በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
በአንድ አነስተኛ የገጠር ከተማ ውስጥ የምትገኝ አንዲት በወጣትነት እድሜ ላይ የምትገኝ የአዕምሮ ህመም ምክንያት ወደ ጎዳና የወጣች ሴት መንገደኛውን ሁሉ “ባለጊዜው ማን ነው?” በማለት አዘውትራ ትጠይቃለች።ባለጊዜው ማን እንደሆነ የምትጠይቀው የምናባችን ወጣት የዛሬን አያድርገውና በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ትታወቅ የነበረው በታታሪነቷ ነበር።
ታታሪዋ ወጣት መንገዴን ላቅና ብላ ወደ አረብ ሀገር ሄዳ የነበረ ሲሆን በአዕምሮ ጤና እክል ወደ ሀገሯ እንድትመለስ ተደረገች።በህመም ወደ ሀገሯ ብትመለስም መፍትሄ ስላልተገኘላት ከአዕምሮ ህመሟ ጋር ጎዳናን ህይወቷ አድርጋዋለች።
የጎዳና ወጣቷ የህይወት ምስቅልቅሏ በጀመረበት ወቅት ምክርን ፈልጋ ደጁን ትጠና የነበረ አጓቷ ምክርን ሊሰጣት ጊዜ በማጣት የሚገባውን ጊዜ ሳይሰጣት አሁን ለያዥ ለጋራዥ አስቸጋሪ የሆነችበት ሁኔታ ውስጥ በመግባቷ እጅጉኑ ያዝናል።
በጊዜ ብደርስላት ኖሮ እያለም ያዝናል።ይህ ሰው መኪና እየነዳ በሚያልፍበት ጊዜ ስታየው ትኩር ብላ ትመለከተውና “ባለጊዜው ማን ነው?” ብላ ትጠይቀዋለች።የእርሱ ምላሽ ዝምታ ነው።በዝምታ በሃሳብ ተውጦ እርሷን ወደ ኋላ ትቶ ወደ ፊት መንዳት።
ባለጊዜ ሲባል
በዙሪያችን ያሉ ሰዎችን ያሉበትን የሕይወት ትግል ተመልክተን ጉዟቸው ወዴት እንደሆነ አቅጣጫውን ለመመርመርና ለውሳኔያቸው የሚረዳ ምክር ለመስጠት ስለምንሰጠው ጊዜ እናስብ።ባህር አቋርጠን ወደ ሌላ ሀገር ለመሰደድ ስንወስን የህይወታችን አቅጣጫ ወዴት ሊሆን እንደሚችል ጊዜ ሰጥተን እንመርምር።በተፈጥሮ ህግ ምክንያት የምድር ቆይታችን ጣሪው ሰባ ግፋ ቢልም ሰማንያ ነውና ከእዚህ አንጻር እድሜያችንን ለክተን የቀሪውን ጉዞ ስናሰላ የሚሰማንን ለራሳችን እንንገር።
ከዚያም ጊዜውን በአግባቡ የሚመረምር ጊዜውን ለክቶ የሚንቀሳቀሰውን በምን እንደምንጠራው ቃል እንፈልግለት።ለዛሬው ግን ባለጊዜው ማን ነው? የሚለውን የወጣቷን የጎዳና ነዋሪ ጥያቄ ለመመለስ እንሞክር።ለጥያቄውም የምንሰጠው መልስ ባለጊዜ ማለት ጊዜውን መርምሮ በጊዜው መልካም ፍሬ ለማፍራት የሚኖረው ሰው ነው ይሁን።
ራስን እንደ ባለጊዜ
እከሌ ባለ ጊዜ ነው እንዲሁም እከሊት ባለ ጊዜ ነች አንዳንዴም እነርሱ እኮ ባለ ጊዜ ናቸው ወዘተ ሲባል እንሰማለን።ይህ አይነቱ አገላለጽ የሚሰጠው ትርጉም ለሁላችንም ግልጽ ይመስላል።በፖለቲካችን አንድ ቡድን ወጥቶ ሌላው ሲተካ ተተኪው ራሱን እንደ ባለጊዜ ቆጥሮ ከህግ በላይ ለመሆን ሲሞክር በብዙ ታዝበናል።ህግ ማለት ከባለ ጊዜዎቹ ውጪ ስላሉት እንጂ ስለሌሎች እንዳይደለም ሆኖ ሥራ ላይ ውሏል።
