ኢያሱ መሰለ
መነሻዬ አዲስ አበባ ከተማ ስትሆን መድረሻዬ ከአዲስ አበባ በስተደቡብ የምትገኘው ወላይታ ሶዶ ከተማ ነች። የሰበታ፣ አዋሽ፣ ጢያ፣ ቡኢ፣ ቡታጂራ፣ ዱራሜ፣ ሀላባ፣ ቦዲቲ ከተሞችን እያቆራረጥን ከአምስት ሰዓት የመኪና ጉዞ በኋላ በከተማዋ እምብርት ላይ ተገኘን።
ወላይታ ሶዶ በደቡብ ክልል ከሚገኙ ማራኪና ታሪካዊ ከተሞች አንዷ ነች። የዳሞት ተራራን ተንተርሳ የምትገኘው ይህቺ ከተማ እፍግፍግ ባሉት ቤቶቿ እና ትርምስምስ በሚሉት ነዋሪዎቿ ትንፋሿ ሞቋል።
ልክ እንደሌሎች ከተሞች ሁሉ በዚች ከተማም ዝብርቅርቅ የህይወት መልኮች ይታያሉ። የፈኩ አንዳንዴም የተከፉ ፊቶች፤ የሚሯሯጡ እግሮች፣ የሚሰሩ እጆች፣ የሚቆሙ ወይም የሚዝናኑ ሰዎች ወዘተ በጎዳናዎች ላይ ይስተዋላሉ። ሞተር ብስክሌቶች፣ ባጃጆችና መኪኖች ወዲያ ወዲህ ይጦዛሉ።
ከተማዋ የዳሞት ተራራን ተገን አድርጋ ስለምትኖር እንዲህ ቀረብ ብለው ካላይዋት በስተቀር ገመናዋ በቀላሉ አይታይም። በተለይም በመኖሪያ ቤቶች አካባቢ ህይወት ምን አይነት መልክ እንዳላት ለማወቅ ሆድ እቃዋ ካልተበረበረ በስተቀር ማወቅ አይቻልም።
‹‹የእናት ሆድ ዥንጉርጉር ነው›› እንዲሉ ወላይታ ሶዶ ከተማ ከኑሮ ጋር ግብ ግብ ፈጥረው በአጭር ጊዜ ያሰቡበት የደረሱ በርካታ ባለጸጋዎችን አፍርታለች፤ ኑሯቸውን ለማሸነፍ በበርካታ ውጣውረድ ውስጥ አልፈው ምንም ጠብ ያላለላቸው ምስኪኖችንም በጉያዋ አቅፋለች ።
በተሰጠኝ መረጃ መሰረት የአንዲት ምስኪን እናት ታሪክ ውስጤን ስለነካኝ የዚህ አምድ እንግዳ ላደርጋት በማሰብ ወደ ቤቷ አመራሁ። መረጃውን ከነገረኝ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሾፌር ጋር ሆነን የአጥር በሩን አንኳኳን። የተጎሳቆለ ፊት፤ የተጎሳቆለ አለባበስ ያላት እናት ከተቀመጠችበት ተነስታ በር ከፈተችልን፤ በጠባብዋ ግቢ ያለስራ የተቀመጠ አንድም ቦታ የላትም፤ በጎመን ፣ በቃሪያ እና በተለያዩ የጓሮ አትክልቶች ተሸፍናለች።
ይህች ምስኪን እናት የቤተሰቧን የእለት ጉርስ ለመሸፈን ስትል በጠባብዋ ጊቢ ሳይቀር ከህይወት ጋር የምታደርገውን ትግል አስገረመኝ፤ የነበረችኝን ጥቂት ሰዓት ለመጠቀም የመጣሁበትን ምክንያት ነግሬያት ወደ ጉዳዬ ገባሁ።
ጥያቄዎቼን ቀጠልኩ፤ ጎስቋላዋ እናት እያለቀሰች የህይወቷን መልኮች ታሳየኝ ጀመር፤ እንዳታለቅስ ላረጋጋት ብሞክርም አልሆነም፤ ብሶቷ ነውና ምንም ማድረግ ስላልቻልኩ እንደዚያው ቀጠልን።
