ኢትዮጵያውያን በየዘመኑ ዳር ድንበራቸውንና ሉዓላዊነታቸውን ለማስከበር ባደረጓቸው ትግሎች ከፍ ያለ የተጋድሎ ታሪክ ባለቤት እንደሆኑ የሀገሪቱ የቅርብም ሆነ የሩቅ ታሪክ ሕያው ምስክር ነው ። ዛሬ ላይ ዜጎች አንገታቸውን ቀና አድርገው በልበሙሉነት መናገር የሚችሉበትን ታሪክ በብዙ መስዋዕትነት በደማቸው የጻፉ ታሪክ ሰሪ ትውልዶች ፍሬ ነን።
ከዚህም ጎን ለጎንም በሀገሪቱ ስለ ፍትህ እና ዴሞክራሲ፤ ስለ ነጻነትና እኩልነት በየዘመኑ ከፍ ያለ መስዋዕትነት የከፈሉ ትውልዶች መኖራቸውም የአደባባይ ሚስጥር ነው። ለመላው ሕዝባችን የተሻሉ ነገዎችን ለመፍጠር ሕልም አልመው ስለህልማቸው ሕይወታቸውን ሳይሰስቱ ዋጋ ከፍለው ያለፉ የብዙ ሰማዕታት መገኛም ጭምር ነን። በዚህም እንደሀገር የታሪክ ድሆች አይደለንም ።
የሚያሳዝነው ግን ስለ ፍትህ እና ዴሞክራሲ ፤ ስለ ነጻነትና እኩልነት የከፈልናቸው ከፍ ያሉ ዋጋዎች በየዘመኑ በሚነሱ ራስ ወዳዶች ፣ ከራስ ወዳድነት በሚነሳ የሴራ ፖለቲካ የጦዙ ግለሰቦችና ቡድኖች ፍሬ ማፍራት አልቻለም ። ከመስዋዕትነት ገድል ባለፈ ማህበረሰባችንን ተጠቃሚ ማድረግ አልተቻለም ።
ከነዚህ ስለ ፍትህ እና ዴሞክራሲ፤ስለ ነጻነትና እኩልነት ሥርዓት ግንባታ ከተደረጉ እልህ አስጨራሽ የሕዝብ ትግል ውስጥ የትግራይ ሕዝብ ያካሄደው፤ ብዙ መስዋዕትነትና ተጋድሎ የጠየቀው የትጥቅ ትግል ተጠቃሽ ነው። ትግሉ የብዙዎችን የመስዋዕትነት ደም ግብር ቢጠይቅም ገና ከጅምሩ ትግሉ በራሱ የጥቂቶችን የስልጣን ጥማት የሚገራ አቅም ባለመፍጠሩ ፍጻሜው ሀገርና ሕዝብን ዋጋ ከማስከፈል ያለፈ ትሩፋት አልነበረውም።
በብዙ የደመቁና የጎሉ የፕሮፖጋንዳ ድምጾች የትግሉት ፍሬ መላው ሕዝብ በተለይም ደግሞ የትግራይ ሕዝብ ተስፋ አድርጎት የነበረ ቢሆንም ፤ እውነታው ግን የኋላ ኋላ የቅዠት ያህል ግራ አጋቢና ተጨማሪ ዋጋ የሚያስከፍል ታሪካዊ ክስተት ሆኗል።
በ1960 ዎቹ የነበረው ተራማጅ ኃይል ከተጨባጭ ሀገራዊ እውነታ በመነሳት ከፍ ያለ ሀገራዊ ራዕይ ይዞ ለራዕዩ ስኬት በቁርጠኝነት ህይወቱን ዋጋ እስከመክፈል የደረሰ ዝግጁነት ቢኖረውም ፤ የትግሉ ሕዝባዊ መሰረቱ በሥልጣን ጥም በጦዙ ቡድኖች ተጠልፎ ፍጻሜው የከፋ ሊሆንና በሀገሪቱ ታሪክም ውስጥ ተጨማሪ ጠባሳ ጥሎ ሊያልፍ ችሏል።
