አገራችን የበርካታ ሃብቶች ባለቤት ናት።የአገራችን መልክአምድራዊም ሆነ የአየር ንብረት ለምርታማነት ምቹና ከራስ አልፎ ለሌሎች መትረፍ የሚያስችል ነው።ለእርሻ ስራ ሊውል የሚችለው መሬትና የተፈጥሮ ሃብት ሰፊ ነው።ከዚህም ባሻገር ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው የአገራችን ህዝብ ወጣት ሃይል በመሆኑ ሃገርን ለማሳደግ ትልቅ አቅም ነው፡፡
ይህ በሆነበት ሁኔታ በሀገሪቱ ለአመታት በነበረው የፖለቲካ ቁርሾ ፣ ያልተረጋጋ ፖለቲካ እና የኢትዮጵያን ማደግ የማይፈልጉ የውጭ ሃይሎች ረጅም እጅ ባለን ተፈጥሯዊ ጸጋ ተጠቅመን ከማደግና፣ በእድገታችን አንገታችንን አቅንተን ከመሄድ ይልቅ አሁንም ድህነት ሊያስከፍል የሚችለውን ዋጋ ሁሉ ለመክፈል ተገደናል ፡፡
አሁን አሁን ደግሞ በቀደመው ዘመን የሰላምና አብሮነት መገለጫ የነበሩ አካባቢዎች ሳይቀሩ የግጭት አውድማ ሆነዋል። ከነዚህ አካባቢዎች አንዱ ደግሞ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የመተከል ዞን አንዱ ነው ።በመተከል ዞን ለውጡን ተከትሎ በተፈጠሩ ያለመረጋጋት ችግሮች በርካታ ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ተፈናቅለዋል፡፡
በአንድ በኩል ስለ ልማት በብዙ በሚዜምባቸው ከለውጡ በፊት በነበሩት 27 አመታትም ሆነ ከዚያ በፊት የአካባቢውን ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች አለማካሄዳቸው ፣ ከዚህም የተነሳ የአካባቢው ነዋሪ በከፋ ድህነትና ኋላቀርነት ውስጥ መኖሩ ፡፡
ከዚህም ባሻገር የውስጥና የውጭ ሀይሎች በአካባቢው የነበረውን የብሄር ብሄረሰቦች አብሮነት ችግር ውስጥ በመጨመር ቀጠናውን የአለመረጋጋትና የግጭት ቀጠና በማድረግ የተጀመረውን ሀገራዊ የለውጥ ጉዞ ለማደናቀፍ አካባቢውን የተሻለ አማራጭ አድርገው በስፋት ተንቀሳቅሰዋል ።
በዚህም ለዘመናት አብሮ የኖረውን ህዝብ በቆዳ ቀለም በመከፋፋል አንዱ በአንዱ ላይ እንዲነሳ፣አንዱ በአንዱ ላይ የጭካኔ በትር እንዲያሳርፍ በዚህም ሞትና መፈናቀል የአካባቢው መለያ እንዲሆን አድርገዋል ።በህዝቦች መካከል እርስ በርስ በጥርጣሬ እንዲኖር ሰርተዋል፡፡
ዞኑ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሚገነባበት ስፍራ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የብዙ የውጭ ሃይሎች በተለይም የግድቡን ግንባታ እውን መሆን የማይፈልጉ ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ትኩረት የሳበ ነው። ሀገሪቱን ቀውስ ውስጥ በማስገባት ግንባታውን ለማደናቀፍ ለሚፈልጉ ሀይሎችም የተሻለ አማራጭ የሆነ ነው ፡፡
በተለይ “እኔ ሀገር ካልመራሁ ሃገር ትጠፋለች፣ ካለእኔ እውቅና ማንም ይህችን አገር መምራት የለበትም” የሚል የእብሪት አስተሳሰብ ያዳበረውና በዚሁ እብሪቱ በመጨረሻ በርካቶችን አጥፍቶ ራሱ የጠፋው የህወሓት ጁንታ በአካባቢው ለተከሰተው ጥፋት ዋናው ባለድርሻ ነው ።
የመተከል ዞን የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች በአንድነት በፍቅርና በመተባበር የሚኖሩበት የትንሿ ኢትዮጵያ ተምሳሌት
ተብሎ የሚጠራ ቢሆንም የጁንታው ቡድን በፈጠራቸው የተሳሳቱ ትርክቶች የተጠለፉ ሀይሎች አካባቢውን ለታሪክ እንግዳ በሆነ መልኩ የጥፋት አውድማ አድርገውታል።