ለምን የሚል ሲነሳ በባለጊዜዎች በሚመሩ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ይጣል ዘንድ ይፈረድበታል።በማተለቅ ከመተለቅ በማሳነስ መተለቅ የባለጊዜዎች ቀመር ሆኖ በሀገራችን ተተርጉሞ ተሰርቶበታል።
ይህን የባለጊዜነት ትርጉም ግን ለዛሬው እኛ በሰጠነው የባለጊዜነት ትርጉም ሽረነዋል።የእኛ የባለጊዜነት ትርጉም ባለጊዜ ማለት ጊዜውን መርምሮ በጊዜው መልካም ፍሬ ለማፍራት የሚኖረው ሰው ማለት ነውና።
ራስን እንደባለጊዜ ለመቁጠር ጊዜን በመመርመር መጀመር ተገቢነቱ ከፍተኛ መሆኑ አያጠያይቅም። የምናውቀው ሰው አንድ ትልቅ ሥልጣን ላይ ስላየን ራስን እንደ ባለጊዜ ከመቁጠር በውስጣችን ባለው አቅም በመረዳት የምንቆጥረው ባለጊዜነት እርሱ የተሻለው ባለጊዜነት ነው።
ወንጀል ብንሰራ በምንደበቅበት ዋሻ ጥንካሬ ከሚመዘን ባለጊዜነት አምላክ ሲፈጥረን ከእኛ የሚፈልገውን መልካምነት በመሆን ውስጥ ያለውን ባለጊዜነትን ማግኘት የተሻለው ነው።በመሆኑም ራስን እንደ ባለጊዜ ስንቆጥር ከውጫዊው ግርግር ይልቅ ወደ ራስ የመመልከቱን አስፈላጊነት እንረዳለን።
ለጎዳና የበቃችው ወጣት ያለፈችበት መንገድ ውስጥ ያለው ውጣ ውረድን ልንፈርድበት በፍጹም ድንጋይ አናነሳም።ጥያቄዋ ግን እያንዳንዱ ሰው ራሱን እንዲጠይቅ በማህበረሰባችን ዘንድ ያለውን የተንሸዋረረ የባለጊዜነት ትርጉም ጠይቀን አዲስ አረዳድ መፍጠር እንዳለብን የሚያሳይ ነው።አዲሱም አረዳድ ራሱን እንደ ባለጊዜ ቆጥሮ በእግሩ እንዲቆም የሚረዳው መሆን አለበት፡፡
ውጫዊው ዓለም ያለው ተለዋዋጭነት ላይ ከመደገፍ በህይወት መኖሬ ጊዜው የእኔ ነው የሚል እምነት እንዲፈጠርብን ሊያደርግ ይገባል።ጊዜው የእኔ ነው የሚለው ባለጊዜው እኔነኝ ብሎ የሚነሳ ሰው ከሚገጥሙት ተግዳሮቶች ባሻገር ራሱ ጋር ያለውን አቅም ፈልጎ እንዲያጎለብት አቅም ይሆነዋል።
ራስን እንደ ባለጊዜ ከመቁጠር ውጪ አማራጭ የለህምና።አለበለዚያ ባለ ጊዜ ነኝ ያለው ሁሉ መጥቶ በሄደ ቁጥር አጃቢ ትሆናለህ።የአጃቢነት ህይወት ደግሞ በቃ አጃቢነት ነው፤ ለተፈጠርክለት ዓላማ ሳትኖር የምታልፍበት።ዛሬ በህይወት ያለሰው ሁሉ ባለጊዜ ነው።ወጣትነት ደግሞ የበለጠው ባለጊዜነት፡፡
ወጣትነት ባለጊዜነት
ከህጻናት እና እድሜያቸው ከገፉ ሰዎች ይልቅ ጊዜ ኖሯቸው በቅርቡ ነገ ላይ ተጽእኖ የማሳደር እድል ያላቸው ወጣቶች ናቸው።ዓለማችን በወጣቶች መሪነት የተመሩ ብዙ ለውጦችን ማስተናገዷ ለዚህ ምስክር ነው።የጥቁር አሜሪካዊው ማርቲን ሉተር ኪንግ የለውጥ ናፍቆት እንቅስቃሴ፤ ዘመን ተሻጋሪ ንግግሮች፤ ስለ ሰው ልጆች እኩልነት የተደረገው ትግል የወጣትነት ዘመን ትግል ነው።
