ሰላማዊት ውቤ
በ2012/13 ምርት ዘመን ለሰብል ልማት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ ቆይታል። ሆኖም ሥራው በሚጠበቀው ልክ ተሳክቷል ለማለት አይቻልም። ሰው ሰራሽና ወቅታዊ የዓለም ሁኔታዎች እቅዱን የተፈታተኑት ምክንያቶች ነበሩ። ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል በዋነኛነት የሚጠቀሰው የአንበጣ መንጋ ፣ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና እንዲሁም የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ መደፍረስና መፈናቀል የምርት ዘመኑን ተገዳድረውታል። መንግስት በእነዚህ ችግሮች ሰበብ የዘመኑ ምርት እንዳይቀንስ ዜጎች ለምግብ እጥረትና ለረሀብ አደጋ እንዳይጋለጡ የተለያዩ ስልቶችን ቀይሶ ተንቀሳቅሷል። ከስልቶቹ አንዱ እንደ ፊቱ ከተማና ገጠር ሳይል ማንኛውም ያልታረሰ መሬት እንዲታረስ ያስቀመጠው አቅጣጫ ነበር። በዚህ አቅጣጫ የሀገሪቱን ዋና መዲና አዲስ አበባን ጨምሮ በሀገሪቱ የሚገኙ ክልል ከተሞች ያልታረሰ ማሣ በሙሉ ለእርሻ አገልግሎት ውሏል። እንደ ሀገር ከምርት ዘመኑ ልምድ ተወስዶ ኬሚካልና የእርጭት መሣሪያዎችን በመግዛትና በእርዳታ በማግኘት አንበጣን መከላከል የሚያስችል አቅም መሰነቅም ተችሏል። በትግራይና የፀጥታ ችግር በነበረባቸው አካባቢዎች ግጭቱ ቀዝቀዝ እያለ ሲመጣ አርሶ አደሩ የደረሰ ሰብሉን እንዲሰበስብ ያላሰለሰ ቅስቀሳ ከማድረግ ጀምሮ አንበጣን የመከላከልም ሥራ ተሰርቷል።
መንግስት አርሶ አደሩ ለዚሁ ዘመን ለዚሁ ምርት ግብዓት ያውለው ዘንድም ለማዳበሪያና ለሌሎች ግብዓቶች መግዣም 26 ቢሊዮን የሀገር ውስጥ ብድርና የውጪ ምንዛሪ መድቧል። አሁን ላይ የ2012/13 ምርት ከሞላ ጎደል ተሰብስቧል። በዚሁ ዙሪያ በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ከሆኑት አቶ ኢሳያስ ለማን ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፦በ2012/13 ምርት ዘመን በሰብል ለማልማትና በዘር በተለይም በዋና ዋና ሰብሎች ለመሸፈን ከታቀደው ምን ያህሉን ለማሳካት ተችሏል ?
አቶ ኢሳያስ፦ ዋና ዋና ሰብሎች የሚባሉት ከመሬት አንፃር አንደኛ ጤፍ፣ በቆሎ፣ስንዴ፣ገብስ፣ማሽላ ናቸው። ከምርት አኳያ ደግሞ በቆሎ አንደኛ፣ ጤፍ ሁለተኛ፣ ማሽላ ሦስተኛ፣ ከዚያ ስንዴ ገብስ እያለ ይቀጥላል። ከክልል ክልል ቢለያይም ከጥራጥሬ ቦሎቄን ጨምሮ እነዚህንና ሌሎች ሰብሎችን እንደ ሀገር ለማልማት ታቅዶ ነው ወደ ሥራ የተገባው። በሁሉም ክልል ታቅዶ የነበረው 13 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልማት ነው። ሆኖም ክንውኑ ከዕቅዱ በላይ 14 ሚሊዮን ሄክታር ነው። ልዩነቱ ወደ 171,000 ሄክታር በላይ ይደርሳል።
አዲስ ዘመን፦ክንውኑ ከፍ ሊል የቻለው ምን ተሰርቶ ነው?
