‹‹ኢትዮጵያ ለበርካታ የውጭ ዜጎች የጭንቅ ጊዜ መጠለያ ናት›› – ሼህ ሀሚድ ሙሳ

– ሼህ ሀሚድ ሙሳየኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፀሐፊ

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም ወዳድ ነው:: ለዘመናት አብሮ ተከባብሮ በመኖርና የሰላም ተምሳሌት በመሆን በአርአያነት ሲጠቀስ የኖረ ሕዝብ ነው:: ከኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ አኩሪ መገለጫዎች መካከል የብሔር፣ የእምነት፣ የቋንቋ፣ የባሕልና ሌሎች ልዩነቶችን ዕውቅና በመስጠት ተሳስቦና ተከባብሮ መኖር ትልልቅ እሴቶቹ ናቸው:: ከዚህም ባሻገር እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ መሽቶ በነጋ ቁጥር በሰላም አውለኝ፤ በሰላም አሳድረኝ ብሎ ፈጣሪውን ይማጸናል:: ሀገሩም በሰላም ውላ እንድታድር እንደየእምነቱ ይለምናል::

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሰላም ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጥ እና የሰላምን ዋጋ የተረዳ ሃይማኖተኛ ሕዝብ ነው:: ይህ ሕዝብ የሃይማኖት ልዩነት ችግር ሳይሆንበት፤ የብሔርን ልዩነት እንደ ጌጥ ተቀብሎ ከመኖሩም ባሻገር ከሌሎች ሀገራት የሚመጡ ስደተኞችን ጭምር እንደ ባሕላቸው እና ወጋቸው ተቀብሎ የሚያስተናግድ ድንቅ ሕዝብ ነው:: ይሄም እኩሪ እሴት በተለያዩ ምሁራን እና የሃይማኖት አባቶች ጭምር እውቅና የሚሰጠው ነው::

የዛሬውም እንግዳችን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ይህንን የኢትዮጵያውያን መልካም እሴቶች የሚናገሩ፤ የሚያስተምሩ እና ቀጣይም እንዲሆኑ አበክረው የሚታትሩ ናቸው:: እንግዳችን ሼህ ሀሚድ ሙሳ እሸቱ ይባላሉ:: ውልደታቸው ቤኒሻንጉል ክልል መተከል አካባቢ ሲሆን፤ ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ የሃይማኖት ትምህርት ሲከታተሉ አድገዋል:: ወደ ወሎ በመሄድም ተጨማሪ የሃይማኖት ትምህርት ቀስመዋል:: ወደ ግብጽ አልሃዛር ዩኒቨርሲቲ አቅንተው የተለያዩ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን አጥንተው ተመልሰዋል::

አሁኑ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ናቸው:: የአ.አ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊም ሆነው ለሶስት ዓመታት አገልግለዋል:: በተለያዩ መስጊዶችም የሃይማኖት ትምህርት በማስተማርም የሚታወቁ ናቸው::

የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ኢትዮጵያ ለእስልምና ያበረከተችው አስተዋጽኦ ምን እንደሚመስል እና ከዚሁ ጋር ተያይዞ እንደ ሀገር ያለው የእንግዳ ተቀባይነት ባሕል እና በሃይማኖቶች መካከል ያለው የመከባበር ዕሴት ምን መልክ አለው? በሚሉ እና መሰል ጥያቄዎች ዙሪያ ከሼህ ሀሚድ ሙሳ እሸቱ ጋር ቆይታ አድርጓል::

አዲስ ዘመን፡- የእስልምና ሃይማኖት የሰላምን አስፈላጊነት የሚገልጸው እንዴት ነው?

ሼህ ሀሚድ፡- ይህ በተደጋጋሚ የሚነሳ ጥያቄ ነው:: ሰላም መተኪያ የሌለው ጸጋችን ነው:: እንደ ውሃ፤ አየር፤ ፀሐይ የመሳሰሉት የተፈጥሮ ስጦታዎችን ያህል እጅግ አስፈላጊ ነው:: ሰላም ለሀገር፤ ሰላም ለሕዝብ፤ ሰላም ለግለሰብ፤ ሰላም ለእንስሳት እና አራዊት አልፍ ሲል ለእጽዋቶች ጭምር አስፈላጊ ነው:: በአጠቃላይ ሰላም ለምድር ፍጡራን ሁሉ ወሳኝ ነው::

