
የተወሳሰቡ ኢኮኖሚያዊ መፍትሔ የሚያሻቸውን ችግሮች ለመፍታት እና የኢትዮጵያንም ኢኮኖሚ ለማነቃቃት መፍትሔ እንደሚሆን ታስቦ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ አዲስ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እንደሚተገበር ሲነገር፤ ብዙዎች ግራ መጋባት ውስጥ ገብተው ነበር:: ይህ የሀገሪቱን የዋጋ ንረት፣ የዕዳ ጫና፣ ሥራ አጥነት፣ ዝቅተኛ ምርታማነት እና አነስተኛ የልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸምን፤ የሀብት ብክነት እንዲሁም ዋና ዋና የኢኮኖሚ ዕዳዎችን ለማቃለል ያግዛል የተባለለት ማክሮ ኢኮኖሚ በራሱ ምንድን ነው? ከሚለው ጀምሮ በሥሩ ምን ምን ጉዳዮችን እንደሚያካትት ተደጋጋሚ ጥያቄዎችም ሲነሱ ቆይተዋል:: ሆኖም ባለፉት ዘጠኝ ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው መተግበር ከጀመረ ወዲህ ብዥታዎች እየጠሩ፤ ይፈጠራሉ የተባሉ ችግሮች መስመር እየያዙ በመምጣታቸው አሁን የተሻለ መግባባት ተፈጥሯል፤ ከአሉታዊ ጎኑ ይልቅ አውንታዊ ጎኑ እንደሚያይልም በተጨባጭ ለማረጋገጥ ተችሏል::
ከላይ የጠቀስናቸውን እና ሌሎችም ከዓለም የኢኮኖሚ ሁኔታዎች ጋር የተሳሰሩ ጉዳዮችን በማንሳት የቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት የፖሊሲ አማካሪ፣ የአፍሪካ ህብረት የፀረ-ሙስና ቦርድ ሰብሳቢ እና የአፍሪካ የሰብዓዊ ተግባር ባለአደራ፣ የሕዝብ አስተዳደር ፖሊሲ ፕሮፌሰር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፉ (ዶ/ር) ጋር ቆይታ አድርገናል::
አዲስ ዘመን፡- ማክሮ ኢኮኖሚ በራሱ ምንድን ነው?
ፕ/ር ቆስጠንጢኖስ፡- አጠቃላይ እይታው ሲቃኝ ኢኮኖሚክስ በሁለት የተለያዩ ምድቦች ይከፈላል:: ከሥሩ ሲታይ ማክሮ ኢኮኖሚክስ (Macroeconomics) እና ማይክሮ ኢኮኖሚክስ (Microeconomics) በመባል ይታወቃሉ::
ማይክሮ ኢኮኖሚክስ የግለሰቦች እና የንግድ ውሳኔዎች ጥናት ነው:: ማክሮ ኢኮኖሚክስ ደግሞ የሀገሮችን እና መንግሥታትን ውሳኔ ይመለከታል። ሆኖም እነዚህ ሁለቱ የኢኮኖሚክስ ዘርፎች የተለያዩ ቢመስሉም፤ በሁለቱ መስኮች መካከል ብዙ ተደራራቢ ጉዳዮች ስላሉ እርስ በርስ የሚደጋገፉ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- በቅድሚያ ማይክሮ ኢኮኖሚክስን በደንብ ያብራሩልን?
ፕ/ር ቆስጠንጢኖስ፡– ማይክሮ ኢኮኖሚክስ የሸቀጦች እና አገልግሎቶችን ሀብቶች እና ዋጋዎችን በተመለከተ በሰዎች እና በንግዶች የተደረጉ ውሳኔዎችን ማዕከል የሚያደርግ ነው። እንዲሁም በመንግሥት የተፈጠሩትን ታክስ እና ደንቦችን ግምት ውስጥ ያስገባል::
በተጨማሪ ማይክሮ ኢኮኖሚክስ በአቅርቦት እና በፍላጎት እና በኢኮኖሚው ውስጥ የዋጋ ደረጃዎችን በሚወስኑ ሌሎች ኃይሎች ላይ ያተኩራል። ኢኮኖሚውን ለመተንተን ከታች ወደ ላይ ያለውን አካሄድ ይጠይቃል። በሌላ አነጋገር ማይክሮ ኢኮኖሚክስ የሰውን ምርጫ እና የሀብት ክፍፍልን ለመረዳት ይሞክራል።
ሆኖም ማይክሮ ኢኮኖሚክስ በገበያ ውስጥ ምን ዓይነት ኃይሎች መፈጠር እንዳለባቸው ለመመለስ ወይም ለማብራራት አይሞክርም። ይልቁንም በተወሰኑ ሁኔታዎች ላይ ለውጦች ሲኖሩ፤ ምን እንደሚፈጠር ለማብራራት ይጥራል:: ለምሳሌ ማይክሮ ኢኮኖሚክስ አንድ ኩባንያ ምርቱን እና አቅሙን እንዴት እንደሚያሳድግ ይመረምራል። በምርመራ ሂደቱ ዋጋ እንዲቀንስ እና በኢንዱስትሪው ውስጥ በተሻለ ሁኔታ እንዲወዳደር ያሉ ምቹ ሁኔታዎችን ያያል::
