እፀገነት አክሊሉ
ህወሓትን ከመሰረቱ ጥቂት ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው፤ ለአስር ዓመታት ያህልም ከድርጅቱ ጋር በጫካ የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ ቆይተዋል፤ በዚህ የትግል ጉዟቸውም ከፍተኛ አስተዋጽኦ የነበራቸው ከመሆኑም በላይ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር በመሆን አገልግለዋል፤ ሆኖም በነበራቸው የፖሊሲ ተቃውሞ እንዲሁም በሃሳብ ልዩነታቸው ምክንያት በድርጅቱ እንዲቀጥሉ አልተፈለገም፤ በህወሓት ውስጥ ማርክሲስት ሌኒንስት የሚለው ርዕዮተ ዓለም ሲመሰረት በተለይም እርሳቸውና ጥቂት መስራች አባላትን ተቃውሞን በማስነሳታቸው በተሸረበባቸው ሴራ አማካይነት ከድርጅቱ እንዲሰናበቱ ሆኗል፤ አቶ ግደይ ዘርዓጽዮን (ኢንጂነር) ለውጡን ተከትሎ ለረጅም ዓመታት በስደት ከኖሩበት አውሮፓ መጥተውና የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን ተቀላቅለው ትግላቸውን ካቆሙበት ቀጥለዋል፤ በአሁኑ ወቅትም ፓርቲውን በምክትል ሊቀመንበርነት እየመሩ ይገኛሉ፤ እኛም ከአቶ ግደይ ዘርዓጽዮን ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታን አድርገናል፤
አዲስ ዘመን፦ ህወሓትን ከመሰረቱት ጥቂት ሰዎች መካከል አንዱ እንደመሆንዎ እስኪ ስለ ድርጅቱ አመሰራረት ጥቂት እንበል፤
አቶ ግደይ፦ በወቅቱ ህወሓትን የመሰረት የተማሪዎች እንቅስቃሴ ሲሆን መስራቾቹም ከትምህርት ቤት የመጡ ናቸው፤ ወቅቱ የፊውዳል (የመሳፍንታዊ ) ስርዓት የተንሰራፋበት ከመሆኑ አንጻር እርሱ መቀየር አለበት በሚል ጥያቄዎችም እየመጡ ስለነበር በተለይም የሰሜኑ ክፍል መሳፍንታዊ የአገዛዝ ሂደትን ሁሉ የሚከተል ከመሆኑ አንጻር እንዲቀየር ለማድረግ የተመሰረተ ነው፤
ከተመሰረተ በኋላም በተለይም ህዝቡ የሚያነሳውን የዴሞክራሲ፤የፍትህ ጥያቄ ከዚህም አልፎ የብሔሮች እኩልነት ጥያቄን ምላሽ ለመስጠት ያለመ እንቅስቃሴ ነበር የሚያደርገው፤
በመሆኑም እኛም ተመሳሳይ አመለካከት የነበረንና ያለን ሰዎች በመሰባሰብ ድርጅቱም ለመመስረት ችለናል፤ ለምሳሌ የብሔር ጥያቄዎች ጎልተው የሚታዩ ስለነበር ይህንን ሁኔታ ደግሞ ትግሉን ሊያቀላጥፍ ይችላል የሚል እምነትን በመያዝ በትግራይ የነበረውን ስሜት በመከተል ድርጅቱ እንቅስቃሴውን ጀመረ፤
ለነገሩ ትግሉ የተጀመረው ደርግ ወደ ስልጣን ከመምጣቱ በፊት ተራማጅ በሆኑ የትግራይ ተወላጅ ወጣቶች አማካይነት ማህበረ ገስገስቲ ብሔረ ትግራይ (ማገብት) የሚል ማህበርን በመመስረት ነው፤ ወዲያው ደርግ ወደ ስልጣን በመምጣቱ እንቅስቃሴው የቆየው ለአጭር ጊዜ ብቻ ነበር፤ ምክንያቱም ደርግ እንደመጣ አንዳንድ አዋጆችን በተለይም ዴሞክራቲክ መብቶችን እያፈነ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሲከለክል በድብቅ እንኳን መንቀሳቀሱ ከባድ ስለሆነ ወደ ገጠሩ ወጣ ብለንና ጫካ ገብተን የትጥቅ ትግል መጀመር አለብን ብለን ወዲያውኑ በ1967 የካቲት ወር ወደ ትጥቅ ትግል ገባን፤ ወደ ጫካም ስንወጣ እንደሚታወቀው ጥቂት ሰዎች ነበርን፤ ነገር ግን እንቅስቃሴያችንን ደርግም ሊቆጣጠረው ስላልቻለ አመቺም ሆነልን፤ በዚህ መልክም ትግሉ ተጀመረ ፤
አዲስ ዘመን፦ እርስዎ ደግሞ ድርጅቱን ከመሰረቱት አንዱ ቢሆኑም ብዙም ሳይገፉበት ለመውጣትዎ ምክንያቱ ምንድን ነው?
