የኢትዮጵያ የዘመናዊ ሙዚቃ ጉዞ መነሻ እየተደረገ በታሪክ የሚነሳው የ40ዎቹ የአርመን ልጆች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት እና የማርሽ ባንድ ማቋቋም ነው። ይሁን እንጂ ገና በአጼ ምንሊክ ዘመን ጀምሮ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሙዚቃ ቡድን የማቋቋም ሙከራዎች ነበሩ።
ፍራንሲስ ፋልሴቶ ስለኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ጉዞ በጻፈው ማስታወሻ ይህን ሃሳብ አስፍሯል፤ አጼ ምንሊክ አድዋ ላይ ጣሊያንን ድል ካደረጉ በኋላ የሩሲያ ሳር (tsar) ንጉሱን እጅ ለመንሳት አምባሳደራቸውን ወደ ኢትዮጵያ ላኩ። አምባሳደሩ ለንጉሱ ይዞ ከመጣው እጅ መንሻ መካከል 40 የብራስ የሙዚቃ መሳሪያዎች ይገኙበት ነበር።
የሙዚቃ መሳሪያ የአጨዋወት ሞያ ለማሰልጠን ደግሞ ሚሌውስኪ (Milewski) የተባለ የሙዚቃ መምህር አብሮ ተልኮ ነበር። ሚሌውስኪም ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን ሙዚቃ ለማስተማር ጥረት ያደርግ ነበር። ከዚህ ከፋልሴቶ ማስታወሻ እንደምንረዳው፤ የአድዋ ድል ለኢትዮጵያ የዘመናዊ ሙዚቃ ጉዞ በር ከፋች ጭምር ነበር።
ከላይ የተጠቀሱት የታሪክ አጋጣሚዎች እንዳሉ ሆነው በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ እጅጉን ያበበበት እና ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሰበት ዘመን ከ1947 ዓ.ም. እስከ አብዮት ፍንዳታ ድረስ ያሉት ሀያ ዓመታት ናቸው። እኚህ 20 ዓመታት ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ወርቃማ ዓመታት ነበሩ። ቀደም ብለው ተቋቁመው የነበሩት የተለያዩ ወታደራዊ ባንዶች ምርጥ ምርጥ ድምጻውያንን በመመልመል አዳዲስ ሙዚቃዎችን እያጠኑ ብቅ ማለት ሲጀምሩ የአጼ ኃ/ሥላሴ እና የሀገር ፍቅር ትያትር ቤቶችም መድረኩን በመቀላቀል ምርጥ ምርጥ ሙዚቃዎችን እያዘጋጁ ማቅረብ ጀመሩ።
በ1950ዎቹ መጨረሻ እና በ1960ዎቹ እንደ ራስ ባን ያሉ የግል ባንዶች በብዛት መቋቋም ጀመሩ። ይህ ጊዜ የተለያዩ እውቅ ሙዚቀኞች ወደ መድረክ የመጡበት እና የኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃ ከምዕራቡ ዓለም ሙዚቃ ጋር እየተዋሃደ የራሱን ቀለም እና መስመር መያዝ የጀመረበት ጊዜ ነበር።
በዚያ ዘመን ከመጡና በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ የማይነጥፍ አሻራቸውን ማኖር ከቻሉ ስመ ጥሩ አቀንቃኞች መካከል አንዱ ማሕሙድ አሕመድ ነው:: በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተወዳጅነትን፣ ተደናቂነትን፣ ተፈቃሪነትን ማትረፍ የቻለ ፈርጥ እንደሆነ ብዙዎች ያምናሉ:: ሙሉ ሕይወቱን በሙዚቃ ያሳለፈው ማሕሙድ በሙዚቃው ይተነፍሳል፣ ይናገራል፣ ሰውን ያዝናናል ይባልለታል።
