ምንም እንኳን ምርጫ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ደራሽ እንግዳ ባይሆንም፤ በምርጫ የሕዝብ ድምጽ አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ ከማድረግ አንጻር ጉልህ ችግር ነበር። በዚህ ረገድ በዘመነ ኢህአዴግ የተካሄዱ አምስት አገርአቀፍ ምርጫዎች ተጠቃሽ ሲሆኑ፤ በዚህም ለሕዝብ ድምጽ ሳይሆን የፓርቲ ፍላጎት አሸናፊነትና ማስመሰል የገነነባቸው እንደነበሩ በርካቶች ይመሰክራሉ።
እዚህ ጋር ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ ግን፣ ባለፉት ምርጫዎች «ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ነፃና ፍትሃዊ እንዲሆን እንሰራለን» የሚል የገዢ ፓርቲ እና የመንግሥት መግለጫዎች ተደጋግመው ይደመጡ የነበረ ቢሆንም፤ ቃልና ተግባር ሳይገናኙ አምስት ምርጫዎች የአንድ ፓርቲ ፍላጎት ማስፈጸሚያ ሆነው ማለፋቸው ነው።
በስድስተኛው ምርጫም በመንግሥት በኩል ይኸው ቃል ተደጋግሞ የተገለጸ ሲሆን፤ ከሰሞኑም የገዢው ፓርቲ (ብልጽግና) ፕሬዚዳንት በዚህ ዙሪያ ጠንከር ያለ መልዕክት ሲያስተላልፉ ተደምጠዋል። በዚህ መልዕክታቸው፣ ብልጽግና እንደ ገዢ ፓርቲም ሆነ እንደ መንግሥት ዋናውና ትልቁ ፍላጎቱ በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያንን አሸናፊ ማድረግ መሆኑን የጠቀሱ ሲሆን፤ ከወዲሁ በምርጫው የማሸነፍ ተስፋ የለኝም፤ ከምርጫ መውጣት ይሻላል ብለው የሚያስቡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ያላቸውን ግምት አስቀምጠዋል።
ሆኖም እንደ ብልጽግናም ሆነ እንደ መንግሥት እንዲህ ዓይነት ምርጫ የማካሄድ ፍላጎት እንደሌለው እና ይልቁንም ሕዝቡ በሚያገኘው አማራጭ ሀሳብ ልክ የሚፈልገውን መርጦ በፓርላማም፣ በመንግሥት ቦታም ሆነ በሌሎች ቦታዎች የተለያዩ ድምጾች እንዲሰሙ ስለሚፈለግ፤ ተፎካካሪዎች ከተስፋ መቁረጥ ወጥተው በምርጫ መወዳደር እና ሃሳባቸውን መሸጥ እንደሚገባቸው መክረዋል።
ይህ መልካምና ከቀና ልብና አዕምሮ የሚመነጭ ቅዱስ ሃሳብ ነው። ዋናው ነገር ግን ይህ በቃል የቀረበው ልባዊ መሻት እንዴት ወደመሬት ይውረድ የሚለው ጉዳይ ነው። ምክንያቱም አንድ እንጨት እንደማይነድድ እና አንድ እጅም እንደማያጨበጭብ ሁሉ፤ የአንድ ሰው ምኞትና ፍላጎት ብቻውን የሚፈለገውን ግብ ሊያስገኝ ስለማይችል ነው። እናም የገዢው ፓርቲ አባላት፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ የሚዲያ፣ የሲቪክና የዴሞክራሲ ተቋማት፣ በጥቅሉ ሁሉም ዜጋ ምርጫው የሕዝብ ድምጽ የሚያሸንፍበት ሆኖ እንዲያልፍ ድርሻቸውን አውቀው ኃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት «በምርጫው ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያንን አሸናፊ ማድረግ…» ሲሉ፤ ይሄን እርሳቸው ብቻ ብለውት ብቻቸውን የሚፈጽሙት አለመሆኑን መላው የፓርቲው አመራሮችና አባላት መገንዘብ ይጠበቅባቸዋል። ምክንያቱም በምርጫ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን እንዲያሸንፉ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሁሉም በነፃነት የሚሳተፍበትና በሃሳብ ልዕልና የሚመረጥበት ሁኔታን ማስፈን ይጠይቃል።
ይህ እንዲሆን ደግሞ ቀደም ባሉት ምርጫዎች በክልል፣ በዞን፣ በወረዳና ቀበሌ መዋቅሮች ሲስተዋል የነበረው የተፎካካሪ ፓርቲዎችን ከሕግ አግባብ ውጪ ማዋከብ፣ ማሰር፣ መግደል፣ ወዘተ ዓይነት ተግባራት እንዳይደገሙ ማድረግ ይገባል። ለግልና ለፓርቲ ፍላጎት ሳይሆን፤ ለአገርና ሕዝብ ልዕልና ለሕዝብ ድምጽም አሸናፊነት ተግተው መስራትንም ይጠይቃል። የእነርሱም ሆነ የፓርቲያቸው መጠቀም ከእነርሱ መመረጥ ጋር ሳይሆን ከአገር ብልጽግና ጋር የተቆራኘ መሆኑን ተገንዝቦ መስራትም ይጠበቅባቸዋል።
ተፎካካሪ ፓርቲዎችም፣ ምርጫ ላይ መሳተፍ ማለት ሁከትና ግርግር ፈጥሮ ወንበር መያዝ አለመሆኑ መገንዘብ ይጠበቅባቸዋል። በቀደሙት ምርጫዎች እንደታየው ደጋፊዎችን በተሳሳተ መንገድ ለአመጽ በማነሳሳት በወጣቶች ሞት ላይ ተረማምዶ የሥልጣን ኮርቻን ለመፈናጠጥ መመኘት ሊበቃ ያስፈልጋል። እናም ከወዲሁ የተደራጀ ሀሳብ፣ የተዋቀረ የፖሊሲ ሰነድ፣ አሸናፊ የሚያደርግ ፕሮግራም ይዞ ለምርጫ መቅረብ፤ ይሄንኑ ለሕዝብ አድርሶ የሕዝብን የካርድ ውሳኔ መጠበቅ እና የሕዝብን ድምጽ አክብሮ ውጤቱን መቀበል የሥልጣኔም የአዋቂነትም መገለጫ መሆኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል።
የመገናኛ ብዙኃኑም ቢሆኑ፤ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ሁሉም በነፃነት የሚሳተፍበት፣ በሃሳብ ልዕልና የሚመረጥበት ሆኖ እንዲያልፍ በማድረግ ረገድ ያላቸውን ሚና በአግባቡ መወጣት ይጠበቅባቸዋል። ለዚህም የሚዲያ ተቋማት የምርጫ ዘገባ ማኑዋል ከማዘጋጀት ጀምሮ ለሁሉም ፍትሃዊ ሽፋን መስጠት፤ ሚዛናዊ ዘገባዎችን መስራት፤ ለሕዝቡ ተገቢውን መረጃ በተገቢው ጊዜ ማድረስን የመሳሰሉ ተግባራት በማከናወን ሙያዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል።
የሲቪክ ማህበራት፣ የዴሞክራሲ ተቋማትና ሌሎችም የምርጫ ተዋናዮች በዚሁ አግባብ ድርሻቸውን አውቀው ኃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል። መላው ኅብረተሰብም የተሻለ ሀሳብና ፕሮግራም ያለውን ፓርቲ በነፃነት መምረጥና ፓርቲዎችም ድምጹን አክብረው እንዲቀበሉ ማድረግ ከቻለ፣ ፓርቲ ሳይሆን አገር፣ የፓርቲ አባላት ሳይሆኑ ሕዝብ አሸናፊ መሆናቸው አይቀሬ ይሆናል!
አዲስ ዘመን የካቲት 10 ቀን 2013 ዓ.ም