አስተያየቱ በዋናነት ፍላጎት፣ አቅርቦት እና ሚዛናዊነት ላይ ያተኩራል:: ዋጋዎች የሚወሰኑት በአቅርቦት እና በፍላጎት ንድፈ ሃሳብ ነው። በዚህ ንድፈ ሃሳብ መሠረት፣ አቅራቢዎች ፍጹም ተወዳዳሪ በሆነ ገበያ በተጠቃሚዎች የሚፈለጉትን ተመሳሳይ ዋጋ ይሰጣሉ። ይህ የኢኮኖሚ ሚዛን ይፈጥራል:: እዚህ ላይ የምርት ጥናት የሆነው የፕሮዳክሽን ቲዎሪ አለ:: እንዲሁም የሸቀጦች ወይም የአገልግሎት ዋጋ የሚወሰነው በምርት ጊዜ ጥቅም ላይ በሚውሉ ሀብቶች ዋጋ ነው። የሠራተኛ ኢኮኖሚክስንም መጥቀስ ይቻላል:: ይህ መርህ ሠራተኞችን እና አሰሪዎችን ይመለከታል:: የደመወዝ፣ የሥራ እና የገቢ ሁኔታን ለመረዳት ይሞክራል።
አዲስ ዘመን፡- ማክሮ ኢኮኖሚክስ ምንድን ነው?
ፕ/ር ቆስጠንጢኖስ፡– ማክሮ ኢኮኖሚክስ የአንድን ሀገር ባሕሪ እና ፖሊሲዎቹ በአጠቃላይ ኢኮኖሚውን እንዴት እንደሚነኩ ያካትታል:: ከግለሰቦች ወይም ከተወሰኑ ኩባንያዎች ይልቅ አጠቃላይ ኢንዱስትሪዎችን እና ኢኮኖሚዎችን ይተነትናል:: ከላይ ወደ ታች የሚደረግ አካሄድ ነው:: እንደ “የዋጋ ግሽበት መጠን ምን መሆን አለበት?” ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ይሞክራል:: ወይም “የኢኮኖሚ እድገትን የሚያነቃቃው ምንድን ነው?” እንደ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) እና በሥራ አጥነት ለውጥ፣ በሀገር አቀፍ ገቢ፣ በእድገት መጠን እና በዋጋ ደረጃዎች ያሉ ኢኮኖሚያዊ ሰፊ ክስተቶችን ይመረምራል።
ማክሮ ኢኮኖሚክስ የተጣራ የወጪ ንግድ መጨመር ወይም መቀነስ የአንድን ሀገር ካፒታል ሒሳብ እንዴት እንደሚያጠቃ ወይም የሀገር ውስጥ ምርት በሥራ አጥነት መጠን እንዴት እንደሚጎዳ ይተነትናል። በኢኮኖሚያዊ ትስስር ላይ ያተኩራል፤ መንግሥታት እና ኤጀንሲዎቻቸው የኢኮኖሚ እና የፊስካል ፖሊሲን ለመገንባት የሚጠቀሙበት ለዚህም ነው። የጋራ ፈንዶች ወይም የወለድ ተመን በተጨማሪ ስሜታዊ የሆኑ ዋስትናዎች ባለሀብቶች የገንዘብ እና የፊስካል ፖሊሲን መከታተል አለባቸው።
ከጥቂት ትርጉም ያላቸው እና ሊለኩ ከሚችሉ ተፅዕኖዎች ውጪ፣ ማክሮ ኢኮኖሚክስ ለተወሰኑ ኢንቨስትመንቶች ብዙ ቦታ አይሰጥም። ጆን ሜይናርድ ኬይንስ ሰፊ ክስተቶችን ለማጥናት የገንዘብ ድምርን መጠቀም ስለጀመረ፤ ብዙ ጊዜ የማክሮ ኢኮኖሚክስ መስራች ተብሎ ይታሰባል።
በአጠቃላይ ማይክሮ ኢኮኖሚክስ ግለሰቦችን እና የንግድ ውሳኔዎችን ያጠናል:: ማክሮ ኢኮኖሚክስ ደግሞ በሀገሮች እና መንግሥታት የተደረጉ ውሳኔዎችን ይተነትናል:: ማይክሮ ኢኮኖሚክስ በአቅርቦት እና በፍላጎት ላይ ያተኩራል እና ሌሎች የዋጋ ደረጃዎችን በሚወስኑ ኃይሎች ላይ ያተኩራል:: ይህም የታችኛውን ወደ ላይ ያደርገዋል። ሆኖም ማክሮ ኢኮኖሚክስ ግን ከላይ እስከ ታች ያለውን አካሄድ በመከተል ኢኮኖሚው ምን መምሰል እንዳለበት ለመወሰን በመሞከር ኢኮኖሚውን ጠቅልሎ ይመለከታል።
ማክሮ ኢኮኖሚክስ በዋናነት የኢኮኖሚ እና የፊስካል ፖሊሲን ለመቅረጽ የሚያገለግል የትንታኔ መሳሪያ ነው። የማይክሮ ኢኮኖሚክስ በግለሰብ የኢንቨስትመንት ፕሮፖዛል ላይ የበለጠ ተጽዕኖ ያሳድራል። ይህን መነሻ በማድረግ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ውሳኔያቸው ማይክሮ ኢኮኖሚክስ ሊጠቀሙ ይችላሉ:: ስለዚህ ኢንቨስተሮች የግለሰብ ባለሀብቶች ከማክሮ ኢኮኖሚክስ ይልቅ በማይክሮ ኢኮኖሚክስ ላይ ቢያተኩሩ የተሻለ ሊሆን ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- ማክሮ ኢኮኖሚክስ ከላይ ወደታች መሆኑን ገልጸዋል:: ግለሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርገው በምን መልኩ ነው?