አላህ የሰላም ጌታ ነው የሚባለው ለዚህም ነው:: ሰላም የሚያሰፍነውም እሱ ነው:: ከአላህ ዘጠና ዘጠኝ ስሞች አንዱ አሰላም ነው:: ነብዩ መሐመድ ለፈጣሪያቸው ‹‹አንተ ሰላም ነህ፤ ሰላምም ከአንተ ነው፤ ሁሉም ነገር ወደ አንተ ይመለሳል፤…›› እያሉ ያወድሱታል:: በሌላ አስተምሮታቸውም ‹‹ሙስሊም ማለት ከምላሱ እና ከእጁ ሰላም የሆነ ሰው ነው›› ሲሉ የእምነትን ጥንካሬ ከሰላም ጋር አያይዘው ተናግረዋል:: በምላሱ ሰዎችን የማይዘልፍ እና በአካሉም ሰዎችን የማይጎዳ ማለታቸው ነው::

የሰው ልጅን አላህ አክብሮታል:: ፈጣሪ ያከበረውን የሚያዋርድ እና ሰላም የሚነሳ ሰው ደግሞ በመጨረሻው ቀን ከፈጣሪ ቅጣቱን መቀበሉ የማይቀር ነው:: ሰዎች በእዚህች ዓለም ላይ ሲኖር መከባበር አለባቸው:: አንዱ የሌላውን ችግር መረዳት እና መፍትሔ ሆኖ መቅረብ አለበት:: ከራሱ ጥቅም እና ፍላጎት ይልቅ የሌሎችን ፍላጎት እና ጥቅም ማስቀደም ተገቢ ነው:: የእኔ ብቻ፤ ከእኔ ብቻ ከሚሉ አስተሳሰቦች ወጥተን የእኛ ወደሚል ዕሳቤ መመለስ አለብን:: እኔ የሚለው አስተሳሰብ ለጸብ እና ላለመግባባት ምንጭ ነው::

አንድ ሰው ትክክለኛ አማኝ የሚባለው በምላሱ ሰዎችን የማይዘልፍ፤ በእጁ ማንንም የማይነካ ሲሆን ነው:: አላህ ሰዎች ለሰላም የተለየ አተያይ እንዲኖራቸው በበርካታ አንቀጾች ላይ ስለሰላም አስፈላጊነት ተናግሯል:: በነብዩ አስትምሮትም ስለሰላም በተደጋጋሚ ተወስቷል:: ሰዎች እነዚህን መልዕክቶች በአግባቡ ተረድተው ወደ ተግባር ለውጠዋቸው ቢሆን ኖሮ፤ ይህቺ ዓለም ለሁሉም የምትመች ትሆን ነበር:: ሆኖም በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ የሚታየው ከዚህ በጣም የራቀ ነው::

አንዳንዶች በምላሳቸው ከግለሰብ አልፎ ሀገርን ሲረብሹ እና ሰላም ሲነሱ ይታያሉ:: በተለይም በአሁኑ ወቅት ዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከግለሰብ አልፎ የሀገርን ሰላም የሚያውኩ ብዙዎች ናቸው:: እነዚህ አዋኪዎች የሌላውን ሰላም የበጠበጡ ይምሰላቸው እንጂ፤ የራሳቸውን ሰላም እያጡ መሆኑን የሚረዱት ዘግይተው ነው:: እነዚህ ሰዎች ሁሉንም ነገር የሚረዱት ሰላም በጠፋ ማግሥት ነው:: ሁሉም ነገር ከተበላሸ በኋላ የሰላምም አስፈላጊነት ሲረዱ እና ሲጸጸቱ እናያለን:: ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ሁሉም ነገር ከጠፋ እና ከተበላሸ በኋላ ስለሚሆን ጸጸቱ ምንም ዋጋ አይኖረውም:: ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ እንደሚባለው ሁሉም ነገር ከእጃችን ካመለጠ በኋላ መጸጸቱ ፋይዳ አይኖረውም::

ለሰዎች ሰላም የማይሰጡ ሰዎች ሁልጊዜም ሌላውን እየረበሹ መኖር አይችሉም፤ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር እነሱም ጋር ይመጣል:: ስለዚህም ሰላም እንዲጠፋ እና ብጥብጥ እንዲነግስ የሚሠሩትን መገሰጽ ይገባል:: ሁሉም ዜጋ ለሰላም ሲል ማንኛውንም ዓይነት መሰዋዕትነት መክፈል ይጠበቅበታል::

አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ግለሰቦች በሚያስተላልፉት መልዕክት ሀገር ሰላም ስታጣ እናያለን:: እነዚህን ሰዎች እንዴት ማረም ይቻላል?

