
“ሰው ሁሉ ሌላ ሰው ነው:: ውጪው ሌላ ውስጡ ሌላ፣ ኑሮው ሌላ ሕልሙ ሌላ፣ ልቡ ሌላ አፍ ሌላ…” ዓለምና ዓለም ያቀፈችው ሁሉም ሌላ ሌላ ነው:: ምስቅልቅል ባለች ዓለም ውስጥ አይሆንም የሚባል የለም:: “ግራጫ…ነጭ የሚጠቁርበትና ጥቁርም የሚነጣበት ሰፊ ግዛት ነው…” ይላል፤ የዶክተር ምህረት ደበበ “ሌላ ሰው” የተሰኘው መጽሐፉ:: በሀገራችን የሥነ ጽሁፍ ታሪክ ውስጥ፣ በምን ጊዜም ምርጥ የልቦለድ መጻሕፍት ዝርዝር ‹ሌላ ሰው› አንደኛው ነው:: የዘመንን ጥበብ ያደመቁ የብዕር ቀለማት የተሰባጠሩበት ነውና አረንጓዴ… ቢጫ… ቀይ… ሰማያዊ…ወይንጠጅ…ጥቁር አሊያም ነጩን መርጠን ለእራፊያችን መልክ እንሰጣታለን:: ብንቀይጠውም ግራጫ ወይንም ዥንጉርጉር ቅኝት…
ጥቂት ስለ ደራሲው…ዶክተር ምህረት ደበበ በሙያው የአዕምሮ ሕክምና ስፔሻሊስት እና የሥነ ጽሁፍ ጠበብት ነው:: የሕይወት መረቡ የተዘረጋችው በኢትዮጵያና አሜሪካ መካከል ሆነና አንዱን መንፈቅ ለዚህ፣ አንዱን መንፈቅ ለዚያ አድርጎ እኩል ይመላለስባቸዋል:: ዶክተርም ደራሲም ነውና ሁለቱንም ቀለማት አዋዶ “ሌላ ሰው” የተሰኘችውን የተቀመመች መጽሐፉን በ2002 ዓ.ም ለንባብ አደረሳት:: ደራሲው ዶክተር ምህረት ደበበ ብዕሩ በሥነ ልቦናና አዕምሮ ላይ ማረፍን ትወዳለች:: “የተቆለፈበት ቁልፍ” በተሰኘው ረዥም የልቦለድ መጽሐፉ ውስጥም እኚህኑ የአስተሳሰብና አመለካከት ለውጦችን ከራስ ጋር ለማረቅ ታግሎበታል:: “ሌላ ሰው” የተሰኘው የዛሬው መጽሐፋችንም ግለሰባዊ፣ ቤተሰባዊ፣ ማኅበራዊ፣ ሀገራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮቻችንን በያዙ ቀለማት ውብ አድርጎ ስሎታል:: ቀለም ከቀለም፣ ሰው ከሰው ይለያያል:: ቀለምና ቀለም ተዋህደው ሌላ ቀለም፣ ሰውና ሰውም ሌላ ሰውን ያስከትላሉ:: እናውቀዋለን ያልነው አንዱ ሰው ደግሞ ውስጡ የማናውቀው ሌላ ሰው አለ::
የመጽሐፉ ዋና ገጸ ባህሪ “ዶክተር ሌላ ሰው” ይሰኛል:: “ሁሉም ሰው ሌላ ሰው…ሌላ ሰውም አንደኛው ሰው ነውና” ‹ሌላ ሰው› በሙያውና በገሚስ ማንነቱ ራሱ ዶክተር ምህረት ደበበን ይመስላል፤ ቢመስልም ሌላ ሰውም ሊሆን ይችላል:: የመጽሐፉን ከ‹ሀ-ፐ› ታሪክ፣ መቼት፣ ግጭት፣ ሴራ…እያንዳንዷን ጠብታ የሚተርክልን ግን የደራሲው ምናባዊ አንደበት ነው:: ይህም ተራኪው እንደፈጣሪ በሁሉም ቦታ የመገኘትና ሁሉንም የማወቅ ሥልጣን ይሰጠዋል፤ የሚደረገው ብቻ ሳይሆን በልብ የታሰበው ሁሉ አይቀረውም:: መጽሐፉ በገጸ ባህሪያት በሚላወስ ልብ አንጠልጣይ ታሪኮቹና በአጻጻፍ ዘውጉ ‹ልቦለድ› እንበለው እንጂ፤ የተሠራበት እያንዳንዱ ቅንጣት የገሃድ ሀቆች ናቸው:: ምናልባትም ከራሱ ሕይወትና በሙያዊ የዕለት ተዕለት ውሎና አዳር ውስጥ ያከማቻቸው ናቸው::
