የሉሲ 50ኛ ዓመት

ርስ ከማንነት፣ ከታሪክ፣ ከሥልጣኔ ጋር የተያያዘ የአንድ ሀገር እና ሕዝብ መታወቂያ ነው:: በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በተፈጥሮ ለበለጸጉ ሀገራት ትርጉሙ ለየት ይላል:: ከኢኮኖሚ፣ ከማህበራዊ ትስስር እንዲሁም ከመሰል ሁኔታዎች አንጻር ሲቃኝ የቅርሶች ዋጋ ዘርፈ ብዙ እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም::

ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ምድር መሆኗ ይታወቃል:: ለዚህ ደግሞ ሉሲ እና ከእሷ በኋላ የተገኙ እንደአርዲ ያሉ ጥንታዊ ቅሬተ አካላት ወሳኝነት አላቸው:: በዓለም ሕዝብ ዘንድ መታወቂያ ከሆኑ ስሞች መካከል የሉሲ ሀገር ሕዝቦች የሚለው ዋነኛው ነው:: ሉሲ የኢትዮጵያን ቀደምትነት በመግለጥ ከዓለም እና ከሰው ልጅ ብኩርና በፊት የነበረውን ጥንተ ማንነት ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ታላቅ ሚናን የተወጣች ቅሬተ አካል ናት::

ከሰሞኑ ‹ምርምር ለቅርስ ጥበቃ› በሚል መሪ ሃሳብ ሁለተኛው ዓመታዊ የምርምር ጉባዔ በኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን አዘጋጅነት ተካሂዷል:: በጉባዔው ከሀገር ውስጥ እና ከውጪ በርካታ እንግዶች የተገኙ ሲሆን፤ የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሰላማዊት ካሳ፣ ፕሮፌሰር ራይሞንድ ቦንፊል፣ ፕሮፌሰር ጅን ሬናውድ ቦይሰሪ፣ ዶ/ር አንዶሳ ሊኪስ እንዲሁም ሌሎች እንግዶች ተሳትፈዋል:: በጉባዔው የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው፤ ሉሲ የተገኘችበትን ሃምሳኛ አመት ምክንያት በማድረግ ንግግር አድርገዋል::

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተሩ፤ የኢትዮጵያ የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን እንደ ኢንስቲትዩት ከተቋቋመ ሰማንያ ዓመታትን ማሳለፉን አመልክተዋል:: በ1936 ዓ.ም የተቋቋመው ተቋም ስምንት አስርት ዓመታትን ተጉዞ፤ አሁን ያለበት ቁመና ላይ እንደደረሰ ገልጸዋል:: በሰማንያ ዓመታት ጉዞ ውስጥ በርካታ ሁኔታዎች ማለፋቸውን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ባለሥልጣኑ በዚህ ሁሉ ጊዜያት ውስጥ በቅርሶች ጥበቃ እና ጥናት ዙሪያ ሃላፊነቱን ሲወጣ መቆየቱን አንስተዋል::

ባለፉት ዘመናት በአንዳንድ የአሠራር ችግሮች ምክንያት በቅርስ ጥበቃ እና ጥናት ላይ ያልተሳኩ ሥራዎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ባለፉት አምስት ዓመታት በተወሰዱ የፖሊሲ እና የአሠራር ለውጦች ምክንያት ችግሮችን በመቅረፍ እንደባለሥልጣን ተቋም ስኬታማ ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቁመዋል::

በዘርፉ ላይ እክል ሲፈጥሩ የቆዩ የተንከባለሉ የአሠራር ክፍተቶች ታርመው፤ ‹‹ቅርስን ለሀገር ሀገርን ለቅርስ›› በሚመስል የትስስር እሳቤ ተፈጥሯል:: እንደመንግሥት ማህበረሰቡን በማንቃት እና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በጎ አጋጣሚዎችን ወደ እድል የመቀየር ሥራዎች ጥሩ ውጤት ማምጣታቸውን ጠቁመዋል::

ከፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በተሰጡ አቅጣጫዎች መሠረት የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ መሪዎች እና ባለሙያዎች አንድ ላይ በተቋሙ ላይ አመርቂ ለውጥ ለማምጣት ውይይት ማድረጋቸውን አንስተው፤ በውይይቱም ችግሮች ተለይተው፤ የመፍትሄ አማራጮች በመወሰዳቸው አመርቂ ውጤት ማምጣት መቻሉንም አብራርተዋል::