ሼህ ሀሚድ፡- ከሁሉም ነገር በላይ የሚገርመኝ አንዳንድ ሰዎች የሚያስተላልፉት መልዕክት የሚያመጣውን ጦስ አይገነዘቡም:: አንዳንዶቹ የሚያደርጉት ሆን ብለው ነው:: ነገር ግን እንዴት አንድ ግለሰብ በሚያስተላልፈው መልዕክት ሀገር ትቸገራለች፤ ሰዎች መውጫ መግቢያ ያጣሉ፤ ይሞታሉ፤ ይፈናቀላሉ:: በአንድ ግለሰብ ሰበብ ዶሮ እንኳን ሊሞት አይገባም::

አሁን አሁን የሚታየው ጉዳይ ግራ የሚያጋባ ነው:: ተማርን የሚሉ ሰዎች በየማህበራዊ ሚዲያው በሚያስተላልፉት መልዕክት የብዙዎች ሕይወት ተናግቷል፤ ሀገርም ብዙ ዋጋ እየከፈለች ነው:: እምነትን ከእምነት፤ ብሔር ከብሔር እያጋጩ መኖርን የሚመርጡ ግለሰቦች እየተበራከቱ ነው:: ተማርን የሚሉ መሃይማን ሀገር እያፈረሱ ነው:: ሆኖም ልብ ሊሉት የሚገባው አውርቶ መኖርም፣ ሆነ እንደ ልብ ሃሳብ መሰንዘር የሚቻለው ሀገር ስትኖር ነው:: ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ለጊዜው ሁከት እና ብጥብጥ እየፈጠሩ ገቢ ቢያገኙም የኋላ ኋላ ተጎጂ የሚሆኑት እነሱ ጭምር ናቸው::

ከዚህ ሁሉ በፊት ግን የሃይማኖት አባቶች ማስተማር፤ መገሰጽ አለባቸው:: ችግሩ እየከፋ ሄዶ እንደ ሀገር ከመጎዳታችን በፊት እነዚህን ሰዎች ልናርማቸው ይገባል:: በምናስተላልፈው መልዕክት የአንድ ሰው ሕይወት ሊጎዳ አይገባም:: ይህን የሚያደርጉ ሰዎች ለጊዜው ገንዘብ ቢያገኙም በኑሯቸው ደስተኛ ሊሆኑ አይችሉም:: ክፉ መልዕክት ለሚያስተላልፉት አጋዥ መሆን እና እነሱ ሃሳብ እንዲያሰራጫ ማድረግም የክፉ ነገር ተባባሪ መሆን ስለሆነ ይህም በአላህ ዘንድ ያስጠይቃል:: ሰዎችን ለሚጎዳ፤ ሰላምን ለሚጻረር፤ ክፉ መልዕክት ለሚያስተላልፍ ሰው አጋዥ መሆን የድርጊቱ ተባባሪ የመሆን ያህል ነው::

አንድነትን ለሚበርዝ፤ የሀገርን ከፍታ ከሚንድ፤ አብሮነትን ከሚጋፋ መልዕክት ራሳችንን ማራቅ ይገባናል:: ለእንደነዚህ ያሉ ሃሳቦች ተባባሪ መሆን የለብንም:: ግለሰቦች በሚያስተላልፉት መልዕክት የሰዎች ሕይወት ከጠፋ ከፈጣሪ ጋር መጣላታቸው አይቀርም:: ስለዚህ እኛ የሃይማኖት አባቶች በአግባቡ ማስተማር አለብን::

አዲስ ዘመን፡ – የእስልምና ሃይማኖት ስለ አንድነት እና በፍቅር አብሮ ስለመኖር ምን ይላል?