‹ዶክተር ሌላ ሰው› ገና ከጅምሩ ደራሲው ያሸከመውን ግራጫ የሕይወት መስቀል ተሸክሞ፣ ከአሜሪካ ኢትዮጵያ በተወጠረው የታሪክና መቼት ችንካር ላይ ቸንክሮታል:: ዶክተር ሌላ ሰውም በሦስት ማዕዘን የሕይወት ሳጥን ውስጥ ሟችም አዳኝም ለመሆን ሲታገል እንመለከተዋለን:: እህት፣ ሚስትና ሁለት ልጆቹ ከአሜሪካ በአንደኛው ማዕዘን፣ በሁለተኛው የማዕዘን ጫፍ ደግሞ ብቅ እያሉ የሚጠፉና ከመሃል መንገድ ተቀላቅለው የሚዘልቁ ገጸ ባህሪያትና ታሪኮች፣ ከሙያው ጋር ተያይዘው ከየአቅጣጫው ወደ ሌላ ሰው ይነጉዳሉ:: ከሁለቱም ማዕዘናት እየወረዱ እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኘው ዶክተር ሌላ ሰው ዘንድ ይደርሱና የሚጋጩባት ቀለበት ላይ ሦስተኛውን ማዕዘን ይሠራሉ:: ግጭትና ሴራ፣ ድርጊትና ስሜት እየተፋጩ ሽቅብ ወደ ጡዘት ያመራሉ::
ውጥንቅጡ ሲጀማምር እህቱ ከአሜሪካ ደውላ፣ ኢትዮጵያን ጥሎ ያልመጣ እንደሆን አሜሪካ ያሉ ሚስትና ልጆቹን ዳግም እንደማያገኛቸው አስረግጣ በጨቀጨቀችው ንግግር ነው:: እያወራ ሳይታወቀው በር ከፍቶ ከቤት ከሰፈሩ ወጣ:: ርቆ ከሄደ በኋላ ድንገት ስልኩ ተቋረጠና የእጅ ስልኩን “…አየት አደረገውና ከእጁ ላይ አሽቀንጥሮ ሊወረውረው ፈለገ::” ስሜቱ ንሮ ወደ አንዲት ሱቅ ሄዶ ፓኮ ሲጋራም ገዛ:: “ከአሥራ አምስት ዓመት በኋላ ሲጋራ በእጁ ሲነካ ለመጀመሪያ ጊዜው ነው::” ከአንዲት ካፍቴሪያ በረንዳ ተቀምጦ ሲጋራዋን እያነደደ፣ በምትግተለተለው ጭስ ውስጥ ታፍኖ “…የውስጥ ስቃዩን ሊደብቅ ፈለገ::” ውስጡ የተወጠረው የስቃይ ስሜት ግን በዚህ ብቻ የሚበጠስለት ይመስለዋል? ጭንቀቱን ለመርሳት ይህ ብቻ በቂ እንዳልሆነ ሌላ ሰውም ተረድቶታልና በሲጋራው እሳትና ጭስ ከማሽን ውስጥ የሚነፍረውን እንደወረደ ቡና አዘዘበት:: “መራራውን ጥቁር ቡና በትኩሱ ፉት ፉት ብሎ ጨለጠው::” አሁንስ? የውስጡ እሳት በሲጋራና ቡና ተዳፈነለት? የዶክተር ሌላ ሰው ድርጊት ‹እሾህን በእሾህ› የመንቀል ሳይሆን ‹ስለትን በስለት› በመቁረጥ ስልነቱን ይጨምር እንደሆን እንጂ መች ሊያዶለዱምለት…
