ማህሔት አብዱል
ባለፉት 27 ዓመታት የፖለቲካ ሥርዓቱ ከገፋቸው ፖለቲከኞች አንዱ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ናቸው። በተለይም የሥርዓቱ መሪዎች በአገርና በሕዝብ ላይ ያደርሱት የነበረውን ግፍና በደል በይፋ በመቃወምና በማጋለጥ ረገድ ከፍተኛ ዋጋ ከፍለዋል።
የህወሓትን ጨቋኝ አገዛዝ ለማስወገድ አገር ጥሎ ከመሰደድ ጦር አንግቦ እስከመፋለም ደርሰዋል። ለሕዝባቸው ነፃ መውጣት ያደርጉት በነበረው የትግል እንቅስቃሴም በሽብርተኝነት ተፈርጀው ለዓመታት በእስር እንዲማቅቁ ተደርገዋል።
የለውጡ መምጣትን ተከትሎ ደግሞ በለውጡ መሪ በዶክተር አብይ ከፍተኛ ትግል ከእስር ተፈተዋል። አሁን ላይ ምንም እንኳን በዜግነት ምክንያት በፖለቲካው ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ ባይኖራቸውም የትግል ሕይወታቸውና ተሞክሮዎቻቸውን የሚዳስሱ መፅሐፎችን በመፃፍ ለአንባቢዎች አድርሰዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎንም የኢሳት ዋና ሥራአስኪያጅ በመሆን ተቋሙን በመምራት ላይ ይገኛሉ። አዲስ ዘመን ጋዜጣ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ አነጋግሯቸዋል። እንደሚከተለው ይቀርባል።
ባለፉት 27 ዓመታት የፖለቲካ ሥርዓቱ ከገፋቸው ፖለቲከኞች አንዱ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ናቸው። በተለይም የሥርዓቱ መሪዎች በአገርና በሕዝብ ላይ ያደርሱት የነበረውን ግፍና በደል በይፋ በመቃወምና በማጋለጥ ረገድ ከፍተኛ ዋጋ ከፍለዋል።
የህወሓትን ጨቋኝ አገዛዝ ለማስወገድ አገር ጥሎ ከመሰደድ ጦር አንግቦ እስከመፋለም ደርሰዋል። ለሕዝባቸው ነፃ መውጣት ያደርጉት በነበረው የትግል እንቅስቃሴም በሽብርተኝነት ተፈርጀው ለዓመታት በእስር እንዲማቅቁ ተደርገዋል።
የለውጡ መምጣትን ተከትሎ ደግሞ በለውጡ መሪ በዶክተር አብይ ከፍተኛ ትግል ከእስር ተፈተዋል። አሁን ላይ ምንም እንኳን በዜግነት ምክንያት በፖለቲካው ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ ባይኖራቸውም የትግል ሕይወታቸውና ተሞክሮዎቻቸውን የሚዳስሱ መፅሐፎችን በመፃፍ ለአንባቢዎች አድርሰዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎንም የኢሳት ዋና ሥራአስኪያጅ በመሆን ተቋሙን በመምራት ላይ ይገኛሉ። አዲስ ዘመን ጋዜጣ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ አነጋግሯቸዋል። እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- በትግራይ ክልል የተወሰደውን ሕግ የማስከበር እርምጃ እንዴት አዩት?
