ዋቅሹም ፍቃዱ
በአገራችን ከአርባ በላይ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚገኙ መረጃዎች ያሳያሉ። የዩኒቨርሲቲዎቹ ቁጥር በዚህ ልክ ቢያድግም የአገራችን የትምህርት ሥርዓት ግን ገና ዳዴ እያለ ያለና በተለይ ከፍተኛ የጥራት ችግር የሚነሳበት ነው።
ከዚህ በተጨማሪም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዩኒቨርሲቲዎች በተደጋጋሚ የሰላም እጦት ችግሮች ይስተዋላሉ። ካለፈው ዓመት ጀምሮ ደግሞ በኮቪድ 19 የተነሳ የአገራችን የትምህርት ሥርዓት ከፍተኛ ፈተና ውስጥ ወድቋል።
በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥም ሆኖ አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች የማህበረሰብ አገልግሎት ለመስጠት የተሻለ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። ከነዚህም መካከል የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ይጠቀሳል። በተለይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ታደሰ ቀነአ ዩኒቨርሲቲውን የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ እያደረጉ ያለው ዘርፈብዙ ጥረትም በተለያዩ በሚያውቋቸው ሰዎች ይነሳል። እኛም ይህንን መረጃ በመያዝ በዛሬው ወቅታዊ ዝግጅታችን ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ አስመልክተን ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ታደሰ ቀነአ ጋር ቆይታ አድርገናል፤ ተከታተሉት።
አዲስ ዘመን፡- ደግነት፣ ለአገርና ለወገን ተቆርቋሪነት፣ ሥራ ወዳድነት የዶክተር ታደሰ መገለጫዎች መሆናቸውን ባገኘነው መረጃ ለመረዳት ችለናል። እነዚህ መልካም እሴቶችን ከማን ነው የወረሱት?
ዶክተር ታደሰ፡– እነዚህ መልካም እሴቶች በአመዛኙ እንደሚገልጹኝ አምናለሁ። እነዚህ ሆን ብሎ በአጋጣሚ የመጡ ጉዳዮች ሳይሆኑ ካደኩበት ማህበረሰብ የወረስኳቸው ናቸው። እንደ ማንኛውም የአርሶ አደር ልጅ የግብርና ሥራን ጠንቅቄ አውቃለሁ፣ እሰራለሁም። እንደ አጋጣሚ ሆኖ አባቴ በልጅነቴ ስለሞተብኝ የግብርና ሥራውን ከእናቴ ጋር እየሰራሁ ነው ኑሮዬን የገፋሁት። በግብርናው ሥራ ሳልሰናከል ለትምህርቴም ልዩ ትኩረት በመስጠት ሁለቱን ጎን ለጎን አስኬድ ነበር።
በትምህርቴም እንደ ግብርናው ጥሩ ደረጃ ነበረኝ። «ባደኩበት ማህበረሰብ የኔ ነው ያንተ ነው» የሚባል አባዜ የለም። ጠዋት ቁርስ አንድ ቤት ከበላን ቀን ለምሳ ሌላ ቤት ሄደን እንበላለን፣ እራትም እንደዚያው። የተቸገር ሰው መንገድ ላይ ካገኘን ያለንን አካፍለን እንሰጣለን እንጂ ከንፈር መጥጠን አናልፍም።
በኦሮሞ ማህበረሰብ አንድ ሰው በወላጅ አባቱና እናቱ ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ማህበረሰብ ይቀረጻል፣ ይረዳል፣ ያድጋልም። ስለዚህ መልካም እሴቶቹ እኔና እኩዮቼ የፈለሰፍነው ጉዳይ ሳይሆን ያሳደገን ኅብረተሰብ ያወረሰን እሴት ነው።
እኛ ያንኑ ነው የተገበርነው። ውስጥን ንገረኝ ካልከኝ ግን ለሰው መኖር ከምንም በላይ ያስደስተኛል። በዚህ ምድር ላይ ሺህ ዓመት መኖር ባትችልም ሺህ መልካም ተግባሮችን ማከናወን ይቻላል። ስለዚህ በተሰጠን በአጭር ዕድሜ ለሌሎች መኖር፣ መልካም ነገሮችን መከወን አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በተለያዩ የሙያ መስኮች ልምድና እውቀት መቅሰም እና በተማሩት ሙያ ሕዝብና አገር ማገልገል ለእርስዎ ምን ትርጉም አለው?