ገና ከጅምሩ የትግራይን ሕዝብ ያለ አማራጭ ያስቀረው፣ ለዚህም ሲል ስለ ፍትህ እና ዴሞክራሲ እንዲሁም ስለ ሕዝቦች ነጻነት ከፍ ያለ የትግል ዜማ እያዜሙ ወደ ትግል የገቡ ተስፈኛ ኃይሎችን ጭምር አርዶ በንጹሃን ደም ላይ መሰረቱን ያዋቀረው የህውሓት ጁንታ በበረሀ ትግሉ ወቅትም ሆነ ከዛ በኋላ በነበረው ዘመን ሀይ ባይ አጥቶ በትግሉ ሰማዕታት ደም እየቆመረ የትግሉን ፍሬ አርክሶታል ።
በትጥቅ ትግሉ ወቅት በፍጹም ሕዝባዊነት ሕይወታቸውን ለሀገርና ለሕዝብ የተሻሉ ነገዎች የገበሩ የቁርጥ ቀን ዜጎችን ተስፋ ፣ የፖለቲካ ቁማር ካርድ አድርጎ ባልተገባ መልኩ በሰማዕታቱ ተስፋና ደም ቆምሯል። ባልተገባው የቁማር ትርፍም ራሱን የተለየ ፍጡር አድርጎ መሳል ባስቻለ ሚዛን የሳተ የአስተሳሰብ መዛነፍ ውስጥ ገብቶ ለመውደቅ ተገዷል ።
በተለይም የጁንታው የፖለቲካ ቁመራ በትግራይ ሕዝብ ላይ ያደረሰው ተደራራቢ ክህደት ከፍ ያለ ነው። ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ ሕዝቡን የመቆመሪያ ካድር አድርጎ ብዙ ዋጋ እንዲከፍል አድርጎታል ። እውነታውን የከፋ የሚያደርገው ደግሞ በገዛ ሀጥያቱ ለሞተው የውርደት ሞት ስርየት አሁንም የትግራይን ሕዝብ ደም የመሻቱ ነገር ጭምር ነው ።
በጁንታው የተጠለፈው ከትውልዶች የፍትህ ፣ የነጻነትና ፣ ዴሞክራሲ መሻት የመስዋዕትነት ትግል የትግራይ ሕዝብ ምን አተረፈ ? ለሚለው ጥያቄ መልስ መስጠት ተገቢና ዘመኑን ለመዋጀት የሚያስችል አቅም መፍጠር የሚያስችል ነው።
በርግጥ ባለፉት 40 ዓመታት ከየካቲት 11 ቀን 1966 ጀምሮ የትግራይ ሕዝብ የፖለቲካ አማራጮችን እንዳይቀበል ሳይሆን ፈጽሞ እንዳይሰማ ሆኗል። ፍትህ እና ነጻነት ለትግራይ ሕዝብ በጁንታው ተለክቶ የሚሸጥ የእድሜው ማራዘሚያ ሸቀጥ ሆኗል። ከሌሎች የሀገሪቱ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችም ጋር በፍቅርና በወንድማማችነት እንዳይኖር በብዙ አግላይ ትርክቶች ሲሞላ የኖረ ሕዝብ ነው።
መላው የትግራይ ሕዝብ ከትግሉ ተስፋ አድርጎ የጠበቀው ይህን አልነበረው ፣የትግሉ ሰማዕታት በሞት ጣር ላይ ሆነው ሞትን ተጋፍተው ያሸነፉበት ፣ ጽናት ሆኖ ያሻገራቸው የተስፋው እውነት ይሄ አልነበረም ።
ጁንታው ትግሉን ጠልፎ ሰማዕታቱን ሁለት ሞት እንዲሞቱ አድርጓቸዋል። በአጠቃላይ የተጋድሎ ታሪካቸውን አቆሽሿል። የመስዋዕትነት ደማቸውን አርክሷል። የተስፋ ብስራት ዜማቸውንም ከንቱ አድርጓል!
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2013