
ነስረዲን አሕመድ ይባላል፡፡ ተወልዶ ያደገው ሐረር ከተማ ነው፡፡ ይህ ወጣት ሕልሙና ምኞቱ ወደ ዓረብ ሀገር ሄዶ ሀብት ማፍራት ነበር፡፡ በዚህም በወቅቱ የሀገሩን በተለይም የመንደሩን ፀጋና በረከት ወደ ኢኮኖሚ የሚመነዝርበትን አማራጭ ከመመልከት ይልቅ ሃሳቡ የሚሰደድበትን መንገድ ማጥናት ላይ ያተኮረ ነው፡፡
በሕገ ወጥ መንገድ የሀገሩን ድንበር ተሻግሮ፣ ሕይወቱን አስይዞ ለአደጋ በሚያጋልጥ ጀልባ ቀይ ባሕርን ሰንጥቆ፤ የመንን እና ኦማንን በእግሩ አቆራርጦ ገና በለጋ እድሜው ዱባይ መግባቱን ይናገራል፡፡ ዱባይ መግባት ሳውዲ ዓረቢያ እንደመግባት አይቀልም የሚለው ነስረዲን፤ ጉዞው እጅግ በጣም ፈታኝ የእግር ጉዞ የነበረው እና የሞት አደጋዎች የበዙበት እንደነበር ያስታውሳል፡፡
ነስረዲን ከስምንት ዓመታት የዱባይ ቆይታው በኋላ ያገኛትን ጥሪት ይዞ ወደ ሀገሩ ይመለሳል፡፡ ሀገሩ እንደተመለሰ የመጀመሪያ ተግባሩ የሥራ አማራጮችን መመልከት ነበር፡፡ በወቅቱ የከተማ ግብርና፣ የሌማት ትሩፋትን የመሳሰሉ ኢኒሼቲቮች እንደሀገር ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸው ለነስረዲን የሥራ ምርጫውን እንዲወስን ጥሩ አጋጣሚ ፈጥረውለታል፡፡
ንብ ማነብ አዋጭ የሥራ ዘርፍ እንደሆነ አምኖ በግቢው ውስጥ ሁለት ቀፎዎችን በማስቀመጥ ሙከራ ማድረግ ይጀምራል፡፡ በሙከራ ሂደቱ ሥራውን እየተለማመደ ጎን ለጎንም የቀፎችን ቁጥር እያበዛ ቀጠለ። በአንድ ዓመት ውስጥ የቀፎዎቹን ብዛት ሰባት አደረሰ፤ ከዚያም በኋላ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት እስከ ሃምሳ ቀፎ ድረስ በዚያው በግቢው ውስጥ ማነብ ቻለ፡፡
ገቢው ከዚያ በላይ ሊያስኬደው ስላልቻለና ሌላ ቦታ መፈለግ የግድ ስለሆነበት ወደ ሐረሪ ክልል ግብርና ቢሮ ሄዶ እገዛ እንዲደረግለት ጥያቄው አቀረበ፡፡ ‹‹የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ኦርዲን በድሪ እቤት ድረስ በመምጣት ሥራዎቼን ከተመለከቱ በኋላ ቦታ እንዲሰጠኝ ትእዛዝ አስተላለፉ›› የሚለው ነስረዲን፤ ‹‹በከተማው ዳርቻ ላይ ቆሻሻ መጣያ የሆነን ሥፍራ አፅድቼ የንብ መንደር እንዳደርግ ተሰጠኝ›› ይላል፡፡
‹‹እንደምታዩት ይህን ቦታ አፅድቼ ከሦስት ሺህ በላይ አትክልት በመትከል ለንቦች ምቹ እንዲሆን አደረግሁት፡፡ የተከልኳቸው ዛፎች ንቦች ማር ለመሥራት የሚቀስሟቸውን አበባዎች የሚያዘጋጁ ሲሆኑ አንዳንዶቹም ለሰዎች በምግብነት የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ አሁን በግቢው ውስጥ 200 የሚደርሱ ቀፎዎች አሉኝ፡፡ ወደፊት ከዚህም በላይ አስፋፍቼ ለአካባቢው ማኅበረሰብም ሆነ ለሌላ አካባቢ ንጹሕ ማር በማቅረብ ገቢዬን ማሳደግ እፈልጋለሁ›› ይላል፡፡
‹‹ወደ ውጭ ሀገር የተሰደድኩት ብዙ ገንዘብ የማገኝ መስሎኝ ነበር፤ እዚያ ስደርስ ግን ያስብኩት አልሆነም›› የሚለው ነስረዲን፤ ዓረብ ሀገር ገንዘብ ለማግኘት በጣም አድካሚ ሥራ መሥራት እንደሚጠይቅ ይገልጻል። ‹‹ዓረብ ሀገር የለፋሁትን ሀገሬ ላይ ብለፋ ኖሮ ከዚያ የተሻለ ጥቅም ማግኘት እንደምችል የገባኝ አሁን ነው›› ይላል፡፡