አቶ አንዳርጋቸው፡– የሕግ ማስከበር ዘመቻው አስቀድሞ አለመከናወኑ የለውጡ መንግሥት ሲወቀስበት የቆየ ጉዳይ ነው። የጁንታው ኃይል ሥልጣኑን በለቀቀ ማግስት በየቦታው ግጭቶችን በማነሳሳት አገሪቱ ወደ ነውጥ እንድትገባ ዋነኛውን ሚና ሲጫወት ነው የቆየው። እኔ ከሞትኩኝ ሰርዶ አይብቀል በሚል ብሂል ሕዝቡ እርስበርስ እንዲባላ ሲያደርግ ነው የኖረው።
ከለውጡ መሪዎች ጋር ያለውን የፖለቲካ ልዩነት በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ጥላቻና ቂም በማሰራጨት የእርስ በርስ መቆራቆዙን ሕዝባዊነት ለማላበስ ያልማሰው ጉድጓድ የለም። የለውጡ መንግሥት ግን በተቃራኒው በሰላማዊ መንገድ ልዩነቶች እንዲፈቱ በሆደሰፊነት ታግሷል። በተግባርም የሰላም አማራጮችን ሲከተል ነው የቆየው።
በተለያዩ ቦታዎች ላይ እየተፈጠሩ ለነበሩት ችግሮች ክስ ሲቀርብበት የነበረው መንግሥት ከሚገባው በላይ ሰላም፣ ፍቅርና ድርድርን በማስቀደም ዋናው የመንግሥት ሥራ የሆነውን ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን አልተወጣም በሚል ነው።
እናም እንዲህ ዓይነት ወቀሳ በመንግሥት ላይ ሲደርስበት በነበረበት ወቅት ነው እንግዲህ በአገሪቱ ውስጥ ሲካሄዱ ከነበሩ ጦርነቶች ሁሉ የላቀና እጅግ አስከፊ፤ አሰቃቂ የሆነ ተግባር በመከላከያ ሰራዊት ላይ ፈፀሙ።
ማዕከላዊ መንግሥት ምንም ምርጫ እንዳይኖረው አድርጎ ይህንን ሕገወጥ እርምጃ በሀገርና በሕዝብ ላይ ጉዳት ያደረሱትን ወንጀለኞች ለሕግ ማቅረብ የተገደደበት ሁኔታ ውስጥ ነው የገባው።
ስለዚህ ሕግ የማስከበሩ እርምጃ አማራጭ የሌለው ብቻ ሳይሆን ትክክለኛ ተግባር ነው። በእርግጥም ከዚህ ውጪ ሌላ ሊደረግ የሚችል ነገር አልነበረም። መንግሥት ሕጋዊ እርምጃውን ባይወስድ ኖሮ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን ያልተወጣ መንግሥት ይሆን ነበር።
የሕግ ማስከበሩ ዘመቻ በጣም ከፍተኛ ሆነ ውድመት ያስከትላል፤ ረጅም ጊዜ ይወስዳል። ሀገሪቱን ወደ ባሰ ምስቅልቅል ይወስዳታል የሚል ስጋት ነበር። በዋነኛነት የእኔን ስጋት ብዙ ሰዎች እንዲጋሩ ያደረገው በተከታታይ የወያኔ ባለሥልጣናት ጉልበታቸውን በመተማመን፤ በእጃቸው ያለውን የሰው ኃይልና ትጥቅ ማንም ሊገዳደር የማይችል ነው እያሉ በነዙት ወሬ ልክ መሆን አለመቻላቸው ነው።
በተጨባጭ እንደታየውም ያ ሁሉ ድንፋታና ፉከራ የራሳቸውንም አቅምም ሆነ የዘመኑን ሁኔታ ያላገናዘበ በመሆኑ መንግሥት በቀላሉ መቆጣጠር የቻለበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው። እናም በትግራይ ውስጥ ያሉትን ከተሞች በአጭር ጊዜ ውስጥ በቁጥጥሩ ያስገባበት ሁኔታ ነው የተከሰተው። ዋነኞቹ ወንጀለኞች የተያዙበትና የተደመሰሱበት ሁኔታ ውስጥ ነው የተገባው።
በነገራችን ላይ ጦርነትን ማሸነፍ ብቻ አይደለም፤ በታሪክ ውስጥ አስቸጋሪ ሆኖ የተገኘው። ብዙ ኃያላን መንግሥታት ከባድ የተባሉ ጦርነቶችን አሸንፈዋል። ነገር ግን ሰላምን ማሸነፍ ከሁሉም የላቀ ከባድ ፈተና ሆኖባቸው ተስተውለዋል።
አሁን በትግራይ ውስጥ ጦርነቱን በዋነኛነት መንግሥት ያሸነፈበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ነገር ግን በጣም አነስተኛ የሆኑ ጥቃቅን ቡድኖች በገጠር አካባቢ እንደሚንቀሳቀሱና በተለያዩ ቦታዎች ችግር እንደሚፈጥሩ እየተረዳን ነው ያለነው። ሁለተኛ በጣም በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝብ በግጭቱ የተነሳ እንዲሁም ከዚያ በፊትም ትግራይ ውስጥ በነበረው ከፍተኛ የሆነ ለከፋ ድህነትና ለምግብ እርዳታ የተጋለጠበት ሁኔታ ነው።
ከዚያም አልፎ የማዕከላዊ መንግሥቱ በመከላከያ ኃይሉ አማካይነት ሰላምን ለማስፈን እየሞከረ ያለው እንጂ ማህበረሰቡ ራሱ የራሱን ሰላም መቆጣጠር በሚችልበት ደረጃ ታችኛው ቀበሌ ድረስ የተደራጀበት ሁኔታ የለም።
ስለዚህ በዋነኛነት ሰላም ማስከበር የምትችይው ከውጭ ባመጣሽው ኃይል አይደለም። ከውስጥ ያለው ሕዝብ የራሱ መኖሪያ በመሆኑ ሰላሙን ማስከበር ያለበት ራሱ ነው። ከፍተኛውን ኃላፊነት መውሰድ ያለበት ራሱ ሕዝቡ ነው። በተጨማሪም የክልሉ ሕዝብ ራሱን ማስተዳደር የራሱን ፀጥታ ማስከበር መቻል አለበት።
አዲስ ዘመን፡- የሕግ ማስከበር ሂደቱ በትግራይ ሕዝብ ላይ ያመጣው የሥነልቦና ጫና ምን ይመስላል?