አቶ ግደይ ፦ እንደ ምክንያት በተለይም በእነሱ በኩል የሚቀርበው ፖለቲካዊ ልዩነት አለን የሚል ነው፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እኛን ለመወንጀል ሲፈልጉ ጥለውን ሄዱም ይላሉ፤ ነገር ግን መነሻው ምክንያት በህወሓት ውስጥ ማርክሲስት ሌሊኒስት ርዕዮተ ዓለም ሲመሰረት በወቅቱ በተለይም ጥቂቶች የስልጣን መወጣጫ ነበር ያደረጉት፤ ስልጣናቸውን ለማሰንበት ሲሉ ደግሞ እኔንና ዶክተር አረጋዊ በርሄን በተለያዩ ምክንያቶች መወንጀል ጀመሩ፤ በተለይም ከእኔ ጋር የሃሳብ ልዩነቶች ስለነበሩ ምንም እንኳን በድርጅቱ ውስጥ ሃሳብን አንስቶ የመከራከር መብቱ ቢኖርም በእኔ በኩል የሚነሱ ሀሳቦችን ግን በማዋደቅ ልዩነቶች እንዲሰፉ በማድረግ እኔን ከድርጅቱ ለመነጠል ይሰራ ነበር፤
በእርግጥ አንዳንዶቹ ጉዳዮች የፖሊሲ ጥያቄዎችም ነበሩ፤ ለምሳሌ ከኤርትራ ጋር በነበረን ግንኙነት ዙሪያ ታክቲካዊ ይባል የሚል ሃሳብ ያነሱ ነበር፤ እኔ ደግሞ ታክቲካዊ ስትራቴጂያዊ ሳንል ዝም ብለን እንቀጥል፤ ስያሜ መስጠቱ ምንም ትርጉም የለውም የሚል አቋም ነበረኝ፤
ሌላው የአልባንያ ተከታዮች ነን፤ እኛ ማርክሲስት ሌሊኒስት ነን፤ ብለን አላማችንን ለዓለም ህዝብ ማሳወቅ አለብን የሚል አመለካከት ነበራቸው፤ እኔ ደግሞ በዚህ ወቅት ይህንን ለማለት አንገደድም አያስፈልገንም አልኩ፤ ምክንያቱም በድርቁ ወቅት እንኳን እርዳታን የምናገኘው ከአውሮፓውያኑ ስለነበር ይህንን ማለታችን ምንም ለውጥ አያመጣም በማለት በአቋሜ ጸናሁ።
በወቅቱም አንድ የእኛ አቻ ልትሆን የምትችለው አልባንያ ነች፤ ይህች አገር ደግሞ ማንም አያውቃትም፤ ከዚህ አንጻር ከላይ የተገለጹትንም ሆነ ሌሎችን ሀላፊነቶች መውሰድ የለብንም የሚል አቋም ነበረኝ፤ ግን ይህንን ሁኔታ እነሱ ተጠቀሙበት።
በተጨማሪም የሀሳብ ልዩነቶች ነበሩን፤ ህዝባዊ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚባለው ትግል የተነሳንበት አገራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት ከበርቴው አሰላለፍ ሰራተኛውን ማስገደዱ እኔ ታክቲካል ነው ስል እነሱ ደግሞ ስትራቴጂካል ነው አሉ፤ እዚህ ላይ ግን ማርክሲስት ሌኒኒስት ነው ብለው ይህንን አቋም መያዛቸው ደግሞ ምን ያህል የአቋም መዋዠቅና እርስ በእርሱ የሚጋጭ ሃሳብ እንደሚያራምዱ ያሳያል፤ በዚህም ልዩነታችን ሰፋ፤ ይህ ደግሞ ወደተግባር ሲመጣ በፖሊሲም ላይ መስማማት አቃተን።
ይህንንም እንደ ልዩነት ወስደው ከድርጅታችን ጋር መቀጠል አትችልም አሉ፤ እንደውም ወደመጨረሻ ላይ ዓላማ የለህም ወደማለት ከመድረሳቸውም በላይ ታጋዩን በዚህ ሁኔታ ለማሳመን ከፍተኛ ጥረት አደረጉ፤ በእርግጥ በወቅቱ ታጋዩ እንኳን ተቀብሎታል ለማለት አይቻልም፤ እኔ ግን ቢያንስ በታክቲካል ደረጃ እንኳን ልታገል እችላለሁ ብዬ ጠይቄ አልተቀበሉትም፤ እነሱ አይቻልም ሲሉኝ ወደ ኢትዮጵያን ዴሞክራቲክ ንቅናቄ በመቀላቀል ትግሉን ለመቀጠል አስቤ ነበር፤ ነገር ግን እንዳትቀበሉት በመባሉ ፍላጎቴ ሳይሳካ ቀረ፤ እንደዚህ ሲሆንም ተስፋ በመቁረጥ ከአገር ለመውጣት በቃሁ።
አዲስ ዘመን፦ እርስዎ የድርጅቱ መስራች እንዲሁም በከፍተኛ ሀላፊነት ላይ ሁሉ የነበሩ ከመሆኖ አንጻር በዚህ መልኩ ከድርጅቱ መሰናበትዎ ምን ዓይነት ስሜት ፈጠረቦት?
