እግር ኳስ በኢትዮጵያ ተወዳጅ ስፖርት ነው። ምንም እንኳ እንደ ሀገር ውጤታማ ብሔራዊ ቡድን መገንባት ባይቻልም ኢትዮጵያውያን ለስፖርቱ ያላቸው ፍቅር ከፍተኛ ነው። በስፖርቱ ዘርፍ ስማቸው በጉልህ ከሚነሱ ግለሰቦች መካከል በተጨዋችነትና በአሰልጣኝነት በርካታ ድሎችን መጎናፀፍ የቻለው አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ አንዱ ነው።
አስራት ኃይሌ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ስማቸው በጉልህ ከሚጠሩ ስኬታማ አሰልጣኞች መካከል የሚጠቀስ ነው። የአሰልጣኝነት ሥራ ከጀመረ ከ40 ዓመታት በላይ የደፈነው አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ በውጤታማነቱ፣ በቆራጥነቱ እና ጠንካራ ሠራተኝነቱ በበርካቶች ዘንድ ይወደሳል።
ከአባቱ ከአቶ ኃይሌ ገብሬ እና ከእናቱ ወ/ሮ አየለች መንገሻ ኅዳር 27 ቀን 1944 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ልደታ ከፍተኛ ፍ/ቤት አካባቢ የተወለደው አስራት፤ እድሜው ለትምህርት ሲደርስ የመጀመሪያ ትምህርቱን በቄስ ት/ቤት ከ1 እስከ 7ኛ በተስፋ ኮከብ ፤ 8ተኛ ክፍል ባልቻ አባ ነፍሶ፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በልኡል መኮንን(አዲስ ከተማ) በመማር አጠናቋል።
በመቀጠል ዝንባሌው ወደ እግር ኳስ በማድላቱ በሰፈር ቡድን በመስከረም ኮከብ ከተጫወተ በኋላ ውጤት በማሳየቱ በ1953 በዳርማር ህጻናት ለመጫወት በቃ። ችሎታውና ለስፖርት ያለውን ፍቅር በማየትም በወቅቱ የድሬዳዋ ጥጥ ማህበር ወይንም ኮተን አሰልጣኝ የነበሩት ሉቻኖ ባሳሎ በ1963 ክለቡን እንዲቀላቀል አድርገውታል። በቆይታውም ባሳየው ብቃት ለሐረርጌ ምርጥና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መመረጥ ችሏል። በድሬዳዋ ጥጥ ማህበር ቆይታው ሁለት ጊዜ የኢትዮጵያ ክለብ ሻምፒዮና ፤ የሐረርጌ ክፍለ ሀገር ምርጥ ቡድን ጋር አንድ ዋንጫ አንስቷል።
ለጥጥ ማህበር በሚጫወትበት ወቅት የሀረርጌ ምርጥ ፣ በቅዱስ ጊዮርጊስ እያለ ደግሞ ለሸዋ ምርጥ እና ለመሰኢማ ተጫውቷል። ለረጅም ጊዜ በቆየው የብሔራዊ ቡድን ቆይታውም በ10ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች እና በ11ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ የመጀመሪያ ተሰላፊ ነበር ።
በመቀጠልም በ1968 ዓ.ም ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ በመምጣት ለ 3 ዓመት በተጫዋችነት እንዲሁም በአምበልነት ቆይታ አድርጓል። አሁንም በመቀጠል ለዋናው ብሔራዊ ቡድን በመመረጥ ለ9 ዓመታት የተጫወተ ሲሆን በተለይ በ1968 ዓ.ም በኢትዮጵያ አዘጋጅነት በተደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ቡድን 4ኛ ሆኖ እንዲያጠናቅቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል።
ከዛም ፊቱን ወደ አሰልጣኝነት በማዞር በመጀመሪያ ለትግል ፍሬ ቡድን በአሰልጣኝ በመሳተፍ በ1972 ዓ.ም የአዲስ አበባ አንደኛ ዲቪዚዮን ሻምፒዮን እንዲሆን አድርጎታል። በመቀጠል ለህንፃ ኮንስትራክሽን 50 ክለቦች በአዲስ ሲዋቀሩ እና ጥሩ 10 ክለቦች ወደ አንደኛ ዲቪዚዮን ሲያልፉ ከህንፃ ጋር አራተኛ በመውጣት ክለቡ ወደ አንደኛ ዲቪዚዮን እንዲገባ አድርጎታል።