ጫልቱ ወርቁ ትባላለች። ተወልዳ ያደገችውና ትዳር መስርታ መኖር የጀመረችው በዚሁ በወላይታ ሶዶ ከተማ ነው። አሁንም በዚሁ ከተማ ዋዱ ቀበሌ መንደር ሁለት ነዋሪ ነች። ጫልቱ ባለትዳር እና የስድስት ልጆች እናት ነች። ባለቤቷ ተድላ ሂዶቶ የመከላከያ ሰራዊት አባል የነበረ ሲሆን በአንድ ወቅት ጭንቅላቱ ላይ ቆስሎ ቀዶ ጥገና እንዲያደርግ ሲነገረው ህክምናው ለሌላ አደጋ ይዳርገኛል በማለት በራሱ ጊዜ ያለ ጡረታ ሥራውን ለቆ ለመውጣት እንደተገደደ ትናገራለች።
ከጊዜ በኋላ በዚሁ ምክንያት የእዕምሮ ህመምተኛ ይሆናል። የጭንቅላቱ ህመም አይኑን ይጋርደው ጀመር። ጫልቱ ባለቤቷን እንዲያሳክሙላት በአካባቢው የሚገኙ በጎ አድራጎት ድርጅቶችን ትማጸናለች። ችግሯን የተመለከተው ኮምፓክሽን በጎ አድራጊ ድርጅት ተድላን በሚኒሊክ ሆስፒታል እንዲታከም ከረዳው በኋላ የአይኑ ህመም መጠነኛ ለውጥ የመጣ ቢሆንም የአእምሮው ችግር ግን መሻሻል ሳይታይበት ይቀራል። በዚሁ የተነሳ ሥራ ሰርቶ መኖር እንዳልቻለና የተወለዱት ስድስት ልጆችም በእርሷ ጫንቃ ላይ እንደወደቁ ጫልቱ ትናገራለች።
ብርቱዋ ሴት ሁለት ልጆቿን ለእናቷ ሰጥታ አራቱን ለማሳደግ ትግሏን ትጀምራለች። ቋሚ የምትለው ሥራ የላትም የቀን ሥራ፣ ጽዳት፣ ጉሊት ወዘተ እየሰራች ኑሮዋን ለማሸነፍ ትጣጣራለች። በዚህ ሥራዋ የቤት ኪራይ፣ የባልዋንና የልጆቿን የእለት ጉርስ፣ የትምህርት ቤት ወጪ መሸፈን ያቅታታል።
በዚህም ጫልቱና ቤተሰቦቿ ለከፍተኛ ችግር ይጋለጣሉ። ምግብ እና ማረፊያ ቦታ እስከማጣት ይደርሳሉ። ይህን ችግሯን የተረዱ የአካባቢው ነዋሪዎች ታዲያ የእድር እቃ የሚቀመጥበትን ቤት እስከተወሰነ ጊዜ እንድትኖርበት ይፈቅዱላታል።
ጫልቱ በዚያች ቤት ውስጥ መኖር መጀመሯ እፎይታን የፈጠረላት ቢሆንም አሁንም የቤተሰቧን የምግብና የተለያዩ ፍላጎቶች ማሟላት ያቅታታል። የልጆቿ ፍላጎት እየጨመረ የጫልቱ ችግር እየበረታ መጣ።
የተወሰኑት ልጆቿ በበጎ አድራጎት ድርጅት የተወሰኑትም በግለሰቦች የመረዳት እድል አገኙላት። በተለይም ቢላቭድ ኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት ለልጆቿ እገዛ ያደርግላቸው እንደነበር የተናገረችው ጫልቱ፣ ድርጅቱ በኮረና መከሰት ምክንያት ድጋፉን ካቋረጠ በኋላ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደወደቀች ትናገራለች። ቢላቭድ ኢትዮጵያ ልጇቿን በማስተማር ብቻ ሳይሆን አልፎ አልፎም የምግብ ድጋፍ ያደርግላት ነበር።