አቶ ግደይ፦ በዚህ መልኩ ከድርጅቱ መሰናበቴ ያልጠበኩት ያልገመትኩት ሆነብኝ ፤ በወቅቱ ከትግሉ ወጥቼ ሌላ ነገር ውስጥ እገባለሁ የሚል ሀሳብም አልነበረኝም፤ ምን እንደማደርግ የት እንደምሄድ ሁሉ በጣም ግራ ገብቶኝ ነበር፤ በወቅቱ የነበረኝ አማራጭ ከኢትዮጵያ ውጪ መውጣት ነበር፤ በዚህም ወደ ውጪ በመሄድ ያቋረጥኩትን ትምህርት በመጀመርና በኮምፒዩተር ሳይንስ ሁለተኛ (ማስተርስ) ዲግሪዬን በማግኘት ስራ ጀመርኩ።
አዲስ ዘመን ፦ ለእርስዎን ከድርጅቱ (ከህወሓት) መስራች አባልነት ለመሰናበት እነ አቶ ስዬ አብርሃና አቶ ስብሃት ነጋ ከፍተኛ ሴራ እንደጠነሰሱ ይነገራልና በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ ግደይ፦ አዎ ድርጅቱ ውስጥ የምንሰራው በእምነት ነው፤ ጓደኞቻችን በእኛ ላይ እንደዚህ ዓይነት ሴራ ይሸርባሉ ብለንም በፍጹም አናስብም ነበር፤ ሆኖም በወቅቱ አራት ሆነው አንድን ሰው ሲከሱ ከእኔ ይልቅ እነሱ ናቸው የሚታመኑትና በዚህ መልኩ የሃሰት ክስና ሴራ እየሸረቡ ለመሰናበቴ ምክንያት ፈጠሩ፤ በነገራችን ላይ በሴራው የተሳተፉት መለስ ዜናዊ፤ ስዬ አብርሃ፤ አባይ ወልዱና ስብሃት ነጋ ጭምር ናቸው፤ በተለይም እኔን ለማስወገድ የዓላማ ልዩነት መያዜ ነገሩን በጣም ነው ያቀለለላቸው፤ እዚህ ላይ ግን የእኔ የሀሳብ ልዩነት ከድርጅቱ የሚያስወጣኝ ነወይ ብለን ብንል በፍጹም አይደለም፤ ነገር ግን ሴራቸውን ጎንጉነውና እኔን ከድርጅቱ አስወጥተው ለስልጣን መረማመጃነት ተጠቀሙበት፤
አዲስ ዘመን፦ በወቅቱ ከድርጅቱ ተወገዱና እርስዎም ወደውጪ ሄዱ፤ ባሉበት ሆነው ግን የህወሓትን አካሄድ ሲመለከቱት ምን ይሰማዎት ነበር?