አሁንም በመቀጠል የአሰልጣኝነት ችሎታውን በማጎልበት ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን በመያዝ ከ1983-1992 ዓ.ም ለዘጠኝ ዓመታት ያህል አሰልጥኗል። በቆይታውም የተለያዩ ዋንጫዎችን ያነሰ ሲሆን በ1975 ዓ.ም ቡድኑ ወደ አንደኛ ዲቪዢን እንዲገባ አድርጓል። በ1987 ዓ.ም ደግሞ የቀረቡትን አጠቃላይ 5(አምስት ዋንጫዎች ማለትም የኢትዮጵያ ሻምፒዮና የጥሎ ማለፍ ዋንጫ፤ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ፤ የፀባይ ዋንጫ፤ ያነሳ ከመሆኑም በላይ እራሱ ኮከብ አሰልጣኝ ከመሆንም በላይ በክለቡም ኮከብ ተጫዋችም እንዲመረጥ አድርጓል።
ወደ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በማደግ የተስፋ ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ ሥራውን የጀመረው አስራት ቀጥሎም የዋናው ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ በመሆን በኢትዮጵያ በተደረገው የሴካፋ ውድድር ላይ ዋንጫ በማንሳት ብቸኛ አሰልጣኝ መሆን ችሏል። በተጨማሪም በመከላከያ የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ባለቤት፤ መብራት ኃይል ሲቲ ካፕ ዋንጫ፤ የኢትዮጵያ መድህን ከአንደኛ ዲቪዚን ወደ ፕሪሚየር ሊግ እንዲገባ አድርጓል።
በመጨረሻም በደደቢት ስፖርት ክለብ በአማካሪነት ገብቶ በማሰልጠን ዋናው አሰልጣኝ ከዋናው ቡድኑ ከተሰናበቱ በኋላ ወደ ዋና አሰልጣኝነት ገብተው በሁለተኛ ደረጃ እንዲጨርስ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ አሰልጣኞች ማህበር መስራችና አባል በመሆን፤ የአዲስ አበባ እግር ኳስ አሰልጣኞች ማህበር ፕሬዚዳንት፤ የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት በመሆን አገልግሏል። በአጠቃላይ በአሰልጣኝነት ሕይወት ዘመኑ ከ30 በላይ ዋንጫዎችን አግኝቷል።
በ1970ዎቹ በተጀመረው የአሰልጣኝነት ዘመኑ በርካታ ክለቦችን አሰልጥኗል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ህንፃ ኮንስትራክሽን፣ መከላከያ፣ ኤሌክትሪክ፣ መድን፣ ደደቢት ከብዙ በጥቂቱ ያሳለፈባቸው ክለቦች ናቸው።
አስራት ኃይሌ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች በመሆን ከተቀላቀለ ጀምሮ በተጫዋችነትና በአሰልጣኝነት በስፖርት ክለቡ ታሪክ ሰርቷል። <<እኔ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የምለየው>> ስሞት ብቻ ነው ያለው አስራት ኃይሌ በሕይወት ዘመኑ የቅዱስ ጊዮርጊስ የዋንጫ መደርደሪያ ካስዋቡ ታሪከኞች ተርታ አስራት ኃይሌ በቀዳሚነት ይሰለፋል።
በ1975 ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር በአዲስ አደረጃጀት ከዋቀረበት ዘመን ጀምሮ እግር ኳስ ለመቆም እና ጫማውን ለመስቀል እድሜው የደረሰበት ዘመን ላይ ቢሆንም የምወደው የልጅነት ክለቤ ተቸግሮ ማየት ህሊናየን ሰላም አይሰጠውም በማለት ከሌሎች የቀድሞ አንጋፋ ተጫዋቾች ጋር በመሆን ዘመን የማይሽረውን ታሪክ ጽፏል።
አስራት ኃይሌ ጫማውን ከሰቀለበት ጊዜ ጀምሮ የቅዱስ ጊዮርጊስን ስፖርት ዋናውን ቡድን በአሰልጣኝነት እየመራ በ1986፤ 1987፤ 1988 ለተከታታይ ሶስት ዓመታት ዋንጫ በማንሳት ታሪክ በመሥራት ቀዳማዊ ሰው ነው።