ፊደል ካስትሮን የመሰሉ የአብዮት አራማጅ ወጣቶችንም ታሪክ እንዲሁ ስንመረምር አብዮት የወጣትነት ዘመን ትግል መሆኑን ይመሰክራል።በመጽሐፍ ቅዱስም ውስጥ ቢሆን እንደ ዮሴፍ እና ዳንኤል የመሰሉ ወጣቶችን አንስተን አንድ ሁለት ብንል ብዙ ማለት እንችላለን።
ከዚህ ተነስተን የለውጥ ጀማሪዎች ወጣቶች ናቸው ብንል ማጋነን አይሆንብንም።ከለውጥ ጀርባ ወጣትነት አለ።ወጣቶች ተስፋ ቆርጠው እጅ የሚሰጡ ሆነው የሚሳልበት ዘመን ሳይሆን ለለውጥ ትልቁን ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ሆነው የተሳሉበት እውነታ ሚዛን ይደፋል።በመሆኑም በወጣትነት ውስጥ ከፍያለው የባለጊዜነት ትርጉም አለ።
ይህ እውነት በወጣቶች ልብ ውስጥ እንዳለ ማሳያ እንዲሆን አንድ መርሐግብር ላይ ወጣቶች ስለ ራሳቸው የተናገሩትን ዋቢ እናድርግ።“ወጣትነት በወጣቶች አንደበት” የሚል ርዕስ የተሰጠው መሰናዶ በአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ በኦገስት 16፣ 2019 (እንደ ጎርጎረሳውያን አቆጣጠር) ተላልፎ ነበር።በመርሐግብሩ ላይ ስለ ወጣትነት አስተያየታቸውን የሰጡ ወጣቶችን ሃሳብ ጋዜጠኛ ኤደን ገረመው አሳጥራ ስታቀርበው “ወጣትነት ሃይል ነው፤ ምንም ሳይኖረው በተስፋ እና በራዕይ የተሞላ ነው።
ወጣትነት ድፍረት ይጠይቃል፤ እችላለሁ በሚል መንፈስ መጎልመስ አለበት” በማለት አስቀምጣዋለች።በዚሁ መሰናዶ ላይ አስተያየቱን የሰጠ አንድ ወጣት በአስተያየቱ ወጣትነትንና አበባን አመሳስሎም አቅርቦታል።አበባን አብቦ ለማግኘት እንክብካቤ እንደሚያስፈልገው ወጣትነትም ወደ ፍሬ እንዲደርስ እንክብካቤ የሚያስፈልገው መሆኑን ወጣቱ ተናግሯል።
በእንክብካቤው ውስጥ ቤተሰብ፣ ጎደኞች እንዲሁም መላ ማህበረሰቡ ኃላፊነት ያለበት ሲሆን ዋናው አካል ግን ራሱ ወጣቱ መሆኑን መሰናዶው ላይ የቀረበው ወጣት ይመክራል።ባለጊዜው! ባለ ሃይሉ! ባለ ራእይው … ወጣቱ ነው!!! ራስን ለመምራት ወደ ራስ መመልከት ያለበት።
በወጣትነት ውስጥ አካላዊ ለውጥ ይሆናል።አካላዊ ለውጡ የሚጋብዘው ፈተናም አብሮ ይመጣል።ስሜታዊ ለውጠም እንዲሁ ይመጣል፤ ስሜታዊ ለውጡም ጥራት ያለው ውሳኔን ለመወሰን መሰናክል ሆኖ የመምጣት አደጋውን ይዞም ይቀርባል።
አዕምሮአዊ /Cognitive/ ማለትም እውቀት /Knowledge/ እና ጥበብ /Skill/ እንዲሁም መስተጋብራዊ /Relationship/ ለውጦች ይከሰታሉ:: በመሆኑም በወጣትነት ወቅት ራስን ለማወቅ የሚደረገው ጥረት ከፍማለት እንዳለበት እንረዳለን።