አቶ ግደይ፦ ከድርጅቱ ከተሰናበትኩ በኋላ ወደ ውጭ አገር ብሄድም ከሌሎች መሰል ድርጅቶች ጋር በመሆን ትግሌን አላቋረጥኩም ፤ ነገር ግን ድርጅቱን ስታዘበው በውስጡ የነበረው ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እንደጠፋ እገነዘብ ነበር፤ ድርጅቱም መስመሩን ስቶ የሴራ ሂደትን አጠናክሮ በመቀጠል ከእኛ በኋላም ብዙዎችን የግደይ የአረጋዊ ተከታይ እየተባሉ ሲገደሉ፤ ሲገለሉ፤ እንደነበር እሰማ ስለነበር ድርጅቱ መስመሩን እንደሳተም እገነዘብ ነበር።
በሌላ በኩልም ድርጅቱ ከጫካ ወጥቶ ስልጣን ከያዘም በኋላ ቢሆን ኢ- ዲሞክራቲክ፤አፋኝ ሌላ ተቃዋሚ እንዳይታይ የሚያደርግ፤ ለይስሙላ ምርጫ የሚያደርግ፤ በጎን ደግሞ ግልጽና ፍትሃዊ እንዳይሆን ጠንካራ ስራን የሚሰራ፤ አገሪቱ በአንድ ፓርቲ ቁጥጥር ስር እንድትወድቅ ያደረገ የተቃወሙትን የገደለ፤፤ ያፈነ፤ ያሰረ፤ ያሰደደ እየሆነ መምጣቱን እታዘብና አዝን ነበር።
ስልጣን እንደያዙም ወዲያውኑ ሙስና ውስጥ ነው የተዘፈቁት፤ ገንዘብ ማካበት ላይ ከፍተኛ የሆነ ትኩረት አድርገው ሰርተዋል፤ እኛም በውጭ አገር ሆነን ከሌሎች ተመሳሳይ ዓላማ ካላቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ሁኔታውን ለመታገል ከፍተኛ የሆነ ጥረትን አድርገናል።
አዲስ ዘመን ፦ ከብዙ ዓመት የስደት ኑሮ በኋላ ለውጡን ተከትሎ ወደ አገር ከገቡ ተቃዋሚዎች መካከል አንዱ ኖትና ይህ በእርስዎ ላይ ምን ፈጠረቦት?
አቶ ግደይ፦ በህዝቡ ግፊት ኢህአዴግ ስልጣኑን የተቀማበት እንደውም ተገዶ ስልጣኑን ያስረከበበት ሁኔታ ነው ያለው፤ ለውጡን አብዛኛው የአገሪቱ ህዝብና ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት የተቀበሉት ቢሆንም እንደ ህወሓት ያሉት ደግሞ ለመቀበል ሳይፈልጉ ቀርተዋል፤ በነገራችን ላይ ለውጡን ተከትሎ እንደ ኢህአዴግ ድክመታቸውን የሰሩትን የሙስና ስራ ሁሉ አምነዋል፤ ፖለቲካል ነጻነት እንደነፈጉ ተቃዋሚዎችንም እንዳሳደዱ የህብረተሰቡን የመናገር ነጻነት ነፍገው አፍነው እንደገዙ ሁሉ አምነው እንታረማለን ብለውም ነበር፤ ነገር ግን ወደ ተግባር ሲመጣ አንድነት ጠፋ። በተለይም ህወሓት ከድሮ አስተሳሰቡ መውጣት አልቻለም፤ በአገሪቱ ላይ የሚካሄዱ ፖለቲካዊ ሁነቶች ላይ ሁሉ ለመሳተፍ ፍጹም ፍቃደኛም መሆን አልቻለም፤ በዚህ ሂደትም ከኢህአዴግ ወጥተው እንደተመለከትነው ትግራይ ላይ ሄደው ነው የመሸጉት፤ እዛም ሄደው ደግሞ የድሮውን ስራቸውን ነው የቀጠሉት። በክልሉ ምንም ዓይነት ነጻነት እንዳይኖር ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ወደክልሉ ገብተው እንዳይንቀሳቀሱ ማድረግ ቋሚ ስራቸው ነበር ፤ በሌላ በኩል ደግሞ እኛ ካልመራን አገር አገር አትሆንም በሚል የድሮ አስተሳሰባቸው መንግስትን ሲሞግቱ ፈተና ሲሆኑበት በመላው አገሪቱ ባሰማሯቸው የጥቅም ተጋሪዎቻቸው አማካይነት እዚህም እዚያም እሳት ሲለኩሱ ነው የነበሩት።