አስራት ኃይሌ ያስመዘገባቸው ውጤቶች በአደባባይ ምስክሮች ናቸው። ከነዚህም መካከል መቼም የማይረሳው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁለት አጋጣሚዎች በ1977 እና በ1991 ከወረደበት ከታችኛው ሊግ ወደ ላይኛው ሊግ ያሸጋገረበት ታሪክ አይረሰም። በዚህ አጋጣሚ ወደ ከፍተኛ ሊግ ባመጣበት ዓመት ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ዋንጫ ያነሳ ብቸኛ ሰው ያደርገዋል።
አስራት ኃይሌ በአሰልጣኝነት ዘመኑ ያሰለጠናቸው ተጫዋቾች አብዛኛውን ዛሬ ላይ በሀገራችን ባሉ ውድድሮች ውሰጥ አሰልጣኝነት በቅተው ለሀገሪቱ የእግር ኳስ እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ በመሆኑ ፍሬውን አፍርቶ በአደባባይ አስመስክሯል።
አስራት ኃይሌ ለሀገራችን ኢትዮጵያ ሁለት ጊዜ የሴካፋ ዋንጫን ያነሳ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ታሪክ ከሀገር ውጭ የምስራቅ አፍሪካን ዋንጫ ለማምጣት ግንባር ቀደሙ ነው። አስራት ለሀገሩ ብሎም ለክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስን እንዲሁም የሚወዳትን ኳስ በጥቅም ሳይደለል ለሚወደው እግር ኳስ ስፖርት መስዋት የከፈለ ጀግና ስለመሆኑ ብዙዎች ይመሰክራሉ።
አስራት ኃይሌ በወጣት ተጫዋቾች ሙሉ እምነትና ተስፋ ስለነበረው አብዛኞቹ ወጣቶች ከታች በማሳደግ ለቅዱስ ጊዮርጊስና ለብሔራዊ ቡድንም የሚታይ ታሪክ ሰርቷል። በህፃናት ክህሎትና ለወጣቶች ባለው ጥልቅ ፍቅር በየዘመናቱ በድካም ሥራውን እስካቆመበት ድረስ በህጻናት ወጣቶች ፕሮጀክት ማስፋፋት ለሚወደው የእግር ኳስ ስፖርት የማይረሳ ታሪክ ሰርቷል።
አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ ስለ እግር ኳስ አሰልጣኝነት ጅማሬው በአንድ ወቅት ሲናገር፤ ‹‹አሰልጣኝነትን ስጀምር ሥራውን ስጀምር በቀጥታ ከትልቅ ቡድን አልጀመርኩም። ራሴን ለማስተካከልና ለማሻሻል፣ እንዲሁም ሥራዬን በልበ ሙሉነት እንድሰራ እና የቋንቋ ችሎታዬን ለማዳበር የሠራተኛ ማህበር (መኢሰማ) ለአራት ዓመታት ያህል አሰለጠንኩ። የአሰልጣኝነት መሠረታዊ ስልጠና (Basic Course) የወሰድኩት በ1971 ዓ.ም. ነው። አቶ ይድነቃቸው ተሰማ (ነፍሳቸውን ይማረውና) “እናንተ ተጫዋቾች መጫወትን ስታቆሙ አሰልጣኝ ስለምትሆኑ ኮርስ መውሰድ አለባችሁ።” ብሎን በአንድ ጀርመናዊ አሰልጣኝ አማካኝነት ኮርስ ወሰድኩ። በሙሉ የአሰልጣኝነት ሥራም ህንፃ ኮንስትራክሽን የመጀመሪያ ቡድኔ ነው።›› በማለት ወደ አሰልጣኝነት የገባበትን ታሪክ ያስታውሳል።
ተጫዋቾቼ በአካል ብቃት ረገድ የተሻሉ እንዲሆኑ እፈልጋለሁ የሚለው አስራት፤ ከክብደት ሥራ ጋር በተገናኘ ለእግር ኳስ ተጫዋቾች በምን ያህል ደረጃ መሆን እንዳለበት ከመጽሐፎች ላይ በማንበብ መረጃዎችን አገኝ ነበር። ተጫዋቾቼን በአቀበት ላይ የትንፋሽ ሥራን አሰራቸው ነበር ፤ የተለያዩ ክብደት ያላቸው ነገሮችን (sand jacket) በማስያዝ ዳገት እንዲወጡ አደርጋቸው ነበር።
ተጫዋቾቹ ከፍተኛ ጉልበት እንዲኖራቸው እና የአካል ብቃታቸው ጥሩ ደረጃ ላይ እንዲገኝ ያግዛቸው ነበር። ሆኖም በኋላ ላይ በዚሁ ጨራዬ እታማ ጀመር። “አስራት ተጫዋቾችን ተራራ ያስሮጣቸዋል።” የሚል ወቀሳና ትችት ተከተለ። ልምምዱ ቢያስተቸኝም ለዘጠኝ ዓመታት ውጤታማ ቡድን ስገነባ የማሰራው ይህን መሠል የአካል ብቃት ሥራ ነበር። ሌሎች ቴክኒካዊ፣ ታክቲካዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ጉዳዮች ላይ የማተኩረውን ያህልም ለአካል ብቃት ልዩ ትኩረት እሰጥ ነበር ይላል።