ሼህ ሀሚድ፡- አብሮ መኖር የሰው ልጅ የተፈጥሮ ባሕሪ ነው:: ሳይንስ እንኳን የሰው ልጅ ማኅበራዊ እንስሳ ነው ይላል:: በደጉም በክፉም አብሮ የሚኖር የሚረዳዳ እና የሚተዛዘን ማለት ነው:: ማንም ሰው ደስታውን ማጣጣም የሚችለው ከሰው ጋር ሲሆን ነው:: ካለሰው ደስታው ሀዘን ይሆናል:: ከሀዘንም መጽናናት የሚቻለው ከሰው ጋር ሆኖ ነው:: በአጠቃላይ ሰው ያለ ሰው ምንም ማለት ነው:: ሰዎች ሁሉ አንድ ናቸው:: ነብዩ መሐመድ ሁላችሁም የአዳም ልጆች ናችሁ ያሉት ለዚህ ነው::

አንዳንድ ጊዜ ግን በዚህ ማህበራዊ መስተጋብር ውስጥ መደነቃቀፍ ይጠፋል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው:: ከሰው ልጅ ባሕሪ አንጻርም የሚጠበቅ አይደለም:: እንኳን ሰው ከሰው ጋር እግር እና እግር ጭምር ይጋጫል:: ጥርስ ምላስን ይነክሳል:: ሆኖም እንዴት ጥርሴ ምላሴን ነከሰኝ ተብሎ አውልቆ አይጣልም:: ልክ እንደዚሁ ሁሉ እንደ ሕዝብ ስንኖር አልፎ አልፎ መደነቃቀፍ ሊያጋጥም ይችላል፤ ይህንን ተፈጥሯዊ መሆኑ መረዳት ያስፈልጋል:: አንዳንድ ሰዎች ይህንን ተፈጥሯዊ ሁኔታ ከልክ በላይ በማስጮህ በሃይማኖቶች መካከል ሰላም እንደ ጠፋ አድርገው ሲናገሩ እስማለሁ፤ ይህ ትክክል አይደለም::

በተለይም በሰፊ ማኅበረሰብ ውስጥ የተለያየ ግንዛቤ እና የእውቀት ደረጃ ባለበት ሁኔታ ሁሉም ሰዎች ተመሳሳይ አመለካከት ይኖራቸዋል ብሎ ማሰብ አይቻልም:: ስለዚህም አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ ጉዳዮችን በልካቸው ማየት ተገቢ ነው::

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የተለያዩ እምነቶች በሰላም የሚኖሩባት ሀገር ነች:: በእንግዳ ተቀባይነቷም በታሪክ ጭምር የምትታወቅ ሀገር ነች:: በእዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ ?

ሼህ ሀሚድ፡- ስለኢትዮጵያ ሲነሳ ሁልጊዜ አብሮ ከሚነሱ እሴቶች ውስጥ አንዱ የሕዝቡ እንግዳ ተቀባይነት ነው:: ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ሕዝቡም እንደ ሕዝብ እንግዳ ተቀባዮች ናቸው:: ይህ የእንግዳ ተቀባይነት መገለጫ ከድሮ እስከ ዘንድሮ የቀጠለና ወደፊትም አብሮን የሚኖር ነው::

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የረመዳንን ጾም ምክንያት በማድረግ የተለያዩ የኢፍጣር (ጾመኞችን የማብላት) መርሃ ግብሮችን ሲያካሂዱ ቆይተዋል:: ሀገራቸውን ጥለው የተሰደዱና ኢትዮጵያን መጠጊያ ያደረጉ የሶማሊያ፤ የሶርያ፤ የየመንና የተለያዩ ሀገር ስደተኞችን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤተመንግሥታቸው ድረስ ጠርተው አስፈጥረዋል:: በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ስደተኞችን ቤተመንግሥት ድረስ ጋብዞ ማስፈጠር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ጊዜ ጀምሮ የቀጠለ በጎ ተግባር ነው:: በዚህ ተግባራቸውም ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የነበራትን እንግዶችን የመቀበል ታሪክ አስቀጥለዋል::

ኢትዮጵያ ስደተኞችን የመቀበል ታሪኳ የሚጀመርው ከመካ ተሰደው የመጡ የእስልምና እምነት ተከታዮችን ተቀብላ ከማስተናገዷ ጋር በተያያዘ ነው:: ነብዩ መሐመድ የእስልምና እምነትን ለማስፋፋት ሲነሱ በመካ የነበሩ የባዕድ እምነት ተከታዮች ተቃውሟቸው እስከማሳደድና የአማኞችንም ሕይወት እስከ ማጥፋት የደረሰ ነበር::