ከ60 ዓመታት በላይ በቆየውም የሙዚቃ ሕይወቱ የተለያዩ ትውልድን በሙዚቃው አንድ ላይ ማምጣት የቻለ ትልቅ አርቲስት ነው:: በተለያዩ ኮንሠርቶች በሚዘፍንበት ወቅት በተለያዩ የዕድሜ ክልሎች የሚገኙ ሰዎች ብሔራዊ መዝሙር በሚመስል መልኩ አብረውት በመዝፈንም በዘፈኑ አንድነትን ያሳያሉ::
ማሕሙድ የዝና ጣራ ላይ መድረስ ችሏል:: በሕዝቡ ዘንድ ከመወደዱ በተጨማሪ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይም ዝናው ናኝቷል:: የሰዎችን ልብ ከማሸነፉ በተጨማሪ ከኮንሠርቱ በፊት ቲኬቶቹ ተሸጦ የሚያልቅበት አጋጣሚም ተደጋጋሚም ነው:: የተለያዩ ሽልማቶችንም ለማሸነፍም ችሏል:: ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የቢቢሲ ወርልድ ሚዩዚክ አዋርድ አንዱና ዋነኛው ነው:: ምንም እንኳን ይሔን ያህል የጣራ ዝና ላይ ቢሆንም ትሁት፣ ሰዎችን የሚያከብርና በቀላሉም የሚግባባ ሰው እንደሆነ ይነገርለታል።
በ1933 ዓ.ም. በሰባት ቤት ጉራጌ ቦዠበር የተወለደው ማሕሙድ፤ ዕድገቱ ደግሞ በአዲስ አበባ አሜሪካን ግቢ አካባቢ ነው:: ሥራንም ሆነ ሕይወትን በራሱ መጋፈጥ የጀመረው ገና በሕፃንነቱ ነበር:: አባቱ በሚሠራበት ግሪክ ክለብ አብሮ በመሔድ ቅርጫት ኳስና የቴኒስ ሜዳዎቹ ላይ ይሠራም ነበር:: በስድስት ዓመቱም ሊስትሮ ሆኖ መሥራት እንደጀመረም ይነገራል::
በትምህርት ቤት ቆይታው ብዙ ጐበዝ እንዳልነበር ፈገግ ብሎ የሚያወራው ማሕሙድ፤ ቤተሰቦቹንና ራሱን መርዳት እንዳለበትም የተረዳው ገና በሕፃንነቱ ነበር:: የሙዚቃ ሕይወቱ ሀ ብሎ የተጀመረው ደግሞ፤ አንድ ክለብ ውስጥ ሳንድዊች እንዲያቀርብ በተቀጠረበት ጊዜ ነው:: እንደ አጋጣሚ ሆኖ በዚያው ክለብ ውስጥ ጥላሁን ገሠሠ ይዘፍንበት ነበር::
በአንድ አጋጣሚም ሁሉም ድምፃውያን ወደ ድሬዳዋ ሔደው ሙዚቀኞቹ ያለ ድምፃዊ እየተለማመዱ ነበር:: የተፈራ ካሣን ‹‹አልጠላሽም ከቶ››ን የተዘራን ‹‹ይሔም አለ ለካ››ንና የጥላሁን ዘፈን እየተለማመዱ ነበር:: በድምፅ መዝፈን እንደሚፈልግም ጠየቃቸው::
‹‹በጣም ቀጭን ነበርኩ እናም ‘ትችያለሽ? ወይ›› ብለው ጠየቁኝ፣ እኔም እሞክራለሁ አልኩ›› በማለት ማሕሙድ ይናገራል:: ‹‹አልጠላሽም ከቶ›› የሚለውን ዘፈን በሚዘፍንበት ሰዓት የኮንጐ ዘማቾች በቦታው ነበሩ፤ እናም አስደነቃቸው:: እንደገናም እንዲዘፍን ተጠየቀ:: የክለቡ ባለቤት በቦታው የነበረ ሲሆን፤ አድናቆት በተሞላ ድምፅም ‹‹የአላህ ያለ መዝፈን ትችላለህ!›› እንዳለው ማሕሙድ ያስታውሳል:: በዚህም አጋጣሚ ከአስተናጋጅነት ወደ ዘፋኝነት ተቀየረ:: የቤቱ ባለቤትም ሙሉ ልብስ ገዛለት::
ጥላሁንና ሌሎቹ ዘፋኞች በተመለሱበት ወቅት የእሱ መዝፈን በጣም አስገረማቸው፤ የግጥም ደብተር ሰጡት:: መዝፈን በጀመረበት ወቅት የተለያዩ ዘፋኞችን ሙዚቃ ይዘፍን ነበር:: በዚህም ክለብ ‹‹አላወቅሽልኝም›› የሚለው የመጀመሪያው ዘፈኑ የሆነው ግጥም ተሰጠው::