ዶክተር ታደሰ፡- ጥሩ እንግዲህ፣ መማር ፊደል መቁጠር፣ ሰርተፊኬትና ዲግሪ መውሰድ አይደለም ለኔ። ይህ ሲባል ግን መማር ራሱ ቀላል ነው፣ ሰርተፊኬትና ዲግሪ ብቻቸው ዋጋ የላቸውም ማለቴ አይደለም። ባንማር የአስተሳሰባችን ድንበር በጣም ይጠብ ነበር። እንደ አሁኑ ሰፋ አድርገን ላናስብ እንችል ይሆናል።
ነገር ግን መማር ሙሉ ትርጉም የሚኖረው በተማሩት እውቀት ዋጋ ከፍሎ ያስተማረህን ማህበረሰብ በሙሉ ይሁን በከፊል ወይም የተወስኑ የማህበረሰብ ኑሮ መቀየር ሲቻል ነው። መማር በመማር ደረጃ ብቻ ከቀረ ነገሮች የከፉ ይሆናሉ።
ለምሳሌ ብዙዎቻችን ከመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ጀምረን ብዙ ሰርተፊኬቶች እጃችን ላይ ሊኖሩ ይችላሉ፣ ነገር ግን በሕይወታችንና በማህበረሰባችን ሕይወት ላይ ያመጡት ለውጥ ሲፈተሽ ምናልባት በእውቀት ደረጃ/በመማር ደረጃ የቀሩ ይሆናሉ። አንዳንዴ ተምረን ለማህበረሰብ ችግር የመፍትሄ አካል መሆን ሲገባን በተለያዩ ምክንያቶች ሳንሆን ቀርተን ኅብረተሰቡ ሲቸገር ቁጭት ውስጥ እንወድቃለን።
ቁጭት ደግሞ ራሱ ጎታች ነው። በእርግጥ ዘርፈ ብዙ ችግር ያለባት አገር ውስጥ ነው ያለነው ሆኖም ግን በተቻለ መጠን የአቅማችንን ያህል ችግሩን ከማጉላት የመፍትሄ አካል ለመሆን መጣር ወሳኝ ነው። እንደ አምቦ ዩኒቨርሲቲ ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ለመገልገል ይመጣሉ።
አቅም በፈቀደው መሰረት አንዳንዶቹ መፍትሄ ያገኛሉ፣ ከአቅም በላይ የሆኑት ደግሞ በይደር እንዲፈቱ ይደረጋሉ። ያም ሆኖ ብዙውን ጊዜ ሰዎች ደስተኛ ሆነው ሲወጡ ሳይ በጣም እደሰታለሁ። ለኔ ሁሉም ሰው ሰውን የማገልገል ፍላጎት አለው፣ ልዩነቱ ወደ ተግባር ከመቀየር አኳያ ክፍተት ይፈጠራል። ይህንን በተግባር በሥራ ባልደረቦቼ ውስጥ ለማየት ችያለሁ።
አዲስ ዘመን፡- አምቦ ዩኒቨርሲቲ ለአገራችን በተለይ ለአምቦና አካባቢዋ ማህበረሰብ ያበረከተው አስተዋጽኦ እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር ታደሰ፡– በእውነቱ፣ ኅብረተሰቡ አምቦ ዩኒቨርሲቲን እንደ ገዛ ልጁ ነው የሚያየው። ምክንያቱም ዩኒቨርሲቲው እውን እንዲሆን የሕዝቡ ድርሻ ከፍተኛ ነበር። አምቦ የምዕራብ ኦሮሚያ በተለይ ደግሞ የምዕራብ ሸዋን ማህበረሰብ ኑሮ ለመቀየር በርካታ ሥራዎችን ከውኗል።
የጥናት ውጤት የሆኑት የተሻሻሉ የላሞች ዝርያና የሰብል ምርጥ ዘሮች ከማቅረብ አኳያ፣ ነፃ ሕግ አገልግሎት፣ ተማሪዎች ትምህርት ገበታ ላይ እንዲቆዩ ለማስቻል «ኡቡንቱ» የሚባለው አገር በቀል መንግሠታዊ ያልሆነ ድርጅት በማቋቋም ድሃ የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ አድርጓል።
በጤና በኩልም የኅብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ መጠነኛ የጤና አገልግሎት እየሰጠን እንገኛለን። የአፈር መሸርሸር ለመቀነስ፣ በረሃማነትን ለመከላከል፣ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ረገድ ዩኒቨርሲቲው በየዓመቱ በርካታ ችግኞችን ይተክላል፣ ለአርሶ አደሮችም ያቀርባል። የተለያዩ የችግኝ ማፊያ ጣቢያዎችም አሉት።
