠል፣ የአይን እና የአፍ ጫፍ መንጋደድ፣ አይንን ሙሉ በሙሉ ለመዝጋት መቸገር፣ እና የአይን ቆብ መድረቅ ጥቂቶቹ ናቸው።
ምርመራ
ይህን ህመም ለማከም ምንም አይነት የደምም ሆነ የራጅ ምርመራዎች አያስፈልጉትም፤ ታካሚውን በማየት ብቻ ህመሙን ማወቅ ይቻላል። ነገር ግን ሃኪምዎ ሌላ ህመም ከጠረጠረ የተለያዩ ምርመራዎችን ሊያዝልዎት ይችላል።
ህክምናው
ይህን ህመም ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት የሚያስችል ህክምና ባይኖርም በሃኪምዎ የሚታዘዙ መድሃኒቶች ከበሽታው በፍጥነት እንዲያገግሙ ያግዛል፤ በተለይ ህመሙ ከጀመረ በጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ ሃኪም ሄደው ህክምናውን ከጀመሩ ውጤቱ አመርቂ ይሆናል።
የአይን እንክብካቤ፦ አይንን ሙሉ በሙሉ ወይም በአግባቡ መዝጋት የሚከብድ ወይም አዳጋች ከሆነ የአይን ቆብ ድርቀት እና ቋሚ የሆነ ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል አርቴፊሻል የሆነ እንባ ጠብታ ወይም ማለስለሻ መጠቀም ይኖርብናል።
መድሀኒት፦ ህመሙ በጀመረ ሶስት ቀናት ውስጥ ወደ ሃኪምዎ ካመሩ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ስቴሮይድ እንክብል ይታዘዝሎታል። ከዚህ በተጨማሪም አንቲ- ቫይራል መውሰድም ይጠበቅበዎታል።
በአጠቃላይ የህመሙ ደረጃ ቀላል ከሆነ ሙሉ ለሙሉ ወደ ቀድሞው ጤንነት ለመመለስ የሚከብድ አይሆንም። ነገር ግን ከባድ ደረጃ ላይ ከደረሰ ከህመሙ ጋር ተከትለው የሚመጡ ችግሮች እድሜ ልካችን አብረው ሊኖሩ ይችላሉ።
በመሆኑም ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶችን ካስተዋልን በፍጥነት ወደ አቅራቢዎ በሚገኝ የህክምና አገልግሎት መስጫ ተቋም በመሄድ የህክምና እርዳታ መጠየቅ ይኖርበዎታል።
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2013