
አዲስ አበባ፦ የሴቶች ቀን በዓልን (ማርች 8ን) ታሳቢ በማድረግ መጋቢት ወሩን ሙሉ ልዩ ልዩ የንቅናቄ ሥራዎችን በማከናወን የመዲናዋ ሴቶችን በተጨባጭ ተጠቃሚ ማድረጉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ።
የቢሮው ምክትል ቢሮ ኃላፊና የሴቶች ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ ዝናሽ ከተማ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ቢሮው የሴቶች ቀን በዓልን (ማርች 8ን) በአዳራሽ ተሰብስቦ ከመዘከር ወይም ከማክበር በዘለለ፤ በዓሉን ታሳቢ በማድረግ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በተግባር የሚያረጋግጡ የተለያዩ የትኩረት መስኮችን ነድፎ መጋቢት ወሩን ሙሉ ልዩ ልዩ የንቅናቄ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። በዚህም የመዲናዋ ሴቶች መሬት ላይ በተጨባጭ ሊቆጠር የሚችል ልዩ ልዩ ጥቅም አግኝተዋል።
እንደ ወይዘሮ ዝናሽ ገለጻ፤ ተቋሙ በዓሉን ታሳቢ በማድረግ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በተግባር ለማረጋገጥ አቅዶ ወሩን ሙሉ ሲያከናውናቸው ከነበሩ የንቅናቄ ሥራዎች ውስጥ አንዱ የትኩረት መስክ የሴቶችን አደረጃጀት መደገፍና ማጠናከር ነው። በዓሉን ታሳቢ ተደርጎ በተከናወነው የንቅናቄ ሥራ ለዓመታት ፈርሰው ከአገልግሎት ውጭ የነበሩ የሴቶች የልማት ኅብረቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ መልሶ የማደራጀትና የማጠናከር ሥራዎች በስፋት ተከናውኗል።
በዚህም 173 ሺህ 171 አባላት ያላቸው 5 ሺህ 319 ዘርፍ ብዙ ጥቅም የሚሰጡ የሴት የልማት ኅብረቶችን መልሶ የማደራጀት፣ የማጠናከር፣ የመደገፍ፣ ያሉባቸውን ጉድለቶችና ክፍተቶች የመሙላት ሥራ መከናወኑን አስገንዝበዋል።
ኅብረት ሥራ ማኅበራት ሰዎች በተናጠል መፍታት የማይችሉትን ችግር ሰብሰብ ብለው ተደራጅተው የሚፈቱበት ቁልፍ አደረጃጀት ነው ያሉት ወይዘሮ ዝናሽ፤ ይህ አደረጃጀት በተለይ ሴቶች የሚገጥማቸውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያው ችግር ከማቃለል አኳያ ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዓሉን አስመልክቶ ሴቶች ዘርፉን እንዲቀላቀሉ በተሠራው ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ፤ በአንድ ወር ውስጥ ከዚህ ቀደም ዘርፉን ያልተቀላቀሉ አንድ ሺህ 175 አዲስ ሴቶች ኅብረት ሥራ ማኅበራትን መቀላቀላቸውን አመላክተዋል።
የሴቶችን የቁጠባ ባህል ማጠናከር ሌላኛው በዓሉን ታሳቢ ተደርጎ የተከናወነ የንቅናቄ ሥራ እንደሆነ ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሮ ዝናሽ ጠቅሰው፤ በዓሉን ታሳቢ ተደርጎ ወሩን ሙሉ በተከናወነው የንቅናቄ ሥራ 4 ሺህ 458 ሴቶች አዲስ የባንክ ሂሳብ ደብተር ከፍተው አንድ ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ቆጥበዋል። በአንጻሩ ደግሞ ተደራጅተው የተለያዩ የሥራ ዕድሎችን ፈጥረው ለሚሠሩ ሴቶች ከስኬት ባንክ ጋር በመተባበር ከ800 ሺህ ብር በላይ ብድር እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።
ወይዘሮ ዝናሽ፤ ማርች /March 8ን አስመልክቶ ለሴቶች ነፃ የማህፀን በርና የጡት ጫፍ ካንሰር ምርመራ እንዲሁም በስፋት ግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መሰጠቱን ገልጸው፤ ወሩን ሙሉ በተሠራው የንቅናቄ ሥራ ለ21 ሺህ 190 ሴቶች ግንዛቤ ተፈጥሯል። ግንዛቤ ከተፈጠረላቸው ውስጥ ደግሞ 3 ሺህ 903 ሴቶች በነፃ የማህፀን በርና የጡት ጫፍ ካንሰር ምርመራ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በዓሉን ታሳቢ በማድረግ የሴቶችን ማኅበራዊ ተሳትፎ ለማሳደግ በተሠራው ሥራ ደግሞ በአንድ ወር ውስጥ አራት ሚሊዮን ብር ገደማ የመዲናዋ ሴቶች የቦንድ ግዥ በመፈጸም ለሕዳሴ ግድቡ ድጋፍ ማድረጋቸውን ወይዘሮ ዝናሽ ጠቁመው፤ በተመሳሳይ በአንድ ሳምንት ውስጥ በተካሄደ የሴቶች የበጎ ፍቃድ ደም ልገሳ መርሐ ግብር ከአንድ ሺህ ዩኒት በላይ ደም ማሰባሰብ መቻሉን አመላክተዋል።
የሴቶችን አብሮነት፣ ሞራል የገነቡና ትውስታ የፈጠረ ልዩ ልዩ የሴቶች ተሳትፎ ጎልተው የታዩበት ስፖርታዊ ውድድሮች እንዲሁም ማኅበረሰቡ ከሴቶች ጎን እንዲቆም ግንዛቤ በስፋት ያስጨበጡ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሁነቶችና መርሐ ግብሮች ወሩን ሙሉ ማካሄዳቸውን ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሮ ዝናሽ ተናግረዋል።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 11 ቀን 2017 ዓ.ም