አዲስ ዘመን፡- «ኡቡንቱ» የሚባለው አገር በቀል ድርጅት ለማቋቋም ያነሳሳችሁ ቁልፍ ችግር ምንድን ነበር? የገቢ ምንጩስ? የተገልጋዮች ቀጥርስ ምን ያህል ነው?
ዶክተር ታደሰ፡- ጥሩ ጥያቄ ነው። ለአምቦ በርካታ ዘመናት በሁሉም ነገር የተገለለች ነበረች። በምታነሳው የመብት ጥያቄ ምክንያት ትርፍ አምራች አካባቢ ነው ብሎ አልሚ ባለሀብቶችና የእርዳታ ድርጅቶች ወደ አምቦ አይላኩም ነበር። ነገር ግን በከተማው ዘርፈ ብዙና ውስብስብ ማህበራዊ ችግሮች አሉ።
መሠረተ ልማቱ በጣም የተረሳ፣ ፋብሪካም የለም። ከዚህ የተነሳ በተለይ በከተማው ሥራ አጥነትና ድህንነት ከሚገለጸው በላይ ነው። የበሽታ ስርጭትም በተመሳሳይ መልኩ። በአጭሩ የአምቦ ጉዳይ ለማንም ያልተገለጠ ጉዳይ ነበር። በዚሁ መሠረት ነው እንግዲህ ኡቡንቱን ለማቋቋም የወሰነው።
ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት የተወሰንን መምህራን ከደመወዛችን ትንሽ ብር አዋጥተን ለድሃ ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ እንገዛ ነበር። ነገር ግን የሥራችን ባልደረባ የሆኑ ዶክተር ሰለሞን አለሙ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በነበሩ ሸማቾች ጋር በመነጋገር የተወሰኑ ሰዎች በወር ሃምሳ ብር እንዲያዋጡ ተደረገ።
ያቺን 50 ብር በወር ለመቀበል ከሩቅ ይመጡ ነበር። ይህች ሃምሳ ብር በዓመቱ መጨረሻ በሰዎቹ ሕይወት ላይ ያመጣውን ለውጥ እንዳመጣ ጥናት አደረገ። ለውጡ ጥሩ ሆኖ አገኘን። ከዚያ በኋላ ነው ኡቡንቱን ማህበረሰቡ ያቋቋመው።
ያኔ አስራ ሁለት ነበርን። ሁሉም ከደመወዙ በወር 100 ብር እንዲያዋጣ ወሰን። ከዚያ ሀሳባችንን ለሌሎች መሸጥ ጀመርን። ዛሬ ላይ ኡቡንቱ ከመምህራንና ከአስተዳደር ሠራተኞች 500 አባላት ያለው ሲሆን በወር 50ሺህ ብር ይሰበሰባል። ኡቡንቱ በአሁኑ ጊዜ በቋሚነት 255 ቤተሰቦችን እየረዳ ይገኛል።
ምናልባት ከቤተሰብ አባላት ጭምር ሲቆጠሩ ወደ አንድ ሺህ ሰዎች ይሆናል። ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ሙያ ያላቸው የምሁራን ማዕከል እንደመሆኑ መጠን ከእርዳታ በዘለለ እነዚህ ድሃ ማህበረሰቦች ራሳቸውን እንዲችሉና ሰርተው እንዲለወጡ ቢዝነስ ፕላን በማዘጋጀት 5ሺህ መነሻ ካፒታል በመስጠት እንዲሰሩ እየተደረገ ይገኛል። ለወደ ፊትም በሥራ ዕድል ፈጠራ ብዙዎችን ተጠቃሚ የሚደርግ እቅድ ተዘጋጅቶ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በጤና ረገድስ ሊገነባ የታሰበው ሪፈራል ሆስፒታል ምን ቁልፍ ችግሮችን ይፈታል ተብሎ ይጠበቃል? የየትኞቹን ዞኖች የጤና ችግር ሊያቃልል ይችላል? ነፃ የሕግ አገልግሎቱስ?
