በበዓል ወቅት የአመጋገብ ጥንቃቄ እንዲደረግ የሕክምና ባለሙያው አሳሰቡ

አዲስ አበባ:- የፋሲካ በዓል የፆም ቀናትን መጠናቀቅ ተከትሎ የሚከበር እንደመሆኑ ተገቢውን የአመጋገብ ሥርዓት መከተል እና የአመጋገብ ጥንቃቄ እንዲደረግ የጨጓራ፤ የአንጀትና የጉበት በሽታ ሰብ ስፔሻሊስት ዶክተር መንግሥቱ እርቄ ገለጹ፡፡

ለረጅም ጊዜ ቅባትና ሥጋ ነክ ከሆኑ ምግቦች ርቆ የቆየ ጨጓራ ቅባትና ሥጋ ነክ ወደ ሆኑ ምግቦች ሲሸጋገር ለሕመም የመዳረግ ዕድሉ ከፍተኛ በመሆኑ አመልክተው፤ ከዚህ አኳያ በበዓሉ ወቅት የአመጋገብ ሥርዓትን ማስተካከል ይገባል ብለዋል፡፡

ለረጅም ጊዜ ቅባት የረሳ፣ በመጠኑ ምግብ መብላት የለመደ አንጀት (ጨጓራ) በአንዴ ከፍተኛ አመጋገብ እና ካሎሪ ሲወስድ የሚጨናነቅና መጠነኛ የጤና መታወክ የሚያስከትል መሆኑን ገልጸው፤ ማኅበረሰቡ በበዓል ወቅት የሚጠቀማቸው ከአቅም በላይ ቅባትና ዘይት ተኮር ምግቦችን በመጠኑ እንዲጠቀም መክረዋል፡፡

ዶሮ ወጥ ለመብሰል እስከ ሦስት ሰዓት እሳት ላይ ይቆያል፡፡ እንደዚህ አይነት ምግቦች አንጀት አይቋቋማቸውም፤ ይከብዳሉ፡፡ ጤናን ከመጠበቅ አኳያም አንድ ሰው ከአንድ ዶሮ ወጥ እስከ ዘጠኝ ጊዜ የሚጎርስ ቢሆን ቀንሶ አምስት ጊዜ ብቻ ቢጎርስ ይመከራል ነው ያሉት፡፡

በጎን ደግሞ እንደቆስጣ፣ ሰላጣ፣ የተቀቀለ ድንች፣ ያሉ አትክልቶችን እንዲሁም ተልባ መቀላቀልና ተመጣጣኝ የሆኑ ምግቦችን መጠቀም እንደሚገባም ነው ዶክተር መንግሥቱ የተናገሩት፡፡

ሁሉንም ምግቦች በጣም አጣፍጦ፣ አቁላልቶ አለመመገብ ይመከራል፡፡ ቀቅሎ መመገብ የተሻለ ነው። በዓመት በዓል ሰሞን ሥጋ አብዝቶ መጠቀም አንጀትን ለከፍተኛ (የቅባት) የፕሮቲን መጠን ያጋልጣል፡፡ የሰውነት ቅርጽና የክብደት መጠንን በአጭር ጊዜ ውስጥ ያዛባል፡፡ የስኳር መጠን እና ክብደት እንዲጨምር ያደርጋል፣ ክብደት መጨመር በራሱ ለጤና ትልቅ ችግር አለው፡፡ ለመቀነስ ብዙ ጊዜ ይወስዳል ብለዋል፡፡

በዓመት በዓል ጊዜ አልኮልና ጣፋጮች ከአቅም በላይ ከመጠቀም መቆጠብና በሂደት ሰውነትን አስለምዶ ቀስ በቀስ መጥኖ መጠቀም አግባብ ነው ያሉት ዶ/ር መንግሥቱ፤ የአመጋገብ ሥርዓት ከመጥገብ አንጻር መቃኘት የለበትም፡፡ ሰዎች በጣም እስኪጠግቡ መመገብ የለባቸውም፡፡ የሚያስፈልገውን መጠነኛ አመጋገብ መጠቀም ጥሩ ነው፡፡ መጠንን መቀነስም አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ምግብን ከአቅም በላይ አለማብሰል፣ ሌሎች ተለዋጭ ምግቦች አትክልትና አትክልት መሰል ነገሮችን ከሥጋ ጋር በተመጣጠነ መልኩ በማዕድ ማቅረብ አስፈላጊ መሆኑንም አመልክተው፤

ከምግብ በኋላ ተገቢ የሆነ እንቅስቃሴ ማድረግ (ወጣ ብሎ መመለስ)፣ ራትን በመዝለል ለሰውነት ዕረፍት መስጠት እንዲሁም አልኮል በብዛት አለመጠቀም ተገቢ መሆኑንም ዶ/ር መንግሥቱ አስገንዝበዋል፡፡

ዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You