ፕ/ር ቆስጠንጢኖስ፡– ማክሮ አጠቃላይ ምልከታ የሚያደርገው የሀገሪቷን አጠቃላይ ኢኮኖሚ ነው:: የጂዲፒ ዕድገቱን እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን የሚገመግም ነው:: ሰዎች በሚጠቀሙባቸው የኢኮኖሚ እሴቶች ላይ፤ በማምረት እና በአገልግሎት ዘርፍ ላይ አንዳንድ አስተዋፅኦ ያደርጋል:: የማክሮ ኢኮኖሚክስ ፖሊሲ ትክክል ካልሆነ፤ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዳለ ይበላሻል ማለት ነው::
የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ለምሳሌ በኮሚኒዝም ሶሻሊዝም ዘመን የተለየ ዓይነት የፖሊሲ አያያዝ ነበራቸው:: ለምሳሌ በባለቤትነትም ሆነ በኃላፊነት በብዛት የሚሠራው መንግሥት ነው:: ሕዝብ ደግሞ እንደ ሠራተኛ ይቀጠራል፤ አገልጋይ መንግሥት ነው:: ሶሻሊስታዊም ሆነ ዴሞክራሲያዊ መንገድን የሚከተሉት ነፃ ኢኮኖሚን ሲከተሉ፤ ሌላ ማክሮ ኢኮኖሚክ ፖሊሲ ይኖራቸዋል:: ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ሁኔታ የካፒታል ገበያ መቋቋም፤ የብር ዋጋ በገበያ ላይ መንሳፈፍ እና ከውጭ ምንዛሪ ጋር የወለድ መንሳፈፍ፤ የውጭ ኩባንያዎች ሀገር ውስጥ አስገብቶ መሥራት ለማክሮ ኢኮኖሚ ትልቅ አንድምታ ያላቸው ነገሮች ናቸው:: ሠሪዎቹ አገልጋዮቹ ግለሰቦች ናቸው::
መንግሥት በእጁ ያሉትን አትራፊም ሆኑ አትራፊ ያልሆኑትን ኩባንያዎች ወደ ግሉ ዘርፍ ወደ ሕዝቡ እና ዓለም አቀፍ ነጋዴዎች በካፒታል ገበያ በኩል እንዲገቡ ተቋም አቋቁሟል:: የመንግሥት ትልቁ ሥራ ሀገር መጠበቅ፣ የሕዝብን መብት ማስጠበቅ እና ሕግ ማስከበር ነው:: ከዛ ውጭ የግሉ ዘርፍ ሊሠራቸው የማይችላቸው ሥራዎችን መሥራት ነው:: ከዚህ ወጥቶ መንግሥት ሆቴሎች ማስተዳደር እና ሌሎችም የግሉ ዘርፍ ሊሠራቸው በሚችሉ ሥራዎች ላይ መሠማራት የለበትም:: በነበረው ሁኔታ ግን መንግሥት የግሉ ዘርፍ ሊሠራው የሚችላቸው ሥራዎች ላይ ገብቶ ሲሠራ ነበር::
የደርግ መንግሥት በዚህ ላይ በስፋት ሲሠራ የቆየ ሲሆን፤ ኢህአዴግም በተወሰነ መልኩ አስቀጥሎታል:: አሁንም አንዳንድ በግል ዘርፍ ሊሠሩ የሚችሉ ሥራዎች በመንግሥት እጅ ውስጥ ናቸው:: ለግል ዘርፉ ቢተው ኪሳራ ውስጥ የገቡት ሳይቀሩ አትራፊ ይሆናሉ:: በመንግሥት እጅ ያሉ ድርጅቶች ወደ ግል በአክሲዮንም ሆነ በሽያጭ ሲዘዋወሩ መንግሥት ገቢ ያገኛል:: መንግሥት ያንን ገንዘብ የሚፈልገውን ፖሊሲ ለማስፈፀሚያ ሊያውለው ይችላል::
ሌላው አትራፊ ድርጅቶች ግብር ይከፍላሉ:: ይህ መንግሥት ገቢ ማግኘቱ ደግሞ የመንግሥት በጀት እንዲደጎም ያደርጋል:: አሁን ያለንበት የማክሮ ኢኮኖሚክስ ፖሊሲ ምናልባት ወደ ነፃ ገበያ ሽግግር ላይ ነው ማለት ይቻላል:: ምክንያቱም ኢኮኖሚውን ሊበራላይዝ በማድረግ የግል ዘርፉ ተሳትፎ እንዲኖረው ያደርጋል:: ወደ ግል ያዘዋውራል ሲባል፤ እንዲሁ የመንግሥትን ንብረት ይሸጣል ማለት አይደለም::
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምናልባት አስር ቢሊየን ዶላር ሊገመት ይችላል:: እዚያ ላይ የኢትዮጵያ አትራፊ ድርጅት በመሆኑ በየዓመቱ ትርፍ እናገኛለን ብለው መቶም ሆነ ሁለት መቶ ሚሊዮን ኢንቨስት ያደረጉ ሰዎች ገንዘብ ሲያስገቡ ገንዘቡ ከፍተኛ በመሆኑ፤ ይህንን ገንዘብ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ራሱንም ለማሻሻል ይጠቀምበታል::