እድሜው ለችግር ተጋላጭነት የሚጨምርበት አንድን ነገር በማድረግ በሌሎች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይት ለማትረፍ የሚሮጥበት እንጂ በሚደረገው ነገር የሚፈጠረው መጥፎ ነገር በውል የማይጤንበት ጊዜ ነውና ባለጊዜነትን በጥበብ መያዝን ወቅቱ ይጠይቃል።
በዚህ ወቅት ከፍተኛ ጾታዊ ፍላጎት የሚቀሰቀስበት እና የወጣቶች አዕምሮ የሚባክንበት፤ ለልዩ ልዩ ሱሶች የሚጋለጡበት በተለይም በአፍላነት ጊዜ ከወላጆች ይልቅ ሌሎችን ማድመጥ ዝንባሌ እኔ ያልኩት ካልሆነ የሚባልበት በመሆኑ ውዱ ባለጊዜነት እንዳያልፍ ወጣቶች ራስን መምራት ሊያውቁበት ይገባል፡፡
ራስን መምራት
በሥራ ማስታወቂያ ውስጥ የሚጻፉ የተለመዱ ነጥቦች አሉ።የኃላፊነት ቦታ ላይ ለሆኑ ሥራዎች ከሚጠቀሱ ነጥቦች መካከል አንዱ ስራን ያለሌሎች ድጋፍ በራስ ቆሞ ማከናወን መቻል ይገኝበታል። ይህን ራስን መምራት ልንለው እንችላለን። እያንዳንዱ ሰው የመጀመሪያው እድገቱ ራስን መምራት መቻሉ ነው።
ራስን መምራት ቀላል መሪነት አይደለም።ጊዜን መተርጎም ለመቻል፤ ጊዜን በአግባቡ ለመጠቀም ወዘተ ራስን መምራት ተገቢ ነው።ራስን መምራት መቻል ውስጥ ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም በመልካምነት ማደግ አለ።ይህን ማድረግ መቻል ባለጊዜነት በሚገባ ለመጠቀም ያስችላል።
ወጣቱ ራሱን ለመግዛት ሲነሳ እንደ ፈላስፋ ለሚጠይቃቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ እያገኘ መሄድ አለበት።ራስን ለመምራት የወጣትነት ጊዜውን ተረድቶ ለመጠቀም መጠየቅ ይገባዋል።በዚሁ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የካቲት 27/2012 ጠና ደዎ (ፒኤችዲ) የተባሉ ግለሰብ “ወጣትነት በፍልስፍና ቅኝት” ብለው ባስነበቡት ጽሁፋቸው የሚከተለውን ብለው ነበር።
“ወጣትነትና ፍልስፍና የሚመሳሰሉበት አንድ ባሕርይ አላቸው። ፍልስፍና እውነትን ለማወቅ ያለመታከት ይሰራል። ሁሉንም ነገር ለመፈተሽ በተለያየ አቅጣጫ ይቧጥጣል፤ ይቆፍራል። በባሕርይው ጠያቂ፤ ምክንያታዊና ሂሳዊ ነው። አሳማኝ ውጤት ካላገኘ ፍተሻውን አያቆምም።ወጣትነትም የማያውቀውን ለማወቅ፤ ያላገኘውን ለማግኘት፤ ካልደረሰበት ለመድረስ ያለ መታከት ይጥራል።
በባህርይው አዳዲስ ነገሮችን ለማወቅና ለመስራት፤ ለመፍጠር ወይም ለማግኘት፤ ፈትሾና አረጋግጦ ለማሳየት ይጓጓል።በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ወጣቶች ላይ የሚያተኩር ፍልስፍናዊ ቅኝት እናደርጋለን።ወጣትነት ፀጋዎች አሉት፤ በፀጋዎቹ ምክንያት ለአደጋም የተጋለጠ ነው።