የአምባገነንነታቸው ብዛት ደግሞ የመንግስትን ትዕዛዝ አንፈጽምም፤ የፓርላማውን ውሳኔ ተግባራዊ አናደርግም፤ እስከማለት አድርሷቸው ነበር፤ በሌላ በኩልም በወንጀል የሚፈለጉ ግለሰቦችን በመደበቅ የመንግስትን ትዕግስት ሲፈታተኑም ቆይተዋል፤ ከዚህ አልፈውም ከድንበር ጋር እያያያዙ ህዝቡን እከሌ ጠላትህ ነው፤ ተነስ ታጠቅ በማለት ወጣቱ በልዩ ሃይል ሲመለምሉ ሲያሰለጥኑና ሲያስታጥቁም ነው የከረሙት።
ይህ ሁሉ ዝግጅት ደግሞ ሲደረግ የነበረው ለውጡን ለመቃወም ነበር፤ ይህንን እኩይ ተግባራቸውን ሲፈጽሙ የነበረው ትግራይ ላይ ብቻ ቁጭ ብለው ሳይሆን በመላ አገሪቱ ተከታዮቻቸውን በማሰማራት የጥቅም ትስስር በመፍጠር ነበር፤ በዚህም በየአካባቢው የተለያዩ ችግሮችን ሲፈጥሩም ቆይተዋል።
በመጨረሻም ምርጫው በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ይራዘም በተባለበት ጊዜ አይሆንም ብለው በመቃወም ህገ ደንባችን ይከበር ቢሉም ህገ ደንቡን ተከትሎ የሚቀርበውንም ውሳኔ ባለመቀበል የሚያክላቸው አልነበረም፤ በመሆኑም ህገ ደንቡ ለእነሱ እኩይ ተግባር ሲስማማ የሚቀበሉት ሳይስማማ ደግሞ የሚሽሩት አይነት
ሆኖ ቀጥሎም ነበር፤ ምርጫ እናደርጋለን ብለው ህገወጥ ስራን ከመስራታቸው ባሻገር ከመስከረም 25 በኋላ መንግስት የለም በማለትን ሲንቀሳቀሱም ታይተዋል።
ይህ ሁሉ መካረር ሲመጣም ነገሩን ለማቀዝቀዝ በሀገር ባህልና ወግ ሽምግልና ቢላክባቸውም አሻፈረን ያሉም ናቸው ፤ በመሆኑም የዚህ ሁሉ ጥጋብ መጨረሻው ጦርነት ሆኗል፤
አዲስ ዘመን፦ እርስዎ ከህወሓት አነሳስ አንጻር የህግ ማስከበር ዘመቻውን እንዴት አዩት?
አቶ ግደይ፦ የሰሜን እዝ ጦር የአገሪቱ የጀርባ አጥንት መሆኑን ስለሚያውቁ የትግራይ ልጆችን ነጥለው በማውጣት ሌላው ላይ ያደረሱት ጥቃት ሁላችንንም ያሳዘነ የድርጅቱንም ሰይጣናዊነት በገሃድ ያሳየ ነው፤ ይህ ሃይል ድንበር ጠባቂ ነው፤ በትጥቅ ይዘትም ትልቅ ነው፤ እዚህ አካል ላይ ይህ መሰሉ ጥቃት ሲሰነዘር መንግስት ምን ሊያደርግ ይችላል፤ ሊያደርግ የሚችለው ብቸኛ ነገር የህግ ማስከበር ዘመቻውን መጀመር ነው ፤ እርሱንም አድርጓል፤ ትክክለኛ እርምጃም ነበር፤ ማንም አገር ይህንን መሰሉን ጥቃት ዝም ብሎ ሊያይ አይችልም፤
እነሱ በወሬያቸው “በሰሜን እዝ ላይ መብረቃዊ ጥቃት” ፈጸምን በማለት ሲኩራሩ ነበር። ነገር ግን ፍጻሜው ያየነው ነው የሆነው፤ በበኩሌ የህግ ማስከበር ዘመቻው ትክክለኛ እርምጃ ከመሆኑም በላይ ሁላችንም ከገመትነው ጊዜ እጅግ ባጠረ የተፈጸመ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፤ በአስራ አምስት ቀን ከሁመራ መቀሌ መድረስ በጣም ከባድ ከመሆኑ አንጻር ለሰላም ወዳድ ዜጋ ሁሉ ትልቅ ውጤት ነው፤ ይህንን የህወሓት ድርጊት የማየው በአገር ክህደት፤ በዘር ማጥፋት ወንጀል ጭምር ነው።
አዲስ ዘመን፦ እንደው እርስዎ ድርጅቱን ከቀድሞ ባህርይው አንጻር በዚህ መልኩ መከላከያ ሰራዊትን መዳፈሩ እንዴት ይገልጹታል?