በዚህም የኢትዮጵያ መንግሥትም እስከ አሁን ድረስ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ኢንቨስት ያደረጋቸውን ገንዘቦች በመመለስ ለምሳሌ ለድህነት ቅነሳ እና ለሌሎችም ለእርሻ ማስፋፊያ ብድሮች እንዲሰጡ ሊያውል ይችላል:: ለማዕድን ሥራዎች ብድሮች እንዲውል ማድረግ ይቻላል:: ይህ ደግሞ ለብሔራዊ ባንኩ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል::
አሁን ባለው ሁኔታ የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚክስ ፖሊሲ ለውጦች ገና የነፃ ኢኮኖሚ አምድ ሊሆኑ በሚችሉ ምሰሶዎች በመንግሥት እየተገነባ ነው:: እስከ አሁን የነበሩት መንግሥታት ለሀገሪቱ በርዳታ ከፍተኛ ገንዘብ ያገኙ ነበር:: ብድርም ወደ ሀገሪቱ ይጎርፍ ነበር:: አሁን ብድር እየከፈልን ነው:: ከአሁን በኋላ ሌላ ብድር መበደር አንችልም:: ከዓለም ባንክ በጥንቃቄ ካልተበደርን በስተቀር በጣም አስቸጋሪ ነው::
ሌላው ርዳታም በከፍተኛ ሁኔታ አሽቆልቁሏል:: ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2020 ወደ 5 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ርዳታ ተሰጥቷት ነበር:: ብድር ሳይሆን፤ በቀጥታ የተሰጠ ርዳታ ነው:: አሁን ግን ይህ በጣም ወርዷል:: ስለዚህ የሚያዋጣው የገበያ ምሰሶዎቹን በማጠናከር፤ የካፒታል ገበያን በማስፋፋት፤ የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ኢንቨስተሮች እየሠሩ መንግሥት ከፍተኛ ግብር እንዲሰበስብ ማስቻል ነው:: ከዚያ የሚሰበሰበው ገቢ መንግሥት ለሚሠራቸው የልማት ሥራዎች ሊያውል ይችላል::
መንግሥት ለምን ክልሎችን እንደሚደጉም ባላውቅም፤ መንግሥት ክልሎችን ይደጉማል:: ምናልባትም ከርዳታ እና ከብድር የሚመጡ ገንዘቦች ለድጎማ እየሔዱ ይሆናል:: ነገር ግን ክልሎች ራሳቸውን መቻል አለባቸው:: ራሳቸውን የማይችሉ ክልሎች ቢኖሩ እንኳ፤ በዚህ ምክንያት ራሳቸውን ስለማይችሉ ድጎማ ይደረግላቸው ተብለው ተለይተው ድጎማ ማድረግ ይቻላል:: ነገር ግን መሆን ያለበት ክልሎች ለፌዴራል መንግሥቱ መክፈል አለባቸው::
በቀጣይም እንዲሁ ለክልሎች ድጎማ እያደረግን ማክሮ ኢኮኖሚክሱ ይመጣል የሚል እምነት የለኝም:: ለ21ኛው ክፍለ ዘመን ኢኮኖሚ በቂ ገቢ ሊኖር የሚችልበትን መንገድ ለመፍጠር የሚያስችሉትን ምሰሶዎች እየተከልን ነው:: በዋናነት መደረግ ያለበት እርሱን ማፋጠን ያስፈልጋል:: ከዚያ ውጭ ለማክሮ ፖሊሲው ትግበራ ትልቅ ችግር የሚሆኑትን ነገሮች ማስወገድ ያስፈልጋል:: ሌላው መነቀል ያለበት ለምሳሌ ሙስና ነው:: ሙስና እስካለ ድረስ ከፍተኛ ሥራ መሥራትም ሆነ ሕግ ማስከበር አይቻልም::