አቶ አንዳርጋቸው፡– እውነቱን እንነጋገር ከተባለ የትግራይ ሕዝብ ከሕግ ማስከበር ዘመቻው በፊትም የተለያየ የሥነልቦና ጫናዎች ሲደርሱበት ነው የኖረው። ለረጅም ዘመን ወያኔዎች ራሳቸውን ብቻ ሳይሆን የትግራይንም ሕዝብ ትክክል ባልሆነ መንገድ የተለየ ሕዝብ እንደሆነ አድርጎ እንዲያስብ እና ከሌላው እንዲገለል አድርገውት ነው ያኖሩት።
በቅርቡ እንኳን ጦርነት ለትግራይ ሕዝብ ባህላዊ ጨዋታው ነው ወደሚል እብሪት የገቡበት ሁኔታ ነበር። ያ ማንንም ማንበርከክ እንችላለን የሚለው ትርክታቸው ሦስት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ያ ሁሉ ፉከራቸው አፈር በበላበት ሁኔታ ነው የተዋረዱት።
ይህንን ሁኔታ የትግራይ ሕዝብ በሚመለከትበት ጊዜ ሌላው ይቅርና ሽንፈት የሚያመጣው የሥነልቦና ጉዳት አለ። ምክንያቱም ለዓመታት ራሱን ህወሓት ከፈጠረው የሃሰት ሥነልቦና ጋር በዚያ መንገድ አገናኝቶ የነበረ በመሆኑ ማህበረሰቡ ከፍተኛ የሆነ ኀዘን ውስጥ መግባቱ አይቀሬ ነው።
በተጨማሪም ብሔርተኝነቱ ዘልቆ እንዲገባ የተሰራበት በመሆኑና ከዚህ ጋር የተቆራኘ ነገር ስላለ የሚፈጥረው የሽንፈትና የውድቀት ስሜት ቀላል አይደለም። ይህንን ጉዳይ ዝም ብለን አድበስብሰን ልናልፈው የማይገባ ጉዳይ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ስንመለከተው እነዚህ ሰዎች 27 ዓመታት በሙሉ በበላይነት ኢትዮጵያን በገዙበትና ባስተዳደሩበት ወቅት ማንኛውንም ነገር ያደረጉት ለራሳቸው ጥቅም እንደሆነ እንዲያስቡ አድርገዋቸዋል።
እውነታው ግን በመላው አገሪቱ የዘረፉት ሀብት በጣም ጥቂት የሆኑ የራሳቸውን የቅርብ ሰዎች ብቻ ሲጠቅሙ እንደነበር አሁን ያለው ሁኔታ በገሃድ አሳይቷል። ሲፈፅሙ የነበረውም ወንጀል ከትግራይ ሕዝብ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳልነበረው ታይቷል።
እንዲያውም የትግራይ ሕዝብ በሌላ ክልል ላይ የሚያገኘውን ነፃነት የነፈጉት እንደሆነ ሕዝቡ በደንብ ጠንቅቆ የሚያውቀው ነው። በዚህ መንገድ ደግሞ ከመጣሽ ይህ ቡድን የሚመራበት መንገድ እጅግ ኋላቀር እንደሆነ ነው።
በሚሊዮን የሚቆጠር ሰው በምግብ እርዳታ በተሰለፈበት ሁኔታ ትግራይን አልምተናል የሚለው የወያኔ ትርክት የትግራይ ሕዝብ እንደማይቀበለው የታወቀ ነው። ሌላ ቦታ የሚያየውን ነፃነት እሱ እንዳላገኘ ሕዝቡ ጠንቅቆ የሚያውቀው ነገር ነው።
ስለዚህ እነዚህ ሰዎች መወገዳቸውና የነፃነት አየር በመተንፈሱ፣ ከሌብነትና ከዘረፋ ነፃ የሆነ አስተዳደር ሊመሰረት የሚችልበት ምህዳር መፈጠሩ፣ ሕዝቡ በልማት ውስጥ ተሳትፎ የዝንት ዓለም የምግብ ተመፅዋች ከሚሆንበት ነፃ የሚወጣበትን፣ እንደሌላው ክልል ሁሉ የትግራይም ወጣት ሥራ የሚያገኝበትን ተስፋ ይፈጥራል።