አቶ ግደይ፦ ንቀትና ትዕቢት በሁሉም አምባገነን መሪዎች ላይ የሚታይ ነው፤ እነዚህ ሰዎች የትምክህታቸው መነሻ እንግዲህ ትልቅ አቅም የነበረውን የደርግ ሰራዊት አሸንፈናል የሚል ነው፤ ሌላው ደግሞ በዘመናቸው በአገሪቱ ውስጥ የፈለጉትን ነገር ሲያደርጉ የኖሩ ከመሆናቸው አንጻር በጦርነቱም የሚያግዘን አናጣም ሁሌም አሸናፊ ነን የተነጠቅነውንም ስልጣን መልሰን እንይዛለን የሚል ተስፋ ሰንቀው ነበር፤ ይህንን ባህሪያቸውን በመጠቀምም ህዝቡን ለማሳሳትና ወደራሳቸው ለመሳብም ሞክረው ነበር ነገር ግን ሳይሳካላቸው ቀርቷል፤ ጦርነቱንም በሚያስደንቅ ሁኔታ ተሸንፈው በየዋሻው ቀርተዋል።
አዲስ ዘመን ፦ ህወሓት አንዱ መሸሸጊያው ህዝቡ ነበር ፤ ህወሓትና የትግራይ ህዝብ አንድ ነው ድርጅቱን መንካት ህዝቡን መንካት ነው እያሉም ሲያስፈራሩ ከርመዋልና እንደው ህዝቡን እንደጠበቁት አግኝተውታል ማለት ይቻላል?
አቶ ግደይ፦ ተቃራኒው ነው የሆነው፤ የትግራይ ህዝብ ለእንደዚህ ዓይነት ጦርነት እንደማይሞትላቸው ነው በግልጽ ያሳያቸው፤ ህዝብ በቀደመው የትጥቅ ትግል ወቅት አላማቸውን በመደገፍ አረጋውያን ጧሪ ቀባሪ እስከሚያጡ ድረስ ልጆቻቸውን ገብረዋል፤ ይህንን አደርገው ግን እነሱ ስልጣን ከያዙ በኋላ እነዚህን አካላት ዞርም ብለው አላዩአቸውም ፤ ረስቷቸዋል፤ ምንም ያገኙትም ነገር የለም፤ ከጥቅሙ ይልቅ ያገኙት ነገር ቢኖር ጭቆና፤ፍትህ ማጣት፤ ፍርሃት፤ታፍኖ መኖርን ነው፤ ለዚህ ውለታቸው ነው ዛሬ ዳግም ለእነሱ የስልጣን እድሜ ማራዘሚያ ሲባል ልጆቹን የሚገብረው፣ የሚሞተው፣ የሚቆስለው፡፡
እዚህ ላይ እኮ ከትጥቅ ትግሉ በኋላ ላለፉት 27 ዓመታት መንግስት ሆነው ህዝቡን አስተዳድረዋል፤ አሁን ህዝባችን ብለው ለተሸሸጉበት ምን ሰጡት ? የእለት ጉርሱን እንኳን ያገኝ የነበረው ከሴፍቲኔት ነው፤ ታዲያ ምንም ላላደረገለት ሃይል ድጋሚ መስዋዕት የሚሆንበት ምክንያትስ ምንድን ነው? ይህንን ደግሞ በተጨባጭ አሳይቷቸዋል፤
ለነገሩ ሆ ብሎ ወደ ግንባር የሄደላቸው በርካታ ሰው ነበር። ምናልባት እነዚህ ወጣቶች ስራ ለማግኘት ለእለታዊ ፍላጎት አልያም በግድ የሄዱ ሊሆኑ ይችላሉ፤ በገፍ አሰልጥኖ ወደጦር ሜዳ ማስገባት ብቻውን ግን አሸናፊ እንደማያደርግ ደግም አሳይተውታል፤
በመሆኑም ህወሓቶች የዘመናት ድርጊታቸው ለዚህ አሁን ላሉበት ውርደት ሞትና መደበቅ ዳርጓቸዋል፤ ይህ እንዳይመጣ ደግሞ ተደጋጋሚ ልመናና ምክር ተሰጥቷቸዋል ነገር ግን እነሱ ከስልጣን በላይ የሚያስቀድሙት ነገር ስለሌለ አሻፈረኝ ብለው እዚህ መሰል ጦርነት ውስጥ ገብተው ተዋርደዋል፤
በነገራችን ላይ ድርጅቱ ለህዝቡ ባዕድ መሆኑን ወይም ምንም እንዳልጠቀመው የሚያሳየው ህዝቡ በዚህች ትንሽ ችግር የገባበትን የኢኮኖሚ ቀውስ ነው፤ ለአጭር ጊዜ እንኳን ችግርን ተቋቁሞ ማለፍ የማይችል ህዝብን ነው ያተረፉት፤ እነሱ አመራር በነበሩነት ወቅትም ያን ሁሉ መስዋዕትነት የከፈለላቸው ዜጋ በሴፍቲኔት ታቅፎ ነው ህይወቱን ለማቆየት ሲጥር የነበረው፤