ሙስናን ሰዎች በአደባባይ የሚደርጉት አይደለም:: ነገር ግን ሰዎች በሞባይላቸው ጉቦ ይቀበላሉ የሚሉ ወሬዎች አሉ:: በተጨማሪ ኮንትሮባንድ ንግድ አለ:: ይህንንም መንግሥት ማስቆም አለበት:: በአብዛኛው ዕቃ በኮንትሮባንድ የሚገባ ከሆነ፤ ገበያ ላይ ግብር የሚከፈሉ እና ለኅብረተሰቡ የተለያዩ አስተዋፅኦ የሚያደርጉ ሰዎች ተወዳድረው መሥራት አይችሉም::
ከሀገር የሚሔድ የውጭ ምንዛሪ የ(ካፒታል ፍላይት) ጉዳይ ላይም በጥንቃቄ መሠራት አለበት:: ገንዘብ ከሀገር መውጣት አለ፤ ውጭ ሀገር ቻይና እና ዱባይ ቤት እየገዙ ቤተሰባቸውን እዚያ የሚስቀምጡ አሉ:: ይህ መጣራት እና እነዚህ ነገሮችን መቆጣጠር ካልተቻለ፤ የማክሮ ኢኮኖሚክ ፖሊሲው ዋጋ የለውም:: ሰላምና መረጋጋት ከመጣ፤ ሙስናን ከታገልን እና ኮንትሮባንድ ማስቆም ከቻልን ድህነትን በመቀነስ በማክሮ ኢኮኖሚክስ ፖሊሲው ሀገሪቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ትደርሳለች የሚል እምነት አለኝ::
አዲስ ዘመን፡- ለኢትዮጵያ የሚሰጣት ርዳታ በከፍተኛ ሁኔታ ያሽቆለቆለው ለምንድን ነው?
ፕ/ር ቆስጠንጢኖስ፡– የውጪ ርዳታ ያሽቆለቆለው በተለያዩ ምክንያቶች ነው:: አንደኛው በኮቪድ ጊዜ ብዙ ርዳታ ወደ ኮቪድ በመሔዱ ነው:: ሀገራቱ ራሱ ርዳታ የሚሰጡት በኢኮኖሚ ደቀው እና ብዙ ሰው እየሞተባቸው ነበር:: በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ እነ ዩክሬን ጦርነት ውስጥ በመግባታቸው አብዛኛው ርዳታ ወደ ዩክሬን መጉረፍ ጀምሯል:: ሶስተኛው በሰብዓዊ መብት ጥሰት ምክንያት ነው በሚል ሰበብ የአሜሪካ መንግሥት አፍሪካውያን ምርታቸውን ከቀረጥ ነፃ ወደ አሜሪካ የሚያስገቡበትን ከአግዋ ከ(አፍሪካን ዕድገት እና ዕድል ድንጋጌ) ላይ ኢትዮጵያ በመሰረዟ ነው:: በእነዚህ እና በሌሎችም በተለያዩ ምክንያቶች ርዳታው ቀንሷል::
አሁን ደግሞ ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካንን ሲመራ ርዳታ የሚባል ነገር እንዳልሰማ ብሏል:: ስለዚህ ያለው አማራጭ ወደ ገበያው ሔዶ ገበያው እንዲሠራ በማድረግ ገበያው ገንዘብ እንዲያመነጭ ማስቻል ብቻ ነው:: መንግሥት በግብር የሚያገኘውን ገንዘብ ለድህነት ቅነሳዎች ሊያውላቸው ይችላል:: በዚህ መልኩ በኅብረተሰቡ መሃል የተጎዱ ዜጎቻችንን መስማት የተሳናቸው፤ ማየት የማይችሉትን በበሽታ እቤት የዋሉትን ለመርዳት የሚቻልበትን መንገድ መፍጠር ይቻላል::
ዋናው ሊሠራ የሚገባው ሀገር መጠበቅ እና የሕዝብን ደህንነት ማረጋገጥ ነው:: የተባበሩት መንግሥታት እና የኢትዮጵያ መንግሥት የተስማሙበት የሰዎች ልማት መለኪያ (ሂውማን ዴቨሎፕመንት ኢንዴክስ) አለ:: ይህ የሰዎችን ጤንነት እና የዕውቀት ደረጃ፤ ሰዎች የሚኖሩበትን ዕድሜ ብዛት ይለካል:: በርግጥ ኢትዮጵያ ባለፉት 25 ዓመታት ሰዎች የሚኖሩበት አማካኝ ዕድሜ ከ47 ዓመታት ወደ 68 ዓመታት ደርሰናል:: ይህ ጥሩ ነው:: ነገር ግን ሰዎች ዕውቀት ኖሯቸው አካባቢያቸውን አሸንፈው መኖር ይችላሉ? የሚለው ማንበብ እና መፃፍ ብቻ ሳይሆን ሰዎች በራሳቸው ተማምነው በጤና መኖር ይችላሉ? የሚለውም ይታያል::
