ሰሎሞን በየነ
ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በመሬት ወረራ፣በጋራ መኖሪያቤቶች፣ ባለቤት አልባ በተባሉና ህንጻዎችና በንግድና በመኖሪያ የቀበሌ ቤቶች ላይ በመመርኮዝ የከተማ አስተዳደሩ ባስጠናው ጥናት ውጤት ላይ ከሰሞኑ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ 10 ሺ 565 የቀበሌ ቤቶች በቁልፍ ግዢ፣ሰብሮ በመግባት፣ ለሶስተኛ ወገን በማስተላለፍ፣ ወደ ግል ይዞታ በማዞርና በሌሎች ህጉ ከሚፈቅደው ውጪ በህገወጥ መንገድ ተይዘው እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
እነዚህን የቀበሌ ቤቶች ከላይ በተጠቀሱት አግባብ ወይም በህገወጥ መንገድ መያዝ የሚያስከትለው የህግ ተጠያቂነት ምን ይመስላል? ስንል ጥያቄ ያቀረብንላቸው የህግ ባለሙያ እንደገለጹት፤ የመንግስት ቤቶችን በህገ ወጥ መልኩ መያዝ በወንጀልም በፍታብሄርም ያስጠይቃል። በወንጀል ከሆነ እንደ ወንጀል ድርጊቱ የተለያየ ነው ። አንዳንዱ ማህተም ያለውን ቤት ሰብሮ የገባ ወይም ደግሞ ያለ አግባብ ወሮ የያዘ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ የወረሩ ከሆነ፣ የመንግስት ቤቶችን ያላግባብ በሆነ መልኩ ወስዶ ከሆነ ህጉ እንደሚለው ማንኛውም ሰው በሌላ ሰው ንብረት ላይ መብት ሳይኖረው ጥቅም ለማግኘት ሲል የሌላውን ሰው ይዞታ፣ የአንድን ሰው ህንፃ ወይም ቤቱን የያዘ እንደሆነ ወይም እንዳይጠቀምበት መከልከል፣ ለሌሎች አካላት አሳልፎ መስጠት ይህ በወንጀል ያስቀጣል።
ይህም አንዳንዱ በቀላል እስራት የሚያስቀጣ ወንጀል ሲሆን፤ አንዳንዱ ደግሞ ከበድ ያለ ቅጣት እንደሚያስቀጣ ባለሙያው ገልጸው፤ ለምሳሌ በተባባሪነት ፣ አደገኛ መሳሪያ በመያዝ ፣ ድርጊቱ ከተፈፀመ ደግሞ ወንጀሉ ከባድ ስለሚሆን አምስት ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራት ሊያስቀጣ ይችላል።
አንዳንዴ ደግሞ ወረው የያዙትን ቤት ይዞታውን ሊለውጡት ይችላሉ።ማለትም አፍርሰው ሌላ ሊሰሩበት ይችላሉ ፣ ወይም ደግሞ አፈር ቤት የነበረውን በብሎኬት
ሊያደርጉ ይችላሉ፣ ወይም በሌላ መልኩ የመኖሪያ የነበረውን ለሱቅ ወይም ንግድ ቤት ወዘተ መልኩ አድርገው ሊይዙት ይችላሉ። ሰለዚህ በዚህ ሁኔታ ይዞታውን የለወጡ ሰዎች ከሆኑ ደግሞ የወንጀል ህጉ 683 ላይ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት እንደሚያስቀጣ በግልፅ ተቀምጧል።ይህ ይዞታን የመቀየር ወንጀል ብዙ ጊዜ አጋጥሟል። ስለዚህ እነዚህ አካላት በወንጀል ህጉ የሚጠየቁ ይሆናሉ።
ሌላው መሰረታዊ ነገር በሰዎችና በመንግስት መካከል በቤቱ ይዞታ ላይ ክርክር ተነስቶ ሊሆን ይችላል፣ ወይም ለሌሎች ሰዎች እሰጣችኋለሁ ብሎ ያስቀመጣቸው ቤቶች ሊኖሩ ይችላሉ ። እነዚህን ቤቶች መንግስት አሽጎ ሊሆን ይችላል ፣ ማንም እንዳደርስባቸው ብሎ ማህተም አድርጎ ያስቀመጣቸው ቤቶች ሊኖሩ ይችላሉ ።እንዲህ ያሉትን ቤቶች ደግሞ ሰብሮ ወይም ቀዶ የገባው ደግሞ ሌላ ተጠያቂነት ነው ያለበት ። ማለትም በር ሰብሮ መግባት፣ መቅደድ ፣ ህጋዊ ሆነውን ማህተም አንስቶ ሊሆን ይችላል የገባው ይህን ያደረገ ከሆነ ደግሞ እንዲሁ በተመሳሳይ በወንጀል ህጉ 433 መሰረት ይቀጣል ማለት ነው።