ክቡር ዘበኛ መቀጠር ፍላጐቱ የነበረ ሲሆን፤ መጀመሪያ ግን ፖሊስ ኦርኬስትራና ምድር ጦር ለመቀጠር ጠየቀ:: በተለያዩ ምክንያቶችም እንደማይቀጥሩት ነገሩት:: መቶ አለቃ ግርማ ሐድጉም (በኋላ ሻለቃ) ክቡር ዘበኛ መቀጠር ይፈልግ እንደሆነ ጠየቁት፣ እሱም ተስማማ ከመቀጠሩ በፊት ግን በሕዝብ ፊት ዘፍኖ ማለፍ ነበረበት:: የዚያን ጊዜ የነበረውን እያንዳንዷን ጥቃቅን ነገር በጥልቅ ያስታውሳል፤ የታምራት ሞላን ‹‹ተስፋ አትቁረጪ›› እንዲሁም ‹‹አላወቅሽልኝም››ን ሲዘፍን የተመልካቹ መልስ ለየት ያለ ነበር::
‹‹የኤልቪስ ፕሪስሊን ዳንስም እየደነስኩ ነበር፣ እናም የተመልካቹ መልስ የማይታመን ነበር፤›› በማለት ማሕሙድ ይገልጻል:: መቶ አለቃ ግርማም ወታደር ሆኖ እንዳይቀጠር መከሩት፣ የክቡር ዘበኛ ሰዎችም በወታደርነትና ሙዚቀኝነት 120 ብር እንክፈልህ ብለው ጠየቁት፤ እሱ ግን ባለመስማማቱም በሙዚቀኝነት ብቻ በ1955 ዓ.ም. አካባቢ ተቀጠረ:: ለአሥራ አንድ ዓመታት ያህልም በዚህ ቦታ ሠርቷል::
‹‹ለእዚህ ያበቃኝ፣ የማውቀውን ነገር ሁሉ ያስተማረኝ ለእኔ ወንድሜ ጥላሁን ገሠሠ ነው:: ሌሎችም ሙዚቀኞች እንዲሁ በእኔ ላይ አሻራ ጥለዋል፤›› ይላል ማሕሙድ::
በዚያን ወቅት ሙዚቀኞች አንድ ላይ ይሰባሰቡበት የነበሩ ብዙ አጋጣሚዎች ነበሩ:: ከእነዚህም ውስጥ ክቡር ዘበኛ ይሠራ በነበረበት ወቅት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ይደረግ የነበረው የሙዚቀኞች ውድድር አንዱ ነው::
የተለያዩ ባንዶች እንደ ምድር ጦር፣ ክብር ዘበኛና የፖሊስ ኦርኬስትራ ባንዶች ከድምፃውያኖቻቸው ጋር ይመጣሉ:: እያንዳንዱም ድምፃዊ አንድ ወይም ሁለት ዘፈን ይዘፍናል:: ይሄም ለሙዚቀኞች ጥሩ አጋጣሚ እንደነበር ይናገራል:: ከአሥራ አንድ ዓመታት ቆይታም በኋላ በተለያዩ ክለቦች መሥራት ጀመረ:: ለዚህም ምክንያቱ የነበረው ያገኘው የነበረው 60 ብር አምስት እህቶቹና ወንድሞቹ በአጠቃላይ ቤተሰቦቹን መደገፍ ስለማይችል ነበር::
በወቅቱ አባቱ ሥራ ያልነበራቸው ሲሆን፤ የምትሠራው እናቱ ብቻ ነበረች:: መጨረሻ ላይ ከክቡር ዘበኛ በለቀቀበት ወቅት ደምወዙ 250 ብር ደርሶ ነበር፤ ከዚያም ከአይቤክስ ባንድ ጋር ተጠቃልሎ ራስ ሆቴል ተቀጥሮ መሥራት ጀመረ:: በሙዚቃ ሕይወቱ ውስጥ ብዙ ውጣ ውረዶችን እንዳሳለፈ የሚናገረው ማሕሙድ፤ ዘመኑ ለሙዚቀኞችም ሆነ ለሙዚቃ ዕድገት የተመቻቸ እንደሆነ ይገልጻል:: እንደሚናገረው ከሆነ ይሄ ዕድገትም የተገኘውና እዚህ መድረስ የተቻለው በድሮ ሙዚቀኞች መስዋዕትነት ነው ይላል።
‹‹እነዚህ ሙዚቀኞች አሻራቸውን ጥለው ማለፍ ችለዋል፤›› የሚለው ማሕሙድ በዚያን ጊዜ የነበሩት ሙዚቀኞች ምንም እንኳን ችሎታው ቢኖራቸውም የሙዚቃ ትምህርት ቤት አልሄዱም:: የዚያን ጊዜውንም በማስታወስ ለሙዚቀኞች እንዴት ከባድ እንደነበር ይናገራል:: ሙያውም እንዴት ይናቅ እንደነበርም ያስታውሳል::
