ለውጥ ማህበረሰብን ከአንድ የታሪክ ምእራፍ ወደ ቀጣይ ምእራፍ ማሸጋገር የሚያስችል መነሳሳት ነው። ይህ መነሳሳት እንደየ ማህበረሰቡ ተጨባጭ እውነታ የሚከወን ይሆናል ። በየትኛውም ወቅትና ማህበረሰብ ውስጥ የሚከሰቱ ለውጦችና ከዚሁ የሚመነጩ አስተሳሰቦች ከተጨባጭ እውነታ አንጻር በአግባቡ ሊገሩ እንደሚገባም ብዙዎች ይመክራሉ ።
ይህንን ማድረግ ካልተቻለና ለዚህ የሚሆን ዝግጁነት ካልተፈጠረ ለውጥ እና የለውጥ አስተሳሰቦች የአደጋና ሁከት ከዛም በላይ የማህበረሰብ መፍረስ ምክንያት ሊሆን እንደሚችሉ የሀገራት ተሞክሮ ያሳያል።
በአግባቡ የተገሩ ለውጦችና የለውጥ አስተሳሰቦች ማህበረሰብን ከአንድ የታሪክ ምእራፍ ወደ ቀጣይ ምእራፍ የማሸጋገሪያ ተጨባጭ አቅም መሆናቸውም በተመሳሳይ ሁኔታ ታይቷል ።
በእኛ ሀገር የለውጥ ጉዳይ በአብዛኛው የሚታሰበው ይዟቸው ከመጣን እና ህዝባችንን እንደ ህዝብ ካስከፈለው ከፍ ያለ ዋጋና ጥሎት ካለፈው ትውልድ ተሻጋሪ ጠባሳ አንጻር ነው ። በየዘመኑ የነበረው የህዝባችን የለውጥ መሻት ከፍ ያለ ቢሆንም በተጨባጭ ይህንን መሻት ወደሚጨበጥ ተስፋ መለወጥ ባለመቻሉ ሕዝባችን ብዙ ትናንቶች ውስጥ እንዲኖር ተገዷል።
በአንድ በኩል በሀይልና በሴራ ላይ የተመሰረተው የቀደመው ዘመን የፖለቲካ አስተሳሰባችን በ21ኛው ክፍለዘመን ውስጥ ገብተን ባለንበት ሁኔታ ሳይቀር ገዥ አስተሳሰብ ሆነው መዝለቃቸው ። ሀይልና ሴራን ያቀናጀ የፖለቲካ አስተሳሰብ ዛሬም በፖለቲካው ዓለም አዋጭ ነው ብሎ የሚያምን ሀይል መኖሩ።
በሀገሪቱ ዘመናዊ የፓርቲ ፖለቲካ ማቆጥቆጥ ከጀመረበት 1960 ዓ.ም መግቢያ ጀምሮ ያለው በመደማመጥ ያልተገራው የፖለቲካ ባህላችን፣ ጥራዝ ነጠቅነት የበዛበት፣ የማህበረሰባችንን የትናንት ማንነት፣ የዛሬ ህይወት እና የነገውን ተሰፋ በተጨባጭ ማገናዘብ ያልቻለ የፖለቲካ ባህላችን ለስድስት አስርት የሚገራው ማጣቱ ።
በተለይም የለውጥ አቅምና ሀይል ነው ተብሎ የሚገመተው ቀለም የቆጠረው የማህበረሰብ ክፍል የህዝቡን የለውጥ ፈላጊነት መንፈስ ና መሻት በአግባቡ ተገንዝቦ ለውጡን ለመምራት የተሻለ ቁርጠኝነት ማሳየት አለመቻሉ ። ከዚህ ይልቅ የህዝቡን የለውጥ መሻት የመቆመሪያ ካርድ አድርጎ በመውሰድ የፖለቲካ ባህሉን በቁማር ስሌት እንዲገራ አድርጎታል ።
በዚህም የሀገሪቱ የፖለቲካ መድረክ እንደ ቁማር ቤት የግርግርና የሁከት ከዚህም አልሆ የመጠፋፋት መድረክ እንዲሆን ተደርጓል ። ሀገራዊ የፖለቲካ ባህሉ ገና ከጅምሩ መርህ አልባ የቤተመንግሥት/የስልጣን / ጉዞ ሆኗል ። በዚህም የህዝቡ የለውጥ መሻቶች አሻጋሪ የለውጥ ሀይል አጥተው ሲከስሙ ዓመታት ተቆጥረዋል።
