ለምለም መንግሥቱ
”የተሰጠኝ ህይወት ዛሬ በነፃነት፣
ሰው ተከፍሎበታል፣ከደምና ከአጥንት
ስንት ወገን ወደቀ በነፃነት ምድር ትናገር
አድዋ፣ትናገር አ-ገ-ሬ
እንዴት እንደቆምኩኝ ከፊታችሁ ዛሬ…
የጥቁር ድል አምባ አድዋ-አፍሪካ እምዬ ኢትዮጵያ…!!‘
እንዲህ ያለው ግጥም በዜማ ተዋህዶ በአርቲስት እጅጋየሁ ሽባባው አድዋ በሚለው የሙዚቃ አልበሟ የቀረበው የሙዚቃ ሥራ ከዛሬ 125 ዓመት በፊት ኢትዮጵያን በኃይል ወርሮ በቅኝ ለመግዛት ነፍጥ አንግቦ የመጣውን ወራሪ ፋሽስት ጣሊያንን በተባበረ ክንዳቸው፣በባዶ እግራቸው፣ጦርና ጋሻ ይዘው አድዋ ላይ ተዋግተው፣ደምና አጥንታቸውን ገብረው ጠላትን አሳፍረው ወደ መጣበት መልሰው ዳርድንበራቸውን አስከብረው ኢትዮጵያን ከነሙሉ ክብሯ ለዛሬው ትውልድ ላስረከቡ ውድ የኢትዮጵያ ጀግኖች አባቶችና እናቶች ማወደሻ የቀረበ ከመሆኑ በተጨማሪ የሙዚቃ ሥራው እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለሀገር ጉዳይ ሊሰጥ የሚገባውን ክብርና ዋጋ ከፍ እንዲል የማድረግ አቅም አለው።
የዓድዋ የድል በዓል ኢትዮጵያ በጀግንነቷ በዓለም እንድትታወቅ፣በነጭ የበላይነት ተጨቁነው ለመከራና እንግልት ተዳርገው ለነበሩ፣በአጠቃላይ ለመላው አፍሪካውያን ኩራት መሆኑ ይታወቃል።ይሁን እንጂ ይህ ከፍ ያለ ሥፍራ የተሰጠው የተጋድሎ መታሰቢያ ቀን አንዴ ሞቅ ፣ሌላ ጊዜ ደግሞ ደብዘዝ ባለሥነ- ሥርዓት ይታወሳል።
ባለፈው ዓመት 124ኛው የድል በዓል ግን እጅግ የተነቃቃ ስሜት የፈጠረና የደመቀ እንደነበር ይታወሳል።በተለይም አዲስ አበባ ከተማ ላይ በዓድዋ አደባባይና በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ከህፃን እስከ አዋቂ ነዋሪው በሀገር ባህል አልባሳት ተውቦና በዘመቻው ወቅት ጥቅም ላይ ውለው የነበሩ ቁሳቁሶች ይዘውና ሌሎችም ወቅቱን የሚያስታውሱ ትርኢት በማሳየት ጭምር ነበር በድምቀት ያከበሩት።
ድምቀቱ በ125ኛው መታሰቢያም ቀጣይ እንዲሆንና የበለጠ እንዲጠናከርም ከዋናው የመታሰቢያ በዓል ከየካቲት 23 ቀን 2013ዓ.ም በፊት ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ‹‹ቱባ ወግ››፣ የዓድዋ ድል ተምሳሌት›› ሚል መሪ ቃል ከየካቲት አንድ ቀን 2013ዓ.ም ጀምሮ ወሩ በሙሉ ስለአድዋ የድል በዓል እንዲዘከር የተለያየ መርሐግብር አዘጋጅቷል።ከመርሐግብሮቹ አንዱ የታሪክ ምሁራንና ህብረተሰቡን የሚወክሉ ተሳታፊዎች የተገኙበት የጋራ መድረክ ነው።
በመድረኩ ላይ ምሁራኑ ‹‹የአድዋ ድል ተምሳሌትነት በዘመናችን ትውልድ ምን መሆን አለበት›› በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ የየራሳቸውን ሀሳብ ሰጥተዋል።በአድዋ ላይ ስለተደረገው ተጋድሎና ዋና ዋና የተባሉትና ተያያዥ ጉዳዮች በጥቂቱ ዳሰዋል።
የመድረኩ ታዳሚም መልሶ ምሁራኑ ቀኑ በየዓመቱ ሲታሰብ ስለበዓሉ ገለጻ ከማድረግ ባለፈ ታሪኩን ፈትሾና መርምሮ ለትውልድ እንዲተላለፍ በመጽሐፍ ሰንዶ በማስቀመጥ ስለሰሩት ሥራ ጠይቋቸዋል።
