አምና ከተተከሉ ችግኞች ውስጥ 6 ነጥብ 6 ቢሊዮኑ ፀድቀዋል

አዲስ አበባ፦ በ2016 ዓ.ም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከተተከሉ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች ውስጥ በመጀመሪያው መጠነ መፅደቅ ልኬት 6 ነጥብ 6 ቢሊዮኑ መፅደቁን የኢትዮጵያ ደን ልማት ገለጸ። በልማት መሥሪያ ቤቱ የአረንጓዴ ዐሻራና የተራቆቱ መሬቶች ማገገም ዴስክ ኃላፊ አቶ ጎራው በለጠ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሩ እቅድ ውስጥ ገብቶ በተቀናጀና ሳይንሳዊ መንገድ በተሠራው የችግኝ የእንክብካቤ ሥራ በ2016 ዓ.ም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከተተከሉ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች ውስጥ በመጀመሪያው መጠነ መፅደቅ ልኬት 6 ነጥብ 6 ቢሊዮኑ ፀድቀዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እንደ ሀገር ችግኝ የመትከልና የመንከባከብ ባህልን ማሳደጉን የሚናገሩት ዴስክ ኃላፊው፤ በአረንጓዴ ዐሻራ ልማቱ በስፋት ችግኝ ከመትከል በዘለለ የተተከሉ ችግኞች ፀድቀው ለታለመላቸው ዓላማ እንዲበቁ የችግኝ እንክብካቤ ሥራ በልማቱ እቅድ ውስጥ ገብቶ ልዩ ልዩ የችግኝ እንክብካቤ፣ ቁጥጥርና ድጋፍ ሥራዎች በተቀናጀና ሳይንሳዊ መንገድ ዓመቱን ሙሉ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ዴስክ ኃላፊው አቶ ጎራው፤ የችግኝ እንክብካቤ ሥራ የአረንጓዴ ዐሻራ አንዱ የትኩረት መስክ ተደርጎ በተቀናጀ መንገድ በትኩረት መሠራቱ ለችግኝ መጠነ ፅድቀቱ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማበርከቱን ገልጸዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ ልማቱ በ2011 ዓ.ም ሲጀመር አንስቶ የተተከሉ ችግኞች መጠነ ፅድቀታቸው ዝቅተኛው 79 በመቶ፣ ከፍተኛው ደግሞ 88 በመቶ መሆኑን አመላክተው፤ ባለፉት ስድስት ተከታታይ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከተተከሉ ችግኞች ውስጥ በአማካኝ 81 በመቶዎቹ በተከናወነው የተቀናጀ የችግኝ እንክብካቤ ሥራ መፅደቃቸውን ተናግረዋል።

አቶ ጎራው፤ በ2016 ዓ.ም የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውን አውስተው፤ ከዚህ ውስጥ በተሠራው የተቀናጀ የችግኝ የእንክብካቤ ሥራ በመጀመሪያው መጠነ መፅደቅ ልኬት 6 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኞች ፀድቀዋል ብለዋል። በሁሉም ክልሎች በተሠራው የአንደኛ ዙር የችግኝ መጠነ ፅድቀት ልኬት ባለፈው ዓመት ከተተከለው ውስጥ በአማካኝ 88 ነጥብ 6 በመቶ የፅድቀት መጠን መመዝገቡን ዴስክ ኃላፊው አመላክተው፤ ሆኖም አንደኛ ዙር መጠነ ፅድቀት ልኬት የሚሠራው ጥቅምትና ኅዳር ውስጥ ነው። ይህ ወቅት መሬቱ እርጥበት ስለማይለየውና የከፋ ፀሐይ ስለሌለ ችግኞች የመሞት ዕድላቸው ዝቅተኛ ነው። አብዛኛዎቹ ችግኞች እንደሚፀድቁ አስረድተዋል።

ዋናውና ትክክለኛ የችግኞችን ፅድቀት የሚያመላክተው የሁለተኛው ዙር መጠነ ፅድቀት ልኬት ነው ያሉት ዴስክ ኃላፊው አቶ ጎራው፤ ይህ ልኬት የሚሠራው ሚያዝያና ግንቦት ወራቶች ላይ ነው። በእነዚህ ወራቶች ፀሐዩ ስለሚበረታ በዙሪያቸው እርጥበትና ውሃ አጥተው በብዛት ችግኞች እንደሚሞቱ አንስተዋል። የሁለተኛው ዙር ልኬት ሲካሄድ በመጀመሪያው ዙር ከተመዘገበው ፅድቀት እጅግ ያነሰ ውጤት እንዳይመዘገብ ማኅበረሰቡ በነቂስ ችግኞችን ውሃ በማጠጣትና መንከባከብ ሥራ ላይ እንዲሳተፍ ዴስክ ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።

በ2017 ዓ.ም የክረምት ወራት ለሚካሄደው 7ኛው ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል እቅድ ተይዞ በሀገር አቀፍ ደረጃ የዝግጅት ሥራዎች እየተጧጧፉ የሚገኝ ሲሆን፤ እስካሁንም ስድስት ነጥብ አራት ቢሊዮን ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸው ተጠቁሟል።

ሶሎሞን በየነ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You