ረዳት ፕሮፌሰር አበባው ፤ በቀጣይም በቅርሶች ጥበቃ ላይ ወሳኝ እና ለውጥ ተኮር የሆኑ ምርምሮች እና ጥናቶች አስፈላጊ መሆናቸው ታምኖበት እየተሠራ እንደሚገኝ አመላክተዋል::

ቅርስ ውርስ ነው:: ከትናንት ወደዛሬ የመጣ ወደነገም የሚሄድ የኢትጵያዊነት ቀለም ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ እነዚህ የማንነት ቀለሞች ተጠብቀው እና ተገቢውን እንክብካቤ አግኝተው ለትውልድ እንዲተላለፉ የአሠራር ሁኔታውን ማዘመን ወሳኝነት እንዳለው አስረድተዋል:: ለዚህም የጥናት እና የምርምር ተቋማት አስፈላጊነት ወሳኝ መሆኑን በማመን እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል::

ከሁለት ዓመት በፊት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በአምስት ማዕከላት ላይ የጥናት እና ምርምር ግብረ ሃይል አቋቁሞ እንደነበር አስታውሰው፤ ይሄን መሠረታዊ የምርምር ዓላማ በመከተል ዛሬ ላይ ‹ምርምር ለቅርስ ጥበቃ እና ዋስትና› በሚል መሪ ቃል ሁለተኛውን ዓመታዊ ኮንፍረስ ማዘጋጀት እንደቻሉ ጠቁመዋል:: በዚህ ጉባዔ ላይ እንደመሪ ቃል ሆኖ ያገለገለው መነሻ ሃሳብ በሳይንሳዊ ጥናት ላይ ጠንካራ እምነት የሚፈጥር እንዲሁም በቅርስ ጥበቃ ላይ ቁልፍ ሚና የሚጫወት መሆኑን አመላክተዋል::

በቅርስ ጥበቃ ላይ ያተኮረው የዝግጅቱ መሪ ሃሳብም እንደመንግሥት ዘርፉን ለማነቃቃት የሄደበትን ርቀት የሚያሳይ፣ ቅርሶች የሀገር ሀብቶች መሆናቸውን የሚያረጋግጥ እና ሊጠበቁ የሚገባውም በሕዝብ መሆኑን የሚያስረዳ ነው ብለዋል:: እንደዜጋ ሃላፊነትን ለመወጣት መልዕክት ያለው፣ እንደባለድርሻ አካላትም የትብብር እና የቅንጅት መንፈስ አስፈላጊ እንደሆነ የሚጠቁም መሆኑንም አንስተዋል::

በቅርስ ዙሪያ የሚወጡ ጥናታዊ ጽሁፎች ተደራሽነታቸው እንዲሰፋ፤ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ጥናታዊ ጽሁፎችን ተደራሽ ከማድረግ አኳያ ከህትመት አንስቶ ለአጥኚዎች ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ ሶፍት ዌሮችን እያበለጸገ ይገኛል ብለዋል::

ዋና ሥራ አስፈጻሚው አያይዘውም በቅርስ ጥናት ዙሪያ የተጀመረውን ዓላማ ከግብ ለማድረስ በሀገር ውስጥ እና በውጪ ካሉ በዘርፉ ላይ እየሠሩ ከሚገኙ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሠሩ እንደሚገኙ ገልጸው፤ በትብብር ከሚሠሩ የውጪ ሀገራት ተቋም ውስጥ ፈረንሳይ አንዷ መሆኗን ተናግረዋል:: በኢትዮጵያ የሚገኙ ወጣት ተመራማሪዎችን ለመደገፍ እገዛ እንደምታደርግ ጠቁመው፤ ሁለተኛው ዓመታዊ ኮንፍረስም በፈረንሳይ ትብብር የተዘጋጀ እንደነበር አመላክተዋል::

በኮንፍረንሱ ላይ ከታሪካዊ እስከ ባህላዊ ቅርስ ድረስ ያሉ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበዋል:: በዩኒስኮ ስር የሚሠሩ፤ በቅርስ ጥበቃ ዙሪያ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው የውጪ ሀገር ዜጎች ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደው ጽሁፋቸውን ለታዳሚ አቅርበዋል:: የዝግጅቱ አጠቃላይ መንፈስ ተስፋን የሚሰጥ ቀጣዩ ጊዜ ከቅርስ እና ቱሪዝም ጋር የተሳሰረ እንደሆነ የተረዱበት እንደሆነ መገንዘብ አይከብድም ብለዋል::