በተለይም ስለበዓሉ ተንትኖ ለመናገር ቀርቶ የመታሰቢያ ቀኑ መቼ እንደሆነ እንኳን በአንዳንዶች አለመታወቁ የታሪክ ምሁራኑን ቁጭት ውስጥ ሊከት እንደሚገባም ታዳሚው ያነሳው ጉዳይ ነበር።
የመታሰቢያ ቀኑ አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ ቀዝቀዝ ባለ ሥነ-ሥርዓት መከናወኑ ተገቢነት እንደሌለውም አንስቷል። እኛም በሥፍራው ተገኝተን የምሁራኑን ገለጻና የመድረኩን መንፈስ እንዲህ ልናካፍላችሁ ወደናል።
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተርና የታሪክ ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ገለፃቸውን በምሥጋና ነው የጀመሩት፣እርሳቸው እንዳሉት ምሁራንም ታዳሚውም ዓመት ጠብቆ ስለአድዋ የድል በዓል ማንሳቱ በቂ አይደለም።አለፍ ማለት መቻል አለበት።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይህን ታሳቢ አድርጎ የካቲት ወር በሙሉ ስለአድዋ መታሰቢያ እንዲነሳና እንዲወሳ የተለያየ መርሐ ግብር በማዘጋጀቱና ትኩረት በመስጠቱ ነው ምስጋና ያቀረቡት።
አድዋ በታሪካችን ውስጥ እጅግ ጎልቶና ደምቆ በትውልድ ቅብብሎሽ ከሚታወሱና ከሚዘከሩ የታሪክ ኩነቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው እንደሆነ ያነሱት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣በተለይም በቅርቡ ወይንም በዘመናዊው የኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ኢትዮጵያን በአህጉርና በዓለም አቀፍ ያሳወቀ፣አሁን ደግሞ የኩራት ምንጭ የሆነ ተስተካካይ የሆነ የታሪክ ፍሰት ጨርሶ የማይገኝ መሆኑን ተናግረዋል።
‹‹አንድ ነገር መታሰብ አለበት›› በማለት ወደኋላ መለስ ብለው ታሪኩን ሲያስታውሱ ‹በዚያን የውጊያ ጊዜ የኢትዮጵያ ሰራዊት ከቀኑ አስራ አንድ ሰዓት ተኩል እስከ ምሽት ድረስ ጠላትን እያባረረ ነበር ሲመታ የነበረው።
በወቅቱም በብዛት ጠላት ወድቋል።ከየካቲት 23ቀን 1988ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ኀዘን ወይንም የለቅሶ ቀን ነበር።ድል መቀዳጀቱ ቢኖርም መስዋዕትነቱ ከፍተኛ በመሆኑ በወቅቱ በሆታና በዕልልታ ያልታጀበ ድል ነበር።
አፄ ምኒልክም እንደአሸናፊና እንደጀግና በወጉ ድል አድራጊነታቸው የተሰማቸው አዲስ አበባ ከተማ ሲገቡ ነበር።የወደቁት ጀግኖች ሙት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት ድረስ ሲዘከር ነበር።›› በማለት ነበር መሥዋዕትነቱ እስከምን ድረስ እንደነበር ያስረዱት።
ከሰባት ዓመት የሙት ዓመት ዝክር በኋላም የዓድዋ የድል በዓል እየተዘከረ ቢቆይም ትኩረት ያገኘው ግን ገና አሁን እንደሆነ እንዲሁም ከጥቂት ዓመታት በፊት በታሪክ ጉዳይ ላይ አለመግባባት አለመኖሩ የፈጠረው ተጽዕኖ ቀላል አለመሆኑን አስታውሰዋል።
