
ያልገባን በውል ያላስተዋልነው፣ ፊደላት ዓለም አላቸው:: ከዚያ ዓለም ጋር እስካልተገናኘን ድረስ ‹ዕውቀትና ጥበብ› የሚሉ ነገሮች ዋጋ አይኖራቸውም:: የፊደላት ረቂቅ ዓለም የገባው ብቻ ነው በዕውቀትና ጥበብ ራሱንም ዓለምንም አሸንፎ ለመሥራት የሚችለው:: ፊደል ስንቀርጽ ይህን መግነጢሳዊ የፊደላት ኃይል ለመግለጥ ችለን ነበር፤ ፊደላቱን መቁጠር ስንጀምር ግን ተላምደነው ይሁን ከናካቴው ጠፋብን:: ለምን? ካልን ማንበብን ፊደላቱን ስለመቁጠር ስላደረግነው ነው:: “ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል” እያልን እንኳን ፊደላትን ለመግለጥ ተስኖን እንታያለን:: መወለድ፣ ማደግ፣ መኖራችን ብቻ፣ አልፎም ፊደል መቁጠራችን ብቻ በምድር ሕይወታችን ሙሉ ሰው አያደርገንም:: በሁለት እግሮች ከመሄድ የቀረውን ሰው የመሆን ምስጢር ከዕውቀትና ከጥበብ ነው:: ሁለቱም ደግሞ ያለፊደላት ህልውና የላቸውም:: ምድር፣ ሰማይ፣ የሰው ልጆችም ሆኑ ራሱ ፈጣሪ ህልውናው አደጋ ላይ መውደቁ አይቀርም:: ‹እንዴት?› ካልን ለዚህ አንዲት ሁነኛ ማሳያ እናነሳለን::
እስቲ ክርስትናን ያለ መጽሐፍ ቅዱስ፣ እስልምናን ያለ ቁርአን እናስባቸው:: የሃይማኖታችንም ሆነ የፈጣሪ ህልውና ገደል ገባ ማለት አይደል? ታዲያ ሁለቱም መሠረታቸው ቃል ነው:: ቃል ደግሞ የፊደላት ሥሪት ነው:: ፊደላትን ማወቃችን ፈጣሪን እንድናውቅ አድርጎናል:: ሰባኪው ሳያነብ እንዴት ስለፈጣሪው ሊሰብክ ይችላል? ሳያነቡና ሳይመረምሩ ያለ ቅዱስ መጽሓፍቱ ሃይማኖታችን ምን መሠረት ሊኖረው ይችል ነበር? የሰው ልጆችና የፈጣሪ ትውውቅም ሆነ ግንኙነት የተመሠረተው በፊደላት ነው:: በሌላ አባባል ፊደላት የሉም ማለት ቃል አይኖርም፣ ቃል ከሌለ ቅዱሳት መጻሕፍት የሉም ማለት ነው:: እነርሱ ከሌሉ ሃይማኖት፣ ፈጣሪ…ካላነበብን አላወቅንም፣ ካላወቅንም አልተጠበብንም ማለት ነው::
‹ፊደላት› ስንል እያወራን ያለነው ‹ሀ ሁ› ስለመቁጠር አይደለም:: ዕውቀትና ጥበብ በቆጠረ ቢሆንማ ኖሮ ብዙዎቻችን አዋቂና ጠቢብ በሆንን ነበር:: የምናወራው ስለ ‹ንባብ› ነው:: ከንባብም ፊደላትን ስላወቅን ብቻ ስለምንጠራቸው ቃላትና ዐረፍተ ነገሮች አይደለም:: ጥያቄው ለሆዳችን ምሳ፣ ቁርስ፣ እራት ስንደክምለት ለአዕምሯችን እየመገብን ነው? የፊደላትን ቫይታሚን፣ ገንቢና ጠጋኝ፣ በሽታ ተከላካይ፣ ፕሮቲን እናቀርብለታለን? ካልሆነ ቀንጭረናል:: የአዕምሯችን ሴሎች ዘይቱ እንደ ደረቀ የመኪና ሞተር ደርቀዋል ማለት ነው::