ከዚህም ባሻገር ቀጥተኛ የሆነ የሰላም መረጋጋት ማጣትና ከዚያ ጋር ተያይዞ የምግብ እርዳታ እንኳን የማይደርስበት ሁኔታ የሚያስከትለው ረሃብ በራሱ በሕዝቡ ላይ የሚፈጥረው ሥነልቦናዊ ጫና መኖሩ አይቀርም።
ወላጆች ለራቸውም ሆነ የልጆቻቸው ሕይወት ቀጣይነት ስጋት ውስጥ የሚጨምራቸው ሌላ የሥነ ልቦነ ቀውስ አለ። እንግዲህ የሥነልቦና ቀውሱ በተለያየ መልኩ የሚመጣ ነው። ዋናው ነገር የትኛው የተሻለ ነገር አምጥቶልናል የሚለው ነው።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ እንዳነሱት ቁጥሩ ቀላል የማይባለው ሕዝብ በክልሉ ረሃብ አደጋ ተጋልጧል። ሕዝቡ ከዚህ ቀደም በሴፊቲኔት ሲረዳ የነበረ ሕዝብ እንደመሆኑ አሁን የደረሰው ጉዳት እንዴት ይገለፃል?
አቶ አንዳርጋቸው፡– በመጀመሪያ ደረጃ መታወቅ ያለበት ከሕግ ማስከበር ዘመቻ በፊትም ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆን የክልሉ ሕዝብ በሴፊቲኔት ሲረዳ የነበረው። በቀጥተኛ እርዳታ የሚኖረው ሕዝብ ቁጥርም ቀላል አልነበረም። ይሄ ከጦርነቱ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። በእርግጥ በዚህ ደረጃ ከ27 ዓመታት የልማት ዘፈንና ፉከራ በኋላ የትግራይ ሕዝብ በችግር ላይ ወድቆ መገኘቱ አሳፋሪ ነው። ተጠያቂም የሚሆነው ያንን ክልል ሲመራ ነበረው የወያኔ ድርጅት ነው።
በሁለተኛ ደረጃ ከማዕከላዊ መንግሥት ጋር መግባባት ተስኖትና ሕገወጥ በሆነ መንገድ ወደ ጭፍጨፋ ገብቶ፤ መንግሥት ምላሹን እንዲሰጥ በማድረግ አርሶአደሮች የዘሩትን እህል ባልሰበሰቡበት፣ የከመሩትን እህል እንኳን በጎተራ ባላስገቡበት ሰዓት ላይ ጊዜውና ወቅቱን ከግንዛቤ ውስጥ ባለማስገባቱና ሕዝብን አስቀድሞ ባለመሳብ እልህ ውስጥ በመግባት የነበረውን ሁኔታ አባብሶታል።
የትግራይ ሕዝብ በምግብ እህል እንኳን ራሱን ባልቻለበት ሁኔታ ሌላ የምግብ እርዳታ ተቀባይ እንዲሆን ያደረገ ሁኔታ የፈጠረው ወያኔ ነው። ስለዚህ እነዚህ ነገሮች በደንብ መጤን አለባቸው ብዬ አምናለሁ። ሕዝቡም በዋነኛነት ረሃቡ ጦርነቱ ያመጣው ሳይሆን ከዚያም በፊት የነበረና ይህንን ግጭት ሆን ብሎ በመቀስቀስ ወያኔ ያመጣው መሆኑን መገንዘብ ይገባዋል።
በመንግሥት በኩል ማድረግ ይቻል የነበረው እነዚህ ነገሮች ተደራርበው ሕዝቡን ያከበዱትን ችግር ግምት ውስጥ አስገብቶ በተቻለው መጠን በተቻለው ፍጥነት ሕዝብ አደጋ ላይ በረሃብ እንዳይወድቅ ማድረግ ነው። በተጨማሪም ሕዝቡ በመድኃኒት እጥረት ችግር ላይ እንዳይወድቅ አስፈላጊውን ነገር በፍጥነት ማቅረብ ይጠበቅበታል። ለዚያ ሕዝብ ለመድረስ መንግሥት የተቻለውን ያህል እያደረገ ነው።
