አዲሱ ገረመው
በጥበብ ቤተ ዘመዶች ቅጥር ግቢ ውስጥ ስነ ጽሁፋዊ ሂስ እንደ ድንኳን የሚያገለግል ሳይንሳዊ ምዘና ነው። የሥነ ጽሁፋዊ ሂስ ቅርጾች በርካታ ሲሆኑ፤ ከእነዚህ ውስጥ ተጠቃሹ አውዳዊ ሂስ ነው።
አውዳዊ ሂስ ማለት የቀረበው የሥነ ጽሁፍ ሥራ ምን ያህል የቀረበበትን ዘመን ማህበረሰብ አንጸባርቋል ወይም በሥነ ጽሁፍ የተመረጡት መደቦች ለተጻፈበት ዘመን ያላቸው ቅርበትና ተዛምዶ የሚያመላክት ነው።
ዛሬ በዘመን ጥበብ አምዳችን ልቦለዱ ውስጥ ያለው ታሪክ የተፃፈበት አውድ መሰረት አድርገን የታሪኩ አውዳዊ ምሰላና የታሪክ ሁነት ላይ የተመለከተ ፅሁፍ አቅርበናል፤መልካም ንባብ።
በእርግጥ በሂስ መልክ አንድን ፅሁፍ ለማሄስ የሚታዩ ዋንኛ የሚባሉ ሌሎች ጉዳዮችም አሉ።በሂስ ሥነ ጽሁፉ ይዞት የመጣው ገጸ ባህሪ፣ ታሪክ እንዲሁም ተያያዥነት ያላቸው ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የቱን ያህል ከእውነታ ዓለም ጋር ይዛመዳሉ የሚለውን ጠለቅ ባለው መልኩ የማጤን ሂደት ሂስ ነው።
አውዳዊ ሂስ ጥልቅ ምዘና የሚያስፈልገው ነው እኛ በዛሬው ፅሁፋችን ማሳየት የፈለግነው በልቦለዱ ውስጥ ባለው ታሪክ መሰረት በወቅቱ በነባራዊው ገጽታ የተመለከቱትን ጉዳዮች በመመልከት ታሪኩ በዘመኑ የነበረውን አጠቃላይ ገፅታና ሁናቴን ነው።
በሂስ ወቅት የማህበረሰቡን ባህላዊ ዳራ፣ ታሪክና መሰል ሁነቶችን ማወቅም ይጠይቃል። ሀያሲው ይህንን እውቀቱን መሠረት በማድረግ የሥነ ጽሁፍ አውድ ይመረምራል።
ማህበረሰባዊና ኢኮኖሚያዊ ገጽታ በጉንጉንበዚህ ልቦለድ ውስጥ አውዳዊ ሂስ ከሚመለከታቸው ነጥቦች መካከል አንዱ መጽሐፉ የተገለጸበትን ዘመን
የማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊ ዳራን ነው። ይህ ምን ያህል በመጽሐፉ ውስጥ ተንጸባርቋል የሚለው አብይ ተጠቃሽ ነው። በተለያየ ጊዜ ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን፣ የታሪክ መጻሕፍት አጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የነበረው የማህበረሰቡ ኢኮኖሚያዊ ገጽታዎች ይዳሰሳሉ።
ታዲያ የዚህ ዘመን ትውልድ እድለኛ ከሚባልባቸው ነገሮች አንዱ የኑሮ ውድነት የሚባል ነገር ጎልቶ አለመኖሩ ነው። ሰዎች በግብይት ሥርዓታቸው በጥቂት ፍራንክ ለመብልም ሆነ ለመጠጥ አስፈላጊ የሆኑ በርካታ ነገሮችን ይገዙ ነበር።