የራሷን ፊደል ቀርጻ፣ የራሷን ሀገር በቀል ዕውቀትና ጥበብ ለመፍጠር ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ነበረች:: በዓለማችን የራሳቸውን ፊደል መቅረጽ ከቻሉ 18 ሀገራት አንዷ ናት:: አንዷ ብቻም ሳትሆን፤ ማናቸውም ያልደረሱበትን ረቂቅ ዕውቀትና ጥበብ የጨበጠች ነበረች:: ‹ነበረች› እንድንል ያዳረሰንም ፊደል መቁጠር እንጂ የፊደላትን ረቂቅ ማወቅ እየተሳነን በመሄዳችን ነው:: ዶክተር፣ ፕሮፌሰር፣ ሳይንቲስት…ወዘተረፈ እስከመሆን ድረስ እንማራለን፤ ግን የምንማረው የራሳችንን አይደለምና በሀገር በቀል ዕውቀትና ጥበብ መሃይማን ነን:: በተቃራኒው ደግሞ ፊደል ቀርጸው የሰጡንን ‹መሃይማን› የነበሩበትንም ዘመን ‹የጨለማ› እንደነበር እናወራለን:: እውነታው ግን ብዙ የተማረ ማኅበረሰብ ተፈጥሯል የምንልበት ዘመን ላይ ነው ጨለማው የበረታው:: ጥንት የራሳቸውን ፊደላት ከቀረጹት ከአሥራ ስምንቱ ሀገራት ጋር አሁን ራሳችንን ለማነጻጸር ከቶ ባናስበው ይሻላል፤ ከመቶ ዘጠና አምስቱ የዓለም ሀገራት በንባብ ወደ መጨረሻዎቹ ተቃርበናል:: ስለ ማናነብ፣ የተጻፉልንን ስለማንመረምር፤ ስለዚህም ነው ብዙ የተማረ እያፈራን በሄድን ቁጥር በብዙ ነገሮች ወደ ዓለም ጭራነት የምንገሰግሰው::
ፊደላት ከምናውቀው የዕውቀትና ጥበብ ማህደርነት ያለፈ ምትሀታዊ ምስጢራትም የያዙ ናቸው:: ታላቋን ኢትዮጵያ የፈጠሩ፣ የጥንት አባቶቻችን ዕውቀትና ጥበብ ያለ ፊደላት፣ ልክ ከሃይማኖትና ፈጣሪ ጋር እንዳነሳነው ዓይነት ነው:: በዕውቀትና ጥበብ ምድርና ሞላዋን የሚዘውሩበትን ምስጢራዊ ቀመር የሠሩት ከፊደላት እንክብል ውስጥ ነው:: መቆጣጠሪያ ሪሞቱንም ‹ምስጢራተ ፊደላት› እንበለው:: የምስጢረ ፊደላት አካል የሆኑትን ስነ ፈለግ፣ ስነ ጥበብ፣ ሳይንስና መድኃኒት…የሚሉት እንዳሉ ሆነው ብዙዎቻችን ልብ የማንለውን የምስጢራተ ፊደላትን አንድ ማሳያ እናንሳ:: ይኸውም ፊደላትና ሉአላዊነት ነው:: ጉዳዩ በቀጥታ ወስዶ ከዓድዋ ድል ጋር ያፋጥጠናል:: የዓድዋ ሉአላዊነትን ከፊደላት ጋር ምን አቆራኘው?
“አንድ ኅብረተሰብ ፊደል አለው ማለት የኢንፔሪያል አገዛዝ ዝንባሌ አለው” ያለው ጣሊያናዊው ሶሾሎጂስት ጄ ሆብስዋም ነበር:: ጉዳዩም ‹ኢንፔሪያሊስት› ስለመሆንና አለመሆን ሳይሆን “…ይህ ማለት በተዋረድ የተደራጀ ባህላዊ ሊህቅ መኖሩን ያሳየናል” ይላል:: ይሄው ምሁር ባደረገው ጥናትም በዓለማችን የራሳቸውን ፊደላት ቀረጽው ከነበሩ ሀገራት ከህንድ በስተቀር በአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ስር የወደቀ እንዳልነበረ ይነግረናል:: ነገሩ ከ18 የፊደላት ባለቤቶች አንዷ የሆነችውን ኢትዮጵያን በይበልጥ ይመለከታል:: ሀገሬው ከዳር እስከዳር ተነቃንቆ ለዓድዋ የተነሳበት ምክንያት ከሀገር ፍቅር ብቻ የመነጨ አነበረም:: ገና ፊደላቱን ስትቀርጽ ባገኘችው ዕውቀትና ጥበብ ችግሮችን በብልሃት የማስወገድና የአሸናፊነትን መንፈስ ተጎናጸፈች:: ባገኙት ረቂቅ ኃይልና ስልጣን በምድር ከመመራት፣ ምድርን በቁጥጥር ስር አድርጎ በበላይነት ወደ መምራት ፍልስፍና ተሻገሩ::