ረዳት ፕሮፌሰሩ ከአድዋ ተምሳሌት የአሁኑ ትውልድ ምን መውሰድ ይችላል? ወደሚለው የዕለቱ ርዕሰ ጉዳይ ሲገቡም አራት አንኳር ነጥቦችን አንስተዋል። ካነሷቸው መካከል አንድነትና ህብረት ወሳኝ ነው የሚል ነው።
የአድዋ ድል የተገኘው በህብረትና አንድነት ስለነበር ነው። ያ አንድነትና ህብረት ምን አይነት ገጽታ ነበረው የሚለው ህዝብን የማስተባበር ችሎታ በዚህ በአንድነትና ህብረት ውስጥ ትልቅ ድርሻ ነበረው።
እርሳቸው እንዳሉት የአድዋ የክተት አዋጅ የተለየና በሶስት ክፍል ይታያል። ‹‹የሀገሬ ህዝብ ወይ እስካሁን በድዬህ ከሆነ ይቅር በለኝ››የሚለው አንዱ ሲሆን፣ሌላው ‹‹የመጣው ጠላት የህዝብ ጠላት ነው››፣ ‹‹ማርያምን አልምርህም›› የሚለው ሶስተኛው ቅጣት አዘል ያለው ቢሆንም ክተቱ ሲታወጅ ግን ሁሉንም በየደረጃው ተደራሽ ያደርጋል።
ወታደር የሆነና የሚችል እንዲዘምት።የማይችለው ደግሞ በሚችለው በፀሎትም እንዲረዳ የሚል መልዕክት መያዙ አንድነትን ፈጥሯል። ይሄ በዘመናት ውስጥ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሊገኝ የማይችል አዋጅ ነው።
ሁለተኛው የአንድነት መማሪያ የጣሊያኖቹ ተንኮልና ሴራ ነው። በ1886ዓ.ም አፄ ምኒልክ የውጫሌ ውልን እንደሌለ ቆጥሬዋለሁ፤ ሰርዤዋለሁ። ካወጁ በኋላ ሁለቱም ለጦርነት እየተዘጋጁ ነበር።በወቅቱ ግን ጣሊያኖቹ ኢትዮጵያን ማሸነፊያ መንገድ አንድ ዘዴ ይዘው ብቅ አሉ።በአፄ ምኒልክ ላይ ቁርሾ ያላቸውን መሳፍንት ወደ ራሳቸው መውሰድ ነበር ዘዴው።
እነራስ መንገሻ፣እነራስ ስብሐት፣ በአፋር በኩል ደግሞ መሐመድ አልፋሪ ለማማለል ሞክረዋል። ይሁን እንጂ ጥረታቸው አልተሳካላቸውም። በቅርብ ጊዜ በኢትዮጵያ የሚታየው ችግር ከራሱ ከኢትዮጵያ ወጥቶ መሳሪያነቱ ለሌላ ወገን የሚሆን መኖሩ ነው።ይህም ከመንግሥት ጋር በመያያዝና የባዕድ መሳሪያ ሆኖ በማገልገል ይገለጻል።
እንደ ኢትዮጵያ ሁልጊዜ ጠላት የበዛበት ሀገር አንድነትን አለማጠናከር ለሌላው መሳሪያ የመሆን ተጋላጭነት ይኖራል።ረዳት ፕሮፌሰሩ ‹‹አድዋ ላይ ያሸነፍነው ዘረኝነትን ነው። ቅኝ ግዛት ይባላል እንጂ አይደለም። ቅኝ ግዛት መነሻው የነጭን የበላይነት፣ የጥቁር የበታችነት ነው።
በመሆኑም ዓድዋ ላይ ጣሊያን ተሸነፈ ሲባል ድል የተመታው ዘረኝነት ነው።በማነው የተመታው ከተባለ ደግሞ ነፃነትን በሚፈልጉ፣ በሰው ልጅ እኩልነት ያመኑ፣ ለሀገራቸው ክብር መስዋዕትነት ለመክፈል በአንድነት የቆሙ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ናቸው ድል የተቀዳጁት›› ሲሉ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፣ ኢትዮጵያ ትልቅ የሞራል ልዕልና እንደሆነ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የማረከቻቸውን የጣሊያን ሰራዊት በክብር በመሸኘትም አቻ አልተገኘላትም።
ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፤ በአድዋ ዘመቻ ላይ ሴቶች የነበራቸውን ሚና አልዘነጉም። እንደእርሳቸው ማብራሪያ ከአድዋ ጦርነት በፊት ክፉ ቀን ነበር። አባሰንጋ በሽታ ብዙ ከብቶችን ጨረሰ።
ቀጥሎ ደግሞ አምበጣና ድርቅ ከፍተኛ ጉዳት አደረሰ።በዚህ ችግር ጊዜ ለአድዋ ዘማቾች ለስንቅ የሚሆን አልነበረም። በዚህ ወቅት በእያንዳንዱ ባላገርቤት ውስጥ በልቶና ጠጥቶ ስንቅ ይዞ እንዲሄድ ይደረግ ነበር።
በተጨማሪ ለሰራዊቱ ስንቅ ለማዘጋጀት በጥቂቱ 50 ሺ የሚሆኑ ሴቶች ከሰራዊቱ ጋር አብረው ዘምተዋል። አድዋ ላይ ሴት ወንዱ ብቻ ሳይሆን፣ ለሰራዊቱ ስንቅ ይዘው አብረው የሚጓዙ አጋሰሶች፣ ፈረሶችና በቅሎዎች ባለውለታ ናቸው።እንዲህ ባለው የተለያየ ነገር ነው ሀገርን ማስቀደም የሚቻለው።
ንጉሠ ነገሥት አጼ ኃይለሥላሴ በስደት ከቆዩበት በ1933ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ በሁለት ትላልቅ ነገሮች ላይ ነበር ትኩረት ያደረጉት። የመጀመሪያውና ቀዳሚው እርምጃ ያደረጉት ወታደራዊ ኃይል መገንባት ነበር።
ሀገሪቱ ያለችበት ቀጠናዊ የፖለቲካ ሁኔታ፣ በድንበር፣ከጎረቤት ጋር በሚነሳ ግጭትና በተለያዩ ምክንያቶች ወታደራዊ ሰራዊት መገንባት የህልውና ጉዳይ መሆኑ ታምኖበታል።
‹‹አድዋ ላይ በተካሄደው ጦርነት የሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራና ጦር የመምራት ብቃት ባይኖር ኖሮ ዘመናዊ መሳሪያ ታጥቆ የመጣን ጦር፤ጦርና ጋሻ ይዞ ድል ማድረግ አይቻልም ነበር›› በማለት የረዳት ፕሮፌሰር አበባውን ሃሳብ በማጠናከር ሌላው ገለጻ ያደርጉት የታሪክ ተመራማሪው ዶክተር አህመድ ሐሰን ናቸው።
እርሳቸው እንዳሉት በአድዋ ጦርነት የሰራዊቱን ሚና ለየት የሚያደርገው ጦርነቱን አቋርጦ የጠፋም የተማረከም አልነበረም። የአድዋ ጦርነት የአንድነትና የመቻቻል ተምሳሌት ነበረው።በጦርነቱ ሥራቸው ጎልቶ ባለመነሳቱ እንጂ የኃይማኖት አባቶችም ሚና ከፍተኛ ነበር።
ሰራዊቱ ውጊያውን በጾምና ፀሎትም ጭምር ማካሄድ እንዳለበት ኃይማኖታዊ ምክር በመስጠት፣ በውጊያ የወደቀውን ሠራዊት ገንዞ በመቅበር ተሳትፈዋል።በአጠቃላይ ድህነትን ይዞ ጦርነትን ያሸነፈ ህዝብ ነው።
ከአድዋ ጦርነት እንኳን ኢትዮጵያውያን አውሮጳዎቹም ለመማር ፈልገዋል የሚሉት ዶክተር አህመድ፤በባዶ እግሩ ሆኖ ዘመናዊ መሳሪያ ሳይታጠቅ ድል የማድረጉ ሚስጥር በዙሪክ ከተማ ላይ የኢትዮጵያ ሰራዊትን በተመለከተ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ መካሄዱን አስታውሰዋል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ በውጊያው ሽንፈትን ተከናንባ ወደ መጣችበት የተመለሰችው ጣሊያን ለኢትዮጵያውያኑ ጀግንነት ምስክር መሆኗ በቂ እንደሆነም ገልጸዋል።