አሁንም በተበጣጠሰ መልኩ በየጉሮኖውና በየጥሻው የተደበቁ የጁንታው ርዝራዦች የመንግሥት ጥረት በተሟላ መንገድ እንዳይሄድ እያደረጉ ናቸው። ምግብና መድኃኒት የጫነውን ተሽከርካሪ ሞት አፋፍ ላይ ለደረሰ ለገዛ ወገናቸው እንዳይደርስ ለማድረግ የሽብር ወሬ እየነዙ ነው። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ አስቀድመንም ያለፍንበት በመሆኑ መንግሥት ይህንን ሁኔታ እልህ አስጨራሽ እንዲሆን ተጋፍጦ መስራት ያለበትን ነገር ከመስራት ምንም አማራጭ የለውም።
አዲስ ዘመን፡- የትግራይ በዚህ ደረጃ ችግር ውስጥ ሆኖ ሳለ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የዲያስፖራ አባላት ሕዝባቸውን ከመታደግ ይልቅ መንግሥትን የመቃወሙን ሁኔታ ሥራዬ ብለው መያያዛቸው ምንን ያመላክታል ይላሉ?
አቶ አንዳርጋቸው፡- በውጭ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ባገኙት መገናኛ ብዙኃን ተጠቅመው የሚፅፉ ከ15 ያልበለጡ ሰዎች እንደሆነ ነው እኔ የማውቀው። እነዚህ ሰዎች ሁልጊዜ በየትኛውም ድርጅትና ሕዝብ ዓይን ቦታ የሚሰጣቸው አይደሉም። ከዚህ በመነሳት ዲያስፖራው በሙሉ እንዲህ ዓይነት አሳፋሪ ተግባር ይፈፅማል ለማለት አልደፍርም። ተደማጭነት አላቸውም ብዬ አላምንም።
በዚህ ሰዓት ላይ እነሱ የሚፈልጉት ነገር ግልፅ ነው። እነሱ የሚፈልጉት ነገር ለትግራይ ሕዝብ ጭራሹኑ የመድኃኒትና የምግብ እርዳታ በአስቸኳይ ደርሶ ከችግር መታደግ ሳይሆን የትግራይ ሕዝብ በሚሊዮኖች የሚያልቅበት ሁኔታ እንዲፈጠር ነው።
ይህም የኢትዮጵያ መንግሥት ሕዝባችንን አስጨረሰ የሚል የፖለቲካ ፕሮፖጋንዳ ለመንዛት ነው። ይህ አካሄዳቸው የተለመደና በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ያለ የኢትዮጵያ ሊሂቃን የትግል አቅጣጫ ነው። የዚህ ዓይነት አመለካከት በእኛ አገር ስር ስለሰደደ ነው። የሰው ልጅ በሰውነቱ የሁሉም ነገር ግብ ሳይሆን የፖለቲካ ሊሂቃኑ የፖለቲካ ግብ ማዳረሻ መሣሪያ ተደርጎ ነው ሲጠቀሙበት የኖሩት።
የሰው ሕይወትን ያህል ነገር ለፖለቲከኛው ወደ ግቡ መድረሻ ቁማር ሆኖ ነው የቆየው። እናም በዚህ መልኩ የተቃኘ የፖለቲካ ባህል ነው ያለን። የሰው ልጅ ሕይወት ክቡርነት የማይታወቅበት ሁኔታ ነው ያለው። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችም የአንቺን ፍላጎትና ግብ ስትዪ እንዲያልቁ ማድረግና ያንን የሚያበረታቱ ነገሮች መስራታቸው ብዙም አይገርመኝም። በውጭ ብቻ ሳይሆን በአገር ውስጥም በእንዲህ ዓይነት አመለካከት የተቃኙ በርካታ የፖለቲካ ሊሂቃን ያሉበት አገር ነው።
አዲስ ዘመን፡- እንደ አጠቃላይ ክልሉን ወደ ነበረበት ሰላም ለመመለስና ሕዝቡን ከመታደግ አኳያ በመንግሥት በኩል ሊሰራ ይጋባል የሚሉት ነገር ካለ?