በዚህ ሀገር በቀል ዕውቀትና ጥበብ ውስጥ ደግሞ፤ ሉአላዊነት፣ ነጻነት፣ አይነኬነት፣ መብትና ፍትሃዊነት የሚሉትን መሰል እሳቤዎች ከውስጣቸው እንዲሰርጹ አደረጋቸው:: በሀገር በቀል ዕውቀቶቻቸው ውስጥ ራስን የመሆን፣ ሀገርን የመውደድ ልዩ የፍቅር ስሜት አመነጩ:: በብራናዎቻቸው በፊደላት ያሰፈሯትን ታላቋን ኢትዮጵያ የሠሩት ከዚህ የራሷ ማንነት ውልፍት እንዳትል አድርገው ከፊደላቱ ጋር ቀርጸዋታልና እጁን ሰዶ የነካት እንደሚያጠፋት ቀድሞውኑ ያውቁታል:: ሀገራቸውን ዕውቀትና ጥበብ አድርገው ያስቀምጧት በልብና ጭንቅላታቸው ውስጥም ጭምር ነበርና እሷን የነካ፣ የሚነካው እነርሱን ነበር::
6ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበረው ቤንጃሚን ፍራንክሊን አንድ ጊዜ ላይ እንዲህ አለ “26 ሠራዊቶችን ብቻ ስጡኝ፤ ዓለምን በቁጥጥሬ ስሬ አደርጋታለሁ” ነበር ያለው:: ታዲያ እኚህ ቤንጃሚን የሚፈልጋቸው ሃያ ስድስቱ ሠራዊቶች እነማን ናቸው? አደገኛ ስልጠናዎችን ጭምር የወሰዱ፣ ጠመንጃና መትረየስ ታጥቀው ከምድር የሚሾሩ፣ ከላይ በሂልኮፕተር በፓራሹት የሚወነጨፉ ወታደሮችን ማለቱ አይደለም:: ቤንጃሚን ስጡኝ ያላቸው ወታደሮች፣ 26ቱን የላቲን ፊደላትን ማለቱ ነበር:: ሌላኛው የጣሊያን መሪ የነበረው ናፖሊዮን ደግሞ “ከሺህ ጦረኛ አንድ ብዕረኛ” የፊደላትን ሀያልነት ገልጾታል:: በየትኛውም ጊዜና ቦታ ፊደላት የቱንም ተአምር የመሥራት ኃይል አላቸው:: ድንጋዩን ወደ አፈር፣ አፈሩን ወደ ውሃ፣ ውሃውን ወደ ድንጋይ የመለወጥ እምቅ ኃይል አላቸው:: በጥይት ጥቂቶችን በቁጥጥር ስር ለማድረግ ብዙ ነብሶች መስዋዕት ይሆናሉ፤ በጥቂት ፊደላት ግን ዓለምን እስከነቅንጣቷ መዳፋችን ስር እናደርጋታለን:: በጥይት በምናገኘው ድል የምናተርፈው በፍርሃት፣ በጥላቻ፣ በጭንቀትና በሰቀቀን መታየትን ነው፤ በፊደላት የረታናቸው ግን በተቃራኒው በፍቅርና በክብር የሚገዙልን ናቸው::
ከላይ ያነሳናቸው ሀሳቦች ስለ ፊደላት ኃይል፣ ስለ ንባብ ታላቅነት በደንብ እንድንረዳው ነውና አብይ መንገዳችን ግን ከወዲህ ነው፤ በእኚያው እርምጃዎች፣ በዚያው መንፈስ ከንባብና የንባብ ማዕከላት ጋር እንቆራኝ:: ከጠፋው አንባቢ ትውልድ ጀርባ፣ እንደ ኖህ መርከብ የጠፉ የንባብ ማዕከላትም ናቸው:: እኚህ መርከቦች ምናልባትም ግዙፉን ሀገር በቀል ዕውቀትና ጥበብ ጭነው ከድሮ ወደ ዘንድሮ በመምጣት ላይ ነበሩ፤ አሊያም ገና ከመነሻቸው ሰጥመው ነበር:: ‹ትውልዱ ከንባብ ተኮራርፎ ከንባብ ሸሽቷል› ስንል ለመሆኑ የሚያነበውን ነገር ሰጥተነው ነበር ወይ? ‹የሚሻለው ሀገር በቀል ዕውቀት ነውና ወደ ሀገር በቀል ዕውቀቶቻችን እንመለስ› ስንልስ ለዚህ የሚሆን ምንስ ግብአት አዘጋጅተን ነው? ከአንደኛ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲዎች አነሰም በዛም ቤተ መጻሕፍት ይገኛሉ፤ ነገር ግን ቤተ መጻሕፍቱን የሞላነው በምንድነው?
