የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል ስላካሄደው የህግ ማስከበር ዕርምጃ እና ከዕርምጃው መጠናቀቅ በኋላ በክልሉ ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ በተመለከተ የተለያዩ መረጃዎች ይደመጣሉ።እነዚህ መረጃዎችም ከህግ ማስከበር ዕርምጃው እስከ መልሶ ግንባታ እና በሰብዓዊ ድጋፍ ላይ ያተኮሩ ሲሆን፤ በተለይ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ የህወሓት ጁንታ ርዝራዦች የቀደመ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ የሚያደርጓቸው ሰፊ የአክቲቪዝም ዘመቻ ውጤቶችም ይገኙበታል፡፡
ከዚህ አንጻር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች እና አጎራባች የአማራ ክልል አካባቢዎች በሁለት ዙር ተዘዋውሮ ጎብኝቷል።አጠቃላይ ሁነቱን በተመለከተም በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚወጡ የተለያዩ መረጃዎች እና የሚቀርቡ ወቀሳዎች በአክቲቪዝም ዘመቻው የፈጠራ ወሬ የተቃኙ እንጂ በተጨባጭ መረጃ ላይ ያልተደገፉ ስለመሆናቸው አረጋግጧል፡፡
በዚህ መልኩ የሐሰት መረጃ የማሰራጨት የአክቲቪዝም ዘመቻው ዋነኛ ምክንያት ደግሞ መንግሥት በወሰደው የህግ ማስከበር ዕርምጃ የእነዚህ ዘራፊ ኃይሎች ህልውና መምከን ሲሆን፤ በውጭም በውስጥም ባሉ ግብረአበሮቻቸው በተደራጀ መልኩ የሐሰት መረጃዎችን የማሰራጨት ተግባራቸው ካፈርኩ አይመልሰኝ ዓይነት የእነሱን ጥፋትና በደል በሌላው ላይ ለማላከክ የሚያደርጉት ጩኸት አካል ነው፡፡
ትንሽም ሀፍረት የማይሰማቸው እነዚህ አካላት በትግራይ ክልል ከአንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ህዝብ በላይ የሴፍቲኔት ጠባቂ አድርገውት ሲያበቁ፤ መንግሥት ህዝቡን ለችግር አጋለጠው ብለው ይወቅሳሉ።በየማረሚያ ቤቱ ያሉ እስረኞችን ለቅቀው ለዝርፊያ አሰማርተው እና በእናትና ልጆቻቸው ላይ የፆታዊ ጥቃት እንዲፈጸም አድርገው፣ የህዝቡ ደህንነት አደጋ ላይ ነው ሲሉ የአዞ ዕንባ ያነባሉ።
ከዚህም ባለፈ ጉዳቱንና የደረሰበትን ጥቃት ችሎ ለአገርና ህዝብ ሲል ዛሬም ለመስዋዕትነት የተሰለፈውንና ለሙያዊ ስነምግባሩ ተገዢና በተግባሩም ዓለምአቀፍ አንቱታ ያተረፈውን የመከላከያ ሠራዊት በሐሰት መወንጀልንም ተያይዘውት ይገኛሉ፡፡
ይሁንና ሊታወቅ የሚገባው ሀቅ በየትኛውም ሀገር ቢሆን ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖር ህዝብ ለረሃብ እና ለሌሎችም ማህበራዊ ችግሮች ሊጋለጥ መቻሉ ነው።ዋናው ነገር ችግሩ ከተረጋጋ በኋላ በአካባቢው ያለው ማህበረሰብ ከችግሩ እንዲወጣ ምን ተሠራ የሚለው ጉዳይ ነው።በዚህ ረገድ ከህግ ማስከበር ዕርምጃው መጠናቀቅ በኋላ በትግራይ ክልል ለሚኖሩ ዜጎች ምግብን ጨምሮ ሌሎች ሰብዓዊ ድጋፎች እየተደረጉ ነው፡፡
ይህ ምናልባት በሁሉም የክልሉ ቀበሌዎች በሚፈለገው ልክ ፍጹም ሆኖ ደርሷል ላይባል ይችል ይሆናል።ነገር ግን ከሰብዓዊ መብት አያያዝም ሆነ ከሰብዓዊ ድጋፍ ጋር በተገናኘ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚቀርቡ ወቀሳዎች በመረጃ ያልተደገፉ መሆናቸውን ነው መርማሪ ቦርዱ ያረጋገጠው።
በተመሳሳይም የመከላከያ ሠራዊት አባላት በንጹሐን ዜጎች ላይ ጥቃት እያደረሱ እንደሆነ ሲነገር የነበረው ወሬም ፍጹም የተሳሳተ መሆኑን ቦርዱ ያረጋገጠ ሲሆን፤ በየአካባቢው ባደረጉት ውይይትም የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጥቃት አድርሰውብኛል የሚል አንድም ሰው አለማግኘታቸው በአጽንኦት ተገልጿል፡፡
የዚህ ማደናገሪያ የመረጃ ምንጮቹ እነዚህ ርዝራዥ ኃይሎችና አክቲቪስቶች መሆናቸው የታወቀ ነው።ይሄን የሚያረጋግጠው ደግሞ ከሰሞኑ የሃይማኖት አባቶች እና የአገር ሽማግሌዎች ወደክልሉ ባቀኑበት ወቅት የታዘቡት እውነት ነው።
ዛሬም በውጪ ሆነው የትግራይ ህዝብ ለሰላሙና ለተሻለ ነገው ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር እንዳይተባበር ለማድረግ የሚጥሩ እና የፖለቲካ ገመድ የሚጎትቱ ግለሰቦች መኖራቸውን ተገንዝበዋል።ይህ ዓይነቱ አካሄድ ደግሞ እነዚህ የፖለቲካ ገመድ ጎታቾች ለጥቅማቸው ሲሉ የሚያደርጉት የፖለቲካ ቁማር እንጂ ለትግራይ ህዝብ የሚፈይደው አንዳች ነገር የለም፡፡
የትግራይ ህዝብ ዛሬ የሚፈልገው ሰላም እንጂ ጦርነትን አይደለም፤ ዘላቂና ህይወቱን የሚለውጥ ልማትን እንጂ በሴፍቲኔት መኖርን አይደለም፤ መድሃኒት እንጂ የጥይት አሩርን አይደለም፤ ዳቦ እንጂ ድንጋይ መወራወርን አይደለም።
ህዝቡ የሚፈልገው በችግሩ ላይ ቤንዚን ለኩሶ እሳት የሚጭርበት ሳይሆን፤ ችግሩን ተረድቶ ዳቦ የሚያቀርብለትን፤ የዛሬን ችግር አሻግሮ የነገውን ብሩህ መንገድ የሚቀይስለትን፤ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ የሚያሰፍንለትን ነው፡፡
እናም ለግል ትርፍና ርካሽ ፖለቲካዊ ፍላጎት ሲባል የፖለቲካ ገመድ እየጎተቱ በህዝቡ ከመነገድና በአክቲቪዝም ዘመቻ ዓለምአቀፍ ማህበረሰብን አሳስቶ የራስን ጥቅም ለማስጠበቅ ከሚደረግ መሯሯጥ መውጣት ይገባል።የትግራይ ህዝብ ዛሬን በብርታት ተሻግሮ የተሻለ ነገር የሚያይበትን የችግሮቹን መፍቻ ቁልፍ ማቀበልም ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ተግባር መሆን ይኖርበታል!
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2013