ህዝቡና ድርጅቱ አንድ ቢሆኑ ኖሮ እኮ ጦርነቱም እንደዚህ ባለ አጭር ጊዜ አይጠናቀቅም ነበር ምክንያቱም ህወሓት አብዛኛውን ሰው አስታጥቃለች ነገር ግን ህዝቡ መሳሪያ ላስታጠቀኝ አካል ብሎ እንኳን አንዲት ጥይት ሳይተኩስ ነው መሳሪያውን እያስረከበ እጅ የሰጠው፤
አዲስ ዘመን፦ አሁን አሁን እየሰማን ያለነው ነገር ደግሞ ከኢትዮጵያ ውጪ ያሉ የህወሓት አመራሮች ድርጅቱን እንደገና እንመሰርታለን እያሉ ይንቀሳቀሳሉና እንደው ህወሓትን እንደገና መመስረት ይቻላል?
አቶ ግደይ፦ በጦርነት አካሄድ ካየነው ድርጅቱ ተመቷል፤ ተዳክሟል፤ ከዚህ በኋላም እንደገና ሊያንሰራራ የሚችልበት እድል የለውም፤ እንደ ድሮው በሽምቅ ውጊያ ህዝቡን አነሳስቼ አፈር ልሼ እነሳለሁ የሚሉት ምን ያህል ህዝቡን የሚያሳምን አጀንዳ ይዘው ነው ይህንን የሚሉት? የሚለው ጥያቄ ሊነሳላቸው ይገባል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን ይዘው እንኳን ማሸነፍ ያቃታቸው አሁን እንደገና ከመሬት ተነስተው አቋቁማለሁ ማለት የማይመስል ነገር ነው።
አዲስ ዘመን፦ ህወሓት እንግዲህ ከድሮ ጀምሮ የሚፈልገውን ለማግኘት የማይፈልገውን ለማስወገድ ይጠቀም የነበረው አካሄድ ሴራ መጠንሰስ ነበር፤ ለዚህ ደግሞ እርስዎ ላይ የደረሰው ብቻ ማሳያ ነው፤ ከዚህ አንጻር ይህ የሴራ ፖለቲካው የት አድርሶታል ማለት ይቻላል?
አቶ ግደይ፦ አዎ ሴራቸውማ በጣም ከባድ ነው፤ እርስ በእርሳቸውም እየተባሉ ነው እዚህ የደረሱት፤ አስተውላችሁ ከሆነ ከእኛ በኋላም በ1992 እና 93 ዓ.ም በውስጣቸው በተፈጠረው ልዩነት ምክንያት እነ አረጋሽና ሌሎችም ተመተው ወጥተዋል፤ ይኸው የሴራ አካሄዳቸው ለስብሃትና ለአባይ መመታት ምክንያት ሆኗል፤ እነ ስዬም አልቀረላቸውም ፤ በመሆኑም ይህ የመጠላለፍና የሴራ አካሄዳቸው እርስ በእርሳቸው እያዳከማቸው እንደመጣ አይተናል፤ በመጨረሻም ድርጅቱ ብቃት ያላቸው ሰዎች የሚሰሩበት ሳይሆን ለእኔ የሚያገለግለኝ፤ ዝም ለጥ ሰጥ ብሎ የሚታዘዘኝ ማነው የሚለውን የማየትና እነዚህን ሰዎች ወደላይ እያመጣ የሄደበት ሁኔታ ነው የተስተዋለው፤ በዚህ ምክንያት ደግሞ ከፍተኛ የሆነ ውስጣዊ ድክመትን ማስተናገድ ጀመረ።
በተለይም አቶ መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ ድርጅቱ ራሱን ችሎ መቆም ተስኖትም ነበር፤ በዚህም አመራሮቹ ደካሞች እርስ በእርሳቸው የሚፋጠጡና የሚጓተቱ ነው የሆኑት፤ ይህም የሴራው ውጤት በመሆኑ መጨረሻው በራሱ አካሄድ መበላት ሆኗል።
አዲስ ዘመን፦ ከህግ ማስከበር ዘመቻው በኋላ የተሰየመው ጊዜያዊ አስተዳደር ደግሞ ክልሉን ከማረጋጋት ጀምሮ በጦርነቱ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን ፤ የመንግስትና የግል ተቋማትን፤አገልግሎት መስጫዎችን መልሶ የማቋቋም አሁን ደግሞ ህዝቡን ከገባበት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር ማላቀቅ ላይ ነው ፤ ለዚህ ስራው ደግሞ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም አብረን እንስራ የሚል ጥሪንም አቅርቧልና ይህንን እርስዎ እንዴት ያዩታል?