በሌላ በኩል ደግሞ ልጆችዋ በትምህርታቸው ስመ ጥር እየሆኑ መጡ። እናቷ ጋር ያደጉት ሁለቱም ልጆቿ ዩኒቨርሲቲ ገቡ። አንዱ የ7ኛ ዓመት የሜዲሲን ተማሪ ሲሆን ሌላውም የ4ኛ ዓመት የኢንጂነሪንግ ተማሪ ነው።
ልጆቿ በትምህርታቸው ጎበዝ መሆን ቢያስደስታትም በምትፈልገው ደረጃ ልትረዳቸው ባለመቻሏ ታዝናለች። አጠገቧ እየተማሩ ያሉት አራቱም ልጆቿ በትምህርታቸው ጎበዝ ናቸው። ይረዳት የነበረው ድርጅት ድጋፉን ሲያቋርጥ ሌሎች ቅን ሰዎች እየደገፏት እንዳሉም ነግራኛለች።
የኡፑፑል ትምህርት ቤት ባለቤት አቶ አንዷለም የሁለት ልጆቿን ወጪ ሸፍኖ እያስተማራቸው መሆኑንና የተቀሩት ሁለቱ ልጆቿም በአንቶኒዮ መረዳታቸው ለጊዜው እፎይታ የሰጣት ቢሆንም የነገው የልጆቿ እጣ ፈንታ ሳያሳስባት ቀርቶ እንደማያውቅ ትገልጻለች።
‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ›› ጫልቱ በአንድ ወቅት የደረሰባትን አሳዛኝ ታሪክ እንዲህ ታስታውሳለች። የቤተሰቦቿን የእለት ጉርስ ለማሟላት ደፋ ቀና የምትለው ምስኪን እናት የአንጀት መታጠፍ ህመም ይገጥማትና በሰዎች ድጋፍ በኦቶና ሆስፒታል ከአንዴም ሁለት ጊዜ ቀዶ ጥገና ተደርጎላት ትተኛለች። በዚህን ወቅት ታዲያ በኮምፓክሽን የበጎ አድራጎት ድርጅት የሚረዳው ልጇ በዓመት አንዴ የተፈቀደለትን ‹‹ቼክ አፕ›› ምርመራ ለማከናወን ‹‹እንያት ክልኒክ ›› ይሄዳል።
የክሊኒኩ ባለቤት ዶክተር አሸብር ለምን ብቻህን መጣህ እናትህስ የት ሄደች ብሎ ሲጠይቀው እናቴ ኦፕሬሽን ስለሆነች መራመድ፤ መነሳት መቀመጥ አትችልም ይለዋል። ልጁ በትምህርቱ ጎበዝ እንደሆነ ይታወቃል ፤ ዶክተር አሸብር ልብስ፣ ጫማ ገዝቶ አንደገና ሶስት መቶ ብር ከሰጠው በኋላ እናትህ በዚህ ስልክ ቁጥር ትደውልልኝ ብሎ ቁጥሩን ላከላት። ደወለችለት፤ ሲሻላት ወደ እርሱ እንድትመጣ ነገራት።
ከተሻላት በኋላም ሥራ ቦታው ድረስ ሄደች። ከዚያ ሥራ ጀምሪ ብሎ የተወሰነ ገንዘብ ሰጣት፤ በዚያ ገንዘብ መነገድ ጀመረች፤ ልጆቿ የተለያዩ ጥያቄዎችን ሲያቀርቡ ሆዷ አልችል እያለ የጠየቋትን ሁሉ ስታደርግላቸው ብሩ ከእጇ ላይ ያልቃል። ከዚያም ከሥራ ውጭ ትሆናለች። ዶክተር አሸብር በየወሩ የሚሰጣትን ሶስት መቶ ብር እየተጠቀመች ለብዙ ጊዜ ያለሥራ ኖረች።
ይባስ ብሎ ደግሞ ጫልቱ በእድር አባላቱ አለመስማማት ምክንያት አስራ ሁለት ዓመታትን የኖረችበትን የእድር ቤት ለቅቃ ዛሬ በምትኖርበት ቦታ ሸራ ወጥራ እዚያው እየቸረቸረች መኖር ጀመረች።