ማክሮ ኢኮኖሚ ጂዲፒን ይጠቅማል:: ይህ ሀገሪቱ ብድር ለመበደር እና ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ይጠቅማታል:: ነገር ግን በጥቂት ኩባንያዎች አንድ ሀገር ጂዲፒዋ በጣም ከፍ ሊል ይችላል:: ለምሳሌ ጋና 34 በመቶ እያደገች ነው:: ይህ የሆነው ነዳጇን ወደ ውጭ በመላኳ ብቻ ነው:: ሌላው በጤና፣ በትምህርት እና ሰዎች በሚኖሩበት ዕድሜ የሚለካው ሂውማን ዴቨሎፕመንት ኢንዴክስ መንግሥት እና የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም አብረው በሚያወጡት የኢትዮጵያ ደረጃ 174ኛ አካባቢ ነች:: ጥሩ ደረጃ ላይ አይደለችም:: ስለዚህ ማክሮ ኢኮኖሚው ቀጥታ የሰዎችን ሕይወት በሚነካ ጉዳይ ላይ ማተኮር አለበት::
ይህ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የጤንነት ሁኔታ የሚያሳይ ሲሆን፤ ወደ ታች በመውረድ የሰዎችን ኑሮ ከፍ ለማድረግ የሚያስችል መዋቅር መሥራት አለበት:: ድህነት ቅነሳን በተመለከተ ፖሊሲዎች ማለትም ከማክሮ ኢኮኖሚክስ በተጨማሪ የእርሻ ፖሊሲ፣ የትምህርት ፖሊሲ፣ የጤና ፖሊሲ እያሉ ይህንን ያሻሽላሉ:: ማክሮ ኢኮኖሚክስ ግን ከላይ ሆኖ የሚያይ ነው::
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በምትከተለው የማክሮ ኢኮኖሚክስ ማሻሻያ ፖሊሲ አማካኝነት መንግሥት በእጁ ያለውን ድርጅት ወደ ግል ማዘዋወሩ ጉዳት የለውም?
ፕ/ር ቆስጠንጢኖስ፡- ወደ ግል ሲዘዋወር እንደውም ሁሉም ተጠቃሚ ይሆናል:: ለምሳሌ በሚድሮክ ሥር የነበሩን ኩባንያዎች ስናይ፤ ምንም አትራፊ አይደሉም ተብለው ብዙ ኩባንያዎች ለሚድሮክ ተሸጠዋል:: መንግሥት አይጠቅሙንም ብሎ አጣርቶ ቢሸጣቸውም፤ አትራፊ ሆነው አሁን ሠራተኞቹ የተሻለ ደመወዝ እያገኙ ነው:: የተሻለ ቴክሎኖጂ ይጠቀማሉ:: ኩባንያዎቹ በጣም አትራፊ ናቸው:: ለሀገር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ነው:: ግብር በመክፈል አንደኛ ሆነው እየተሸለሙ ይገኛሉ:: አሁን የሚድሮክ ኩባንያዎች ከ300 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን የሚያስተዳድሩ ናቸው::
በሚድሮክ ሥር ያሉ ኩባንያዎች ደርግ ትቷቸው እንደሄደው በስብሰው እንደቀሩት ሳይሸጡ ቢተው አይቀጥሉም ነበር:: ጉዳቱ ከፍተኛ ነበር:: ደርግ ብዙ ያሻሻላቸው ነገሮች ቢኖሩም፤ በአጼ ኃይለሥላሴ ጊዜ የነበሩ ኩባንያዎች በእርሱ ዘመን ከስረዋል:: ማሽኖቹ በስብሰው ተበላሽተው ከሥራ ውጭ ሆነው ነበር:: አሁን ግን በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ተተክተዋል:: የግል ዘርፉ ለራሱ ሲል ጥሩ ሥራ ይሠራል:: ኢንቨስት ያደርጋል፤ ጥሩ ትርፍ ያገኛል:: ጥሩ ደመወዝ ይከፍላል::
የግል ባንኮች ከመጀመራቸው በፊት ንግድ ባንክ ደመወዝ የሚከፍለው ለዋና ሥራ አስፈፃሚ አንድ ሺህ አምስት መቶ ብር ብቻ ነበር:: በኋላ ውድድር ሲመጣ እስከ ሶስት ሺህ ብር መክፈል ጀመረ:: አሁን የግል ባንኮች ሁሉም ለሥራ አስኪያጆች ከመቶ ሺህ ብር በላይ መክፈል ጀምረዋል:: ስለዚህ የግል ሥራ መስፋፋቱ ለሠራተኛውም ጠቃሚ ነው:: የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እየተሻሻለ፤ አገልግሎት እየተፋጠነ ይመጣል:: ሠራተኞችም ጥሩ ገቢ ያገኛሉ::