መንግስት ችግሩን ለመፍታት በርካታ ሙከራዎችና ጥረቶችን አድርጓል።ችግሩ በተፈጠረባቸው ጊዜያት ከአንድም ሶስት ጊዜ በአካባቢው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ሆኖ እንዲተዳደር ወስኗል ።
ከዚህም አልፎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጭምር በርካታ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በቦታው በመገኘት ከአካባቢው ማህበረሰብ ፣ ከሃገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች ጋር ምክክር አድርገዋል፡፡የጥረቱን ያህል መፍትሄ ባለመገኘቱም በሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ የሚመራና የተለያዩ አካላት የተሳተፉበት የተቀናጀ ግብረ ሃይል በማቋቋም አካባቢውን ወደሰላማዊ ኑሮ የመመለስ ስራውን መስራት ጀምሯል፡፡
ግብረ ሀይሉ ባለፉት አርባ ቀናት በአካባቢው በነበረው ቆይታ አካባቢውን ወደ ቀድሞ ሰላምና መረጋጋት መመለስ የሚያስችሉ በርካታ ስራዎችን አከናውኗል።ከነዚህ መካከል ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ የማስጠበቅ፣ የፀጥታ መዋቅሩን ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ላይኛው መዋቅር ድረስ ያለውን የአስተዳደር መዋቅር በአዲስ መልክ መልሶ የማደራጀት እንዲሁም ህብረተሰቡን የማረጋጋት ስራ ሰርቷል፡፡
በተለይ የፀጥታ ስራውን በተመለከተ አካባቢውን ነዋሪ የሚመስል ሚሊሻ በማዋቀር ህብረተሰቡ ራሱን በራሱ የሚከላከልበት አሰራር በመዘርጋት ተግባራዊ እያደረገ ነው ።ከዚህም ጎን ለጎን አመራሩን የማጥራት ስራም እያካሄደ ይገኛል። ባደረገው የማጥራት ስራ እስካሁን 42 አመራሮችን በህግ ጥላ ስር በማድረግ ምርመራ እየተደረገ ይገኛል ። በጥፋት ውስጥ የነበሩ ሀይሎችም እጃቸውን ለግብረሃይሉ በመስጠት ላይ ናቸው ።
ግብረሀይሉ በአካባቢው በነበረው ችግር ከቀዬኣቸው ተፈናቅለው የሚገኙ ዜጎችን ለመመለስ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እያካሄድ ይገኛል።የሰብአዊ ድጋፍ ከማድረስ ባለፈ ተገፈናቃዮች ወደ ቀድሞ ቄያቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ እያመቻቸ ይገኛል ። በተለይ ወደ ቄያቸው ከተመለሱ በኋላ ዳግም ተመሳሳይ ችግር እንዳይከሰት ለማድረግ ሰፊ ስራ እየተሰራ ነው፡፡
በግብረሀይሉ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችና እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች የሚያበረታቱ ቢሆኑም አሁንም ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልጉ ጉዳዮች መኖራቸው አጠያያቂ አይደለም ። ችግሩ የብዙ ሀይሎች ፍላጎት ያለበት፣አጠቃላይ ከሆነው ሀገራዊ ለውጥና ለውጡ ይዞት ከመጣው አስተሳሰብ ጋር የሚቃረን ከመሆኑ አንጻር ሰፊ አስተሳሰብ የማጥራት ስራ የሚፈልግ ነው።
ከችግሩ ማንም ተጠቃሚ እንደማይሆን ካለፈው ትምህርት መውሰድና በቀጣይ እንዲህ አይነት ችግር እንዳይደገም ተቀናጅቶ መስራት ከሁሉም ይጠበቃል።ሴረኞች በሚጎነጉኑት ተንኮል በመጠለፍ መገዳደል እና መፈናቀል በአካባቢው ሊያበቃ ይገባል።
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2013