በተለይ ያልዳበረ የፖለቲካ አስተሳሰብና ሥርዓት፤ ያልበለፀገ ግብረገባዊና ሥነ-ምግባራዊ ባሕል በሰፈነበት ሁኔታ ውስጥ ወጣትነት ፈተናው እጅግ ብዙ ነው።ከዚህ አንፃር ስለ ወጣትነት ብዙ መማርና ማስተማር፤ ማወቅና ማሳወቅ፤ መምከርና መመካከር፤ መስራትና ማልማት ያስፈልጋል።
ጸሐፊው በመቀጠል ወጣትነትን እንደ አንድ ማንነት ያቀርቡታል።ባለጊዜ የሆነው ወጣቱ ራሱን በመቀበል ሊዘልቅ የሚገባበትን ጥግ ሲያሳዩ ይመስላል።የወጣትነት ማንነቱ ግን በሦስት ጊዜያት ውስጥ የተተረጎመ ነው ይላሉ፤ በዛሬ፣ በትላንትና በነገ ውስጥ።
“ወጣትነት በራሱ ማንነት ነው። ማንነቱ የሶስት ጊዜያት ክንውኖች ጠቅላላ ድምር ነው።ውጤቱ ቀደም ሲል የሆነው፤ አሁን በመሆን ያለውና ለወደፊት መሆን የሚፈልገው ነው። ስለዚህ የወጣትነት ማንነት በዛሬ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በትላንትና በነገ ውስጥ ይገኛል።ይህ ማለት ወጣትነት የሚለማ፤ የሚገነባ ወይም የሚታነፅ ማንነት ነው።ያለቀለት ሳይሆን በመሆን ሂደት ውስጥ ያለ ማንነት ነው።
የሚታነፀው በራሱና በሌሎች ነው።ሌሎች ሲባል ወላጅን ወይም ቤተሰብን፤ ጎረቤትን፤ ሕብረተሰብን፤ መንግሥትን፤ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትንና የመሳሰሉትን ለማለት ነው።ይህ ማንነት በእውን ያለው በሆነና መሆን በሚፈልገው፤ በያዘውና ማግኘት በሚመኘው መካከል ነው።
የመጀመሪያው ከመድረሻው አንጻር ሲታይ ዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ ያለ ማንነት ነው።ሁለተኛው ገና የሚደርስበት ወይም ከርቀት የሚታይ ማንነት ነው።ሽግግሩን ለማሳካት ያለውን አቀበትና ቁልቁለት መውጣትና መውረድ፤ መውደቅና መነሳት የግድ ይላል።ወጣትነት እንደ ውበቱና ድምቀቱ፤ እንደ ብሩህ ተስፋውና ትኩስ ጉልበቱ ሁሉ አደጋው የበዛ ነው።እንደ ተሰባሪ ዕቃ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል።”
ጸሐፊው ሙግታቸውን በመቀጠልም ወጣቱ በእግሩ መቆሙ ግድ እንደሆነ ሲያሰምሩበት እንዲህ ይላሉ “አንድ የወጣቶች በርቱ ድክመት የራስን ዋጋ ማሳነስ ነው።ራስን ለማምጣት በመጀመሪያ ተገቢውን ዋጋ ወይም እሴት ለራስ መስጠት ያስፈልጋል።
ሰው ክቡር ፍጡር ነው።ወጣቶች ይህን መረዳት ብቻ ሳይሆን የሚመሩበት እምነት ማድረግ አለባቸው። እንደ ሰብአዊ ፍጡር ክቡር ነኝ ብሎ ማመን ያስፈልጋል። ሰብአዊ ፍጡርነት የተሰጠ ብቻ ሳይሆን ያለማቋረጥ የሚታነፅ ወይም የሚሰራ ነው።
በማፍቀርና በመፈቀር፤ በመጥላትና በመጠላት፤ በማክበርና በመከበር፤ በመሆንና ባለመሆን፤ በመስጠትና በመቀበል፤ በማግኘትና በማጣት ውስጥ ሰብአዊ ማንነት የሚሰራው።የወጣት ማንነት በዋናነት በራሱ፤ በከፊል ደግሞ በሌሎች ይሰራል።