አቶ ኢሳያስ፦እንደ ሀገር ኮቪድ-19፣ የአንበጣ መንጋና በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች ሊያስከትሉ የሚችሉትን ጨምሮ በዓለም ደረጃ የምግብ እጥረት ክፍተት ሊኖር እንደሚችል የሚጠቁሙ ስጋቶችን ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎች በመሠራታቸው ነው። የተቀመጠውን አቅጣጫ ተከትሎ በኮቪድ ምክንያት አርሶ አደሩ ባለበት አካባቢ በቂ ድጋፍ እንኳን ባይደረግ ግብዓቶች በወቅቱ እንዲቀርቡ ሆኗል። ዘርና ማዳበሪያ በወቅቱ ተሰራጭቷል። በ2012/13 ምርት ዘመን ለአርሶ አደሩ 14 ሚሊዮን 585 ሺ ኩንታል ኬሚካል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ግዢ ተፈፅሟል። 99ነጥብ 9 በመቶው ወደ ሀገር ውስጥ ማጓጓዝም ተችሏል። ከዚህ ግብዓት ውስጥ 1ነጥብ 45 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶኑ ወይም 14 ነጥብ 5 ኩንታሉ ለተጠቃሚ አርሶ አደር ተሰራጭቷል። ይሄ በመጠንም ሆነ በዓይነት ከሌሎች ምርት ዘመኖች ጋር ሲነፃፀር እጅግ ከፍተኛ ነው። እንዲሁም በዚሁ ምርት ዘመን 812ሺ 680 ነጥብ 2 ኩንታል የተለያዩ ምርጥ ዘር ግብዓቶች ቀርቧል። ከዚህ መካከል በቀጥታ ለአርሶ አደሩ የተሰራጨው 745 ሺ 80 ኩንታል ነው። ግብዓቶቹን ለማቅረብ መንግስት 26 ቢሊዮን ብር የሀገር ውስጥ ብድርና የውጪ ምንዛሪ መድቧል። በአጠቃላይ ይሄ ድጋፍ ፈጣንና በወቅቱ ባለው የትራንስፖርት አማራጭ መቅረብ ችሏል። ስልጠናዎች ተሰጥተዋል። በቂ ዝግጅትም ተደርጓል። ቢሆንም የድጋፍና ክትትል ሥራው ከኮቪድ ጋር ተያይዞ የተጠናከረ አልነበረም።
አዲስ ዘመን፦ ኮቪድና የአንበጣ መንጋ ድንገት መከሰት ያሳደረው ተፅዕኖ ፣ ይሄን ተፅዕኖ ለመቀልበስና ለመቋቋም የተደረጉ ጥረቶች ምን ይመስላል ?
አቶ ኢሳያስ ፦ ኮቪድ- 19 በምርት ዘመኑ ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ለመቋቋም መንግስት እንደሌሎቹ ዘርፎች ሁሉ በግብርናውም መስክ ማንኛውም ተጨማሪ መሬት የሚለማበት ራሱን የቻለ አቅጣጫ አስቀምጦ ነበር። ኮቪድ-19 ሁሉም የዓለም አካባቢዎች ተፅዕኖ ቢያሳድርም እንደኛ ሀገር ተጨማሪ መሬት በመልማቱ ጉዳቱንና ተፅዕኖውን መቀነስ ተችሏል። አቅጣጫውን ተከትለው እንዲያለሙ ‹የኮቪድ ዕቅድ› ተብሎና ስትራቴጂ ተነድፎ ለክልሎች ደርሷል። ይሄም ጉዳቱን ለመቀነስ ያስቻለ ነው። በምርት ዘመኑ በግብርና ሚኒስቴር እንደ ሀገር የተቀመጠውን አቅጣጫ መሰረት በማድረግ ስትራቴጂ ተነድፎ እንቅስቃሴ ተደርጓል። ስትራቴጂው ማንኛውም ክፍት የነበረ መሬት ወደ ግብርና እርሻ ሥራ እንዲገባ የተደረገበት ነው። ወደ እርሻ ከገቡት ውስጥ በትምህርት ቤቶችና በሌሎች አካላት የተያዙ እንዲሁም ሳይታረሱ የቆዩ መሬቶች ይገኛሉ። ለአብነት በመኸር በመስኖ እንቅስቃሴም በሰብል እንዲሸፈኑ የተደረገበትን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ማየት ይቻላል። የነዚህ ከተሞች ተጨማሪ መሬት መጠን እንደ ሀገር ዜሮ ነጥብ 28 ሚሊዮን ሄክታር ነው። በዚህም ተጨማሪ የሰብል ምርት ተገኝቶና ጥሩ ውጤት ታይቷል። የተገኘው የሰብል ምርት ይሄን ያህል ነው ማለት ባይቻልም የተሄደበት ሁኔታ እጅግ አበረታች ነበር። ኮቪድ 19 እና አንበጣ የመጡበት ወቅት ተመሳሳይ በመሆኑ በምርት ዘመኑ ላይ ያሳደሩት ተፅዕኖም ተመጋጋቢ ነበር ማለት ይቻላል።