በ1963 ከአይቤክስ ባንድ ጋር ራስ ሆቴል በሚሠራበት ወቅት ‹‹ኩሉን ማን ኳለሽ››፣ ‹‹አምባሰል››፣ ‹‹ችቦ አይሞላም ወገቧ›› እና ‹‹አልማዝ ምን ዕዳ ነው›› የመሳሰሉ ዘፈኖችን ይዘፍን ነበር:: እነዚህ ዘፈኖች ከአንዳንድ ወገኖች ከፍተኛ ትችትም አጋጠመው:: የዱሮ ዘፈኖችን በአዲስ መልክ ትጫወታለህ ለማለት አንድ ጋዜጠኛ ‹‹ፍራሽ አዳሽ›› ብሎ የጠራውን አጋጣሚም አሁንም አይረሳውም::
‹‹አላዘንኩም:: የድሮ ዘፈኖችን አዲስ ሕይወት በመስጠት ዘፍኛለሁ:: ፍራሽም እንደ አዲስ ሲታደስ ይተኛበታል›› ይላል:: ማሕሙድ ከዚህም በተጨማሪ ‹‹ዓባይ ማዶ››፣ ‹‹ደኑን ጥሰሽ›› እና ‹‹የት ነበርሽ›› የሚሉት ዘፈኖቹም የተለየ ርዕዮተ ዓለም ያስተላልፋሉ በሚልም ተወቅሶ ነበር::
የማሕሙድ ዓለም አቀፍ ዕውቅና የመጣው ፍራንሲስ ፋልሴቶ ኢትዮጲክስ የሚለውን የሙዚቃ ስብስብ ካወጣ በኋላ ሲሆን፤ ማሕሙድም ውለታውን የረሳ አይመስልም:: ፋልሴቶ ፈረንሣዊ ፕሮሞተር ሲሆን፤ የማሕሙድን ‹‹መላ መላ›› የሚለውን ዘፈን ሬዲዮ ላይ ሰምቶ አብረን እንሥራ ብሎ ጠየቀው፤ ማሕሙድ መጀመሪያ ላይ ተጠራጥሮ እንደነበር ያስታውሳል:: እየተደራደሩ ባሉበት በ1960ዎቹ አካባቢ ማሕሙድ ወደ ፈረንሣይ አቅንቶ ሙላቱ አስታጥቄ ጋር አብሮ ዘፍኗል::
ከ1955 ዓ.ም ጀምሮ በይፋ ክቡር ዘበኛን በሲቪልነት በመቀላቀል ወደሙዚቃ የገባው አንጋፋው የትዝታው ንጉስ መሀሙድ አሕመድ በአዘፋፈን ችሎታው እና በድምፁ ውበት ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካ፣ አውሮፓ እና አሜሪካ ሳይቀር ሰፊ ተቀባይነት እና ተወዳጅነትን ያተረፈ ነው።
አርቲስት ማሕሙድ ከ60 ዓመታት በላይ በተሻገረው የጥበብ አበርክቶው ሀገሩን እና ወገኑን በከፍተኛ ፍቅር በብዙ ያገለገለ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ከባህላዊ ሙዚቃዎች ጋር አዋህዶ በመዝፈን በአገራችን የሙዚቃ ንጉስ ነው እስከመባል የደረሰ ታላቅ የጥበብ ሰው ነው።
የትዝታው ንጉስ ጋሽ ማሕሙድ አሕመድ በኢትዮጵያ ከ50 ዓመታት በላይ ከልጅነቱ አንስቶ የኢትዮጵያንን ሙዚቃ በተለያዩ ቋንቋዎች በመዝፈን የአገራችንን ሙዚቃ ከአገር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲደመጡ ያስቻለ ያበረከተው አስተዋጽኦ ለአሁኑ ትውልድ አርአያ የሆነ የሙዚቃ ንጉስ ነው።
እኛም ድምፃዊ ማሕሙድ ከ60 ዓመታት በላይ የተሻገረው የሙዚቃ ሕይወቱን በክብር ለመቋጨት በወዳጅ አድናቂዎች አማካኝነት ዝግጅት እየተደረገ ባለበት በዚህ ወቅት ለሕዝብና ለሀገራቸው መልካም ያደረጉና በተሰማሩበት ዘርፍ ሁሉ የማይነጥፍ አሻራ ማኖር የቻሉ ግለሰቦች ታሪክ አንስተን ለአበርክቷቸው ክብር በምንሰጥበት የባለውለታዎቻችን አምድ ስም ለኢትዮጵያ የሙዚቃ ዕድገት ለዋለው ውለታ አመሰገንን። ሰላም!
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ጥቅት 27/207 ዓ.ም