በዚህ የጭንቅ ወቅት ነብዩ ሙሐመድ ተከታዮችን ለሁለት ጊዜ ያህል ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ከባዕድ አማኞቹ ጨካኝ በትር ማዳን ችለዋል:: ይህን ዓለም አቀፋዊ መልዕክት መሠረት ለመጣል በወቅቱ እንደ ሀገር፤ እንደ መንግሥትና እንደ ሕዝብ መስዋዕትነት የከፈለ ከሐበሻ በቀር ማንም የለም::

ነብዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) ሐበሻን ‹‹የእውነት ምድር» ብለዋታል፣ ይህ አባባል ምንም እንኳ መካ የተከበረው የአላህ ቤት የሚገኝበት ቢሆንም በወቅቱ ፍትህና እውነት ስለጠፋ ነብዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) እና ተከታዮቻቸው ለስቃይና ችግር ተጋልጠው ነበር:: የሚፈለገው ፍትህና እውነት ግን በሐበሻ መሬት በጊዜው ተግባራዊ መሆን ችሏል:: ስለዚህ ነብዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) ሲታገሉለት የነበረው ፍትህና እውነት ከመካ ከ16 ዓመት በፊት በሐበሻ ምድር ተረጋግጦ ነበር:: ለዚህ ነው ሐበሻ የፍትህና የእውነት ምድር በመሆን መካን የቀደመችው::

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ስደተኞችን ስትቀበል ባሕላቸውን እና ሃይማኖታቸውን አክብራ እንደሆነ ይነገራል:: እውነት ነው ?

ሼህ ሀሚድ፡- በትክክል:: ከኢትዮጵያውያን አስደናቂ ስብዕናዎች አንዱ የስደተኞችን ባሕል እና ሃይማኖት አክብረው እንዲኖሩ መፍቀዳቸው ነው:: ቀደም ሲል ከመካ ወደ ኢትዮጵያ ስደተኞች ምንም እንኳን ከሐበሻ ጋር ቋንቋ፣ ብሔር፣ ባሕል፣ ወግ፣ ቀለም ባያዛምዳቸውም ባደረጉት የ16 ዓመት ቆይታ፤ በእነሱ ላይ የተፈፀመባቸው ግፍም ሆነ በደል ፈፅሞ አልነበረም:: እምነታቸውን በነፃነት ተግባራዊ እያደረጉ ከመንግሥትም ሆነ ከሕዝቡ አስፈላጊ ድጋፍ፣ ድጐማና እንክብካቤ እየተደረገላቸው መቆየት ችለዋል::

የስደት ቆይታቸውን ጨርሰው እስከሚመለሱ ድረስ ከነሱ ውስጥ አንድም ቅሬታ ያቀረበ ስደተኛ አልነበረም:: እንዲያውም ለሐበሻ ምድር፣ ለንጉሡና ለሕዝቧ ከፍተኛ ፍቅርና ክብር ነበራቸው:: ባሕል እና ሃይማኖታቸው ተከብሮላቸው በመኖራቸው ሁልጊዜም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍ ያለ ክብር አላቸው:: በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ በማኖርና እምነታቸውንም በነፃነት እንዲያከናውኑ በማድረግ ደማቅ ታሪክ ያላት ሀገር ነች:: የአይሁድ፤ የክርስትና እና የእስልምና ሃይማኖቶችን ተቀብላ በአንድነትና በወንድማማችነት በሀገራቸው እንዲኖሩ ያደረገች ድንቅ ሀገር ነች::

አዲስ ዘመን፡- አሁንስ ይህ ሁኔታ ቀጥሏል?