አሁን ያለው የዋጋ ግሽበት ከ30 በመቶ ወደ 15 በመቶ ቢወርድም፤ 15 በመቶውም በጣም ከባድ ነው:: ቋሚ ገቢ ያላቸው ተጎጂ ይሆናሉ:: ቋሚ ገቢ ያላቸው የመንግሥት ሠራተኞች ናቸው:: የግል ዘርፉ የኑሮ ውድነቱን እያየ ደመወዙን በየጊዜው እያሻሻለ ነው:: ዘመን እየጠበቀ እርከን አያሻሽልም:: ሠራተኞቹን ማቆየት ካለበት ደመወዝ እየጨመረ ሊያኖራቸው የሚችል ገንዘብ ይሰጣቸዋል:: እነርሱም በአንፃሩ ጥሩ ውጤት እያመጡ ይሔዳሉ:: ድርጅቱም አትራፊ ይሆናል:: ትልቅ ግብር ለመንግሥትም ይከፍላሉ:: ይሄን በተመለከተ ምንም የሚያስጨንቅ ነገር የለም::
የመንግሥት ድርጅቶች ሕዝብንም ሆነ መንግሥትን ምንም የጠቀሟቸው ነገሮች የሉም:: መንግሥትን አክስረውት ነበር:: ከባንክ አንፃር ከተባለም አብዛኛው የንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ይዘጋ ነበር:: የመንግሥት ድርጅቶች የሚከስሩት ለምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት፤ የግል ዘርፉ በኪሳራ መሥራት አይችልም:: ምክንያቱም ከከሰረ ይዘጋል:: የመንግሥት ድርጅቶች ግን ከመንግሥት ካዝና እየተዘገነ ስለሚሰጣቸው እነሱ አይዘጉም:: ትርፋቸው በጣም ትንሽ ነው:: በመጨረሻ የሕዝብ እና የመንግሥት ዕዳ ሆነው ይቀራሉ::
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በምትከተለው የማክሮ ኢኮኖሚክስ ማሻሻያ ፖሊሲ የውጪ ተፅዕኖ እስከምን ሊደርስ ይችላል?
ፕ/ር ቆስጠንጢኖስ፡- በማክሮ ኢኮኖሚክስ ላይ ከውጭ ያለ ጫና ከተነሳ ሀገሮች አሁን እርስ በራሳቸው የተያያዙ ናቸው:: ቻይና እና አሜሪካ ትልቅ የንግድ ጦርነት ውስጥ የገቡት ኢኮኖሚያቸው በመተሳሰሩ ነው:: አሜሪካ በእኛም ላይ 10 በመቶ ታሪፍ ጥላለች:: ኢኮኖሚያችን የተሳሰረ ነው:: ስለዚህ ኢኮኖሚያችን በርዳታ እና በብድር ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በንግድ ልውውጥም ከፍተኛ ተፅዕኖ አለው:: ይሄንን መካድ አይቻልም::
የውጭ ተፅዕኖ ቀላል አይደለም:: ለምሳሌ አግዋን ስናስብ ከግንዛቤ ውስጥ መግባት ያለበት፤ ወደ እዚያ ይላክ የነበረው ዶላር ብቻ አይደለም:: ዋናው ነገር ኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ናት ተብሎ ኢንቨስተሮች እኛ ሀገር እንዲመጡ ማድረጉ ነው:: ከ200 ሺህ በላይ ሴት ልጆቻችን እንደዚህ ዓይነት የሥራ ዕድል ተፈጠረላቸው ሲባል ነበር:: ያ ትልቅ ትሩፋቱ ነው:: ሀገሩ ሰላም ሆኖ አግዋ ቢቀጥል 200 እና 300 ሺህ ሰዎች ሥራ ይቀጠሩ ነበር:: ይሄ ዕድል ሀገር በቀል የሆነ የኢንዱስትሪ ኃይል ማመንጫት እና ሀገር በቀል ባለሀብቶችን የማካበት ዕድል የነበረው ነው::
ሀገር ውስጥ ጦርነት ስለነበር ያንን አቋረጡ:: ሀገራችን ውስጥ ጦርነት እስካለ ድረስ ኢንቨስተሮች የሚመጡበት ሁኔታ አይኖርም:: የውጭ ኃይሎችም አይረዱንም:: ሀገራችን ሰላም ከሆነችና መንግሥት ከሙስና፣ ከኮንትሮባንድ እና ከሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውሮች ጋር ያለውን ችግር ከፈታ አበዳሪዎችም ሆኑ ርዳታ ሰጪዎች ተስፋ አድርገው ይህች ሀገር በቀጣይ ተስፋ አላት ራሷን ትችላለች ብለው ይሰጣሉ:: ኢትዮጵያ ዕዳ መክፈል አቃታት መባል የለበትም:: እንደዚያ ከሆነ ማንም ወደ ኢትዮጵያ አይመጣም::
