የአፍሪካ እግር ኳስ ዋንጫ ሲታወስ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ስማቸው ቀድሞ ከሚታወሱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ባለውለተኞች መካከል ስሙ በቀዳሚነት ይጠቀሳል። የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋችና አሠልጣኝ እንዲሁም የሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ባለድሉ የብሔራዊ ቡድን አምበል ሉቺያኖ ቫሳሎ።
ትውልዱ በኤርትራ በ1927 ዓ.ም. እንደሆነ የሚነገርለት ሉቺያኖ ቫሳሎ፣ ትውልድ የማይረሳው የዘመን ጀግና፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ሁሌም ከፊት የሚያስቀድመው በታሪካዊ ውለታው አይረሴ የሆነ የኢትዮጵያ እግርኳስ ባለውለታ ነው።
በእግር ኳስ ሕይወቱ ቀድሞ ድሬዳዋ ጥጥ ማኅበር (ወደ ኋላ ላይ ድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ) እንዲሁም ለቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ በመጫወት ይታወቃል። በዘመኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ሆኖ ባደረጋቸው በተለያዩ የአፍሪካ ዋንጫዎች ላይ ኢትዮጵያን በመወከል፣ ከቡድኑ ጋር ታሪካዊ ተብሎ እስካሁን የሚጠቀሰውን ሦስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ለኢትዮጵያ ከፍ ያደረገ ድንቅ እግር ኳሰኛ እንደነበርም የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።
በ1954 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በተደረገው የ3ኛ አፍሪካ ዋንጫ ፍጻሜ ግብፅን 4 ለ2 ኢትዮጵያ ስታሸንፍ ወሳኝ ግብ ያስቆጠረው ሉቺያኖ ቫሳሎ፣ እግር ኳስ እንዲህ እንደ አሁኑ ባልዘመነበት በዚያን ዘመን ከተጫዋችነት ሕይወቱ በተጨማሪ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን በማሠልጠን ታሪክ የሚያስታውሰው ድንቅ እግር ኳሰኛ ነበር።
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ብቸኛው እና ትልቁ ድል ሲገኝ የቡድኑ መሪ በኤርትራ የተወለደው፣ ባለ ቅይጥ ዜግነቱ፣ በጣሊያንኛ ስም የሚጠራው የያኔው ታላቁ ተጫዋች ሉቺያኖ ቫሳሎ ነበር። ሉቺያኖ የተወለደው ከጣሊያናዊ የቱስካን ወታደር አባት ቪቶሪዮ ቫሳሎ እና ከኤርትራዊት እናቱ ምብራቅ አብርሃም ነበር።
ከምንም ነገር ቀልድና ጨዋታ በመፍጠር የሚታወቀው ሉቺያኖ በአስመራ ጭርንቁስ መንደሮች እግር ኳስን መጫወት ጀመረ። በአርነት ወይም (ነፃነት) ጎዳና ለሲኒማ ኢምፔሮ ቅርብ የሆነውና በአስመራ ከሚገኙ ኃይማኖታዊ ትምህርት ቤቶች አንዱ የነበረው ኮሌጂዮ ላቬላ የሉቺያኖ የእግርኳስ ሕይወት በጥሩ ሁኔታ እንዲጀምር መንገድ ከፍቷል። ይህ የካቶሊክ ካቴድራል ትምህርት ቤት ስቴላ አስመሪና (የአስመራ ኮከብ) ተብሎ የሚጠራ የእግር ኳስ ቡድን ነበረው።
ጥቁርና ነጩ የቡድኑ መለያ በጣልያን- ኤርትራዊ (ኢታሎ-ኤርትራ) ጥንድ-ማንነት ላይ የተመሠረተው ቡድን መገለጫ ሆነ። በወቅቱ ክለቡ የተቋቋመበት ዋነኛ ምክንያት የቤተክርስቲያኗ አስተዳደሮች በከተማዋ በሚኖሩ ክልስ ታዳጊዎች አዕምሮ ውስጥ የሰፈነውን አሉታዊ የሥነ-ልቦና ተጽዕኖ ለማስወገድ እንዲያስችል ታስቦ ነበር። በጊዜው ከጣልያናውያን አባቶች የሚወለዱ ልጆች በአባቶቻቸው ያለመፈለግ ችግር ይገጥማቸዋል። በኤርትራውያኑ ዘንድም ቢሆን የጨቋኙና ቅኝ ገዢው ዘር በመሆናቸው የመገለል እና የመነጠል ጫና ይደርስባቸዋል።
ሉቺያኖ በስቴላ አስመሪና በግራ መስመር ተከላካይነት መጫወት ቢጀምርም ከቡድኑ ጋር ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ቆይታ አላደረገም። የእግርኳስ ክለቡ የተጫዋቹን ፍላጎት ማሟላት አልቻለም። ሉቺያኖም የሌሎች ክለቦችን ትኩረት አገኘ። የሀገሪቱ የምድር ባቡር ሠራተኞች ጠርተው አወያዩት። ግሩፖ ስፖርቲቮ ፌሮቬሪ በኤርትራ የባቡር ድርጅት ክለብ ነበር። ድርጅቱ በባቡር መንገድ ጥገና ሠራተኝነትና በተጫዋችነት ሉቺያኖን ለመቅጠር ቢደራደርም የተጫዋቹ ልብ ግን ወደ ሰማያዊ ለባሾቹ ገጀረት አደላ።
በከፍተኛ የኑሮ ውጣ ውረድ ውስጥ ያለፉ የኤርትራ ተወላጆችን የያዘው ይህ ቡድን የሉቺያኖ ማረፊያ ሆነ። የቡድኑ አባላት በከፍተኛ አንድነትና ጠንካራ የቡድን መንፈስ የተሳሰሩ ነበሩ። የተለያዩ የገንዘብ ማግኛ ዘዴዎችን በመጠቀምና በየሳምንቱ መጠነኛ መዋጮ በማሰባሰብ የቡድኑን የበጀት እጥረት ለመቀነስ ይጥሩ ነበር።
ሉቺያኖ በገጀረት እ.ኤ.አ ከ1953 -1958 ዓ.ም ባሳለፈው የስድስት ዓመታት ቆይታ ቡድኑ ወደ ከፍተኛው የሊግ እርከን እንዲያድግ አይነተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። ወደ ከፍተኛው ዲቪዚዮን ባለፉበት ዓመትም ገጀረት ከጣልያን ቡድኖች አንዱ በነበረው ግሩፖ ስፖርቲቭ ቪስቲኒቲ ላይ የተቀዳጀው የ 4-0 ድል የሉቺያኖን የላቀ ችሎታ ያሳየ ነበር። በጨዋታው ሉቺያኖ ያሳየው ብቃት ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለመጫወት ያስቻለውን የመጀመሪያ ጥሪ አስገኘለት።
የሉቺያኖ ቀጣይ ማረፊያ ግሩፖ ስፖርቲቮ ነበር ይህ ቡድን አስመራ በአሠልጣኝ ኤንዞ አርቺዮሊ አማካኝነት ሶስት የሊግ ዋንጫዎችን እ.አ.አ. በ1945፣ በ1947 እና በ1948 ማሸነፍ ቻለ። ሉቺያኖ ወደዚህ ክለብ በገባበት ጊዜ ቡድኑን በአምበልነት የሚመራው በአስመራ የሚገኙ የጣልያን ስፖርተኞች ምልክት የነበረው እና ‘ኤርትራዊው ሄሬራ’ በመባል የሚታወቀው ማሲሞ ፌኒሊ ነበር። ፌኒሊ በጣሊያን እንደተወለደ ቤተሰቦቹ ይዘውት ወደ አስመራ መጡ። ጣልያናዊው ተጫዋች እ.ኤ.አ. እስከ 1974 ዓ.ም በነበረው የኤርትራ ቆይታው በሀገሪቱ እግር ኳስ ላይ ትልቁን ዐሻራ ያሳረፈ ሰው መሆን ችሏል።
ቀጣዩ የሉቺያኖ የክለብ ዝውውር በክልስነቱ የሚፈጠርበትን አሉታዊ ተጽዕኖ በጉልህ ያመላከተ ነው። በ1950ዎቹ መጨረሻ ግሩፖ ስፖርቲቮ አስመራ የተባለው የጣልያኖች ቡድን ለሉቺያኖ የኮንትራት ጥያቄ አቀረበለት። የወቅቱ የክለቡ ፕሬዚዳንት ሰርጂዮ ሴሬኞ ወርሀዊ 600 የኢትዮጵያ ብር ደመወዝ እና በጣሊያኖቹ በሚተዳደረው የባቡር ትራንስፖርት ከፍተኛ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ውስጥ በመደበኛ ሥራ የመቀጠር እድል አመቻቹለት። ለተጫዋቹ የቀረበለት ይህ ግብዣ እምቢ የሚለው አልነበረም።
እናቱን እንዲሁም ሁለቱን ታናናሽ ወንድምና እህቱን (ኢታሎ እና ሊና) የሚረዳበትን አጋጣሚ ፈጠረለት። ይህን መጠሪያ ያገኘውም ታዋቂው ጣልያናዊ ሥራ ፈጣሪ (ኢንተርፕረነር) ፍራንቼስኮ ሲሴሮና በዘመኑ በፋሽስቶች ከሚመሩት የእግርኳስ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው ይህ ክለብ በጋራ የመስራት ስምምነትን ከፈጠሩ በኋላ ነው።
የዓድዋው ሽንፈት በተለይ በጣሊያን ከፍተኛ ውዝግብን ፈጥሯል። በሽንፈቱ ምክንያት በሀገሪቱ የነበሩት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተዘግተው የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ፍራንቼስኮ ክሪስፒም ከሥልጣን ራሳቸውን አገለሉ። አዲሱ የስታዲየሙ ስያሜም እ.ኤ.አ. በ1962 በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ለተፈጠረው የመዋሀድ ውሳኔ መንገድ አመቻቸ። እ.ኤ.አ. በ1953 የኤርትራ የእግር ኳስ ሻምፒዮና ከኢትዮጵያ የእግር ኳስ ውድድር ጋር ተቀላቀለ። ከኤርትራ ሦስት ቡድኖች፣ ከሸዋ ክፍለ ሀገር እና ከሐረር ጠቅላይ ግዛት ሌሎች አምስት ቡድኖች ተውጣጥተው የ8-ክለቦች ሻምፒዮና ተጀመረ።
በወቅቱ በኤርትራ ይኖር የነበረው 1.5 ሚሊዮን ሕዝብ ከ23 ሚሊዮኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንፃር ሲታይ አነስተኛ መጠን የነበረው ቢሆንም ኤርትራውያኖቹ ከጣሊያን ባገኙት ልምድ የስፖርት ባህላቸው ከኢትዮጵያ የተሻለ ደረጃ ነበረው። ያኔ የኤርትራ ቡድኖች በተለያዩ ውድድሮች ይሳተፉ ነበር። ይህ “ፕሮፓጋንዳ” የሚል ስያሜ የነበረው ውድድር በተለያዩ የኤርትራ ክፍሎች ወዲያው ተስፋፋ።
እ.ኤ.አ በ1940ዎቹ የኤርትራ ቡድኖች ከጣልያኖቹ ጋር በመቀላቀል በሻምፒዮናው መሳተፍ ጀምረው ነበር። ሀማሴን የተባለው ቡድንም በውድድሩ ከቀድሞው አሸናፊ ግሩፖ ስፖርቲቮ አስመራ ጋር በተመሳሳይ ነጥብ የሁለተኛ ደረጃን ይዞ ለማጠናቀቅ በቃ። እጅግ ወሳኝ ተጫዋቻቸው አብርሃ ግዛው ነበር።
ሉቺያኖ ለባጎዚ በሰጠው ቃለ-ምልልስ አብርሃን “ ከትውልዱ የላቀና እውነተኛ አሸናፊ!” ሲል ይገልፀዋል። አብርሃ ጥሩ የቅጣት ምት ባለሟል እንደነበር ይነገራል። ኤርትራዊ ሆኖ የጣልያን ክለብን መለያ የለበሰ የመጀመሪያው ተጫዋች ነበር። እ.ኤ.አ በ1950ዎቹ መባቻ የአብርሃ የፊዮረንቲና ዝውውር ጫፍ ደርሶ በዘረኝነት ችግር እንዳልተፈፀመ በጊዜው በምስራቅ አፍሪካ ከነበሩ ጣሊያናውያን የስፖርት ጋዜጠኞች መካከል ታዋቂው ኤንሪኮ ማንዴ እ.ኤ.አ በ1952 አካባቢ በወጣው መጽሔት ላይ ባሰፈረው ጽሁፉ ያስረዳል።