ሼህ ሀሚድ፡- የኢትዮጵያ እንግዳ ተቀባይነት ዘመን የማይሽረው ነው:: ዛሬም ድረስ የተለያዩ ሀገራት ሲቸገሩ የሚመጡት ወደ ኢትዮጵያ ነው:: የጎረቤት ሀገራትም ሆኑ የሩቅ ሀገራት ግጭት፤ ጦርነት እና ስደት ሲያጋጥማቸው የሚመጡት ወደ ኢትዮጵያ ነው:: ከኢትዮጵያ የተሻለ ሀብት እና የኑሮ ደረጃ ያላቸው እና ሊያሳድዷቸው የሚችሉባቸው የቅርብ ሀገራት እያሉ በርካታ የጎረቤት ሀገራት ስደተኞች ምርጫቸው የሚያደርጉት ኢትዮጵያን ነው::

የተለያዩ ሀገራት ስደተኞች ኢትዮጵያን የሚመርጡት ሕዝቡ እንግዳ ተቀባይ በመሆኑ ነው:: ከዚህም ባሻገር ማንኛውም ስደተኛ ባሕሉ እና እምነቱ ተከብሮለት የመኖር መብት የምትሰጠው ኢትዮጵያ ብቻ ነች:: ሌሎች ሀገራት በቂ ሀብት ቢኖራቸውም መጀመሪያውኑ ስደተኞችን የመቀበል ፍላጎት የላቸውም:: ቢያስገቡ እንኳን የስደተኞችን ባሕል እና እምነት እንዲሁም የተለያዩ የአኗኗር ዘይቤዎችን ማክበር ይሳናቸዋል::

እንደ መንግሥትም የኢትዮጵያ መሪዎች ለስደተኞች ልዩ ክብር ይሰጣሉ:: ከራሳቸው ዜጋ ባልተናነሰ መልኩ እንዲኖሩ ሁኔታዎችን ያመቻቻሉ:: የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ፤ ስደተኞች በሰላም እንዲኖሩም ጥበቃ ይደረግላቸዋል::

ኢትዮጵያ ለብዙዎቹ ሀገራት የጭንቅ ጊዜ መጠለያ ናት:: ከ25 ዓመታት በፊት ሶማሊያ ውስጥ ባጋጠመው ግጭት በርካታ ሶማሊያውያን ለስደት ተዳርገው ነበር:: ሕዝቡ የፈለሰው ወደ ሳኡዲ፤ የመን ወይም ጅቡቲ አይደለም:: ወደ ኢትዮጵያ ነው:: በአሁኑ ወቅትም በሱዳን፤ በደቡብ ሱዳን ባለው ግጭት እና ጦርነት መጠጊያ የሆነችው ኢትዮጵያ ነች::

ሱዳን በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ ጋር የድንበር ውዝግብ አለባት:: ሆኖም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ ላይ ትገኛለች:: ኢትዮጵያ ሀገራት ሲቸገሩ፤ በጦርነት እና በግጭት ሲጎዱ ተቀብላ ታስጠልላለች እንጂ ስደተኞችን አልቀበልም አትልም:: ወይም ደግሞ ሀገራት ሲቸገሩ የራሷን ጥቅም ለማስጠበቅ ሙከራ አታደርግም:: በሥነ ምግባር የታነጻ ሕዝብ እና መንግሥት ያላት ጥንታዊ ሀገር በመሆኗ የምትፈጽማቸው ድርጊቶች በከፍተኛ ስብዕና የሚገለጽ ነው::

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር አላት፤ በዓለም አቀፋዊ እና ሀገራዊ ሁኔታ ምክንያት የኑሮ ውድነት እና የኢኮኖሚ ችግር አለ:: ይህም ሆኖ ግን ስደተኞችን ከመቀበል ተቆጥባ አታውቅም:: በዚህም ላይ ለስደተኞች የሥራ ዕድል ከመፍጠር እና ነገሮችን ከማመቻቸት በስተቀር ከስደተኞች የምትፈልገው ገንዘብ የለም:: ግብጽን የመሳሰሉ ሀገራት ከእያንዳንዱ ስደተኛ እስከ 3ሺ ዶላር ይቀበላሉ:: ኢትዮጵያ ለቪዛ እና መሰል ጉዳዮች የምትጠይቀው ከ10 ዶላር ያነሰ ነው::

በሱዳን እርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት በርካታ ሱዳናውያን ወደ ግብጽ ለመሰደድ ሞክረው ነበር:: ሆኖም 3ሺ ዶላር በመጠየቃቸው ወደ ግብጽ ሊገቡ አልቻሉም:: 3ሺ ዶላር ለአንድ ስደተኛ ከፍተኛ ገንዘብ ነው:: ከየትም አምጥቶ ሊከፍል አይችልም:: በየትኛው ሀገር ያለ ስደተኛ የቆይታውን ጊዜ ሲያራዝም ከፍተኛ ገንዘብ ይከፍላል:: ከላይ እንደገለጽኩት በርካታ ሀገራት 3ሺ ዶላር ቪዛ ለማደስ ያስከፍላሉ:: ኢትዮጵያ አሁንም ቢሆን እያስከፈለች ያለችው ከ10 ዶላር ያነሰ ነው:: ይህም የሚያመላክተው ከፍ ያለ ሰብዓዊነት የሚታየው ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑን መረዳት ይገባል::

