በኢትዮጵያ የህብረት ሥራ ማህበራት የህብረተሰቡ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች በመፍታት ጉልህ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ ማህበራቱ እየተስፋፉ ያሉበት ሁኔታ፤ የአባሎቻቸው መጠን ፣የሚያንቀሳቅሱት ካፒታልና የሚሰጡት አገልግሎት እየጨመረ መምጣትም ይህን ያመለክታል፡፡ ይሁንና ማህበራቱ የማህበረሰቡንና የአገሪቱን ችግርና ድህነት ከመፍታት አንጻር የሚጠበቅባቸውን በማከናወን በኩል ገና ጅምር ላይ ናቸው ሲሉ የዘርፉ እና የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡
በዘርፉ ለረጅም ጊዜ የሠሩትና የህብረት ሥራ ማህበራት አባት በሚል ቅጽል ስም የሚታወቁት አቶ ኃይሌ ገብሬ ‹‹ማህበራቱ የችግር መፍቻ መሳሪያ ናቸው ይባሉ እንጂ ገና ጅምር ላይ ናቸው፡፡ ጉዟቸውም የእንፉቅቅ ነው፡፡ ሊፈቱ የሚችሉትን ያህል ችግርና ድህነት አልፈቱም›› ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
ሀገሪቱ በአነስተኛ እርሻ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ እንደምትመራ የሚናገሩት አቶ ሀይሌ፣ ‹‹ይህን ወደተሻለ ኢኮኖሚና ወደ ኮሜርሻላይዝድ ለማሸጋገር በሚችል ደረጃ ተሠርቷል ወይ ቢባል ምላሹ ገና ነው ቢባል ይቀላል›› ይላሉ፡፡
እንደ እሳቸው ገለጻ፤በቁጠባ ደረጃ መልካም የሚባል ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡ ይህ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ ቁጠባ አሁን ወደ 15 ቢሊዮን ብር መድረሱ ይነገራል፡፡ 15 ቢሊዮን ብር ወደ ኢንቨስትመንት ገብቶ ማንቀሳቀሱ ቀላል ለውጥ አይደለም፡፡
‹‹አገሪቱ ካለባት ድህነት አኳያ አሁንም ብዙ ሥራ ይቀራል›› የሚሉት አቶ ኃይሌ፣ድህነቱንም መቅኔ ውስጥ የገባ ሲሉ ይገልጹታል፡፡ ሀገሪቱን ከዚህ ድህነት ለመፈወስ አጥንትንና ስጋን አክሞ ቆዳ ላይ ውጤቱን ለማየት ከባድ ሥራ እንደሚጠይቀም ነው የሚያስገነዝቡት፡
‹‹እንዲያም ሆኖ አሁን ያለው እንቅስቃሴ አበረታች ነው፡፡ መሰረት እየተጣለ ነው፡፡ ከሌሎቹ አገራት አኳያ ሲታይ አሁንም ገና በጅምር ላይ ይገኛል›› በማለት ማህበራቱ ብዙ እንደሚቀራቸው ያመለክታሉ፡፡
አቶ ኃይሌ እንደተናገሩት፤ ማህበራቱ በተገቢው መንገድ ላለማደጋቸው አንዱ ምክንያት ኢኮኖሚው ሜካናይዜሽን በአግባቡ አለመጀመሩ ነው፡፡ በዚህ የተነሳም መሬቱ አንዴ ብቻ ምርት ሰጥቶ ለሰባትና ስምንት ወራት ባዶውን ይቀመጣል፡፡
አቶ ኃይሌ ኢኮኖሚውን ለማንቃት የህብረት ሥራ ማህበራተን ማጠናከር ዋና ጉዳይ ተደርጎ መወሰድ አለበት ይላሉ፡፡ መስኖን ብቻ በአግባቡ ማንቀሳቀስ ከተቻለ ብዙ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻልም ያመለክታሉ፡፡ በአሜሪካ ሚሲሲፒ ከጉድጓድ ውሃ ለማውጣት 500 ሜትር መቆፈርን እንደሚጠይቅ ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ውሃ ከአራት እስከ 12ሜትር ርቀት ላይ ተቆፍሮ መውጣት እየቻለ በመስኖ ላይ አለመሠራቱን በችግርነት ይጠቅሳሉ፡፡