የሌላው እገዛ እንዳለ ሆኖ ለማንነቱ ግንባታ ዋናው መሐንዲስ ራሱ መሆን አለበት።የጥገኝነት መንፈስን ማስወገድ አለበት።ስብእናውን ማነፅ የሚኖርበት ራሱን ችሎና በእግሩ ቆሞ ነው።”
ባለጊዜ ማለት ጊዜውን መርምሮ በጊዜው መልካም ፍሬ ለማፍራት የሚኖረው ሰው ነው ባልነው ትርጉም ውስጥ ሆነን ወጣቱ ፍሬን ማፍራት ይችል ዘንድ ባለጊዜነቱን መጠቀም እንዲችል ራሱን እንዲመራ መሆኑን አስቀድመናል።በመቀጠል የሌላው ማህበረሰብን ቁልፍ ኃላፊነት እንጥቀስ፤ ወጣቱን መረዳት።ወጣቱን በመረዳት ውስጥ መርዳት መቻል።
ወጣቱን መረዳት
ወጣቶቹ ራሳቸውን እንዲመሩ ከማስተማር ወይንም በራሳቸው እንዲቆሙ ከመርዳት ባሻገር ወጣቶቻችን መረዳት ከማህበረሰብ ይጠበቃል።ወጣትነት የበረከተ ውስጣዊ ለውጥ የሚሆንበት ውጫዊ ለውጥም ለመፍጠር ውስጣዊ ግፊት የሚፈጠርበት ወቅት መሆኑ በብዙ ተብሎበታል።ወጣቶቹን ከመምራት ወጣቶችን መረዳት የሚቀድም ይመስላል።ወጣቶቻችን ራሳቸውን እንዲመሩ እድል ከተሰጣቸው ራሳቸውን ሊመሩ ይችላሉ፤ ነገርግን የሚረዳቸው ይሻሉ።
እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ቤተሰብ ወጣቶችን ለመረዳት የምንሄድበት እርቀት ወሳኝነቱ ለውይይት አይቀርብም።ወጣቶቹ ሊያደርጉ የሚገባውን ዝርዝር ከማስቀመጥ እነርሱ የሚያስቀምጡትን ዝርዝር በመመልከት መረዳት መቻል ሊቀድም ይገባል።
በምናባችን ላይ የሳልናት ጎዳናን ቤቷ ያደረገችው ወጣት የአዕምሮ ህመምተኛ መፍትሄን ፍለጋ ከደጁ የቆመችው አጎቷ ሊሰጣት ያልቻለው ጊዜ የፈጠረባትን ጸጸት ስናስታውስ በዙሪያችን ያሉ ወጣቶች ነገ የሚኖሩት ኑሮ የእኛ ጸጸት ምክንያት እንዳይሆን ማድረግ ያለብንን ለማድረግ ዛሬ ላይ ባለጊዜ ልንሆን ይገባናል።የአውስትራሊያ መንግሥት “Effective Communication with Young people” በሚል ርእስ ባሳተመው የጥናት ህትመት ውስጥ ወጣቶችን እንዴት መረዳት እንደሚገባን የሚያስገነዝቡ ነጥቦችን አትሟል።
በጥናቱ ላይ ወጣቶቹ በህይወታቸው ውስጥ ተጽእኖ የሚያሳድሩባቸውን አካላት እንዲያሳውቁ ለተጠየቁት ጥያቄ ከሰጡት ምላሽ መረዳት የተቻለው ቤተሰቦቻቸው እና ጎደኞቻቸው ቀዳሚዎቹ በህይወታቸው ላይ ተጽእኖ ፈጣሪ መሆናቸውን ነው።ከጎደኞች በፊት የተቀመጡት ደግሞ ቤተሰቦች ናቸው።
ይህም ቤተሰብ እንደ ቤተሰብ ልጆችን፣ ታዳጊዎችን እንዲሁም ወጣቶችን ለመረዳት የሚሄደው እርቀት ከፍተኛ መሆኑን ያስረዳል።በጎዳና ያለችው “ባለጊዜው ማን ነው?” እያለች እየጠየቀች የምትውለው ወጣት ምናልባት አብረዋት የሚኖሩት የቅርብ ቤተሰቦቿ ትኩረት ስላልሰጧት ይሆን ወደ ሩቅ ቤተሰብ አጎት ጋር የሄደችው?
