ሶሎሞን በየነ
ኢንሱሊን የስኳር ህመም ላለባቸው ህሙማን (ዓይነት1 ስኳርና ለተወሰኑት ዓይነት 2 ስኳር ህመም) ለማከም ከሚያግዙ መድኃኒቶች መካከል ዋነኛውን ስፍራ የሚይዝ ነው፡፡ የስኳር ህመምን ለመቆጣጠር ደግሞ ይህንን መድኃኒት ታካሚዎች በተገቢው መንገድ መውሰድ የሚጠበቅባቸው ቢሆንም ቅሉ፤ አሁን ላይ በአገሪቱ እየታየ ያለው የኢንሱሊን እጥረትና የአቅርቦት መቆራረጥ ስጋት የፈጠረባቸው አንዳንድ ህመምተኞች መንስኤው ምን ይሆን? ሲሉ በኢሜል አድራሻችን ጥያቄያቸውን ለሚመለከተው አካል እንድናደርስ ለዝግጅት ክፍላችንን ጠይቁልኝ በሚል ጠይቀውናል።
በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የመድኃኒት የመጋዘን አያያዝና ክምችት አስተዳደር ዳይሬክተር ወይዘሮ ገዳምነሽ አስፈራሁ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ እንደገለጹት፤ ኤጀንሲው ከተቋቋመበት ዓላማ አንጻር ከህይወት አድን መድኃኒቶች ባለፈ ሌሎች መድሃኒቶችን ጭምር ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በአገሪቱ ለ18 ቅርንጫፎች መድኃኒቶቹን ተደራሽ ያደርጋል። በዚህም እያንዳንዱ ቅርንጫፎች ምን ያህል የኢንሱሊን መጠን እንደሚጠቀሙ ይታወቃል። ቅርንጫፎቹ ደግሞ በስራቸው ያሉ የመንግሥት የጤና ተቋማትና የከነማ መድኃኒት ቤቶች በወር ምን ያህል መጠን ኢንሱሊን እንደሚጠቀሙ ይታወቃል።
ነገር ግን በዓለም ላይ የተከሰተውን የኮረና ቫይረስን ተከትሎ በሎጅስቲክና በውጭ ምንዛሬ እጥረት ሳቢያ ከዚህ በፊት በግል ኢንሱሊን ሲያስመጡ የነበሩ ተቋማት አሁን ላይ እያስመጡ አለመሆኑን ተከትሎ መድኃኒቱ ህይወት አድን በመሆኑ ህመምተኞች ወይም ተጠቃሚዎች ይጠፋል በሚል ስጋት በፊት በወር በወር ይወስዱ የነበሩ አሁን ላይ የሁለትና የሦስት ወር መድሃኒት የመውሰድ ነገር ታማሚዎች ላይ መታየቱን ይናገራሉ።
ይህንን ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ ውይይቶችን በማድረግ የግሉ ሴክተር የውጭ ምንዛሬ ተፈቅዶላቸው ኢንሱሊን እንዲያስመጡ እየተደረገ ያለበት ሁኔታ ስላለ እጥረቱ ይከሰታል የሚል ስጋት ህብረተሰቡ እንዳያድርበት የሚሉት ዳይሬክተሯ፤ በተለይ ችግሩ በመዲናዋ ጎልቶ መታየቱን ተከትሎ ከዚህ በፊት ኢንሱሊን በመንግሥት ተቋም የማይወስዱ ህመምተኞች በከነማ መድኃኒት ቤት በኩል እንዲያገኙ ከ40 በላይ የከነማ መድሃኒት ቤቶች ጋር በመወያየት ህመምተኞች ሳይጉላሉ መድሃኒቱን እንዲያገኙ የማድረግ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።
ዳይሬክተሯ ብዙ ጩኸት ያለው አዲስ አበባ ላይ በመሆኑ ኤጀንሲው ከ40 በላይ የከነማ መድኃኒት ቤቶች ጋር በመነጋገር ኢንሱሊንን እንዴት ማስተዳደርና መያዝ አለበት? እንዴትስ ለህብረተሰቡ ተደራሽ መደረግ አለበት? አንድ በሽተኛ ምን ያህል መጠን በምን ያህል ጊዜ መውሰድ አለበት? እየተባለ በጥልቅ እየተሰራ በመሆኑ ምንም አይነት እጥረት እንደማይፈጠር ተናግረዋል።
ማዕከል ላይ በቂ የኢንሱሊን ክምችት ከመኖሩ ባሻገር ከውጭም ተገዝቶ እየተጓጓዘ ያለ በቂ ኢንሱሊን እየገባ መሆኑን ወይዘሮ ገዳምነሽ ጠቁመው፤ ስለዚህ የኢንሱሊን እጥረት ያጋጥማል ብለው ስጋት ያላቸው ሰዎች መረጋጋት አለባቸው። በኮሮና ቫይረስ በፈጠረው ጭንቀት ሳቢያ የኢንሱሊን እጥረት ይኖራል የሚል ስጋት በህመምተኞች ቢያድርም ቅሉ ዘንድሮ በማዕከሉ ያለው የኢንሱሊን ክምችት ከ2011 እና 2012 ዓ.ም የበለጠ ክምችት እንዳለ ገልጸዋል።