በሌላ በኩል ቤቶቹን ለሶስተኛ ወገን አሳልፎ መስጠትንና የግል ይዞታ እያለው የቀበሌ ቤት ይዞ መገኘትን በተመለከተ አስተዳደራዊ ተጠያቂነት ይኖራል። ለአብነት አንድ ሰው ኮንደሚኔም ቤት ደርሶት እያለ የቀበሌ ቤት ይዞ እየኖረ ቢሆን በወንጀል መክሰስ ላይቻል ቢችል እንኳን በአስተዳደራዊ ተጠያቂነት ይኖርበታል።
በአጠቃላይ በቀበሌ ቤቶች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ሰዎች ብቻቸውን ሳይሆን ከባለሥልጣናት ጋር በመመሳጠር የሚያደርጉት ነው። ማለትም ቤቱን የሚወሩት ሰዎች በራሳቸው ተነሳስተው አይደለም ። ከመንግስት ባለሥልጣናት ድጋፍ በማግኘት፤ ወይም ደግሞ ሀሰተኛ ሰነድ በመጠቀም ቤቶቹን ለመያዝ ይሞክራሉ ። በዚህ መልኩ ከሆነ ደግሞ ኃላፊነቱ ሌላ ነው የሚሆነው ። እንዲህ ከሆነ ስልጣንን ያላግባብ መገልገል የሚባል ወንጀል አለ። በህጉም ተጠቅሷል እንዲሁም የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ በ2007 ዓ.ም በወጣ አዋጅ 881/ 7 መሰረት፤ እነዚያም ደግሞ በስልጣናቸው ያለ አግባብ በመገልገል ይጠየቃሉ ማለት ነው።
ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች የመንግስት ሰራተኞች ናቸው ። የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ብለው ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት ወይም በሌላ ሰው ጥቅም ላይ ጉዳት እንዲደርስ አስበው በተለያየ መስክ የተሰጣቸውን ሹመት ወይም ስልጣን ያለ አግባብ ተጠቅመው ወይም ደግሞ ከተሰጣቸው ስልጣን ውጭ አልፈው የማይገባቸውን ፈፅመው ወይም በስልጣናቸው የማይፈቀደውን ነገር አድርገው ከስራ መደባቸው ውጭ ወይም በህጉ ከተፈቀደላቸው አልፈው ሰርተው እነዚህን ቤቶች ለሰዎች አሳልፈው ሰጥተው ሊሆን ይችላል፣ ለራሳቸው ወስደው ሊሆን ይችላል ። እንደዚህ አይነት ሰዎች ከተገኙ ደግሞ በሥልጣን ያለ አግባብ በመገልገል ወንጀል ይጠየቃሉ ማለት ነው ።
ቅጣቱም በጣም ከባድ ነው የሚሆነው። ከአስር ዓመት የማያንስ ፅኑ እስራት ያስቀጣል። ወንጀሉ እየበዛ በሄደ ቁጥር፣ ኃላፊነቱ ከፍ ያለ ሰው ከሆነ እንዲሁም በወሰደው ነገር ያገኘው ጥቅም ከፍ ያለ እንደሆነ ወይም ደግሞ በመንግስት እና በህዝብ ላይ የደረሰው ጉዳት በጣም ከባድ ከሆነ አፈጸፀሙ ከፍ ስለሚል ወንጀሉ ቅጣት እስከ 15 ዓመት ሊደርስ ይችላል። ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ስልጣናቸውን ተጠቅመው ጥፋቱን ሲፈጽሙት በሁለት መንገድ ነው። አንደኛ ለራሳቸው ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት። ሁለተኛ ደግሞ ሌሎች ሰዎች እንዲወስዱ ሊያመቻቹ እንደሚችሉ የህግ ባለሙያው ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 05/2013