ከቀደምት የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች መካከል ፍራንክሊን ዲ. ሮዝቬልት “ሁልጊዜ የወጣቶቻችን ነገን መስራት አንችልም፤ ነገርግን ወጣቶቻችንን ለነገ ልንሰራቸው እንችላለን” በማለት ተናግረዋል።ዛሬም ወጣቶቻችንን ለነገ መስራትን ስናስብ የምንሰራቸው እነርሱን በመረዳት በመጀመር ነው።ባለጊዜዎቹን ባለንጊዜ እንረዳቸው፤ እነርሱም የዘመናቸውን ወጣቶች ለነገ ይሰሯቸዋል።
ኢትዮጵያ ወጣቱን በተጨባጭ በመረዳት በታቀደበት አግባብ ልትደርስበት ካልቻለች የሚባክነው ወጣት ሰቆቃ ቀላል አይደለም።በኢትዮጵያ እድሜያቸው ከ 15 ዓመት በታች ያሉት ታዳጊዎች ከ 40 ከመቶ በላይ መሆናቸውን ስንመለከት ኢትዮጵያ ዛሬም ሆነ የቅርብ ጊዜ ነገ የወጣቶች ሀገር መሆኗን እንረዳለን።
በ 15 እና በ29 ዓመት መካከል ያሉት ደግሞ ከ 28 ከመቶ በላይ ናቸው።የወጣቶች የሥራ አጥነት ምጣኔ ከ 25 ከመቶ በላይ መሆኑ ግን የሚቀረውን ሥራ ስፋት ያሳያል።ለሥራ አጥነቱ ትልቁ አስተዋጽኦ አድራጊ ደግሞ ዝቅተኛ የሆነ የትምህርት ተደራሽነት ነው።
የትምህርት ተደራሽነቱ እንዲሁም ጥራቱ በሌለበት ሁኔታ የዛሬ ወጣቶችን ለነገ መስራት በፍጹም አይቻልም።ወጣቶቻችን ያሉበትን ችግር በመረዳት፤ ለመፍትሄው እነርሱን በማሳተፍ፤ በእግራቸው እንዲቆሙ በማድረግ እውነተኛ ባለጊዜዎች እንደርጋቸው።
ወጣቶቻችን ዛሬን መኖር ሳይችሉ በነገውስጥ ባለ የፖለቲካ አጀንዳ ቆልፈንባቸው እንደ ሀገር ያለንበት አሉታዊ ገጽታ መቀየር የማይታሰብ ነው።
ባለጎዳናዋ ወጣት ግን ዛሬም ትጠይቃለች “ባለጊዜው ማን ነው?” ማን ነው እያለች።እኛ ግን ለጥያቄዋ ባለጊዜ ማለት ጊዜውን መርምሮ በጊዜው መልካም ፍሬ ለማፍራት የሚኖረው ሰው ነው ስንል መልሰንላታል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 06/2013