ስለዚህ ብሄራዊ የኢንሱሊን የክምችት መጠኑ ስለሚታወቅ ህብረተሰቡ ኢንሱሊን የለም ብሎ መጨነቁን ማቆም አለበት። አሁን ላይ አገሪቱ በቂ የኢንሱሊን ክምችት ነው ያላት። እነዚህ የህይወት አድን መድሃኒቶች ሳይኖሩ ለሰው ተስፋ አንሰጥም። ተቋሙም እነዚህን አይነት መድሃኒቶችን ለማቅረብ ከመቋቋሙ ባሻገር ባለሙያውም ሙያዊ ኃላፊነት ስላለበት እነዚህን ግብዓቶች በትክክል የማቅረብ ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ተገዝቶ መጋዘን ውስጥ የገባና ተገዝቶ በመጓጓዝ ላይ ያለ በቂ ክምችት የኢንሱሊን ክምችት ስላለ ህብረተሰቡ ሳይጨነቅ ተረጋግቶ እጁላይ ያለውን መድሃኒት መጠቀም እንዳለበት አሳስበው፤ እዚህ የመንግስት የጤና ተቋም ወይም ከነማ መድኃኒት ቤት ሂደን አገልግሎቱን ወይም አቅርቦቱን አጥተናል (ኢንሱሊን አጥተናል) የሚል መረጃ ካለ ኤጀንሲው ከነዚህ ተቋማት ጋር በመነጋገር ሳይውል ሳያድር ችግሩን ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።
አንዳንድ ነጋዴዎች ማዕከል ላይ ያለውን የኢንሱሊን ክምችት ካወቁ፤ ነጋዴዎች ክምችቱን ባወቁ ቁጥር የአቅርቦት ግዠበትና የዋጋ ከፍ ዝቅ ማለት ሊፈጠር ስለሚችል ያለውን የክምችት መጠን መጥቀሱ አላስፈላጊ መሆኑን ዳይሬክተሯ ጠቁመው፤ ነጋዴዎች የሚፈጥሩት ቅዠት ካልሆነ በስተቀር አሁን ላይ የኢንሱሊን መቆራረጥም ሆነ እጥረት እንደማይኖር ተናግረዋል። ምክንያቱም ምንም እንኳን መድኃኒቱን የሚጠቀም ቢበዛ ቅሉ ከአምናና ታች አምና በበለጠ የክምችት መጠኑ ዘንድሮ መጨመሩን በባለሙያዎች ተረጋግጧል። ስለዚህ በየትኛውም የመንግሥት የጤና ተቋምና የከነማ መድሃኒት ቤቶች የኢንሱሊን እጥረት የለም። የኢንሱሊን እጥረት አለ ያለ የመንግስት የጤና ተቋም ወይም የከነማ መድኃኒት ቤት ካለ መነጋገር ይቻላል።
ምክንያቱም ማዕከሉና ቅርንጫፎች የክፍፍል መርሐግብር አለ። ማዕከሉ የሚያከፋፍላቸው 18 ቅርንጫፎች በየወሩ ምን ያህል እንደተጠቀሙ፣ ምን ያህል ቀሪ እንዳላቸው እንዲሁም በቀጣይ ምን ያህል እንደሚያስፈልጋቸው ሪፖርት ሲያደርጉ የሚያስፈልጋቸው ታውቆ ከማዕከል ይለቀቅላቸዋል (ይላክላቸዋል)። እያንዳንዳቸው ቅርንጫፎች ደግሞ በስራቸው ያሉትን የጤና ተቋማትና ተጠቃሚዎች ስለሚያውቁ በዛመሰረት የሚያሰራጩ ይሆናል። ስለዚህ ማዕከሉ ቅርንጫፎቹ በሚያቀርቡት ሪፖርት መሰረት ምላሽ ይሰጣል። ከዚህ ውጭ በቅርንጫፎች ህመምተኞች ጨምሮ አስቸኳይ እርዳታ ከተጠየቀ በአሰራሩና ቅርንጫፉ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት የአስቸኳይ አቅርቦት ምላሽ የሚሰጥ ይሆናል ብለዋል።
በአጠቃላይ ኢንሱሊን ብቻ ሳይሆን ኤጀንሲው የሚያቀርባቸው ሌሎች የህይወት አድን መድሃኒቶች አሉ። በተቻለ መጠን እነዚህ መድሃኒቶች እንዳይቆራረጡ እየተሰራ ይገኛል። ስለዚህ በቂ ክምችት ስላለ ህመምተኛው በጭንቀት ሌላ በሽታ ሳይጨምር የሁለትና የሶስት ወር መድሃኒት ካለው ተረጋግቶ መጠቀም አለበት። መረጋጋት ከሌለ አንድ ሰው የአምስትና የስድስት ወር ኢንሱሊን በአንዴ ከወሰደ ኤጀንሲው ኢንሱሊን ተፈልጓል ብሎ በአንዴ ከመጠን በላይ ኢንሱሊን ቢያስገባ መድሃኒቱ የሚቀመጥበት ፍሪጅ ስለማይበቃ ሌሎች እንደ ኮረና ቫይረስ የመሳሰሉ ክትባቶችን አስገብቶ ፍሪጅ ውስጥ ለማከማቸት ቦታ ጠፍቶ መድሃኒቶች ለብልሽት ከመዳረጋቸው ባሻገር ከውጭ መግባት የሚገባቸው ሌሎች መድሃኒቶች እንዳይገቡ ቦታ ይይዛል።
ስለዚህ ህብረተሰቡ ተረጋግቶ ከዚህ በፊት በ2011 ዓ.ምና ከዚያ በፊት ይወስድ የነበረውን የኢንሱሊን መጠን በመውሰድ የመድሃኒት ክምችቱና ስርጭቱ የተረጋጋ ይሆናል። ስለዚህ ህዝቡ መረጋጋት አለበት። ምንም የኢንሱሊን እጥረት ስለሌለ ህብረተሰቡ ካላስፈላጊ ጭንቀት ውስጥ መውጣት እንዳለበት ዳይሬክተሯ አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 05/2013