ከኢትዮ-ኤርትራ የእግርኳስ ሊግ ውህደት በኋላ በነበሩት ሰባት ዓመታት ከኤርትራ የመጡ ቡድኖች አራት ጊዜ ሻምፒዮን መሆን ችለዋል። ሐማሴን እ.ኤ.አ በ1955 እና በ1957 ሻምፒዮናውን ሲያሸንፍ፣ አካለ ጉዛይ በ1958 እና የቴሌኮሙኒኬሽን ስፖርት ክለብ (ኋላ ገጀረት ተብሎ የተጠራው) በ1959 የሻምፒዮንነት ክብርን ተጎናጽፈዋል። እ.ኤ.አ በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባላት ከኢትዮ-ኤርትራ ውህደት የተገኙ ተጫዋቾች ነበሩ።
ከእነዚህ ተጫዋቾች አንዱ ሉቺያኖ ቫሳሎ ነበር። ሉቺያኖ እ.ኤ.አ በ1956 የመጀመሪያ የብሔራዊ ቡድን ጥሪ ደረሰው። ከዚያ በኋላ ከአስር ዓመታት በላይ ቁልፍ ተጫዋች ሆኖ ኢትዮጵያን አገልግሏል። ሉቺያኖ ለብሔራዊ ቡድን ከተመረጠ በኋላ የተለያዩ ተግዳሮቶች ገጥመውታል። በጊዜው ኤርትራውያኑ ተጫዋቾች በኢትዮጵያውያኑ ላይ የነበራቸው ቅራኔ የሕብረት ግንኙነቱን ቀላል አላደረገውም። ሉቺያኖ እንዲያውም ከታላቁ ኢትዮጵያዊ የእግር ኳስ ሰው አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ጋር የነበረው ግንኙነት መጀመሪያ ላይ ጥሩ የሚባል አልነበረም።
ሉቺያኖ በግሩፖ ስፖርቲቮ አስመራ ለሁለት ዓመታት ከተጫወተ በኋላ ወደ ድሬዳዋው ጥጥ ማህበር (ኮተን) አመራ። የወቅቱ የኢትዮጵያ ሻምፒዮን የነበሩት ኮተኖች ቡድናቸውን ለማጠናከር በሐማሴን ጥሩ አጥቂነቱን ያስመሰከረው የሉቺያኖ ታናሽ ወንድም ኢታሎን ጨምረው አስፈረሙ።
በኮተን የሉቺያኖ የመጀመሪያ የውድድር ዘመን የተሳካ አልነበረም። ቡድኑ በከተማ ተቀናቃኙ ኢትዮ ሲመንት ከባድ ፉክክር ገጥሞት የዋንጫ ድሉን ማስጠበቅ ሳይችል ቀረ። እ.ኤ.አ ከ1960-1965 ድረስ ሁለቱ የምስራቅ ኢትዮጵያ ኃያላን በኢትዮጵያ ሻምፒዮና ላይ ከፍተኛ የበላይነት አሳይተዋል። ኮተን ክለብም በቫሳሎ ወንድማማቾች ብቃት ታግዞ ሶስት የሊግ ድሎችን እ.ኤ.አ በ1962፣ በ1963 እና በ1965 ተጎናፀፈ። ቡድኑ በአፍሪካ የአሸናፊዎች–አሸናፊ ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ መድረስ ችሎ ነበር።
በ3ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የቫሳሎ ወንድማማቾች የብቃት ከፍታ በገሀድ ታየ። የፍጻሜው ጨዋታ እ.ኤ.አ በጥር 1962 በአዲስ አበባ ስታዲየም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተመልካችነት የተደረገ ነበር። ከሁለት ዓመት በፊት እ.ኤ.አ በ1960 አበበ ቢቂላ በሮም ኦሎምፒክ በባዶ እግሩ ሮጦ ባመጣው ተዓምራዊ የወርቅ ሜዳልያ ድል የሀገሪቱን የስፖርት ግርማ ሞገስ ከፍ አድርጎት ነበር። በእርግጥ በ1960ው የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውጤት አስከፊ የሚባል ነበር። በሶስት ቡድኖች ተሳትፎ ብቻ በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ኢትዮጵያ በተባበሩት አረብ ሪፐብሊክ (ግብጽ) እና ሱዳን 5 ጎሎች ተቆጥረውባት፤ ምንም ጎል ሳታስቆጥር ከውድድሩ ተሰናበተች።