በሚቀጥሉት ዓመታት ኢትዮጵያ ለምታደርገው የቅርስ ጥናት ወሳኝ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን ያነሱት ረዳት ፕሮፌሰር አቶ አበባው ለዚህ ኮንፈረንስ መዘጋጀት፤ መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል::

በዝግጅቱ ላይ የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ንግግር አድርገዋል:: በንግግራቸው ኢትዮጵያ በተፈጥሮ እና በባህላዊ ቅርሶች ያጌጠች ሀገር ናት:: ብዙ የውጪ ሀገር አጥኚዎች በሀገሪቷ ያለውን አስደናቂ ሀብት ምስክርነት በመስጠት ኢትዮጵያን እውነተኛ የተፈጥሮ ቅርስ ሙዚየም በማለት ይገልጿታል ሲሉ ተናግረዋል:: እንደባለጸጋ ሀገር ለቅርሶች የሚሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑን አንስተው፤ ቅርሶች ለማህበረሰብ ያላቸው ፋይዳን ከመረዳት አኳያም አነስተኛ ግምት እንደነበር ገልጸዋል::

የቅርሶች አስፈላጊነት ከጥበቃ እና ከእንክብካቤ የሚጀምር እንደሆነ ያነሱት ሚኒስትሯ፤ ያሉትን ሀብቶች በጥበቃም ሆነ ሀገርና ሕዝብን ከመጥቀም አኳያ በተገቢው ልክ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ገልጸዋል::

ከዚህ በፊት በነበረው አሠራር ለቅርሶች ልዩ ትኩረት እንዳልተሰጣቸው አንስተው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት በወሰደው ልዩ አቅጣጫ ለቅርሶች የሚሰጠው ትኩረት እና ጥበቃ እያደገ መምጣቱን አመላክተዋል:: ቅርሶች ለሀገርና ለሕዝብ ያላቸውን ሚና በማስገንዘብ እና ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በተሠራ ሥራ ለቅርሶች ልዩ ትኩረት በመስጠት ለውጦች እንዲመጡ መደረጉን ጠቁመዋል::

ፖሊሲዎችን በማሻሻል፣ ሕግና ደንቦችን በመቅረጽ በቅርሶች ላይ የነበረው አስተሳሰብ እንዲቀየር፤ ብሎም በሀገሪቱ የሚገኙ ሁሉንም ቅርሶች ከመለየት፣ ከመንከባከብ፣ ከመጠበቅ እና ዋስትና ከመስጠት አኳያ አመርቂ ውጤቶች ታይተዋል ሲሉ ገልጸዋል:: ሚኒስትሯ አያይዘውም የተረሱ ቦታዎችን በመጠበቅ ለሕዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ ረገድ ስኬታማ ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል::

እንደዩኒቲ ፓርክ፣ ብሔራዊ ሙዚየም የመሳሰሉ ቦታዎችን በመጠበቅ እና ምቹ በማድረግ ባህላዊ ቅርሶች ላይ አትኩሮት ተሰጥቶ መሠራቱን አንስተው እየተሠሩ ያሉት እንደማሳያ ቢሆኑም በቀጣይ በርካታ የቅርስ ቦታዎች ለአገልግሎት እንዲውሉ አቅጣጫ መቀመጡን ሚኒስትሯ ገልጸዋል::

ያለሳይንሳዊ ምርምር የቅርሶች ጥበቃ ብቻውን ትርጉም የለሽ ነው ያሉ ሲሆን፤ ያለፉት ሰባ ዓመታት አብዛኞቹ የሀገሪቱ ቅርሶች አስተማማኝ ባልሆነ የጥናት ውጤት ስር እንደነበሩ ጠቁመዋል:: የቅርስ ጥንታዊነት እና ዘላቂነት እንዲሁም መሰል ሁኔታዎች በምርምር መደገፉ ከጥበቃ እና ከዋስትና ባለፈ አዳዲስ ሁኔታዎችን ለማየት እድል የሚሰጥ መሆኑን አንስተዋል:: ሁለተኛው ዓመታዊ ኮንፍረንስ ቀጣዩን ጊዜ በማስተካከል በጥናት ላይ የተመረኮዘ የቅርስ ጥበቃ ልምምድ እንዲኖር እድል የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል::