“ለምፈልገው የጨዋታ ሥርዓት ሁሉም ተጫዋቾች ሙሉ ትኩረታቸውን እንዲሰጡኝ እፈልጋለሁ። የምናገረውንና የማስረዳውን መሠረታዊ ነገር እንዲገነዘቡ እሻለሁ። ሳስረዳ ሃሳቡ ከኔ ጋር የማይሆን ተጫዋች አልፈልግም። በቡድን የጨዋታ እንቅስቃሴ ተጫዋቾች በሜዳ ውስጥ በሚኖራቸው ሚና ላይ ያላቸውን ግንዛቤና አረዳድ መገምገም እፈልጋለሁ። ይህንንም በልምምድ ወቅት በትክክል እንዲተገብሩት እፈልጋለሁ።
“ለስህተቶችም እርማት እሰጣለሁ። በልምምድ ወቅት በቀጣይ ጨዋታ ላይ የተሻለ ታክቲካዊ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ተደጋጋሚ ትምህርቶችን አስተምራለሁ። ተጫዋቾቼ በደንብ እንዲገባቸው እፈልጋለሁ። በምነግራቸው ነገሮች ላይም እንዲወያዩበት አደርጋለሁ። የተረዱበትን መጠንም ለማወቅ ጥያቄዎችን እጠይቃቸዋለሁ። በሜዳ ውስጥ የተጋጣሚ ቡድኖችን አሰላለፎች እንዲሁም የተጫዋችን የግል ብቃት እንዲያዩ አዛቸዋለሁ፤ በዚህም ውጤታማ ሆኛለሁ ይላል።
አስልጣኝ አስራት በሕይወት እያለ ከተለያዩ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ጋር በነበረው ቆይታ በሰጠው አስተያየት እንደተናገረው፤ በአካል ብቃት ልምምዴ ላይ የነበረብኝ የትችት ውርጅብኝ ከመጠን በላይ ነበር። ከአሰልጣኞችም ራሱ ከፍተኛ ትችት ይገጥመኝ ነበር። ጋዜጦችም በብቃት መውረድ ምክንያት ከቋሚ አሰላለፍ ውጪ የሆኑ ተጫዋቾችን ቃለ መጠይቅ እያደረጉ እኔን ጫና ውስጥ ይከቱኝ ነበር። ዋንጫዎችን አሸንፌም ከክለቦች የለቀኩባቸው ጊዜዎችን አሳልፌአለሁ። ሆኖም በማምንበት ነገር በመጽናቴ አሸናፊ በመሆኔ እና በሥነ ልቦና ዝግጅቴ ስሜቴ አልተጎዳም። እንዲያውም ይበልጥ እየጠነከርኩ ሄድኩ ይላል።
ሥራውን በውጤት አድምቆ፥ ስኬቱን በዋንጫና በሜዳሊያዎች አጅቦ፤ ከአንዴም ሁለቴ ኮከብ አሰልጣኝ ተብሎ ተሸልሞ፤ ስሙን በደማቁ ፅፎ 38 ዋንጫዎችን የወሰደው አስራት በሕይወት ብያልፍም ለኢትዮጵያ የእግር ኳስ ስፖርት የዋለው ውለታ ስሙን ከመቃብር በላይ እንዲነሳ ያደርገዋል።
በቤተሰብ ሕይወቱ አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ በ1970 ከወ/ሮ በየነች ሰለሞን ጋር ትዳር መስርቶ የአምስት ሴቶችና የሁለት ወንድ ልጆች አባትና የስድስት የልጅ ልጆች አያት ነበር። አሰልጣኙ ባደረባት ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ጥቅምት 15 ቀን 2017 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ሥርዓተ ቀብሩም ዊንጌት አካባቢ በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ጳውሎስ ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል።
እኛም በዚህ ለሕዝብና ለሀገራቸው መልካም ያደረጉና በተሰማሩበት ዘርፍ ሁሉ የማይነጥፍ ዐሻራ ማኖር የቻሉ ግለሰቦች ታሪክ አንስተን ለአበርክቷቸው ክብር በምንሰጥበት የባለውለታዎቻችን አምድ እውቁን የስፖርት ሰው አሰልጣኝ አስራት ኃይሌን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ለዋለው ውለታ አመሰገንን። ሰላም!
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥቅምት 20 ቀን 2017 ዓ.ም