ከዚሁ ባሻገር ከኢትዮጵያ በስተቀር ስደተኞች እንዲለምኑ የሚፈቅድ ሀገር የለም:: ሌሎች ሀገራት የደህንነት ስጋት ናቸው በሚል እንዲዘዋወሩ አይፈቅዱላቸውም:: ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚታየው በየመንገዱ እና በየመስጊዱ ስደተኞች እየለመኑ ራሳቸውን እያስተዳደሩ ይገኛሉ:: የኢትዮጵያ ፖሊሶች እንኳ ለስደተኞች ከማዘናቸው የተነሳ የማይገባ ቦታ ሁሉ ሲለምኑ እያዩ እንዳላዩ የሚያልፉ በጎ ሰብዓና የተላበሱ ባለሙያዎች ናቸው::

አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በሃይማኖት ተቋማት መካከል ያለው መተባበር ምን ይመስላል ?

ሼህ ሀሚድ፡- በአሁኑ ወቅት በሃይማኖቶች በኩል ያለው መደጋገፍ እና መተባበር የሚያስደንቅ ነው:: መቻቻል ከሚለው የተለመደ አባባል ወጥተን መከባበር እና መደጋገፍ ወደሚለው እሳቤ ገብተናል:: የአንዱ ችግር የሌላው ችግር መሆኑን ሁላችንም ተረድተናል:: አንዱ ችግር ሲገጥመው ሌላው ቀድሞ ይደርሳል:: በአንዱ ፕሮግራም ላይ ሌላው ቀድሞ ተገኝቶ ይሳተፋል::

እምነቶች የሚኖሩት በኢትዮጵያ ጥላ ስር ነው:: የኢትዮጵያ ጉዳይ ሁሉንም ያገባዋል:: እንደ በፊቱ አንዱ ባለቤት ሌላው ተመልካች የሚሆንበት አስተሳሰብ ተዘግቷል:: ስለዚህም በሀገራችን ጉዳይ ላይ እኩል እንጨነቃለን፤ እንወያያለን ፤ እንመካከራለን:: ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረው አንዱ ለአንዱ እውቅና የሚነፍግበት ሳይሆን እውቅና የሚሰጥበት ሁኔታ ነው :: እስላሙም ሆነ ክርስቲያኑ ወይም ሌላው የሃይማኖት ተቋም በጨዋነት እና በመልካም ሥነ ምግባር የተገነባ በመሆኑ መከባበር እና የሌላውን ሃሳብ የመረዳት ችሎታ ያለው ነው:: ስለዚህም ሰዎች ከውጭ ሆነው እንደሚያስቡት ሳይሆን በአሁኑ ወቅት በሃይማኖት ተቋማት መካከል ያለው መተባበር እና መከባበር በጣም የሚያስደስት ነው:: አሁን ያለው አንዳንድ ግለሰቦች በሚፈጥሩት የተዛባ መልዕክት የሚደፈርስ ግንኙነት አይደለም:: ይህም ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው::

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት መብቷን ለማረጋገጥ እየሠራች ነው:: ይሄንን እንዴት ያዩታል ?

ሼህ ሀሚድ፡– ኢትዮጵያ ለሺህ ዓመታት የቀይ ባሕር ንጉሥ ሆና የኖረች ሀገር ነበረች:: ስለዚህም ኢትዮጵያ ወደ ቀደመ ማንነቷ ወደ ቀይ ባሕር መመለስ አለባት:: ለዚህም በአሁኑ ወቅት የባሕር በር አማራጮችን በሰላማዊ መንገድ በማፈላለግ ላይ ትገኛለች:: ይህ ሰላማዊ ጥያቄ አፋጣኝ መልስ ሊያገኝ ይገባል::

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ በአንባብያን ስም አመሰግናለሁ::

ሼህ ሀሚድ፡- እኔም አመሰግናለሁ::

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You