የሌላ ሰውን የአሜሪካ ኑሮ አስጥሎ እዚህ ያናወዘው ነገር አባቱና መከረኛው የአባቱ ደብዳቤ ነበር:: “…ባለፉት አሥራ ሦስት ዓመታት ሙሉ ወህኒ በነበርኩበት ጊዜ ይህንን ሁሉ እያሰቡ ከመንገብገብ በቀር ምን ሥራ ነበረኝ ብለህ ነው ልጄ?…ሀገሪቱ የደማች የቆሰለች ብዙ ሕክምና የሚያስፈልጋት ናት:: …ልጄ ሙያህን የፈረንጅ ሀገር ሐኪም ሆነህ ያሜሪካንን ምቹ ኑሮ ለማጣጣም ብቻ ብትጠቀምበት ትልቅ ክስረት ነው:: አቅም ሳይከዳህ፣ ጉልበትህ ሳያልቅ ወደ ሕዝብህ ተመለስ፤ ወደ ሀገርህ ግባ:: የቆሰለውን የሀገሪቱን ነፍስ እያከማችሁ የተፈረካከሰውን የኢትዮጵያዊነት ክብርና ማንነት ፈልጋችሁ ከወደቀበት አንሡት:: …የኢትዮጵያንና የልጆቿን ፈውስና እድገት፣ ብልጽግናዋንና ከፍታዋን በሰው ሕይወት ክቡርነትና እኩልነት ላይ መሥርቱ:: …ሰውነት ከጾታና ከዕድሜ በላይ ነው፤ ከብሔርና ቋንቋ ይረቃል፤ ከቁሳዊ ሀብትና ሃይማኖታዊ ቀኖናም ይገዝፋል:: ያንተ ሥራ ይህንን በየልቦናውና በየቤቱ እንደገና መፍጠር ነው” በማለት አባቱ ይህን አደራ አውርሰውታል:: ሌላ ሰው ደብዳቤውን አንብቦ ሲጨርስ ግን ዝብርቅርቅ ስሜት ውስጥ ገባ:: “የትናት ጸጸትና ጥፋት በነገ ተስፋና ሕልም ማከም ይቻላል ብሎ ለማመን ከራሱ ጋር ግብግብ ገጠመ:: …ተስፋ መቁረጥና መሸነፍን አማራጭ አድርጎ ማየት ግን አልፈለገም::”
‹ቃል የእምነት እዳ ነው› ደግሞም ባሕላችን ‹ቃል ለሰማይ ቃል ለምድር…› ብሎ የተገዘተ ነው:: የኑዛዜ ቃል ደግሞ እዳ ብቻ ሳይሆን የሕሊና ፍዳም የሚያስከትል ነው:: እና በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ተወልዶ ለኖረው ዶክተር ሌላ ሰው ይህን ቃል ወዲያ አሽቀንጥሮ የራስን ኑሮ ማደላደል እንደምን ይቻለዋል? እርሱም ይህንኑ አውቆ፣ አባቱ ከሞቱ ከዓመታት በኋላ የአሜሪካውን ምቹ ኑሮ ጥሎ ወደ እናት ሀገሩ እቅፍ ገባ:: በእርግጥ እቅፉ የሚያሞቅ ሳይሆን የሚባረድ፣ የሚያመቻች ሳይሆን የሚቆረቁር ሊሆን ይችላል:: ምክንያቱም “ሀገሪቱ የደማች የቆሰለች ብዙ ሕክምና የሚያስፈልጋት ናት…” ብለዋል አባቱ::
ሌላ ሰው ራሱ ውስጡን ታሞ፣ ሌሎች ወንድም እህቶቹን ለማከም አንዲት ክሊኒክ ውስጥ ሥራውን ጀምሯል:: ይህቺ ክሊኒክ ግን፤ እንደ ሆስፒታልና ጤና ጣቢያ የታመመን አካል፣ ስጋን ማከሚያ ብቻ አይደለችም:: ውስጧ ሰምና ወርቅ ነው:: በወርቋ ውስጥም፤ በታመመች ሀገር የሚኖሩ የታመሙ ልቦች፣ የተረበሹ መንፈሶች፣ የተወላገዱ አዕምሮና የሥነ ልቦና ቀውሶችን ለመሻር ትግል የሚደረግባት ናት:: ዶክተር ሌላ ሰው መርፌ ጨብጦ የሚዋጋው ከታይፎድና ታይፈስ አሊያም ከግለሰባዊ የአዕምሮና የሥነ ልቦና ቀውሶች ጋር ብቻ ሳይሆን እነርሱን ከመሳሰሉ ግላዊ፣ ቤተሰባዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ከሆኑ የአመለካከትና አስተሳሰብ ባክቴሪያና ጀርሞች ጋርም ጭምር ነው::