እኚህንም ጥያቄዎች አየር ላይ እናክርማቸውና ቤተ መጻሕፍት መኖር ከነበረባቸው ግን የተከለከለ ያህል መጻሕፍት ዝር ከማይሉባቸው ብዙ ስፍራዎች መካከል ወደ አንደኛው እናምራ…ማረሚያ ቤቶቻችን መጻሕፍትን ተጠምተዋል:: ማረሚያ ቤቶች ለጥበብ ሥራዎች አመቺ ስፍራዎች ቢሆኑም ጥበብን የተራቡ ናቸው:: ጥበብን የሚናፍቁ፣ ማንበብን የሚወዱ፣ ልዩ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው በርካቶችን በማረሚያ ቤቶች ውስጥ እናገኛቸዋለን:: ስለ መብቶቻቸው፣ ስለሚበሉት፣ ስለሚጠጡት፣ ስለ እስረኞች አያያዝ ብዙዎቻችን ብዙ እንጠይቃለን፤ ስለ መንፈሳዊ፣ አዕምሯዊና ስነ ልቦናዊ ነገሮች ስናነሳ ግን አይሰማም አይታይም፤ ለምን? ድሮ ከርቸሌ፣ ዘብጥያ፣ ዓለም በቃኝ፣ ወህኒ፣ እስር ቤት… የነበረውን ስም አሁን ላይ “ማረሚያ” በሚል ስንለውጠው፣ ለማረሚያነት የሚሆን ምንስ ሥራ ሠርተናል? አሊያ የስም ለውጥ ብቻውን የሚፈጥረው የለምና ምንም ዋጋ አይኖረውም::
‹እስረኛ ለመጠየቅ ሁላችንም በአገልግል ፍትፍት ቋጥረን እንሄዳለን:: ለእስረኛው የመንፈስ ምግብ የሚሆነውን አንዲት መጽሐፍ ይዘን ግን አንጠይቅም› የሚል ዓይነት ንግግር በአንድ ወቅት የተናገረው ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ ነበር:: ለአንድ እስረኛ የሚያስፈልገው ምግብና ዉሀ፣ የሚለብሰው ብቻ አይደለም:: ከሌላው በተለየ ብዙ ጭንቀት፣ ድብርት፣ መቋጫ የሌለው ሀሳብና ጸጸትም አይጠፋውም:: ወጣ ብሎ ሊዝናና ከዚያ ቅጥር ውጪ እንዳለነው ወደሻው ሄዶ ያሻውን ለማድረግ አይችልም:: ያለበትን ረስቶ መንፈሱን ሊያድስ የሚችልበትን ሁኔታ የሚፈጥርበት ሌላ የለውም:: ያለው ነገር ጊዜና ሰፊ ጊዜ ብቻ ነው:: ይህ ጊዜ ግን እየታረመ ራሱን የሚሠራበት መሆን ነበረበት:: ከታሰረበት የቅጣት ጸጸት ይልቅ ከፊደላት ጋር የሚያወጋበትን ጥቂት ዕድል ብንፈጥርለት ትክክለኛውን እርምት ባደረገ ነበር:: ማረሚያ ቤቶቻችን ግን ከመጻሕፍት ዓለም ያልተዋወቁ፣ ከጥበባት ጋር ያልታረቁ ሆነው ይታያሉ::
ወዲህ ግን የኢትዮጵያ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት አገልግሎት አንዳንድ መልካም ጅምሮችን እያሳየ ይገኛል:: ሀገር በቀል ዕውቀትና ጥበብ ዳግም እንዲያንሰራራ እያከናወናቸው ካሉ ሥራዎቹ ጎን ለጎን ‹የንባብ ሳምንት› በሚል በየወሩ ወደተለያዩ ከተሞች ጎራ ይላል:: ታዲያ ሲሄድ ባዶ እጁን አይደለም፤ በሺዎች የሚቆጠሩ መጻሕፍትና ለድጋፍ የምትሆን የገንዘብ ስንቅም ቋጥሮ ነው:: በሄደባቸው ስፍራዎች ሁሉ አብዛኛው ድጋፍ ለተለያዩ ትምህርት ቤቶች የሚውል ቢሆንም፤ እኚህን የተዘነጉ ማረሚያ ቤቶችን አይዘነጋም:: ከዚህ ቀደም በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚገኙ በርካታ ማረሚያ ቤቶችን መድረስ ችሏል:: መጻሕፍቱንና ለመጻሕፍት ግዢ የሚውለውን ገንዘብ መስጠት ብቻ ሳይሆን፣ በማረሚያ ቤቶቹ ውስጥ የቤተ መጻሕፍት አገልግሎት እንዲደራጀ ማድረጉ የሚያስመሰግነው ነው:: ከሰኔ 5 ጀምሮ ለሁለት ቀናት በአሰላ ከተማ ባካሄደው የንባብ ሳምንትም በተለመደው መልኩ መልካም ግብሩን ፈጽሟል::
ማረሚያ ቤቶቻችን ምን ያህል መጻሕፍትን የተራቡና ጥበብን የተጠሙ እንደሆኑ በአሰላው ማረሚያም ልክ እንደዚህ ቀደሞቹ ሁሉ ለመገንዘብ የሚቻል ነበር:: በመጻሕፍቱ ፊታቸው ምን ያህል ፈክቶ እንደነበር ሲያስገረምኝ ይባስ እንዴት ያሉ ባለተሰጥኦዎችን ተመለከትኩ:: “አምስት ያልታተሙ መጻሕፍትን ጽፌያለሁ” ሲል ተጠርዘው የተከመሩ ሥራዎቹን በሁለት እጆቹ ተሸክሞ የመጣውን እስረኛ የተመለከተስ መገረሙ አይቀርም ነበር:: እስር ቤቶች የወንጀለኞች መናኸሪያ ብቻ አይደሉም፤ እጅግ አስገራሚ የሆኑ ተሰጥኦዎችም አብረው የታሰሩበት ነው:: ተሰጥኦዎቻቸውን ነጻ እንዲያወጡት ብናግዛቸው ብዙ ተአምር ነገሮችን እንመለከት ነበር:: ‹ትውልዱ ከንባብ ባህል አፈንግጧል› ለምንለው ሁነኛው መድኃኒት ማረሚያዎች ናቸው:: ፊደል ያልቆጠረ ብቻ ሳይሆን ከመቁጠርም አልፎ ምሁር የተባለ ስንቱ ከዚያ ይገኛል:: በብዙ ምክንያቶች ከሌላው በተለየ ከማረሚያ ያለው ንባብን አማራጩ ለማድረግ የሚፈልግ ነው:: መንግሥትም ሆነ ራሳቸው ማረሚያ ቤቶቹ ሊሠሩበት ይገባል:: ስንቱን በጎ ተግባር ሲያከናውኑ ያሉ ድርጅቶችና ግለሰቦች እነርሱም ቢያስቡበት ደግ ነው:: ይህን ስናደርግ አንድም እያነጽን፣ ሁለትም ከሚያሳልፉበት የስሜት ውጥረት ነጻ እያወጣናቸው፣ ሦስትም ተሰጥኦዎቻቸውን እንዲያወጡና እንዲያዳብሩ እያደረግን ነው:: ካወቅንበትና ካወቁበት እስር ቤት አስደናቂ ጀብዱ የምንሠራበት ነው::
ዓለማችን ከእስር ቤቶች ውስጥ ያስተናገደቻቸው ብዙ አስገራሚ ነገሮችም አሉ:: በመጽሐፍ ደረጃ እንኳን ብንመለከት፣ ደራሲያን ከሥራዎቻቸው ሁሉ ‹ምርጥ› የተባሉላቸው መጻሕፍት እስር ቤት ውስጥ ተጽፈዋል:: ደራሲ የመሆን ሀሳቡም ሳይኖራቸው እስር ቤት ደራሲ ያደረጋቸውም ብዙዎች ናቸው:: በተለይ በቀደመው ዘመን አብዛኛዎቹ አንድ ተመሳሳይ ታሪክም አላቸው፤ ወረቀት ለማግኘት አዳጋች ሲሆንባቸው በሲጋራ ማሸጊያ፣ በሽንት ቤት ወረቀትና በጋዜጦች ጠርዝ ባለች መስመር ታግለው ‹አጃኢብ!› የተባለለት መጽሐፍ አውጥተዋል::