ዳግም ከ40 ዓመት ቆይታ በኋላ የበለጠ ቴክኖሎጂ ጨምራና ጠንካራ ሰራዊት መልምላ ለመመለስ የቻለችበትን ምክንያትም በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ዶክተር አህመድ የአድዋን ድል ከባለቤቶቹ ከኢትዮጵያውያን በላይ ላቲን አሜሪካኖች፣ አውሮጳዎች፣ ሌሎች አፍሪካውያን እየተጠቀሙበት እንደሆነ ይጠቅሳሉ። ካሜሩን ያሁንዴ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ስለአድዋ ጦርነት በታሪክ ትምህርት ሲሰጥ ማየታቸውንና ምስክር እንደሆኑ ተናግረዋል።በኢትዮጵያ ግን ጅምር እንጂ የተጠናከረ ሥራ አለመሰራቱን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያውያን፤የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብን የራሳቸው አድርገው እንደተቀበሉት ሁሉ የአድዋንም ድል የኩራታቸው፣ የአንድነታቸው፣የማንነታቸው መገለጫ መሆኑን ተገንዝበው በተመሳሳይ ሁኔታ ሊከበር እንደሚገባ፣የአድዋ ድል አንድ መገለጫ (ብራንድ) ይኑረው ከዓድዋ የድል በዓል በኋላ ያሉት የተጋድሎ ጦርነቶችና የተመዘገቡ ድሎች መዘንጋት የለባቸውም፣ ኢትዮጵያውያን ምሁራን የኢትዮጵያን ታሪክ ፈትሸው በመጽሐፍ ሰንደው ለትውልድ ያስተላልፉ፣የሚልና ሌሎችም ከዕለቱ መድረክ ተሳታፊዎች ከተነሱት ሀሳቦች ጥቂቶቹ ናቸው።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጥናት የሁለተኛ ዲግሪ ድህረምረቃ አስተባባሪ፣የአፍሪካ ዴስክ ኃላፊና የአፍሪካ ባህል መምህር ፕሮፌሰር ጌታቸው ካሳ የዓድዋ የድል በዓልን ዓመት ጠብቆ ከመዘከር ባለፈ የቱሪስት መዳረሻ በማድረግ ታሪኩ ከፍ ብሎ ዘርፈብዙ ጠቀሜታዎችን እንዲያስገኝ ማድረግ እንደሚቻል ይናገራሉ።
እርሳቸው እንዳሉት ስለዓድዋ የተነገሩ አፈታሪኮችን፣ዓድዋ አካባቢና በሌሎችም የሚገኙ ሀገር በቀል እውቀቶች ተሰብስበው በታሪክ አጥኚዎች ተሰንደው በታሪክ ሙዝየምነት ለተደራሹ የሚቀርቡበት ሁኔታ ቢመቻች፣ ከተለያየ ዓለም የሚመጡ ታሪክ አጥኚዎች ጭምር ወደ ሥፍራው ለመሄድ ይነሳሳሉ።
እውቅናም ገቢም ይገኛል።በተጨማሪም በፊልምና በሙዚቃ የተለያዩ ሥራዎች ቢሰሩ ኢትዮጵያውንም ትክክለኛውን የሀገራቸውን ታሪክ ለማወቅ ጉጉት ያድርባቸዋል። የዓድዋ ተራሮችና መልክዓምድሩ እንዲሁም በዓመት አንዴ በአካባቢው የሚከሰቱ አዕዋፋት ተጨማሪ ቱሪስትን የሚስቡ በመሆናቸው ልማቱን ማጠናከር ያስፈልጋል።
የዛሬ አምስት ዓመት የአድዋ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ እንዲመሰረት ኮሚቴ ተዋቅሮ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲደረግ መቆየቱ ይታወሳል።የዩኒቨርሲቲው መቋቋም የድሉን ታሪካዊ ይዘቶች ከማጉላት ባለፈ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆንና ለአህጉራዊ ውህደትም ሚናው የጎላ እንደሆን ያግዝ ነበር።ይሁን እንጂ እንዲህ ያሉ እንቅስቃሴዎች ከወቅታዊነት ባለፈ ተከታታይነት ሥራ ባለመሰራቱ ውጤቱን ማየት አልተቻለም።
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2013