አቶ ኃይሌ የአየርላንድ ዴይሬ ማህበረሰብ በዓመት የሚያንቀሳቅሱት ሀብት አስር ቢሊዮን ዩሮ መድረሱን በመጥቀስም የማህበራትን ሚና ያመለክታሉ፡፡ ማህበረሰቡ ለመላ አውሮፓ ወተት እንደሚያቀርብ፣ የመላ ገበሬዎቻቸውን ችግር እንደሚፈታ ያጠቅሳሉ፡፡
የህንድ ህብረት ሥራ ማህበራት ከአገሪቱ ዓመታዊ አጠቃላይ ምርት ወደ 40 በመቶውን እንደሚይዝ ጠቅሰው፤ ‹‹ህንድ ከድህነት የወጣችው በዚህም ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ሲታይ እኛ ጅምር ላይ ነን››› ይላሉ፡፡ ማህበራቱን በመጠቀም በእርሻ ሥራ፣በቁጠባ፣በወተት እርባታና በመሳሰሉት ላይ ቢሠራ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ንቁ ማድረግ እንደሚቻል ያስረዳሉ፡፡
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ሙሼ ሰሙ እንደሚሉት፤ ማህበራቱ ኢኮኖሚውን በማረጋጋት፣ የግብይት ስርዓቱን በማሳለጥ፤ በተጨማሪም ግብይቱን በማገናኘት በኩል ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ዋጋ እንዲረጋጋ ቀላል የማይባል ሚና ያበረክታሉ፡፡ በተለይ ዝቀተኛ ገቢ ላለው ማህበረሰብ በመድረስ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡ ገበያው በግለሰቦች ብቻ እንዳይዝ የበኩላቸውን ሚና ይጫወታሉ፡፡ በነጋዴው ማህበረሰብ ብቻ የአገሪቱ ሀብት ተይዞ እንደልቡ ነጋዴው ብቻ ዋጋ እየወሰነና እየተመነ እንዳይሸጥም ያደርጋሉ፡፡
አቶ ኃይሌ ፣ ህብረት ሥራ ማህበራቱ የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ለማድረግ መፍትሔ ያሉትንም ይጠቁማሉ፡፡ በዘርፉ ላሉ ባለሙያዎች ስልጠና መስጠት ፣የዘርፉ አመራሮችም ቁርጠኞች መሆን ፣ልብን የሚገዛ የጠበቀ ህግ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ መፍትሔዎች መሆናቸውን ያመለክታሉ፡፡
‹‹ማህበራቱ የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው መፍታት የሚያስችል ደረጃ ላይ መድረስ አልቻሉም፡፡ እስከ አሁንም በሞግዚት እጅ ነው ያሉት›› ያሉት አቶ ኃይሌ፣ከሞግዚትነት በማውጣት በራሳቸው እንዲቆሙ ለማድረግ መሥራት ያስፈልጋል›› ይላሉ፡፡
እንደ አቶ ኃይሌ ማብራሪያ፤መንግሥትም የሞግዚትነቱን የጊዜ ገደብ መወሰን ይኖርበታል፡፡ አሁንም ድረስ በ30 እና በ40 ዓመቱ እናት ጀርባ ላይ መሆን አያስኬድም፡፡ ስለዚህ ራሳቸውን እንዲችሉ መለቀቅ ይኖርባቸዋል፡፡ እሹሩሩው ከበዛ በሁለት እግራቸው መቆም አይችሉም፤ አይሄዱም፡፡ ስለዚህ መንግሥት የቁጥጥር ሥራውን አጠንከሮ ቢቀጥል እንዲሁም ባለሙያቹም ገብተው እንዲንቀሳቀሱ ቢያደርግ አገሪቱን በብዙ መለወጥ ይችላሉ፡፡
ማህበራቱ ጠንካራ እንዲሆኑ ካስፈለገ የሜካናይዜሽን ስትራቴጂ ተግባራዊ እንዲሆን የሚጠይቁት አቶ ኃይሌ፣‹‹እኛ እንደሌላው አገር መሬት፣ አፈር፣ ውሃ፣ ድንጋይ አለን፡፡ ሌሎችም አፈርን ነው ወደ ብረት የለወጡት፡፡ ዋናው ነገር አስተሳሰብና በጉዳዩ ላይ መሥራት ተገቢ ነው›› ይላሉ፡፡
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ሙሼም የማህበራቱ ችግር መነሻ ሀብት ማጣት መሆኑን በመጥቀስ፣ መነሻቸው ሁሌም ዝቅተኛ በመሆኑ የመቋቋማቸው ጉዳይ ችግር ሲገጥመው እንደሚታይ ይገልጻሉ፡፡
