አንተነህ ቸሬ
‹‹ሁለት እጆቹን ያጣው ሰው ድንቅ ሰዓሊ ሆነ›› መባልን ‹‹ተዓምር›› ከማለት ውጪ ምን ሊሰኝ ይችላል? ሁለቱንም እጆቻቸውን ገና በልጅነታቸው ቢያጡም እጅግ ተደናቂ ሰዓሊ መሆን የቻሉ ተዓምረኛ ሰው ናቸው::
‹‹እጆች ሳይኖሯቸው እንዴት ጎበዝ ሰዓሊ መሆን ቻሉ?›› የሚለው ጥያቄ አሁንም ድረስ ብዙዎችን እንዳነጋገረና እንዳስገረመ ቀጥሏል:: የዚህ ድንቅ ምስጢር ባለቤት የሆኑትን የአንጋፋውን ሰዓሊና መምህር ወርቁ ማሞ የሕይወት ጉዞን በአጭሩ እንቃኛለን::
ወርቁ የተወለደው በ1927 ዓ.ም አዲስ ዓለም አካባቢ ነው:: ፊደል የቆጠረው በተወለደበት አካባቢ ነው:: ከፋሺስት ኢጣሊያ ወራሪ ኃይል መባረር በኋላ ከቤተሰቦቹ ጋር ወደ አዲስ አበባ ሄዶ መኖር የጀመረው ወርቁ በ12 ዓመቱ ያጋጠመው ነገር አሳዛኝ ነበር:: በጳጉሜ ወር 1939 ዓ.ም ታዳጊው ወርቁና ጓደኞቹ የወርቁ አባት ወደሚሰሩበት ጋራዥ በመሄድ መኪና ውስጥ ተጠቅልሎ ያገኙትን ዕቃ መፍታት ይጀምራሉ::
የተጠቀለለውን ነገር በድንጋይ ሲቀጠቅጡት በድንገት ያልታሰበ ፍንዳታ በአካባቢው ይሰማል:: ወርቁና ጓደኞቹ ሲፈቱትና ሲቀጠቅጡት የነበረው ዕቃ ቦምብ ነበር:: ቦምቡ ፈንድቶ የወርቁን እጆች አሳጣ:: ‹‹ሁለት እጆቹን ያጣ ሰው ከእንግዲህ ምን ይሰራል ብሎ?›› ቤተሰብና ዘመድ እጅግ አዘነ::
ሕይወት ገና በጠዋቱ ለታዳጊው ወርቁ ጨለማውን ጎኗን አሳየችው:: ምግብ ለመመገብና ልብስ ለመልበስ እንኳ የሌላ ሰው እርዳታ አስፈለገው:: ይሁን እንጂ ሲፈጠር ጀምሮ መንፈሰ ጠንካራ የነበረው ታዳጊው ወርቁ ለሕክምና በገባበት ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ውስጥ የአካል እንቅስቃሴ በማድረግ ሁሉንም ነገር በራሱ ለመፈፀም መጣር ጀመረ::
በዚያ ፈታኝ ወቅት ታዳጊውን እየተንከባከቡና ‹‹ … አይዞህ ብዙ የምትሰራው ሥራ አለ:: ጠበቃም፣ ዳኛም… መሆን ትችላለህ፤ እኔ እናትህ እያለሁ! … ›› እያሉ የወደፊት አቅጣጫውን የመሩት ወላጅ እናቱ አበረታቱትና መንፈሰ ጠንካራው ልጅ የጀመረው ጥረት ፍሬ አፈራለት::
በተጎዱት እጆቹ ስንጥር በመያዝ እግሮቹ ላይ መሞነጫጨር ሲጀምር የስዕል ጥበብ እየተገለጠለት እንደነበር እርግጠኛ አልነበረም:: ግን ያ አጋጣሚ የስዕል ጥበብ ለታዳጊው ግብዣ እያቀረበችለት እንደሆነ የሚጠቁም ነበር::
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን እስከአምስተኛ ክፍል ድረስ በሽመልስ ሐብቴ ትምህርት ቤት ተማረ:: በዚያን ጊዜ በሁሉም የትምህርት ዓይነቶች ደብተሮቹ ላይ ስዕሎችን ይስል ነበር:: ከዚያም ወደ ደጃዝማች በየነ መርዕድ ትምህርት ቤት ተዛውሮ ሲማር ሥዕል መሳልን ቀጠለበት:: ሌሎቹ ተማሪዎች በእረፍት ሰዓታቸው ጂምናስቲክ ሲሰሩ ወርቁ ስዕል ይለማመድ ነበር::
ከዚያም ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ተዛውሮ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን መማር ቀጠለ:: በዚህ ጊዜም ከሌላው ትምህርት በተጨማሪ የፈረንሳይኛ ቋንቋና የሥዕል ትምህርት ተምሯል::