የዘመኑ የገቢ ምንጭ የከብትና የእህል ንግድ ነበር። በእርግጥም የመንግሥት ሠራተኞች በጥቂት የወር ደመወዛቸው ብዙ ቤተሰብ ማስተዳደር ይችሉ ነበር። ጉንጉን ልብ ወለድ የጊዜ መቼቱ ለአጼው ሥርዓት ቅርብ እንደመሆኑ ይህን አይነቱን ጉዳይ በምን መልኩ አመላከተ? በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በርከት ያሉ የወቅቱን ኢኮኖሚያዊ ሁነቶች የሚገልጹ ጉዳዮች ሰፍረው እናገኛለን።
ከመጽሐፉ ገጾች በአንደኛው ላይ “…ወይዘሮ ደጅ ይጥኑ የአስር ሳንቲም የገብስ እና የሽምብራ ቆሎ አዘዙለት…” የሚል አረፍተ ነገር እናገኛለን። ይህም በወቅቱ አስር ሳንቲም ምን ያህል ፋይዳ እንደነበረው በዚህ ሁኔታ ተንጸባርቋል። በነባራዊው የነበረውን እውነታም አሳውቋል።
በሌላ በኩል ቀኝ አዝማች እቃቸውን በ”ኩሊ” አሸክመው ወደ ቤታቸው ሲገቡ፤ ኩሊው ለተሸከመበት ሶስት ፍራንክ ይጠይቃቸዋል። ይህም እንዲሁ በወቅቱ የነበረውን ትንሽ ገንዘብ ብዙ የማድረግ አቅም እንዳለው ማሳያ ነው።
በዚህ ዘመን በጥቂት ክፍያ ያሹትን ማድረግ ይቻላል። በዚህ ልብ ወለድ ውስጥ ከተጠቀሱት የምዕናብ ዓለም ሰዎች መካከል ‘ምንዳ” የተባለው ገጸ ባህሪ አዲስ አበባ ውስጥ በወር 15ብር እየተከፈለው የራሱን ሙሉ ወጪ ሸፍኖ ገጠር ላሉት ቤተሰቦቹ የተለያዩ አልባሳትን ሲልክላቸው እናያለን።
እንደ ዛሬው ቴክኖሎጂና ዘመናዊነት ባልተስፋፋበት ጊዜ ሰዎች ማመልከቻዎችንና ደብዳቤዎችን “ራቦር” ጸሐፊ በሚባል ሰዎች ያስጽፉ ነበር። ይህ እውነት በዚህ ልብ ወለድ ከመገለጹ በተጨማሪ ራቦር ጸሐፊው ምንዳ ለቤተሰቡ የላከውን ደብዳቤ ለማንበብ 20 ሳንቲም ሲቀበል እናየዋለን።
በእኔ እይታ ጉንጉን የዘመኑን የገንዘብ አቅም ዘመኑ ላይ ከነበረው እውነታ አንጻር የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ አውድ በሚገባ የገለጸ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ያስደርሳል። በትንሽ ገቢ ብዙ ሸመታ ማድረግ፣ ይቻልበት የነበረውን ዘመን በልብ ወለዱ የምናብ ዓለም ሰዎችና የታሪክ አወቃቀር ላይ ተመስርቶ አንጸባርቋል።
የወቅቱ ፖለቲካዊ ሥርዓትና ጉንጉን
የአጼ ኃይለ ሥላሴ መንበረ ንግሥና የተሰጠው ከፈጣሪ ስለመሆኑ ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች ይነገራል። ለዚህም አጼው ራሳቸው፤ “ስዩመ እግዚአብሔር ሞ አንበሳ ዘ እምነገደ ይሁዳ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ” በማለት ሹመታቸው ከፈጣሪ የተሰጠ መሆኑን ይናገራሉ። በሥራቸው ያሉት ሹማምንት ደግሞ ለዚህ ማንነታቸው ትልቅ ክብር ይሰጧቸዋል። ይሰግዱላቸውም ጭምር ነበር።