ዶክተር ታደሰ፡- ቀደም ብዬ ለማንሳት እንደሞከርኩት አምቦ፣ በጤና ተቋማት እንኳ የተገለለች ናት። በተጨማሪ ደግሞ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና በጳውሎስ ሆስፒታል ባደረግነው የጤና አገልግሎት ማፒንግ ጥናት በርካታ ተገልጋዮች ከምዕራብ ኦሮሚያ የመጡ ናቸው።
አያይዘን ሁለት ዋና ዋና ችግሮችን ለመለየት ችለናል። አንደኛ ከሕዝቡ ብዛት የተነሳ ሆስፒታሎቹ የሚፈለገውን ደረጃ አገልግሎት መሰጠት አለመቻላቸውን። ሁለተኛ ደግሞ ከሌሎች አካባቢዎች ጋር ሲደመር ታካሚዎች በሆስፒታሎቹ ላይ የፈጠሩት መጨናነቆች እጅግ ከፍተኛ ነው።
በዚህ ጉዳይ ላይ በሁለቱ ሆስፒታሎች ጋር ስምምነት ላይ ደርሰናል። ስለዚህ የሁለቱንም ሆስፒታሎች ጫና ለመቀነስ ብሎም የተሻለ ህክምና በቅርበት ለመስጠት ትልቅ ሪፈራል ሆስፒታል በ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር እየገነባን እንገኛለን። ግንባታው ሲጠናቀቅ ለማዕከላዊ ምዕራብ ሸዋ፣ ለደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ ለምዕራብ ሸዋ፣ ለምሠራቅ ወለጋና ለሆሮ ጉዱሩ ወለጋ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ ደግሞ በአዲስ አበባ ስር ያሉ ጤና ተቋማት ትልቅ እፎይታ ነው። የኅብረተሰቡ ጤና አገልግሎት መስጠት እንደመሆኑ መጠን ከጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና ከጳውሎስ ሆስፒታል ጋር በጋራ እየሰራን እንገኛለን። ነፃ የሕግ አገልግሎቱ በመጀመሪያ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን ነው የጀመርነው።
ለድሃ ፍትህ ከባድ ነው የሚባለው ነገር ሁሌ እንሰማለን። ስለዚህ ከባለቤቶቻቸው ጋር እንኳ ተጋጭተው ፍትህ ያጡ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞችና ድሃ የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ አድርጓል። መሠረታዊ የህግ ስህተት እንዳይፈጸምም የህግ ተማሪዎችን በመላክ ኅብረተሰቡን እያስተማርን እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፡- በግብርና ዘርፍ በምግብ ዋስትና ራስን ከመቻል አኳያ እንደ ዩኒቨርሲቲው ምን ተጨባጭ ሥራ ተሰራ? የተገኘውን ለውጥስ እንዴት ገመገማችሁት?