እ.አ.አ 2023 ጀምሮ የኢትጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ቅርሶች ላይ ጥናት በማድረግ ወሳኝ ተግባራትን የሚያከናውን የምርምር ማዕከል እንዳቋቋመ ገልጸው፤ ይህ እንቅስቃሴ ከቅርስ ጥበቃ ጎን ለጎን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትንም የሚያረጋግጥ እንደሆነ አንስተዋል:: አያይዘውም የምርምር ቡድኑ ከጥናት እና ምርምር ባለፈ በቅሪተ አካል ጥናት ዘርፍ ላይ የራሱን ዐሻራ ማሳረፍ የሚችል እንደሆነ ጠቁመዋል::

አሁን ላይ በሀገሪቱ የወጣት ተመራማሪዎች ቁጥር በማደግ ላይ ይገኛል ያሉት ሚኒስትሯ፤ በማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች፣ በሥነጽሁፍ፣ በጥንታዊ ቅርሶች ላይ ወጣቱ በሙያው የራሱን አስተዋጽኦ በማድረጉ አስደሳች ሁኔታ መፈጠሩን አመልክተዋል:: በሃይል እና በፈጠራ የተሞላው የወጣቱ ሥነልቦና ሀገር በመፍጠር፤ አዳዲስ ነገሮችን ከማስተዋወቅ አኳያ የማይተካ ሚና ያለው በመሆኑ እድል አግኝቶ ሚናውን እንዲወጣ መደረጉ የሚበረታታ እንደሆነ አመላክተዋል:: በማያያዝም ወደፊት በእውቀታቸው ከኢትዮጵያ አልፈው በዓለም አቀፍ ደረጃ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ወጣቶች ይፈጠራሉ ሲሉ ተናግረዋል::

የኢትዮጵያ የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ከፈረንሳይ ምርምር እና የትምህርት ተቋም ጋር በመቀናጀት እያደረጉ ያለውን አድንቀው፤ ምርምር ብዙ ችግሮችን ፈቺ ከመሆኑ አንጻር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያሉ መቀራረቦችን በማጠናከር በቅርስ ጥበቃ ላይ መነሳሳትን የሚፈጥር ነው ብለዋል:: በቀጣይ በተቀመጡ አቅጣጫዎች መሠረት ያሉትን ቅርሶች በመጠበቅ፤ ለሀገር እና ሕዝብ ጠቃሚና አስፈላጊ የሚሆኑበትን ሁኔታ ከማመቻቸት አኳያ የተሻሉ እድሎች መኖራቸውን ጠቁመዋል::

በጥቂት ዓመታት ውስጥ በተወሰዱ ርምጃዎች የታዩ የለውጥ ተስፋዎች ለቀጣዩ የስኬት ጉዞ አበረታች መሆናቸውን አንስተው፤ ቅርሶችን ለቱሪዝም፣ ቱሪዝምን ለቅርስ ከማመቻቸት አንጻር ጥሩ ማሳያ የሚሆኑ ናቸው ብለዋል:: ኢትዮጵያ በርካታ አስደናቂ ቅርሶችን ያቀፈች ናት:: እነዚህ ቅርሶች እንደህጻን ልጅ እንክብካቤ እና ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ በልዩ ትኩረት መያዝ የሁሉም ሃላፊነት ነው ብለዋል::

ቅርሶች ለአንድ ሀገር የባህል፣ የታሪክ፣ የሥልጣኔ፣ የማንነት እና የመሰል ሁኔታዎች ማሳያዎች ናቸው:: ወሳኝ ከሚባሉ የእድገት እና የዘመናዊነት ምሰሶ በመሆንም ይጠራሉ:: የሉሲ ወይም የድንቅነሽ መገኘት ኢትዮጵያዊነትን በዓለም አደባባይ ገልጦታል:: የሉሲ መገኘት የሰው ልጅ መገኛ ከመሆን ባለፈ አጥኚዎች የኢትዮጵያን ምድር መርጠው የተለያዩ ጥናቶችን እና ምርምሮችን እንዲያደርጉ መንገድ ከመክፈቱም በላይ በብዙ የሚነሳ መልካም አጋጣሚዎችን የፈጠረ እንደነበር በመድረኩ ላይ ተነስቷል::

ዘላለም ተሾመ

አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You