ወደ ክሊኒኩ የሚመጣው ብቻ ሳይሆን ዶክተር ሌላ ሰውም በራሱ የውስጥ ሕመም የሚሰቃይ ነው፤ በአንድም ሆነ በሌላ ሁሉም የራሱ የሆነ ሌላ ችግር አለበትና:: ባሕር ውስጥ ከሰጠመች መርከብ ላይ ሆኖ ትግሉ ራስን ወይንስ ሌላውን ለማዳን? አንዳንዴ…ከትልልቅ ታሪኮች ውስጥ የሚወጡ ሌሎች ትንንሽ ታሪኮች፤ በትንሽ ልብ ውስጥ ትልቅ ፍቅርን ይሠራሉ:: የግል ሕይወቱን ካመሰቃቀሉት ጉዳዮች አንዱ በእናትና እህቱ ሴራ ጥሏት ወደ አሜሪካ የሄደባትን የልጅነት ፍቅሩን ገነትን ፈልጎ የማግኘቱ ነገር ነው:: ታዲያ ሚስቱስ? “እኔ እኮ ገነትን አገኛለሁ ብዬ ስነሳ ንጹሕን አጣለሁ ብዬ አይደለም:: …‹እውነት ታዲያ ምን ፈልጌ ነው?› አለ በውስጡ” ይለናል ተራኪው:: ገነት…ሚስትና ልጆቹ… እህቱ…የአባቱ አደራ…ክሊኒኩ…ሌላም ሌላም በቅስት ወጥረው ይዘውታል:: ሌላ ሰው የአሜሪካ ኑሮውን ጥሎ ሲመጣ እንደ ነብስ አድን ሠራተኛ ቢሆንም፤ ክሊኒኩና ሌላም ያስከተሉበት ጣጣ፣ እርሱንም የሚረዳውና ጎኑ የሚቆምለት ሌላ ሰው አስፈልጎታል፤ የሚያዋየው እህ! ብሎ የሚያደምጠው:: ሌላ ሰው…ሌላ ልባም ሰው ያስፈልገዋል:: ምናልባት ወዳጁና ባልደረባው ምስጢር ትሆን?
ከሌላ ሰው እራፊ ታሪኮች መካከል ሌላ አንዲት ምስኪን ሴት ትገኛለች:: እርሷም ‹ዝናሽ› የተሰኘችው ገጸ ባህሪይ ናት፤ የማትረሳ፣ አሳዛኝ ምስኪን ነብስ:: እና ዝናሽ የማን፣ ምንድናት? ዝናሽ የአዕምሮ ታማሚ ናት:: ዝናሽ ነፍሰጡር ናት:: ታዲያ ምን ሆነች? …ሞተች:: የሞተችው ግን በምን ምክንያት ነበር? በወሊድ ወቅት በፈሰሳት ብዙ ደም ሳቢያ ላትመለስ እስከወዲያኛው አሸለበች:: እና ግን ስለዚህች ነብስ፣ ምኑም ስላልገባው ጨቅላው ሕጻን ማንስ ይጠየቅ? ለዚህ ጥያቄ ግን እንደሌሎቹ በቀላሉ መልስ የምናገኝለት አይደለም:: ብዙ ማወቅ፣ ብዙ ማሰላሰል፣ መርማሪም፣ ዳኛም መሆንን ሊኖርብን ነው:: ‹የተራኪው ዓይኖች ከሁሉም ቦታ ተገኝተው ሁሉን የሚያዩ ናቸው› ብለናልና የተሻለው አማራጭ ሕሊናችንን የእውነት ሚዛን ላይ አስቀምጠን የተራኪውን እውነት መከተል ነው::
ስለ ዝናሽ ከሚነገርን ሀቆች ውስጥ አንዱ ከአማኑኤል ሆስፒታል ሪፈር ተጽፎላት ወደ ሁለት ሆስፒታሎች እንደሄደችና በዚያ ግን የአዕምሮ ታማሚ ስለሆነች ብቻ እንደሌሎች እናቶች ትኩረትና ተገቢውን ሕክምና የሚሰጣትን የጤና ባለሙያ ስለማጣቷ ነው:: “አእምሯቸውን በታመሙ ሰዎች ላይ የጤና ባለሞያዎች እንኳን ሳይቀር እንደዚህ የሚጨክኑት ለምንድነው?” ሲል መልሶ ይጠይቃል:: በዚህ ጥያቄ ብቻ ሳይቆምም፣ በስሜት ሽቅብ እየነደደ “…ሰው አይመስሏቸውም ማለት ነው? ልቡን፣ ጉበቱን ለታመመው የሚራሩ ሰዎችስ ለምንድነው አእምሯቸው በታመመ ሰዎች ላይ የሚጨክኑት? ጋኔን ተሸክመው፣ እርግማን አዝለው የሚዞሩ ስለሚመስላቸው ይሆን?” እንጃ:: እንጃላቸው:: እንጃልን::