ወርቁ ሁለቱንም እጆቹ ሳይኖሩት የሚፅፈው ጽሑፍ ከብዙዎቹ የክፍል ጓደኞቹ የተሻለ ስለነበር ተማሪዎችና መምህሮቹ ይደነቁበት ነበር:: በትምህርቱ ጎበዝ ተማሪ ስለነበር በየጊዜው ይሸለም ነበር:: ሳይፈፀም ቀረ እንጂ በጠንካራ መንፈሱ በርትቶ በመማሩ ሰው ሰራሽ እጅ እንደሚገዛለት ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ተስፋ እየሰጡ ያበረታቱት ነበር::
በስዕል ችሎታው ከቀን ወደ ቀን እመርታ እያሳየ የመጣውና የስዕል ፍቅሩ ያየለበት ወርቁ ማሞ፣ በ1952 ዓ.ም ሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት ገባ:: ቀደም ብሎ በትርፍ ጊዜው የስዕል ትምህርት በመማሩና ተደናቂ የሆኑ የስዕል ሥራዎችን በማቅረቡ ምክንያት የሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት ገብቶ የስዕል ትምህርት የጀመረው በሁለተኛ ዓመት ተማሪ ደረጃ ነበር::
ወርቁ በትምህርት ቤት ቆይታው በችሎታው የሚደነቅ ሰው ሆነ፤ ሥራዎቹም መወያያ ሆኑ:: በትምህርት ቤቱ ባሳየው የላቀ ችሎታ እውቀቱን የበለጠ እንዲያጎለብት የውጭ የትምህርት ዕድል ተሰጠው::
ለትምህርት ወደ ሶቭየት ኅብረት ተጓዘ:: በዚያም በሌኒንግራንድ (ፒተርስበርግ) የሥነ-ጥበብ አካዳሚ የስዕል ጥበብን ከሌሎች ተጓዳኝ ትምህርቶችና ከፔዳጎጂ ጋር ተምሮ በጥሩ ውጤት በሁለተኛ ዲግሪ ተመረቀ::
ወርቁ ሩስያ ሳለ በትምህርቱና በችሎታው ያሳየው ብቃት ላቅ ያለ ስለነበር በወቅቱ ሩስያ የሚማሩ የስዕል ተማሪዎች ደከም ያሉ ከሆኑ ‹‹… በትምህርታቸው እንዲበረቱና የተሻለ ችሎታ እንዲያሳዩ እንደ ወርቁ ማሞ እጃቸውን እንቁረጠው እንዴ?›› ይባል ነበር::
ከዘጠኝ ዓመታት የባሕር ማዶ ቆይታው በኋላ 1964 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት መምህር ሆነ:: እስከ 1987 ዓ.ም ድረስ ስዕል በማስተማር አገልግለዋል:: ከቀዳሚዎቹ የሥነ-ጥበብ መምህራን ምድብ ውስጥ የሚካተቱ ታላቅ ባለሙያ ናቸው:: ከወርቁ ማሞ ታዋቂ ስዕሎች መካከል ‹‹ሞዴል››፣ ‹‹እናቶች..፣ ‹‹ንጋት››፣ ‹‹ዓድዋ››፣ ‹‹ወደ ዘመቻ›› እና ‹‹የመጨረሻ ዙር›› የሚሉት ሥራዎቻቸው ይጠቀሳሉ:: ከእነዚህ ሥራዎቻቸው መካከል ሦስት ሜትር በስድስት ሜትር ሆኖ የተሰራው እጅግ ግዙፉና ‹‹ዓድዋ›› የተሰኘው ሥራቸው ዛሬ የት እንደሚገኝ እርግጠኛ ሆኖ መናገር እንደማይቻል ስለሰዓሊው የሚናገሩና የጻፉ ሰዎች ገልፀዋል::
እርሳቸውም በአንድ ወቅት ስለዚህ ጉዳይ ተጠይቀው እንዲህ ዓይነት ትልቅ ስዕል በአሁኑ ወቅት ለመሳል ከፍተኛ የገንዘብና የቁሳቁስ አቅም እንደሚፈልግና ስዕሉን ግን መስራት እንደማያቅታቸው በወኔ ተናግረዋል:: በሥራዎቻቸው ጎልተው ከሚንፀባረቁ ጉዳዮች መካከል እናትነትና ተፈጥሮ ዋነኞቹ ናቸው::
ሰዓሊና መምህር ወርቁ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ሆነው ለ22 ዓመታት ያህል ስዕልን በማስተማር በርካታ ሰዓሊያንን ማፍራት የቻሉ አንጋፋ ባለሙያና የአገር ባለውለታ ናቸው:: ሰዓሊ ወርቁ የስዕል ሥራዎቻቸውን በብዙ ኤግዚቢሽኖች ላይ ለሕዝብ አቅርበዋል:: ከአገር ውጭም በአሜሪካና በሶቭየት ኅብረት ኤግዚቢሽኖችን አሣይተዋል::