ችግሯን የተረዱ በጎ አድራጊ ድርጅቶች በተለይም ቢላቭድ ኢትዮጵያ የስድስት ወር ክፍያ ፈጽሞ ሱቅ ተከራየላት። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አከራዩ ዋጋ ሲጨምር ሥራው አዋጭ ባለመሆኑ ሥራዋን አቁማ እዚያው ሸራ ወጥራ በምትኖርባት አካባቢ መጠነኛ እቃዎችን መቸርቸር ጀመረች።
ቢላቭድ ኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት የመኖሪያ ቤት ችግሯን ተረድቶ ከወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደርና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር አንገት ማስገቢያ ጎጆ ሊቀይስላት አሰበ።
በዚሁ መሰረት ከልጆቿና ከባለቤቷ ጋር ተደራጅታ ቦታው ላይ ፈቃድና ካርታ በማስወጣት ስያሜውንም ከኑሮዋ ጋር በማስተሳሰር ‹‹ትግል በትግል›› የሚል መጠሪያ ትሰጠውና ቤቱ ተሰርቶ ያልቃል። ከቢላቭድ ኢትዮጵያ ድጋፍ በተጨማሪ አንቶኒዮ የተባለው ኢጣሊያዊ ቆርቆሮና በር መስጠቱንም ትናገራለች።
ጫልቱና ቤተሰቦቿ የቤት ጥያቄያቸው ተመለሰላቸው። አሁንም ግን ይህ ነው የሚባል ገቢ የላቸውም። ጫልቱም ጥረቷን ቀጥላለች። በአዲሷ ጎጆዋ አጠገብም አንዳንድ ነገሮችን ለመሸጥ ሞክራለች። ያም ውጤታማ አላደረጋትም።
ጉልበት ባላት ጊዜ ተሯሩጣ ቤተሰቦቿን ለማኖር ደክማለች። አሁን ግን ሁኔታዎች ከበፊቱም በላይ ከፍተውባታል። ድሮ መስራት የምትችለውን የቀን ሥራ ዛሬ በተከሰተባት የጤና ችግር ምክንያት መስራት አትችልም። እንደዚያም ሆና በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ጊዜያዊ የጽዳት ሥራ እየሰራች ቤተሰቦቿን ለማኖር ትጥራለች።
ጫልቱ ካለባት ኢኮኖሚያዊ ችግር በተጨማሪ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ድርጅትና ግለሰብ ተረዳድተው በሰሩላት ቤት ላይ እየደረሰባት ያለው በደል ሌላ ፈተና እንደሆነባት ትናገራለች። ድርጅቱ በስሟ ለእርሷና ለቤተሰቧ የሰራውን ቤት ማዘጋጃ ቤቱ አላጸድቅልሽ ብሏት እንዲያውም ኦርጂናል የቦታ ማረጋገጫ ካርታው ሳይቀር እንደተሰወረባት ትናገራለች።
ማዘጋጃ ቤቱ ምንም አይነት የእውቅና ማረጋገጫ እንዳልሰጣትና እንደውም ግቢው ውስጥ ህገ ወጥ ሽንት ቤት በማስቆፈርሽ ትጠየቂያለሽ እንዳላት ትገልጻለች። ይሁንና ሽንት ቤቱ ከመቆፈሩ በፊት የጤና ቢሮ ኃላፊዎችም ሆኑ የመስተዳድሩ ሹማምነቱ በቦታው ተገኝተው አይተው ይሁንታ ሰጥተዋታል።
