መንግሥት የተለያዩ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ እንደ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች፣ የባቡር መስመር ዝርጋታዎች፣ የመንገድ ግንባታዎችና ለሌሎች የልማት ስራዎች በብዙ ቢሊዬን የሚቆጠር ገንዘብ ይመድባል።
ሆኖም የመንግስት ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው መርሀ ግብር፣ የጥራት ደረጃ እና በጀት ተከናውነው በኢኮኖሚ ውስጥ ሊያመጡ የሚችሉት ውጤት በሚጠበቀው ደረጃ መሆንን በተመለከተ ብዙ ጊዜ ጥያቄ ይነሳል።
በ2013 በጀት ዓመትም በፌዴራል ደረጃ ለሚገነቡ መንገዶች ከ56 ቢሊዮን ብር በላይ የተመደበ ሲሆን፣ በዓመቱ ውስጥ 117 የመንገድ ፕሮጀክቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ። ባለፉት ስድስት ወራት የተፈረሙት 21 የመንገድ ፕሮጀክቶች በጥቅል ሲታዩ ከ43.3 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ዋጋ የሚገነቡ ናቸው።
ከተፈረሙት 21 የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ በ14 የአገር ውስጥ የሥራ ተቋራጭ ድርጅቶች የሚገነቡ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ሰባቱ ደግሞ በውጭ የሥራ ተቋራጭ ድርጅቶች የሚገነቡ እንደሆኑም ታውቋል።
ከአሰራር አንፃር የሚታዩ የተጠያቂነት እና የግልፅነት ክፍተቶችን ለመፍታት ባለፈው ዓመት መገባደጃ ላይ መንግስት የፕሮጀክቶች አስተዳደርና አመራር ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል።
ሊያጋጥሙ ይችላሉ ተብለው ከሚጠበቁ ተግዳሮቶች በጥልቀት ለመለየትም በፌደራል መንግስት የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ተከታታይ ጥናት እንደሚከናወንም ይታሰባል። በተለይ ከፕሮጀክት ጥናት፣ አመራረጥ እና ውሳኔ አሰጣጥ እንዲሁም በትግበራ ላይ የሚታዩ የፕሮጀክት ኮንትራት አስተዳደር፣ አፈፃፀም ክትትል እና የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን በውጤታማነት ማስተዳደር ዙሪያ ሰፊ ጥናት ማድረግ አስፈላጊ ነው።
ከዚህ ቀደም እንደሚታወቀውና ብዙ ጊዜ እንደሚስተዋለው በርካታ የመንግስት ፕሮጀክቶች ላይ የመሰረት ድንጋይ ይጣላል እንጂ ግንባታቸው ተጠናቆ ለምረቃ ሲበቁ አይታይም ነበር። ነገር ግን ባለፉት ሶስት ተከታታይ የለውጥ ዓመታት ውስጥ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች አፈፃፀማቸው ሲታይ በርካታዎቹ ቀድመው ሲጠናቀቁ፣ የተወሰኑት ዘግየት የማለት
ሂደት ያሳያሉ እንጂ ሙሉ በሙሉ የቆሙ ወይም ስራቸው የተጓተቱበት ሁኔታ አይታይም። ለዚህም እንደምክንያት የሚቀርበው በፕሮጀክት ዝግጅት እና ትግበራ ላይ የታዩ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ መከናወን ያለባቸውን ጉዳዮች መለየት በመቻሉ ነው።
በተጨማሪም የፕሮጀክቶቹ የመሰረት ድንጋይ የሚቀመጠው ግንባታቸው ከሃያ በመቶ በላይ ከደረሰ በኋላ እየተደረገ በመሆኑ በፕሮጀክቶቹ አፈፃፀም ስኬት ጥሩ መሰረት ሆኗል።
ነገር ግን በተቃራኒው እንደ መኖሪያ ቤት ግንባታ ያሉ ጥቂት ፕሮጀክቶች ላይ ችግር መኖሩ በተለያዩ ጥናቶች የተገለፀ ከመሆኑ ባሻገር በተቀመጠላቸው ጊዜ ተጠናቀው በትክክል ለተጠቃሚ ሲተላለፉ አይታይም። በመሆኑም መንግስት በቀጣይ ጊዜያት የትኩረት አቅጣጫው ሊያደርጋቸው ይገባል።
ይህን ጉዳይ ሊከታተሉ ስልጣን እና ሃላፊነት የተሰጣቸው የፌደራል መንግስት ፕሮጀክቶች አስፈፃሚ አካላት፣ የፕላንና ልማት ኮሚሽን፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ የፌደራል ግዥ ኤጀንሲ፣ የፌደራል መንግስት የተቀናጀ የመሰረተ ልማት ማስተባበሪያ እና የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የመንግስት የልማት ፕሮጀክቶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ ብሎም የሀገሪቱን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ለማፋጠን የተናበበ አሰራር መዘርጋትና ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ምክንያቱም ፕሮጀክቶች እየተራዘሙ በሄዱ ቁጥር የወጣባቸውን ገንዘብ ለመመለስ የማይችሉበት ሁኔታ ይፈጠርና አዋጭነታቸው ጥያቄ ውስጥ ይገባል። ለኪሣራም ሊዳረጉ ይችላሉ። ቀጥሎም ፕሮጀክቱ የታለመለትን ግብ ሳይመታ ሊቋረጥ ይችላል፡፡
ይህ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ ሀገር የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያደናቅፍና ከደህነት የመውጣት ጥረቱን የሚያጓትት ይሆናል።
የኢኮኖሚያችን ህልውና ለማስጠበቅና ካለንበት የድህነት አረንቋ በቶሎ ለመውጣት የተያዙትን ፕሮጀክቶች በጊዜው በማጠናቀቅ ወደ ምርት ማስገባትና ምርቶቹን ወደ ውጭ በመሸጥ ከሚገኘው ገቢ ተጠቃሚ መሆን ይኖርብናል። ለዚህ የሚያበቃን ደግሞ ጠንካራ የፕሮጅክት አፈፃፀምና ክትትል ሲኖር መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።
በአሁኑ ወቅት እየተጀመሩና እየተሰሩ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶችን ለምርጫ ቅስቀሳ እንደታሰቡ አድርጎ የሚያዩና የሚያጣጥሉ ጨለምተኛ የፖለቲካ ቡድኖች እንዳሉ ይስተዋላል። ነገር ግን መንግስት ሊያመጣ ላሰበው የኢኮኖሚ ዕድገት ፈተና የሆኑ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ችግሮችን በመቋቋም ለሃገርና ለህዝብ የሚጠቅሙ ፕሮጀክቶችን ከመስራት ለአፍታም መዘናጋት የለበትም።
ለዚህ ደግሞ ግንባታው ያልተቋረጠው የህዳሴ ግድብ አንዱ ማሳያ ነው ማለት ይቻላል። በአጠቃላይ መንግስትም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የተጀመሩና አዳዲስ ፕሮጀክቶች ከድህነት በቶሎ ለመውጣት እና ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፉ እንደሚሆኑ ብቻ በማሰብ በአፈፃፀማቸው ላይ የጋራ የሆነ ክትትል ማድረግና ለስኬቱ መረባረብ ይጠበቅባቸዋል!
አዲስ ዘመን የካቲት 9/2013