ይህ ደካማ ውጤት አቶ ይድነቃቸው ተሰማን አነቃቸው። በኤርትራውያን ተጫዋቾች ላይ የነበራቸውን ቸልተኝነኝትም እንዲተው አደረጋቸው። የቡድኑ ድክመት አቶ ይድነቃቸው ቀድሞ በብሔራዊ ቡድኑ የሚታየውና ኤርትራውያንን ያለማካተት ልማድን እንዲለውጡ አስገድዷቸው በቡድኑ ውስጥ ከስድስት በላይ ቋሚ ተሰላፊ ኤርትራውያን ታዩ። አቶ ይድነቃቸው የአምበልነት ማዕረጉን ለሉቺያኖ ለመስጠት ባይፈልጉም በቡድን አጋሩ መንግሥቱ ወርቁ ጉትጎታ ሉቺያኖ በአምበልነት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን እንዲመራ ተደረገ።
በአራት ቡድኖች መካከል በተካሄደውና በ3ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ። በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ስታዲየም በተደረገው የመጀመሪያ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ በሉቺያኖ 2 ጎሎች፣ በመንግሥቱ 1 ጎል እና በተክሌ ኪዳኔ ተጨማሪ 1 ጎል አማካኝነት ኢትዮጵያ ቱኒዝያን 4-2 ረታች።
በፍፃሜው ጨዋታ ግብጾች ባልተረጋጋው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ላይ በ35ኛው ደቂቃ በበደዊ አብድልፈታህ አማካኝነት ጎል አግብተው እስከ 75ኛው ደቂቃ ድረስ በመሪነት ዘለቁ። በ75ኛው ደቂቃ ላይ ተክሌ ኪዳኔ ኢትዮጵያን አቻ አደረገ። የበደዊ ሁለተኛ ግብ ግብፅን ዳግም መሪ አደረገ። ጨዋታው ሊጠናቀቅ 6 ደቂቃዎች ሲቀሩ ሉቺያኖ ያስቆጠራት ግብ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ወደ ዳግም አቻነት መለሰች። ይህች ጎል የግብጾችን ሞራል አወረደች። በጭማሪው ሰዓት ኢትዮጵያውያኖች በተዳከሙት ግብጾች ላይ ከፍተኛ ብልጫን አሳዩ። ኢታሎና መንግሥቱ አከታትለው ጎሎችን በማስቆጠር ለብሔራዊ ቡድናቸው የ 4-2 ድልን አስገኙ። ኢትዮጵያም የመጀመሪያውንና ብቸኛውን የአፍሪካ ዋንጫ አሸነፈች።
በእግር ኳስ ሕይወት የመጨረሻ ዓመታት የቅዱስጊዮርጊስ ስፖርት ክለብን በአሠልጣኝነት ጭምር ያገለገሉት የኢትዮጵያ እግርኳስ ባለውለታ ሉቺያኖ ቫሳሎ ኑሮአቸውን ባደረጉበት ጣሊያን ሀገር በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በመስከረም 2014 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። እኛም እኚህን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ባለውለታ ነፍስ ይማር ለማለት እንወዳለን።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ህዳር 11/2017 ዓ.ም