አጥሬ ጥግ ሽንት ቤት አስቆፍራብኛለች እያለ ለሚከሳት ጎረቤቷ በመወገን በደል እንደሚያደርስባት ትገልጻለች። እንደውም እርሷና ባለቤቷ በዚሁ ጉዳይ ለሁለት ቀናት ታስረው እንደነበር ታስታውሳለች። የከተማው ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮና ሌሎች ተቆርቋሪ አካላት እንዳስፈቷቸውም ገልጻለች።
አሁን ተቃለለልኝ ያለችው የመኖሪያ ቤት ችግር ሌላ የህይወት ፈተና ሆኖባታል። ድርጅቱ ችግሯን ተመልክቶ ያሰራላትን ቤት የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር ሊነጥቋት እንደሚፈልጉ ትናገራለች።
የቀበሌ አመራሮች በፈጸሙት ህገ ወጥ በደል ምክንያት ከስራቸው ቢወርዱም አሁንም በተለያዩ ሰዎች በኩል ማስፈራሪያ እንደሚደርሳት ጫልቱ ትናገራለች። ቤቱ ሳይት ፕላን የለውም፣ ግብር አይከፈልበትም የሚል የማሰናከያ ሃሳብ እንደሚያቀርቡላት ታስረዳለች። “ግብር ልክፈል ስል ደግሞ ፈቃደኛ አይሆኑም” ትላለች።
በመንግሥት አስተዳደር ውስጥ የሚሰሩ ባለስልጣናት ግለሰቦችን በመደገፍ በደሃ ላይ ኢፍትሃዊ ውሳኔ ማስተላለፋቸው ተገቢ እንዳልነበር ትናገራለች። እንደጫልቱ አባባል አሁንም ቢሆን ድርጅቱ ቦታ አስፈቅዶ በስሟ የሰራላትን ቤት ከተማ አስተዳደሩ እውቅና አልሰጥም ማለቱና ግብር አላስገብርም ማለቱን አጥብቃ ትቃወማለች።
የቀበሌ ቤትን ወደ ግል የሚያዞሩ ሰዎች ባሉበት ሀገር በሰዎች ድጋፍ በስሟ የተሰራን ቤት እንደእርሷ ካለ አቅመ ደካማ ሴት ላይ መቀማት ትክክል አይደለም በማለት ከተማ አስተዳደሩ አሰራሩን ሊፈትሽ ይገባል ትላለች።
ድርጅቶች ቤቱን የሰሩላት የቤት ችግሯን ሊያቃልሉ ነው፤ ልጆቿም እርሷም ሳይሳቀቁ እንዲኖሩ ነው። አስተዳደሩም በወቅቱ ተስማምቶ ቦታ ሰጥቷቸው ቤቱ ከተሰራና መኖር ከጀመረች በኋላ በስሟ ያለማድረጋቸው የሞራል ውድቀትና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል።
ጫልቱ ለጋሾች በስሟ የሰሩላትን ቤት ከተማ አስተዳደሩ እውቅና አለመስጠቱ በኑሮዋ ላይ ሌላ ችግር የፈጠረባት በመሆኑ የመንግሥትን ግብር በአግባቡ እንድትከፍል እና ልጆቿን በሰላም እንድታሳድግ የሚመለከተው አካል እንዲረዳት ጥሪ አቅርባለች።
ጫልቱ አሁንም በጥረቷ ሰርታ መለወጥን ትመርጣለች፤ ነገር ግን የመንግሥትና የሌሎች በጎ አድራጊ ድርጅቶች እገዛም ያስፈልጋታል። ጫልቱን እናግዛት በማለት ተሰናበትን።
አዲስ ዘመን የካቲት 06/2013