በትርፍ ጊዜያቸው ፎቶ ማንሳት የሚያዘወትሩት አንጋፋው ሰዓሊ፤ በእጆቻቸው መቆረጥ ከመማረር ይልቅ እርሳቸው ትልቅ ደረጃ ላይ መድረሳቸው ሌሎችን እንደሚያበረታታ በጽኑ የሚያምኑ ሰው ናቸው:: ‹‹ … የእኔን መቆረጥ አይተው በዚህ ላይ እዚህ ደረጃ ላይ የደረስኩ ሰዓሊ መሆኔን ሲያዩ ብዙዎች ተበረታተዋል:: እኔን አይተው ጠንክረዋል:: እኔን አይተው የማይቻል ነገር እንደሌለ አረጋግጠዋል:: በርትተዋል:: ስለዚህ የእኔ እጆች መቆረጥ ለብዙዎች ጥንካሬን ስለፈጠረ ለበጐ ነው … ›› ብለው ያስባሉ::
ስለልጅነታቸው ዘመንና ስለእናታቸው ውለታ ሲገልፁም ‹‹… ሥራዎቼን ስሰራ የማስታውሰው ነገር በልጅነቴ የኖርኩትን ነገር ነው:: እናቴ ሁልጊዜም ይረዱኝና ያግዙኝ ነበር:: ሁልጊዜም ከጎኔ ነበሩ::
ወደፊት ራሴን እንደምችል ተስፋ ነበራቸው … ደምን በልጅነቴ ከፈነዳው ቦምብ በስተቀር በጦርነት ያላየሁ ቢሆንም የቤተሰቤና የእኔ ሕይወት በጦርነት የተሞላ ነው:: በዚያ ጎምዛዛ ዘመን ሁሉ ወላጅ እናቴ ያደረጉልኝ ውለታ ከቶ የሚከፈል አይደለም::
ሰዎች ሁሉ እጅ አልባ ጨቅላነቴን እያዩ ‹ምነው ወይ ወዲያውኑ ሞቶ ባረፈው› እያሉ እናቴን ቁም ስቅላቸውን ሲያሳዩዋቸው፤ ጠንካራዋ እናቴ ግን ‹ለእርሱ የሚሆን ቦታ ሞልቷል፤ ቢያንስ ጥብቅናም ቢሆን ሰርቶ ይበላል› እያሉ በመንፈስ ፀንቶ ከማፅናታቸው ሌላ ምግቤን በዚያው በተረፈው እጄ መመገብን ከማስተማር ጀምሮ የንድፍ ሥራዎችን ማረምና ማበረታታት፣ ለእኔም ሲሉ ስዕል መንደፍንና መተቸትን ሳይቀር ሥራዬ ብለው መያዛቸው ለእኔ ታላቅ ትውስታዎቼ ናቸው …›› በማለት ተናግረዋል::
ሰዓሊ ሥዩም ወልዴ ስለወርቁ ማሞ ‹‹… ወርቁ ማሞ ከብዙ ሰዓሊዎች የሚለይበት አንድ የተለየ የሰዓሊነት ፀጋ አለው:: ይህም የመስመር አጣጣሉ ነው:: በስዕል ቴክኒክ ውስጥ ብዙ ሰዓሊዎች የማይታደሉትን የመስመር ቀጥተኛ መተጣጠፍና ተመልሶ መዘርጋት የወርቁ መንደፊያ ቁሳቁሶች በቀላሉ ያወጡታል::
በመስመር አማካኝት የሚገልፃቸው ወንዴነትና ሴቴነት ተዋህደው የላቀ የቅኔነት ጠባይ ያሳያሉ:: ታያተው አይጠገቡም:: የወርቁን ረቂቅ የሕይወት ፍልስፍና ይናገራሉ:: የወርቁ ቁስ አካላዊ ግንዛቤ የጠነከረ ነው:: ማንኛውም አካል አጠገቡ ከሚገኘው ሌላ አካል ላይ ላዩን ሳይሆን እጅግ ጠበቅ ብለው እንደሚነካኩ ያሳያል::
በዕይታችን ላይ የሚኖራቸውን ተፅዕኖ በጣም በበለፀገ ቴክኒካዊ ችሎታ ያስቀምጣቸዋል:: በቀለማት ቅላፄ የሚያደርገው ጨዋታ በተመልካቹና በስዕሉ መካከል የሞቀ ግንኙነት ለመፍጠር ያስችላል … ›› ብሎ መናገሩን የ‹‹የካቲት›› መጽሔት የኅዳር ወር 1976 ዓ.ም ዕትምን ጠቅሶ ፍፁም ወልደማርያም ‹‹ያልተዘመረላቸው›› በተሰኘው መጽሐፉ ላይ ጠቅሷል::
ከቀድሞ ተማሪዎቻቸው መካከል አንዱ የሆኑት ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ስለአንጋፋው መምህራቸው በሰጡት ምስክርነት ‹‹ … ወርቁ ማሞ ጥልቅ ባሕር ነው:: ወሰን የለሽ! ሁልጊዜም የሚያበቅለው ደግ ደጉን ነው::