አቶ ግደይ፦ ይህ በጣም ትልቅ ፈተና ነው፤ በተለይም ክልሉ ካለበት ሁኔታ አንጻር ጊዜያዊ አስተዳደሩ በደንብ የተጠናከረ ሃይል ነው ለማለት አይቻልም፤ ይህንን አስተካክሎ መልሶ እንደነበረ በማድረግ ህዝቡን መምራት በጣም ፈታኝ ነው፤ አሁን ባለው አካሄድም እየታየኝ ያለው ነገር ከብልጽግና ፓርቲም ይሁን ከሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ያለው አካሄድ ላይ የተጠናከረና የተደራጀ አሰራር አለመከተሉን ነው፤ በመሆኑም አሰራሩን መፈተሽ ከእነዚህ ድርጅቶች ባሻገር ተሰሚነት ያላቸውን ሰዎች ማሳተፍ አለበት የሚል እምነት አለኝ፤
በእርግጥ የእኛ ፓርቲ አባላትም ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር በመሆን የተለያዩ እገዛዎችን እያደረጉና እየሰሩ ነው። ነገር ግን ይህ በቂ ባለመሆኑ ስራውን እንደገና ማየትና ሌሎችንም ሃይሎች ማሳተፍ ማማከር ያስፈልጋል፤
አዲስ ዘመን ፦ አሁን ላይ የትግራይ ህዝብ ችግር ላይ ወድቋል፤ ነገር ግን በተለይም በውጭ አገር የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ችግሩን ከማራገብ በዘለለ ምንም ዓይነት ድጋፍ ሲሰነዝሩ አይታይምና እንደው እነዚህ ዜጎች ሚናቸው ምን ሊሆን ይገባል ይላሉ?
አቶ ግደይ ፦ በእርግጥ መጀመሪያ በአገር ውስጥ ያለውን ህዝብ በደንብ ማንቀሳቀስ ያስፈልጋል ፤ ምክንያቱም ውስጥ ያለው ህዝብ ነው ትልቅ ሚና ሊጫወት የሚችለው፤ በመሆኑም በዚህ ላይ የሚያስተባብር አካል ተፈጥሮ ሰፋ ያለ ስራ መሰራት ይኖርበታል፤ በውጪም ሆነው እንረዳለን የሚሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አሉ፤ ነገር ግን አሁን ላይ እርዳታውን ይዘን ለመግባት አልተፈቀደልንም ሲሉ ይሰማል፤ መንግስትም ግቡ እያለ ነው፤ በመሆኑም በዚህም በኩልም ጥሩ ድጋፍ ሊያደርጉ ስለሚችሉ የእነሱንም ደህንነት እየጠበቁ የሚሰሩትንም ስራ በአይነ ቁራኛ እየተከታተሉ መጠቀም ያስፈልጋል፤ ነገር ግን በትግራይ ህዝብ ላይ በተፈጠረው ነገር መንግስት ተከሳሽ ሊሆን አይገባም ባይ ነኝ።
ውጪ ያሉት አካላትም የሚጮሁት ያኔ በስልጣን ላይ እያሉ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የፈጠሩት ቁርኝት ትልቅ ስለነበርና የጥቅም ተካፋይ ስለነበሩ ነው፤ ይህንን ወሬያቸውን አደብ ለማስገዛት ወይም በዜሮ ለማባዛት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሃላፊነት ያለበት ከመሆኑም በላይ መንግስትም ያለምንም ድበቃ መሬት ላይ ያለውን እውነት ግልጥ አድርጎ ማሳየት ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ፤
አቶ ግደይ፦ እኔም አመሰግናለሁ
አዲስ ዘመን የካቲት 05/2013