ሙያና ዕውቀት አለኝ ብለን እግዜርን የምንፈታተን:: ሃይማኖተኛ ነኝ እያልን ሃይማኖት የማያውቀን:: ሰብአዊ ነን ስንል ሰብአዊነት ያልነካን:: የርህራሄና ደግነት ልብ አለኝ ስንል ባዘቶአም ደረቅ ወይራ ውስጣችን የተሸከምን…ሌላም ሌላም ዓይነት ሰዎች ነን:: ለምን? ዝናሽ ስትሞት ከመሃከል ግድ የሚለው አንድ ሐኪም ለምን ጠፋ? ቀድሞውኑ የአዕምሮ ታማሚዋን የሚያስረግዝ እንዴት ያለው ስብእና ነው? ከዚያስ በኋላ፤ የደግነት ሁሉ ጥግ አድርገን የምንዘምርለት የማኅበረሰባዊ እሴታችን ርህራሄ ዝናሽን ምን አላት? ምንስ ፈየደላት? …ምንም…ምክንያቱም እንዲህ ባሉ በደሎች ውስጥ አብዛኛዎቻችን ከሳሾች እንጂ የሕሊና ዳኞች አንሆንም:: ደግነትን እናጎራጉራለን፤ ግን ግጥምና ዜማውን አናውቀውም::
“አሁን ዝናሽ የአእምሮ ሕመምተኛ ባትሆንና ገንዘብ ያላት የተማረች ነፍሰጡር ብትሆን የጥቁር አንበሳው ተረኛው ዶክተር ሳያያት በግዴለሽነት ይመልሳት ነበር? ጳውሎስ ሆስፒታልስ ያን ያህል ጊዜ እንደወደቀ እቃ ተጥላ በደሟ እንደተነከረች ትረሳ ነበር? የሰው ዋጋ የሰው ያህል እንዲሆን ገንዘብ…ዘመድ…ሥልጣን…ታዋቂነት…የመሳሰሉ ኮተቶች ያስፈልጋሉ ማለት ነው?” ይሄም መልሱ እንጃልን ነው:: አንዳንዴ ወይንም ብዙ ጊዜ ግን፤ ጎበዝ፣ ብርቱ ባልነው የማዳንን ጥበብ በያዘ ሐኪም ውስጥ ሌላ የማናውቀው ነብሰ ገዳይ ሐኪም ይኖራል:: ቅዱስ ነው ብለን በምንከተለው የሃይማኖት ፊታውራሪ ውስጥ ለሲኦል የከበዱ የመናፍስት መንጋ ይኖሩ ይሆናል:: በእውነትና በሀቅ ለመፍረድ በመሃላ ችሎት ከተሰየመው ዳኛ ውስጥ የወንጀለኞች ወዳጅ፣ ሆድ አምላኩ የሆነ ሌላ ዳኛ ሲኖርም እንመለከታለን:: ሀገር ለማዳን ሲሉ በስጋና ነብሳቸው እስከ እሳት የቆረጡ የመሰሉን፣ ውስጣቸው የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች የሚፈረጥጡበት ሜዳና መጨረሻቸው ሀገርን ዶግ አመድ ለማድረግ ያሴሩ አፍራሽ ግብረ ኃይል…ይህም ሊሆን የሚችል ነው:: ነገር ግን፤ ሁሉንም ሐኪምነት፣ ሁሉንም ዳኝነት፣ ሁሉንም ፖለቲካ…እዚህ የማንነት አዙሪት ውስጥ አስገብቶ ጅምላ የመረሸን እንዳልሆነ ልብ ይሏል:: ትልቁ ነገር፤ የምናውቀው የትኛውን ሰው ነው? ከምንታወቅበት ነገር አንጻር እኛስ የምንኖረው ሙያዊ ኃላፊነታችን መልኩ ምን ይመስላል ነው?