ለረጅም ዓመታት አስተምሮኛል:: ወርቁ በጥበብ ዓለም ውስጥ በጀግንነት የተፈጠረ አንድና ብቸኛ ሰው ነው:: ወርቁ በፒራሚድ ይመሰልብኛል:: እርሱ ጫፉ ሲሆን እኛ ደቀ መዛሙርቱ ደግሞ ግርጌው ነን:: የመሳል ኃይሉን፣ ጊዜውን እውቀቱን፣ ያዋለው ለተማሪዎቹ ነው::
በዚህም አያሌ ወርቆችን ፈጥሯል:: የመምህርነት አሻራው እስከዛሬ ድረስ ይታያል፤ ንፍገት የሌለው መምህር ነው … ›› ብለዋል:: ሠዓሊ እሸቱም ለትምህርት ወርቁ ወደተማሩበት ወደ ሩሲያ ባቀኑበት ወቅት፣ ወርቁ በተማሩበት ተቋም ወደር ከማይገኝላቸው ተማሪዎች አንዱ እንደነበሩ መስማታቸውን ተናግረዋል::
ሰዓሊና ቀራፂ በቀለ መኮንን በበኩላቸው ‹‹ … ይህ ሰው ከዚያ ወዲያ ማዶ አድማሱ ላይ አነጣጥሮ ያስተውላል:: ሊደነቅ የሚችል ሩቅ አስተሳሰብ እንዲሁም የአሠራርና የአኗኗር ፍልስፍናዎች አሉት … ማስተላለፍ የሚፈልገውን መልዕክት ዘወር ባለ አማርኛ መግለጹን አልረሳውም … ጎበዝ ሠዓሊ ነው የሚባለው እጆቹ ስለሌሉ አይደለም፤ እጅ ካላቸው በበለጠ ሠርቶ ስላሳየ እንጂ … ›› በማለት ስለአንጋፋው ሰዓሊ ችሎታ መስክረዋል:: እንግዲህ እነዚህ ሁሉ ምስክርነቶች የአንጋፋውን ሰው አስደናቂ ባለሙያነት የሚያሳዩ ናቸው::
ሰዓሊና መምህር ወርቁ ማሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት በተጨማሪ በአቢሲኒያ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት በርካታ ሰዓሊያንን ማፍራት ችለዋል:: በ1994 ዓ.ም በስዕል ጥበብ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ ሆነዋል:: በ2002 ዓ.ም በብሔራዊ ሙዚየም ግቢ ውስጥ የልደት በዓላቸው ተከብሮላቸዋል::
አያሌ የሥነ ጥበብ ልሂቃንን ስለማፍራታቸው እንዲሁም በኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ተጠቃሽ የሆኑ ሥራዎቻቸውን ለመዘከር፣ በ2008 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር የምስጋና መርሐ ግብር ተዘጋጅቶላቸው ነበር::
ገጣሚ ታገል ሰይፉ በአንድ ወቅት ስለአንጋፋው ሰዓሊና መምህር ወርቁ ማሞ እንዲህ ብሎ ገጥሞ ነበር፡-
‹‹እጆቹን ቢያጣ እጅ አበቀለ
እልል በይ ጥበብ፣ ጉድ በል ተማሪ፣
እጁን ሲቀጥል እንደ ፈጣሪ::
እጅ የሌለው ተብሎ ቢናቅም፣ ፀንቶ ታሪክ ሠራ፣
እጅ የሌለው ወርቁ እጀኞች አፈራ:: ››
ሰዓሊና መምህር ወርቁ ማሞ ከጥበብ አርበኞች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ አንጋፋ ባለሙያና የአገር ባለውለታ ቢሆኑም ለአበርክቷቸውና ለውለታቸው የሚመጥን እውቅና እንዳልተሰጣቸውና ድጋፍም እንዳልተደረገላቸው የቀድሞ ተማሪዎቻቸውና የጥበብ አፍቃሪያን በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል:: አንጋፋው የጥበብ ሰው በአሁኑ ወቅት የ86 ዓመት አዛውንት ናቸው::
አዲስ ዘመን የካቲት 10/2013