በዚህ ልብ ወለድ ውስጥ ለንጉሡ የሚሰጠው አክብሮት ሳይገለጽ አልቀረም። በልብ ወለዱ የተጠቀሰው የንጉሥ ከበሬታ በእውነታው ዓለም ሲሰጣቸው የነበረው ነው። በአንዱ የድርሰቱ ገጽ ላይ ንጉሡ ወደ ምክር ቤት አዳራሽ ሲገቡ በከፍተኛ ሁኔታ ታጅበው ጭብጨባና እልልታው ደምቆ ማንም ከማይደርስበት ዙፋናቸው ላይ ሲቀመጡ እናያለን። በሌላ በኩል ማንም ንጉሡን ቀና ብሎ ማየት እንደማይቻልም በልብ ወለዱ ውስጥ ሰፍሮ እናገኛለን።
በዚህ ጊዜ የነበረውን የምርጫ ሥርዓት ወይም ለፓርላማው ምክር ቤት የሚመረጡት ተወካዮች በአራት ዓመታት ውስጥ ነበር። ይህም በልብ ወለዱ ገጽ 348 ላይ ቀኝ አዝማች በላይነህ ከአራት ዓመታት በኋላ ድጋሚ ለምርጫ ወደ አገራቸው ሲመለሱ እናያለን።
አጼ ኃይለ ሥላሴ ፍርድ የሚወስኑባቸው ህግ መወሰኛና ህግ መምሪያ የሚባሉ መዋቅሮች አሉ። የህግ መወሰኛው ራሳቸው አጼው የሚፈርዱበትና ከፍተኛ ባለሥልጣናትን የሚሾሙበት የሥልጣን እርከን ሲሆን ህግ መምሪያው ደግሞ ከየክፍላተ ሀገራቱ የተውጣጡ ባለሥልጣናት የሚመክሩበት የሥልጣን ደረጃ ነው። በዚህ ልብ ወለድ ይህ አይነቱ እውነት የሆነው ሥርዓት በሚገባ ተንጸባርቋል። በልብ ወለዱ ገጾች ውስጥ በሥርዓተ መንግሥቱ የነበሩ የህግ መምሪያና መወሰኛ ህልው ሆነው ቀርበዋል።
የዚህ ዘመን መገለጫ ከሆኑት ነባራዊ እውነታዎች አንዱ የጭሰኛና የመሬት ባለቤት የሚባል ተዋረዳዊ አስተዳደር ነው። ጭሰኛ የሚባለው የመሬት ባለቤት በሆነው ሰው ሥር ሆኖ እንደ ዳረጎት አይነት ግልጋሎት የሚሰጥ ነው። ልብ ወለዱም በገሀዱ የነበረውን ይህንኑ እውነት በማንሳት ቀኛዝማች በሥራቸው የተለያዩ ጭሰኞች እንደነበሯቸው አውስቷል።
በታሪክ እንደሚታወቀው የአጼውን ሥርዓት የሚቃወሙ ተማሪዎች፣ ጭሰኛ ገበሬዎችና ሌሎችም አካላት በተለያየ ጊዜ አመጽ እያስነሱ ሠልፍ ይወጡ ነበር። ጉንጉንም ይህንን እውነታ ቀድቶ ያሳያል። በታሪኩ ፍጻሜ አካባቢ ገበሬዎች በአንድ ጽንፍ ሆነው የመሬት ባለቤቶችን ሲያጠቁና ሲማርኩ እናያለን። ይህም የአጼውን ዘመን ማብቃት ተከትሎ ለደርግ መንግሥት በር የከፈተ ታሪክ ሆኖ ተከትቧል።
በዚህ ልብ ወለድ ውስጥ አቻዊ የገሀዱ ዓለም ነጸብራቆች ጽሁፉ የተጻፈበትን ዘመን በሚገልጹ በርካታ መልኮች ተከስተዋል። ምንም አንኳን የአምዱ የቃላት ብዛት ውስንነት ገድቦን ከላይ ያለውን አባይን በማንኪያ ያህል ጨለፍነው እንጂ ነገረ ጉንጉን በዚህ የሚቋጭ አልነበረም። ከላይ ከተጠቀሱት ዘርፎች በተጨማሪም የማህበረሰቡ ሃይማኖታዊ ክዋኔዎችና ማህበራዊ እውነታም ከጊዜው እውነታ አንጻር ቀርቧል።
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2013