በንግግሮቹ ብቻ ሳይሆን በብዕሩም የዓለምን ልብ መርታት የቻለው ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ በርሚንግሃም አላባማ እስር ቤት ውስጥ ሆኖ የጻፈው “ሌተር ፍሮም በርሚንግሃም ጄይል” ዛሬም የሚነገርለት ነው:: አፍሪካዊው የነጻነት አባት፣ ታላቁ ኔልሰን ማንዴላ ደግሞ “ሎንግ ዎክ ቱ ፍሪደም” የተሰኘችው ግለታሪኩ እስር ቤት የተወለደች ናት:: ሁለቱም ተደብቀው ሲጽፉ የነበሩት በጋዜጣና በመጸዳጃ ቤት ወረቀቶች ነበር:: በዚያን ዘመን በሚሊየን ኮፒዎች የተሸጠውና በናዚው አዶልፍ ሂትለር ተጽፎ በ1925 የታተመው “ሜይን ካምፕ(ማይ ስትራገል)” ተጠቃሽ ነው:: ዓለም ከጥቂቶች መካከል የምትጠራው ራሽያዊው ደራሲ ቲዎዶር ዶስቶቭስኪ “ዘ ሃውስ ኦፍ ዘ ዴድ” የተባለች መጽሐፉን ጽፏል:: በ1970ዎቹ አምባገነን ሥርዓት ዘብጥያ የተወረወረውና ከአፍሪካ ምርጥ ደራሲያን መካከል ስሙ የሚጠቀሰው ናይጀሪያዊው ደራሲ ዎሌ ሶዪንካ ከጠባቂ ወታደሩ እስክሪፕቶ ሰርቆ “ዘ ማን ዴድ” የሚለውን ጽፏል:: ብቻ ከተውኔት እስከ መጻሕፍት ዓለምን ያስገረሙ ብዙ ተጽፈዋል:: ላወቀበት እስር ቤት ልዩ ከራስ ጋር የመገናኛ አደባባይ እንደሆነ ለማሳየት ነው::
በማረሚያ ቤቶቻችን ውስጥ መጻሕፍትና ቤተ መጻሕፍት ብቻ ሳይሆን የተለያዩ የጥበብ ማዕከላት ወሳኝ ናቸው:: ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሽመናና በመሰል እንቅስቃሴዎች እንዲሠሩ ምቹ ሁኔታዎችን እያመቻቸን እንዳለው ሁሉ በኪነ ጥበብ ዘርፍም መከወን አለበት:: ታራሚው ሁሉ የሚዝናናበትና መንፈሱን የሚያድስበትን ነገር ይፈልጋል:: ለዚህ ደግሞ ኪነ ጥበብን የሚያህል የለም:: በሙዚቃ፣ በስዕል፣ በትወና፣ በስነ ጽሁፍ የሚሠሩበትን መንገድ ብናመቻችላቸው፣ የኢትዮጵያን የጥበብ ኢንዱስትሪ የሚለውጥ ብዙ ነገር እናገኝበታለን:: ከውጪ ከመጋበዝ እዚያው ባሉ ባለተሰጥኦዎች ራሳቸውን እንዲያዝናኑና ያላቸውንም እንዲያወጡ ቢደረግ በእርግጥም የማናየው አይኖርም:: በሲኒማና ቲያትር ቤቶች አፉን በከፈተ አዳራሽ ‹የተመልካች ያለህ› የምንለውን በተቃራኒው ከማረሚያ ቤቶች ‹የወንበር ያልህ› ሲሆን እንመለከት ነበር:: ‹ውይ ዛሬ እንኳን አልችልም…እዚያ ቀጠሮ አለብኝ…መንገደኛ ነኝ… ሥራ ቦታ…ከጓደኞቼ ጋር ሆቴል፣ ግሮሰሪ ብዝናና ይሻለኛል…› የሚባሉ ሰበባ ሰበቦች እዚያ አይኖሩም:: ድብርት… ጭንቀት… ሀሳብ…ጸጸት…ቁጣውን ሁሉ የሚያራግፍበትን ነገር የሚፈልግ ነውና ጥበብን ወግ ማዕረጓን ሊያሳዩዋት ይችላሉ:: እነርሱንም እንደፊደላቱ ቀርበን እናንብባቸው:: አንብበን ያልተነበቡ ገጽታዎቻቸውን እንግለጥላቸው::
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 12 ቀን 2017 ዓ.ም