ዶክተር ታደሰ፡- እንዳልከው በምግብ ራስን መቻል ትልቅ ፈተና እየሆነ መጥቷል። ዩኒቨርሲቲያችን ከአገራችን ዩኒቨርሲቲና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመሆን ምርትና ምርታማነትን ከመጨመር አኳያ በርካታ ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል።
በትንሽ ማሳ ላይ እንዴት ትልቅ ምርት ማምረት እንደሚቻል ለአርሶ አደሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየሰጠን እንገኛለን። በተለይ ዘንድሮ የተሻሻሉ የጤፍ ዝርያዎችን አምርተን በመላው የምዕራብ ሸዋ አርሶ አደሮች ለማድረስ ዝግጅት ላይ ነን።
የተሻሻሉ የላሞች ዝርያ በተመጣጣኝ ዋጋ ለአርሶ አደሩ የማድረስ ሥራ እንደ ጅምር እየተሰራ ያለው ነገር ጥሩ ቢሆንም በስፋት ለማቅረብ ግን እቅድ ይዘን እየሰራን እንገኛለን።
በተለይ ከሁሉም ለመካናይዝድ እርሻ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቷል። ምክንያቱም በማይጨመር መሬት ላይ የሕዝብ ቁጥር በከፍተኛ እየጨመረ ስለሆነ ምርታማነቱን በማሳደግ ትንሽ መሬት ላይ ማምረት የግድ ሆኗል።
በተመሳሳይ መልኩ ሕዝቡም ስድስት ሰባት ላም የምትተካ አንድ የምርጥ ዘር ላይ እንዲጠቀሙ ዶክተሮቻችን ወደ አርሶ አደሮች ወርደው እያሳዩ፣ እያስተማሩ ይገኛሉ። እነዚህ ሥራዎች ጎን ለጎን ችግር ፈቺ እንዲሁም የእውቀት ጥናትና ምርምሮች እየተሰሩ ነው።
አዲስ ዘመን፡- እስቲ አወዛጋቢ የነበረው የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ሐውልት ግንባታ በማን ተሰራ? ዓላማውስ?
ዶክተር ታደሰ፡– ምናልባት የሀጫሉን ነገር ብዙ ማንሳት ይቻላል። ሀጫሉ አንድ ሕይወቱን አስይዞ በሚሊኒየም አዳራሽ ወጥቶ በቴሌቪዥን መስኮት በአጠቃላይ የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ለዓለም አፈረጠረጠው።
ማንም ይቅር አገር ውስጥ ሆኖ ያውም በህወሓት ባለሥልጣናት የደህንነት ካሜራ ውስጥ እንኳን ሊያደርግ ለማሰብም የሚከብድ ነገር አደረገ። እኔ እንደሚገባኝ፣ ሥራዎቹም እንደሚመሰክሩት ሀጫሉ የፍትህ ተምሳሌት፣ ለተጨቆኑት ድምጽ ነው።
ደፋሮች ባይኖሩ ኖሮ የዛሬውን ነፃነት ባላየን ነበር። የሐውልቱን ግንባታ በተመለከተ ሀሳቡን ከማስተባበር አኳያ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብና ማኔጅመንት አባላት ሚና ከፍተኛ ነበር። ነገር ግን የሀጫሉን ሐውልት ራሱ መስራቱን ማወቅ ተገቢ ይመስለኛል። የሀጫሉ ሐውልት በሕዝባችን ልብ ውስጥ እንዳለ ሆኖ መልካም ሥራ ባይሰራ ኖሮ የሚታየው ሐውልት አይቆምለትም ነበር።
ለዚያ ነው ራሱ ነው የሰራው ያልኩህ። እኔ እንደሚሰማኝ ሐውልቱ ሀጫሉን አይተካም ግን ደግሞ ቀጣዩ ትውልድ ለፍትህ፣ ለሰላምና ለልማት ጥብቅና እንዲቆም ያስተምራል። ለሐዝቡ ደግሞ ምናልባት ሞራል ሊሆን ይችላል። ከዚህ በኋላ አምቦን የማልማት ጉዳይ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ስለሚጠይቅ በዚያው ልክ አሻራችንን ማሳረፍ የሁላችን ግዴታ መሆን አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ወድ ጊዜዎን መስዋዕት አድርገው በተነሱ ጥያቄዎች ላይ ሰፊ ማብራሪያ በመስጠትዎ ከልብ አመሰግናለሁ።
ዶክተር ታደሰ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን የካቲት 09/2013