እነቻይና፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬት፣ ቬትናም፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ራሳቸውን በኢንቨስተር አሳድገው ዛሬ ቻይና በዓለም በጂዲፒ ሁለተኛ ሆናለች:: ኢኮኖሚዋም አንደኛ ሆኗል:: ስለዚህ ከላይ ያለውን አራት ተግዳሮቶች ካልፈታን በስተቀር ብቻችንን ምንም ልንሆን አንችልም:: የዓለም የንግድ ድርጅት ውስጥ እንገባለን የምንለው ብቻችንን ተጫውተን የትም መድረስ ስለማንችል ነው:: የዓለም አካል መሆን አለብን:: ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት፤ የሊጎፍኔሽን፣ የአፍሪካ ሕብረት አባል ብቻ ሳትሆን መሥራች እና እያንዳንዱን ያስጀመረች ናት:: የዓለም የንግድ ድርጅት ግን ሁሉም ሀገር ሲገባ፤ እነጅቡቲ እንኳን መጀመሪያ ሲገቡ እኛ ግን ‹‹ሰሊጥ እና ቡና ለመሸጥ ለምን እንገባለን ›› ብሎ መንግሥት እምቢ አለ::
አዲስ ዘመን፡- አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ የጣለችውን አስር በመቶ ታሪፍ ጥቅምና ጉዳቱን ቢያብራሩልን?
ፕ/ር ቆስጠንጢኖስ፡– ቁሳቁሶች ላይ ምንም የምለው የለም:: ነገር ግን ቡናን በተመለከተ ከእኛ ጋር የሚገዳደሩ ሀገሮች በከፍተኛ ደረጃ ታሪፍ ተጨምሮባቸዋል:: ለምሳሌ ቬትናም 36 በመቶ ፣ ብራዚልም በተመሳሳይ መልኩ በከፍተኛ ደረጃ ተጨምሮባቸዋል:: የቡና ዋጋ እየጨመረ ቢሄድ፤ ለምሳሌ አራት ዶላር የሚሸጠውን ቡና ታሪፉን ስንጨምር አንድ ኪሎ ቡና አራት ዶላር ከአርባ ብቻ ይሆናል:: የእነርሱ ዋጋ ግን እጅግ ከፍ ስለሚል በዚህ አንጎዳም:: እንደውም ከሌሎቹ በቀነሰ ዋጋ ለመሸጥ ያመቸናል:: ችግር የሚሆነው አስር በመቶ ለምን ተጣለብን የሚለው ነው::
የብሪክስ አባል ስለሆንን እና ትራምፕ ብሪክስን ስለማይወዱት ነው? በዶላር መገበያየት እናስቀራለን ስለሚሉ ነው:: ወይስ ሌላ ምክንያት አላቸው የሚለውን በዲፕሎማሲያዊ መልክ መነጋገር እና በዚህ ጉዳይ ላይ ልታስረዱን ይገባል ብሎ እዚህም ባሉት በአምባሳደራቸው በኩል እንዲሁም እዚያም በእኛ አምባሳደር በኩል መነጋገር ነው:: ሌላው በአብዛኛው ከአሜሪካን የምናመጣው ይበዛል:: ቦይንግ አውሮፕላን የምንገዛው ከዚያ ነው:: አንዱን አውሮፕላን በ100 ሚሊዮን በሚቆጠር ዶላር የሚገዛ ነው:: ስለዚህ ወደፊት መነጋገር ከፈለግን በብዙ መልኩ መነጋገር ይቻላል:: እኛም ቦይንጉን በምንገዛበት ሁኔታ ላይ እንነጋገራለን ብንላቸው ይደነግጣሉ::
ለእኔ ይህ ታሪፍ ችግር ያመጣብናል የሚል እምነት የለኝም:: ነገር ግን ቁጭ ብሎ መነጋገር ያስፈልጋል:: ችግሩ ምን ያህል ነው? ወደ ውጭ የምንልከው ምን ዓይነት ነገር ነው? የሚቀርብን ምንድን ነው? የሚለውን አውቆ መሥራት ያስፈልጋል:: መንግሥት በዚህ ላይ ይሠራል የሚል ግምት አለኝ::
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ::
ፕ/ር ቆስጠንጢኖስ፡- እኔም አመሰግናለሁ::
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም