ለአራት ክልሎች የተሽከርካሪዎች ድጋፍ ተደረገ

ዲስ አበባ፡- የጤና ሚኒስቴር ለአራት ክልሎች ከ154 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ አምቡላንሶች፣ የመስክ ተሽከርካሪዎች እና ሞተርሳይክሎች ድጋፍ ማድረጉን ገለጸ፡፡

የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለፁት፤ ተሽከርካሪዎቹ የተገዙት ከአውሮፓ ኅብረት በተገኘው ድጋፍ ነው፡፡ በአውሮፓ ኅብረት የገንዘብ ድጋፍ የተገዙት ተሽከርካሪዎችም ተመጣጣኝ ልማት በሚሹ ክልሎች ማለትም በአፋር፣ ሶማሌ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ ክልሎች ተሰጥተዋል፡፡ የተገዙትን 16 አምቡላንሶች፣ 9 የመስክ ተሽከርካሪዎች እና 30 ሞተር ሳይክሎች ሲሆኑ እነዚህም በክልሎቹ በተመረጡ 16 ወረዳዎች አገልግሎት ላይ የሚውሉ ናቸው ብለዋል፡፡

ቀደም ሲል ከ94 ሚሊዮን ዶላር በላይ የተገዙ የሕክምና መሣሪያዎች ለአራቱም ተመጣጣኝ ልማት ለሚሹ ክልሎች በተመረጡ 16 የፕሮጀክቱ ወረዳዎች ማሰራጨታቸውን አውስተዋል፡፡

ሚኒስትሯ እንዳሉት፤ የጤና ሚኒስቴር የጤና ፍትሐዊነት ለማረጋገጥ ለተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፤ በጤናው ሴክተር በዋናነት መልክዓ-ምድራዊ ኢ-ፍትሐዊነት ለማጥበብ በተለይ ተመጣጣኝ ልማት በሚሹ ክልሎችና ዝቅተኛ አፈፃፀም ባላቸው ዞኖች የጤና ሥርዓት ግንባታ ላይ ያተኮረ ተግባራትን በማከናወን አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ የጤናው ሴክተር መልካም-ምድራዊ ኢ-ፍትሐዊነት በተጨማሪ ሌሎች ኢ-ፍትሐዊነት እይታዎችን በማካተት በሁሉም ክልሎች እየተተገበረ ይገኛል ብለዋል፡፡

ለክልሎች የምናስረክባቸው አምቡላንስ እና ሌሎች ተሽከርካሪዎች የጤና ተቋማትን አቅም በማሻሻል የእናቶች እና ሕፃናት ጤና አገልግሎት ተደራሽነትን በማሳደግ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል፡፡

ለዚህም የአውሮፓ ኅብረት ላደረገልን የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ እንዲሁም ለቀጣይ አጋርነት ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ያሉት ሚኒስትሯ፤ በቀጣይ ከዚህ ፕሮጀክት የተገኙ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመር የምናስፋፋ ሲሆን ለዚህም ስኬት የአውሮፓ ኅብረትና ሌሎች አጋር አካላት ትብብራችሁ እንዳይለየን ጥሪዬን አስተላልፋለሁ ሲሉ ተናግረዋል።

ሚኒስትሯ፤ ለክልል ጤና ቢሮ ኃላፊዎች ተሽከርካሪዎች ያስረከቡ ሲሆን፤ ተሽከርካሪዎቹ ለታለመላቸው ዓላማ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማስታወስ እወዳለሁ ሲሉ አሳስበዋል።

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You