ሰላማዊት ውቤ
የእንስሳት ሀብት ሀገራችን ከታደለችው የኢኮኖሚያዊ ምንጭ አንዱ ነው። በዘርፉ ያለው የወጪ ንግድ በቂ ነው ባይባልም ገቢ ግን ያመነጫል። እንደ ሀገር ከእርሻው ዘርፍ ከሚገኘው ገቢ 47 ከመቶው ከእንስሳት የሚገኝ ነው።
ሀገራችን በከብት ሀብቷ ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ሰባተኛ ደረጃ ላይ ናት። በሀብቱ ላይ የኑሮ መሰረቱን የጣለው የህብረተሰብ ክፍልም ቁጥር ቀላል አይደለም።
በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የእንስሳት ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና ተመራማሪ ዶክተር ፈቀደ ፈይሳ በአጠቃላይ በሀገሪቱ ካለው ከ110 እስከ 120 ሚሊዮን የሚጠጋ ዜጋ ቁጥሩ 10 ሚሊዮን የሚሆነውና በቆላው የሀገሪቱ አካባቢ የሚኖረው ህብረተሰብ ቋሚ መተዳደሪያው የእንሰሳት ሀብት መሆኑን ይናገራሉ።
በእርሻው መስክ እንስሳት እያበረከቱ ያለውን አስተዋጾኦ እንኳን ለአብነት ቢነሳ በአሁኑ ወቅት ከ14 ሚሊዮን በላይ በሬዎች እርሻውን እያገዙ ይገኛሉ። ሀብቱ ለአያሌ ዜጎች ቀላል፣አጭርና ወጪ ቆጣቢ ስልጠና ሰጥቶ የሥራ ዕድል በመፍጠርም ወደር የለውም ሲሉ ተመራማሪው ዶክተር ፈቀደ ይገልጻሉ።
የዜጎችን የሥጋ፣የወተትና የወተት ተዋፅኦ እና ሌሎች ፍላጎቶችን በማሟላት ረገድም የጎላ ሚና እንደሚጫወትም ያሰምሩበታል።በተለይ እነዚህን የዜጎች ፍላጎቶች እንዲያሟላና የወጪ ንግድ ምንዛሪ ገቢ እንዲያመነጭ ለማስቻል እንደ ሀገር ባለፉት አምስት አሥርት ዓመታት በምርምሩ ዘርፍ ብዙ ሥራዎች ተከናውነዋል።
በእንስሳት ዝርያ፣ በእንስሳት ጤና ፣በበግ፣ በፍየል፣ በበሬ፣ በወተት ላም፣የሀገር ውስጥና የውጭ የእንስሳት ዝርያዎችን በማዳቀልና የተሻሻሉ ዝርያዎችን በማብዛት፣ በመኖ የተሰሩት ተጠቃሽ ናቸው። በእርግጥ ቀደም ብለው በተሰሩት በነዚህ ሥራዎች የተገኙ ውጤቶች አሉ።የእንስሳት ምርትና ምርታማነት በመጠኑም ቢሆን ጨምሯል።
ከእንስሳት የሚገኘው እንደ ሥጋ፣ ወተትና የወተት ተዋጾኦ ያለው ምርምር ባፈለቀው ቴክኖሎጂ እንዲታገዝና ውጤታማ እንዲሆን ተደርጓል።አርሶ አደሩ ከአንዲት ላም በቀን እስከ 40 ሌትር ወተት የሚሰጡ የተሻሻሉ የወተት ከብቶች ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችል ሥራ መሠራቱን ማሳያ ነው።በመስኩ የግለሰብ አርሶ አደር የቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች ተፈጥረዋል። ሆኖም እነዚህ እንደ ሀገር ሲቃኙ ውሱን መሆናቸውን ያስረዳሉ።
በመሆኑም ኢንስቲትዩት ሀገራዊ የእንስሳት ልማቱን ለማገዝ አሁንም እየተሰራ ይገኛል ያሉት ተመራማሪው፤ ሥራው የሦስቱን ኢንስቲትዩት ተልዕኮዎች መሰረት አድርጎ እየተከናወነ መሆኑን ይናገራሉ ። ኢንስቲትዩቱ ሶስት ተልዕኮዎች ሲኖሩት የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችንና ዕውቀቶችን ማመንጨት አንዱ ነው።
ምርትና ምርታማነትን የምርት ጥራትንና የገበያ ተወዳዳሪነትን ሊያሻሽሉ የሚችሉ ዕውቀትና ቴክኖሎጂዎችን ማበልፀግ ነው።ሁለተኛው የሚመነጩ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን ማስተዋወቅና በሕብረተሰቡ ዘንድ ፍላጎት መፍጠር ሲሆን ሶስተኛው ደግሞ ዘር አባዝቶ ማቅረብ ነው።