‹‹በሀገርህ እና በመሬትህ ላይ ክብርህ ተጠብቆ ሠርተህ መለወጥ ከቻልክ ሰው ሀገር መሄድ አያስፈልግህም፡፡ እኔ አሁን በሀገሬ፤ ለዚያውም በመንደሬ ሠርቶ መለወጥ እንደሚቻል እያሳየሁ ነው፤ ለብዙ ወጣቶችም ምሳሌ
መሆን ችያለሁ፤ ጊዜያቸውን በአልባሌ ቦታ የሚያሳልፉና በሱስ የተጠመዱ ወጣቶች በተለያዩ ሥራዎች ላይ ቢሠማሩ በጣም ይቀየራሉ ብዬ አስባለሁ ሲል መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡
በሥራ ሂደት የሚያጋጥሙ ብዙ መሰናክሎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በዚህን ጊዜ እጅ መስጠት ወይም ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግም፡፡ ንቦች 30 እና 40 ቀፎዎችን ትተው የተሰደዱበት ጊዜ አጋጥሞኛል፤ ተስፋ ባለመቁረጥ እንደገና ጥረት አድርጌ ሥራው እንዲቀጥል በማድረግ ዛሬ ያለሁበት ደረጃ ላይ መድረስ ችያለሁ ነው ያለው፡፡
እዚህ ቦታ ላይ ንብ ማነብ ብቻ ሳይሆን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ዘመናዊ አሠራሮችን ማስፋፋትና የተሻለ አቅም መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ የሠራተኞች መጠለያና የምርት ማከፋፈያ መሥራት ግድ ይላል፡፡ ማርን በጥሬው ከመሸጥም ባለፈ እሴት ጨምሮ መሸጥ የሚቻልበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል ይላል ወጣቱ፡፡
እንደ ፑል፣ ጄል የመሳሰሉ ምርቶችን ከማርና ከተረፈ ምርቶቹ ማምረት ይቻላል፡፡ ንብ እያናቡ ከነቀፎው ለአካባቢው ማኅበረሰብ እስከ 15 ሺህ ብር የሚሸጥበት ሁኔታም መኖሩን ጠቁሞ፤ በዚህ ሂደትም በርካቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል፡፡
ሥራውን ለመሥራት አንዱ ችግር የቀፎ እጥረት እንደሆነ የሚጠቅሰው ነስረዲን፤ ወጣቶችን አደራጅቶና ማሽኖችን ገዝቶ ቀፎዎችን ማምረት ተያያዥ ሥራ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ቀፎውን ለራሱ ከመጠቀምም ባለፈ ለአርሶ አደሩ በማከፋፋል ብዙኃኑን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚችልም ይጠቅሳል፡፡ በዚህ ሂደትም ለበርካቶች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚቻል ይገልጻል፡፡ እስከ አሁንም 20 ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ነግሮናል፡፡
‹‹ያሰብኳቸውን ሥራዎች ሁሉ ለመተግበር ሕጋዊ የሆነ ቦታ ሊኖረኝ ይገባል›› የሚለው ነስረዲን፤ ‹‹የክልሉ መንግሥት ቀደም ሲል ድጋፍ እና ትብብር እንዳደረገልኝ ሁሉ አሁንም የደረስኩበትን የአቅም ደረጃ ተመልክቶ ተያያዥ ሥራዎችን ሠርቼ የበለጠ ውጤታማ እንድሆን የማስፋፊያ ቦታና የይዞታ ማረጋገጫ ሊሰጠኝ ይገባል›› ሲል ይጠይቃል፡፡
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 11 ቀን 2017 ዓ.ም