‹‹ማህበራቱ የሚቋቋሙት ማህበረሰባዊ አገልግሎት ለመስጠት እንጂ ለትርፍ አይደለም፤ የመንግሥትንም ሸክም የሚቀንሱ ናቸው›› ሲሉ ጠቅሰው፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ንቁ ለማድረግ ባለው ነፃ የገበያ ስርዓት በመጠቀም ተወዳድረው ማሸነፍ እንደሚኖርባቸው ያመለክታሉ፡፡ ‹‹በመጀመሪያ ግን እርሾ ሊሆናቸው የሚችለው ነገር መንግሥት አመቻችቶ ሊሰጣቸው ይገባል›› ይላሉ፡፡
እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ማህበራቱ መነሻ የማይኖራቸው ከሆነ በገበያው ላይ ለመቆየት የሚያስችል አቅም አይኖራቸውም፡፡ በመጨረሻም የመፍረስ ዕጣ ፈንታ ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ ተጠናክረው መቀጠል እንዲችሉ ከባንክ ጋር መተሳሰር እንደሚኖርባቸው፣ የብድር ስርዓትም ሊኖራቸው እንደሚገባ ያመለክታሉ፡፡ በሰለጠነ የሰው ኃይል መመራት፣ ለዚህም በስልጠና መስጠትና ማብቃት በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ፡፡
ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዲችሉ በመጀመሪያ ደረጃ ለማህበራቱ ባለቤት እንደሚያስፈልጋቸው በመጥቀስ የአቶ ኃይሌን ሃሳብ ያጠናክራሉ፡፡ መንግሥት ሥራቸውን በአግባቡ እንዲመሩ ሊያግዛቸው እንደሚችል ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ሞግዚታቸው መሆን አይጠበቅብትም ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡
አቶ ሙሼ ማህበራቱ በደንብና መመሪያ መሰረት ክትትል እየተደረገ የማይሠራ ከሆነ የታለመላቸውን ያህል ውጤት ማስመዘገብ እንደማይችሉም ያመለክታሉ፡፡
ከፌዴራል ህብረት ሥራ ማህበራት ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤በኢትዮጵያ የህብረት ሥራ ማህበራት በዕድገት ላይ ይገኛሉ፡፡ባለፉት 6 ዓመታት ውስጥ የአባላት ዕድገት ከ6ነጥብ6 ሚሊዮን ወደ 20 ሚሊዮን ከፍ ያለ ሲሆን፣በዓመት በአማካይ 2 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች አባል እየሆኑ ናቸው፡፡ካፒታላቸውም በ2001 ዓ.ም ከነበረበት 1ነጥብ5 ቢሊዮን ብር በ2010 ዓ.ም 22ነጥብ8 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡
ማዳበሪያ የማሰራጨት ድርሻቸው 98 ከመቶ ደርሷል፣ምርጥ ዘርና ኬሚካሎችን በስፋት ያቀርባሉ፣ በፍጆታና በኢንዱስትሪ ምርቶች አቅርቦት ይሠራሉ፡፡ ባለፉት 4ዓመታት ብቻ ማህበራቱ ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት ፈጽሟል፡፡
የህብረት ሥራ ማህበራት የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሮች የሚፈቱ እንዲሁም በሀገር ኢኮኖሚ ውስጥ ጉልህ ስፍራ እንዳላቸው ይታመናል፡፡ማህበራቱ እስከ አሁን በተግዳሮቶች ውስጥ ሆነውም ለውጦች አስመዝገበዋል፡፡ተግዳሮቶቻቸውን ከአባላትና ከመንግሥት ጋር ሆኖ በመፍታት የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ማድረግ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 30/2011
አስቴር ኤልያስ