አቶ አንዳርጋቸው፡- በእኔ በኩል መናገር የምፈልገው አንዱ ጉዳይ በተለያየ ምንጮች የሚመጡ ዜናዎችን መንግሥት ማጥራት አለበት ብዬ አምናለሁ። ከፊሉ መንግሥት የተሻለውን እያደረገ ነው ሲል፤ ሌላው ደግሞ ምንም እየተደረገ አይደለም ችግሮች እየተባባሱ ነው ይላል።
መያዣ መጨበጫ የሌላቸው መረጃዎች እየወጡ ነው። ሁሉም ደግሞ ለራሱ ፍላጎት መሳኪያ ሲል እያጋነነ የሚያቀርባቸው ነገሮች እንዳሉ አውቃለሁ። በእኔ በኩል በቦታው ስለሌለሁ ትክክለኛውን መናገር አልችልም።
ነገር ግን መደረግ ያለበትን ትክክለኛ ነገር በማድረግ ያንንም ጩኸትና የተጋነነ ወሬ እንዲሁም በሃሰት ላይ የተመሰረተ ክስ ከቁብ ሳይቆጥር ሙሉ ትኩረቱን የትግራይ ሕዝብ አሁን ካለበት ችግር ለማውጣት መስራት አለበት ብዬ አምናለሁ። ለዚህም ጉልበትና አቅም ያለው መንግሥት ነው። የሚሰራው ነገር ከአቅሙ በላይ ሆኖ ከመጣ የሕዝቡን ድጋፍ መጠየቅ ይገባዋል።
ምክንያቱም እኔ ሊሂቁን ኢትዮጵያዊ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብን ነው ሁሌም የማምነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ድሃ እንጂ ደደብ አይደለም የሚል አምነት አለኝ። ለዚህ ሕዝብ ጥሪ ቢያደርግ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሚበላው ቆርሶ፤ ከልጆቹ አፍ ቀምቶ የሚያጎርስ በመሆኑ የትግራይን ሕዝብ ለመታደግ ችግር የለበትም። ዋናው ነገር መንግሥት ማድረግ ያለበት በንፁህ ህሊና ማድረግ ብቻ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ በህወሓት ከፍተኛ በደል እንደደረሰበት አንድ ኢትዮጵያዊ የጁንታው መወገድ ያሳደረብዎትን ስሜት ይግለፁልን?
አቶ አንዳርጋቸው፡- እውነቱን ለመናገር እኔ አንድም ቀን ቢሆን በዚህ መልኩ ሰዎች እንዲጎዱ ፈልጌ አላውቅም። ፖለቲካ ውስጥ በነበርኩባቸው ዘመናት ሁሉ በተለያዩ ሥርዓቶች የተለያዩ በደሎች ደርሶብኛል። ነገር ግን ሥርዓቱ እንጂ ግለሰቦች በደል አድርሰውብኛል ብዬ አላምንም።
የነበረው የፖለቲካ ሥርዓት ይህንን ሕዝብና አገር በከፍተኛ ደረጃ የጎዳ በመሆኑ ይሄ ኃይል ከፖለቲካ መድረኩ መገለሉ በራሱ ትልቅ አገራዊ ፋይዳ አለው ብዬ አስባለሁ። በግለሰብ ደረጃ ስትመነዝሪው እኔ የታሰሩትንም ሆነ በየጉድጓዱ ሞተው የተገኙ ሰዎችን ምስል ባየሁበት ሰዓት እነዚህ ሰዎች የእጃቸውን አገኙ የሚል ደስታ አልተሰማኝም። ይልቁንም በመሳቀቅና የሚዘገንን ስሜት ነው የተሰማኝ።
እኔ በበኩሌ እንዲህ ባለ ሁኔታ አገሪቱን ባይጨምሩና እኛም የእነሱን አሰቃቂ ምስል ባናይ ነበር ምርጫዬ የሚሆነው። ስለዚህ ለእኔ በግለሰብ ደረጃ የሥነልቦና ቀውስ ነው የሚያመጣው። ለሀገርና ለሕዝብ ግን ሥርዓታቸው ከፖለቲካው መነቀሉ ትልቅ ትርጉም አለው ብዬ ነው የማስበው።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ አንዳርጋቸው፡- እኔም በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ሃሳቤን እንድሰጥ ስላደረጋችሁን አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን የካቲት 09/2013