ከጥንት አባቶቻችን የተቀበልነውና ዛሬ ለልጅ የምናስተላልፈው ውርስ ምን ይሆን? ‹የአባት እዳ ለልጅ› ዓይነት ነገር? ትናንት ምንም ይሁን ምን ባለችን ዛሬ፣ የምትመጣን ነገን ማቅናት እንደምንችል የሌላ ሰው አባት አሳይተውናል:: በእኔ ዘመን የተበላሸና ጥፋተኛም ነኝ ብለው ሲጸጸቱበት የነበሩበትን ነገር በልጃቸው ለማቅናት መላ ዘይደው አንድ መስመር አበጅተዋል:: በፖለቲካው ለውጥ ለድፍን 13 ዓመታትን በእሥር ሲቆዩ፣ ለራሳቸው ከማኩረፍ ይልቅ ሀገር ከፖለቲካ በላይ ናት በማለት ያደረጉት ነገር የሀገር ፍቅር ምን ማለት እንደሆነ እየነገረ ያስደምመናል:: ጀግና አባት ጀግና ልጅ ወለዱ ሳይሆን ሠሩ::
‹ከራስ በላይ ንፋስ› ሳይሆን ‹…ሀገር› መሆን አለባት:: ቀላል ነገር በሚመስለው የሌላ ሰው ውሳኔ ውስጥ ለሀገር መስዋዕትነት ጦር ሜዳ ብቻ ሳይሆን በተገኙበት ሁሉ እንደሆን ማሳያ ነው:: ከሌላት ተቆርሶ በየዓለማቱ የተማረ ስንቱ፣ ከአውሮፓና አሜሪካ ፈርጥጦ የራሱን የማይሞላውን የኑሮ አኮፋዳ ለመሙላት ሲርመሰመስ፣ ዶክተር ሌላ ሰው ግን የተደላደለ ኑሮውን ጥሎ ስቃይ መሃል ለመኖር መወሰኑ ሀገር ወዳድነት ብቻ ሳይሆን ትልቅ ጀግንነት ነው:: ዳር ቆመን ‹ሀገሬ ሀገሬን…› ስላልን ብቻ ሀገር ወዳድ አሊያም አርበኛ አያደርገንም:: የተማረው ሁሉ ጥሎ ሀገር ሲጠፋ ‹ታዲያ ለማን ብሎ እዚህ ይሰቃይ› ለምንል አጋጣሚና ዕድል ጠባቂዎችም ሆንን ተምረን በውጭ ለምንበሰብስ፣ ሀገራችን ከእኛ ውጪ የሚመጣላት ሌላ ማንም እንደሌለ እንወቅ:: ሁሉም የሚማረው ለሻንጣ መግዣ ከሆነማ ትምህርት ቤቶቻችን እና ዩኒቨርሲቲዎቻችን ሁሉ ክስረት ናቸው:: ዳሩ ግን “…ካመለጠ ትናንት ያልመጣ ነገ ይሻላል:: በእጅ ያለ ዛሬ ግን ከሁሉም ይበልጣል” ይለናል ሌላ ሰው፤ ልክ እንደ አባቱ ያመለጠንን በሚመጣው አክመን እንድንሽረው::
የሥነ ጽሁፍ ጉልበት፣ የጥበብ ኃያልነት እንዲህ ነውና ከመሃከል ባነሳናት አንዲት ወይንም ሁለት ቀለማት እራፊያችን ሞላች:: እንቁራሪቷን አግዝፈን ዝሆን፣ አሊያም ትልቁን ዝሆን አሳንሰን እንቁራሪት አድርገን ሊሆን ይችላል እንጂ ሌላ ሰው ከያዘው አንጻር ግን ምኑም አልተነካም:: የያዝነውም እራፊውን ጨርቅ እንጂ፤ የመጽሐፏን መላ አካል የሚሸፍን ሽንሽን ቀሚስ አነበረምና:: የሌላ ሰው ዓለም ውስጡ ሌላ ነውና ቀሪውን አንብበን እንድረስበት
በሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 28 ቀን 2017 ዓ.ም