ይህ ዘመን የማይሻገርና ትውልድ የማይዋጁ የፖለቲካ አስተሳሰብ ሀገርና ህዝብን የቱን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለ ለመረዳት ብዙ የሚያስቸግር አይደለም ። ያለንበትን ዘመንና የተሸከምነውን የፖለቲካ ባህል ማየት በራሱ በቂ መልስ የሚሆን ነው።ዛሬም የሚገራው ባጣው የሀይልና የሴራ የፖለቲካ ባህላችን ምክንያት ዜጎች እየሞቱ፣ እየተፈናቀሉ ነው ።
ሀገሪቱ በየዘመኑ ያጋጠሟትን ተግዳሮቶች አሸንፋ እንደ ሀገር ሀገር ሆና ለዚህ ትውልድ እንድትሸጋገር የቀደሙት አባቶቻችንና አያቶቻችን የከፈሉትን ከፍ ያለ መስዋዕትነትና በተጋድሏቸው ጽፈውት ያለፉት የደመቀ ታሪክ ሳይደበዝዝ እኛ ሀገር ካልገዛን ሀገር ትፍረስ የሚሉ ፖለቲከኞች በዚህ ዘመን ተፈጥረዋል ። ሀገርን የቁማርተኞች የመቆመሪያ እድል አድርገው የሚመለከቱም ተገኝተዋል።
እነዚህ ሀይሎች ሀገርን በዚህ ደረጃ አውርዶ ለማየት ያስቻላቸው ምንድነው ? የሚለውን በአግባቡ ማየት ፣ለዚህ ተገቢውን መልስ መስጠት ያስፈልጋል። ለዚህ መልስ ሳንሰጥ ወደ ሚቀጥለው የታሪክ ምእራፍ ለመሻገር የምናደርገው ጥረት ባልተገቡ መጎረባበጦች መስተጓጎሉ የማይቀር ነው ።
ለእነዚህ እና እነሱን መሰል ለሀገር ደንታ ለሌላቸው ሀይሎች ሀገር ማለት ምን ማለት ነው ? ለሀገር የሚሰጡት ትርጉም በአንድ ወቅት ሀገር ተወረረች ድንበር ተደፈረ ብለው ባወጁት የክተት አዋጅ ሕይወቱን የገበረው ተራ ዜጋ ለሀገር ከሰጠው ትርጉም በምን ይመሳሰላል ? በምንስ ይለያል ? ያ ተራ ዜጋ የከፈለው የህይወት መስዋእትነት ለነሱ ሀገር ካላት ትርጉም አንጻር ምን ማለት ነው ? በታሪክ ውስጥ ያለው ስፍራስ የት ነው? ከፖለቲካ ቁማር መቆመሪያ ካርዳቸውስ በምን ይለያል ?
ሕዝባችን ለሀገር ያለው ትርጉምና ፖለቲከኞቻችን ለሀገር ያላቸው ትርጉም ምንና ምንድን ነው ? ፖለቲከኞቻችን ፖለቲከኛ የመሆናቸው ትርጉም የሚመነጨው ከየት ነው ? የትስ ላይ ቆመው ነው ፖለቲከኛ የሚሆኑት ? በዚህ ጉዳይ እራሳችንን በአግባቡ ልንፈትሽ ይገባል ።
በህዝቡና በፖለቲከኛው መካከል ስለሀገር ያለው ትርጓሜ ወጥ ሊሆን ይገባል። ወጥነት ያለው ትርጓሜ ከሌላቸው የፖለቲከኞቻችን የፖለቲካ ጉዞ መቼም ቢሆን የህዝባችንን ለውጥ መሻት ወደሚጨበጥ ለውጥ ሊተረጉመው አይችልም ።ህዝባችንም ከተቸከለበት የታሪክ ምእራፍ እና ከዚህ ከሚመነጨው የታሪክ አዙሪት ሊታደገው አቅም አይኖረውም ።
አዲስ ዘመን የካቲት 8/2013