ተመራማሪው እንደሚሉት የምርምር መስኩ ብዙ የሚቀሩና ያልተሰሩ የቤት ሥራዎች አሉበት።ገና ፈርጀ ብዙና ሰፋፊ የእንስሳት ዘርፉን ችግሮች ለመፍታት የሚረዱ ምርምሮችን ማድረግ ቴክኖሎጂዎችንም ማፍለቅ ይጠበቅበታል።እንደ ሀገር አንኳር ተብለው ያሉ ችግሮች እንኳን ቢጠቀሱ ብዙ ናቸው።
ከነዚህ መካከል የእንስሳት ሀብቶቿን ለሕዝብ ጥቅም እንዲውሉ ለማድረግ የሚያስችሉ ፖሊሲዎች ቢቀረፁም በአግባቡ አለመተግበራቸው፣የውጭ ምንዛሪ ምንጮች የሆኑ የግብርና ምርቶችን ሳያቀነባብሩ በጥሬያቸው ወደ ውጭ መላካቸው፣ በተለይም ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ምርት በዓይነትና በጥራት አለመዘጋጀቱ ፣በዚህ መልክም የሚላኩት ተገቢውን ዋጋ አለማግኘታቸው፣የመኖ ዋጋ በየጊዜው መናር፣ የርቢ ላሞች፣ጊደሮች፣ጥጆች መታረዳቸው፣ ባልተገባ መንገድ የሚወልዱ ጊደሮች፣ ጥጆችና ላሞች ለእርድ እየዋሉ በመምጣታቸው ዘራቸው እየጠፋ መሆኑን አንስተዋል።
በተለይም ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ምርት በዓይነትና በጥራት አለመጨመሩ፣በዘርፉ የተደረጉ በርካታ የምርምር ሥራዎችን መጠቀም አለመቻልን በተግዳሮትነት ይጠቅሳሉ።
ምርታማነት በሚፈለገው ደረጃ አለማደጉ ፣የሀገር ውስጥ እንስሳት ፍላጎት አለመሟላቱ ፣የሀገራችን እንስሳት አረባብ በዘመናዊና በሳይንሳዊ መንገድ አለመመራቱ ፣የእንስሳት ሀብትን ለእርሻ ሥራ አጋዥ አድርጎ እንጂ ራሱን ችሎ የሚሠራ ሥራ አድርጎ አለማየት ከተጠቀሱት ችግሮች መካከል ናቸው።
በኢትዮጵያ በተለይም ባለፉት ሦስት ዓመታት የለውጥ ዘመን ለሰብል የተሰጠው ትኩረት ለእንስሳት ሀብት አለመሰጠቱ፣ የውጭ ምንዛሪ ምንጮች የሆኑ የግብርና ምርቶችን ሳያቀነባብሩ በጥሬያቸው ወደ ውጭ መላካቸው፣ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ምርት በዓይነትና በጥራት አለመጨመሩ፣ የአመለካከት ችግር መኖሩን ዶክተር ፈቀደ አጫውተውናል።
በእንስሳት ሀብት ብዛት ታዋቂ ብንሆንም አንድ አርሶ አደር ከአንድ ላም በቀን እስከ 40 ሊትር ወተት የሚያገኝበት የከብት እርባታ ስራ ማጠናከር አቅቶት የቆርቆሮ ወተት ከውጪ ሀገር በከፍተኛ ምንዛሬ የሚገባበት ሁኔታ መኖሩን ይጠቅሳሉ።
ይህም እንስሳት በሀገራችን የሚረባው እርሻን ለማገዝ ነው የሚል የአመለካከት ችግር መኖሩን ይናገራሉ ። በአሁኑ ወቅት ከ14 ሚሊዮን በላይ በሬዎች እርሻውን የሚያግዙበት ሁኔታ በቂ ወተትና ሥጋ ለማግኘት አዳጋች እንዳደረገውም ይጠቅሳሉ ።
የእርሻ ስራውን በፈረስ ፣በአህያና በሌሎች እንስሳት የሚከወንበት አማራጭ ቢኖር ኖሮ ግን የእርሻ በሬዎችን ለሥጋ ፍላጎት ማዋል ይቻል ነበር።በእርግጥ ሁሉም የእርሻ መሬት በአህያ፣ በፈረስም ሆነ በትራክተር ለማረስ አይመችም።
አዲስ ቴክኖሎጂ እስካልተገኘ ድረስ አሁንም አርሶ አደሩ ሁልጊዜም በሬዎች እንዲኖሩት ይፈልጋል።ይሄን ፍላጎቱን ለማሟላትም የእነዚህን ሁለት እጥፍ የሆኑ ወላድ ላሞች ማራባትና በሬ እንዲወልዱ ማድረግ እንደሚኖርበትም ይመክራሉ።
ሀገራችን ትንሽም ቢሆን ስጋና የቁም እንስሳት ወደ ውጪ ልካ ገቢ ታገኛለች ።በዚህ በኩል ይገኝ የነበረው ገቢ ቀደም ሲል እስከ 200 ሚሊዮን ብር እንደነበር ያስታውሳሉ ።ይሄ ገቢ በአሁኑ ወቅት ከ100 ሚሊዮን በታች በመውረድ እያሽቆለቆለ መጥቷል ብለዋል።
እሳቸው እንደሚሉት ይሄ የሆነው ደግሞ በሕገወጥ የእንስሳት ንግድ ምክንያት ነው።ሶማሌ ላንድ፣ ሱዳን ካላቸው በላይ ወደ ውጭ እንስሳት ይልካሉ የሚባል ግምት እንዳለም ይናገራሉ። ‹‹ ከብት ብቻ ሳይሆን አህያም እንዲሁ ይላካል ።
ቻይና ላይ የአህያ ቆዳ ለባህላዊ መድሃኒት እጅግ ተፈላጊ በመሆኑ ዋጋውም ውድ ነው።እኛ ሀገር ግን በዚህ ለመጠቀም ቢሞከርም ከጅምር አላለፈም።›› ሲሉ ይጠቅሳሉ።
ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ምርምር ማዕከል በ2009 ዓ.ም ያወጣውን መረጃ እንዳመለከተው በ2009 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ በኮንትሮባንድ ንግድ ምክንያት ሶማሌ ላንድ 4ነጥብ 5 ሚሊዮን፣ ጂቡቲ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን እንስሳትን ለውጭ ገበያ አቅርበዋል። እንደ ጥናቱ ይሄ ሕጋዊ የእንስሳት ንግዱን የሚያቀጭጭ እንቅፋት ነው ።
ሀገራችን ኢትዮጵያም ማግኘት ያለባትን የውጪ ምንዛሪ እንዳታገኝ ያደርጋል። ከዚህም በተጨማሪ ገቢ የሚያሳጡ በርካታ ሌሎች እንቅፋቶችም አሉ። የትኛውም የዉጪ ንግድ ምርት ኤክሳይዝ፣ ቫትና ሌሎችም ታክሶች አይከፈልበትም።
ቆዳና ሌጦን በጥሬው ወደ ውጭ መላክ ግን የ150 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ የሚጠየቅበት መሆኑ አንዱ ነው። ለላኪዎች የውጭ ምንዛሪ ያስገኛሉ ተብሎ ስለሚታሰብ ለሚወስዱት ብድር የሚጠየቁት ወለድ 8 ነጥብ 5 በመቶ ቢሆንም፣ የእንስሳት ሀብት በማልማት ለሚሠሩ ተበዳሪዎች ግን 17 በመቶ ወለድ እንዲከፍሉ መደረጉም ሌላው ነው።
የቁም እንስሳት ላኪዎች ለሚያቀርቧቸው ትልልቅም ሆኑ አነስተኛ ቁመና ላላቸው ሰንጋዎች በእኩል ግምት 600 ዶላር በቅድሚያ ክፍያ እንዲያስገቡ በብሔራዊ ባንክ ሲጠየቁ መኖራቸው የእንስሳት የወጪ ንግድ ጉልህ ችግር ሆኖ መቆየቱ በጥናቱ ተመላክቷል።
ተመራማሪው ዶክተር ፈቀደ ህገወጥ ንግድ በእንስሳት ምርት ተጠቃሚው ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑን ይናገራሉ። ህገወጥ ንግዱ የሚያመርተውና መጨረሻ ላይ ገዝቶ የሚመገበው እንዲሁም በእንስሳቱ አጠቃላይ በንግድ ስርዓቱ ውስጥ ተጠቃሚ እንዳይሆን አድርጎታል ይላሉ።
ምርትን በጥራት ከማቅረብ አኳያም ችግር ሆኖ መቀጠሉን ይናገራሉ። ለምሳሌ ፣አርሶ አደሩ ለገበያ የሚያቀርበው ምንም ያልወጣለትን ወተት ነው። በሌላ ወገን ክሬሙና ቅቤው የወጣ ወተት የሚያቀርብ አለ።
በመሆኑም አርሶ አደሩንና ሕብረተሰቡን የእንስሳት ምርት ተጠቃሚ ለማድረግ አሰራሩ በምርምርና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በሕግ ማዕቀፍ መስተካከል አንዳለበት አጽንኦት ሰጥተው ነው የሚናገሩት ።
‹‹በተጨማሪም ከእንስሳት ቴክኖሎጂ አንፃር አባዝቶ በስፋት የሚያቀርብ አካል የለም›› ለምሳሌ በቀን 15 ሊትር ወተት የምትሰጥ የወተት ላም ጊደር ካለች ይህችን አባዝቶ በብዛት ለተጠቃሚው የሚያደርስ ተቋም አለመኖሩን መጥቀስ እንደሚቻልም ያሰምሩበታል።
ዶክተር ፈቀደ እንዳሉት እንደ ምርምር ተቋም እዚህ ላይ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች አሉ።እንስሳት እጅግ ረጅምና ቋሚ እንክብካቤም ከመፈለጋቸው ጋር እንዲሁ እየተሰራ ነው።
እኛም ይሄን ተከትሎ እንስሳት ላይ ከተሰራ ሀብቱ አለ፤ አካባቢውም ምቹ ነው። በመሆኑም ከኢንስቲትዩቱ የሚቀርበውን ምርምር ተከትሎ በዘርፉ ብዙ ሥራዎችን መሥራት ይቻላል። ተቋሙ ምርምሩ በኤክስቴንሽን አማካኝነት እንዲዳረስ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል በማለት ጽሑፋችንን ቋጨን ። ሰላም!
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2013