አንበጣ በአፋር፣ በሶማሌ፣ በአማራ ክልል፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች አካባቢ በምርት ዘመኑ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። በእነዚህ ምክንያት 45 በመቶ ምርት እንዲቀንስ አድርጓል። ሰብል ምርት ላይ፣ በመኖ ዕፅዋት በተለይ ወደ አፋር አካባቢ ሲኬድ በግጦሽ መሬት ላይ የተከሰተበት ነበር። በሶማሌና በአማራ ክልል ቆላማ አካባቢ ከፍተኛ ተፅዕኖ አድርጓል። ሆኖም ጉዳቱ ከወረዳ ወረዳ ከአካባቢ አካባቢ ይለያያል። በተለይ በአማራና በአፋር ክልል በተወሰኑ ሰብሎች ላይ ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው። ሆኖም የጉዳቱ ሽፋን ከሀገራችን ሰፊ የቆዳ ስፋት አንፃር ሲታይ ከፍተኛ ነው የሚባል አይደለም። ጉዳቱ ሊደርስ የቻለበት ምክንያት ከኮቪድ ጋር ተያይዞ የመረጃ ልውውጡ ላይ ክፍተት በመኖሩ ነው። በነገራችን ላይ አንበጣ ከውጪ ከየመን አካባቢ በነፋስ ኃይል ነው የሚመጣው። እዛ ይፈለፈልና ራሱን የማኖር ሥራ ይሰራል። የሚበላው ምግብ ካጣ በኤርትሪያ በአፋር በኩል ያደርግና በነፋስ ኃይል ወደ ኢትዮጵያ ይገባል። በኤርትራ በኩል አድርጎ በትግራይም በሶማሌም በኩል የሚገባበትም ሁኔታ አለ። አልፎ አልፎ ደቡብ አካባቢ የታይበት ሁኔታ ነበር። እንቁላል ከጣለ በኋላ እንቁላሉ መሬት ውስጥ ይቆያል፤ ይፈለፈላል። እንቁላሉ የሚጣለው ዝናብ የሚዘንብበትን ሁኔታ ታሳቢ አድርጎ ነው። በዚህ ወቅትም የሚበላው ማግኘት አለበት። አንበጣ ይሄን የዝናብ ወቅት የመተንበይ ተፈጥሯዊ ባህርይ አለው። አፈር ውስጥ ይቆይና ይፈለፈላል። እዚህ አካባቢ ያለውን የመመገብና የማውደም ሥራ ይሰራል።
በዚህ ሂደት ጉዳይ መረጃ ያቀብል የነበረው የዓለም ምግብ ድርጅት ነው። ድርጅቱ አንበጣን በሚመለከት ሀገራችንን ጨምሮ ምስራቅ አፍሪካን የሚያካትት መረጃ ይሰጣል። ነገር ግን ይሄን የሚከታተለው አካል በኮቪድ-19 ምክንያት ወደ ቤቱ እንዲገባ በመደረጉ የመንና አጎራባች ሀገሮች ላይ ያለውን ሁኔታ በየወቅቱ እየተነተኑ መረጃ ለመለዋወጥ አላስቻለም። ይሄ ክፍተት በመኖሩ ሀገራችንም ሰብሉ ለመመገብ በደረሰበት ሁኔታ ነው የነቃችው። ይሄም ሆኖ ተፅዕኖውን ለመከላከል ከዚህ በፊት ባልነበረ ሁኔታ ለእርጭት የሚያገለግሉ አውሮፕላኖች ገብተዋል። በመኪና ላይ ተገጥመው ለመርጫ የሚያገለግሉ መርጫ መሣሪያዎች እና ኬሚካል ወደ ሀገር ውስጥ ማስመጣት ተችሏል። እስራኤል በግዢ ከላከችው ውጪ ሦስት አውሮፕላን ተገዝቷል። እስራኤል በእርዳታ 20 ተጨማሪ ድሮል ሰጥታለች። የዓለም ምግብ ድርጅትም ኬሚካል መርጨት የሚያስችሉ ፒካፕ መኪናዎችን እያንዳንዱ ክልል ሦስት ፒካፖች ተከፋፍሎ ርጭት ሲካሄድ ቆይቷል። ፌዴራልም ላይ በእርጭቱ የተሳተፉ መኪኖች አሉ። በመከላከል ግብዓት በቂ ነው ባይባልም ጥሩ ስርዓት ዘርግቶ ለማስተማር አስችሏል ።
የክልልና የወረዳ የግብርና ባለሙያዎች ተቀናጅተው መሥራት ችለዋል። ከፌዴራልም ባለሙያዎች ወደ እያንዳንዱ ክልል ተመድበው ሲሰሩ ቆይተዋል። የጉዳቱን መጠን የሚገመግም ባለሙያም ተመድቦ እንዲሰራ ተደርጓል። ከአደጋ ስጋትና መከላከል ጋር ተያይዞ ላለው ጉዳት መጠን ምላሽ መስጠት ተችሏል። በዚሁ ላይም የጋራ ጥናት ተደርጓል። የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ምን ያህል ናቸው? ከመቼ እስከ መቼ ነው? የመኖ እጥረት ያለባቸው ከመቼ እስከመቼ ይቀርብላቸዋል? የሚለውም ትኩረት ተሰጥቶት ተሰርቷል። በአጠቃላይ አንበጣን ለመከላከል እንደ ግብርናው ዘርፍ አቅም ተፈጥሯል።
አዲስ ዘመን፡- የምርት አሰባሰቡ እና ግኝቱ ምን ይመስላል? በተለይ በትግራይ ክልል የተዘራውና አሰባሰቡ እንዴት ነበር ?
አቶ ኢሳያስ፦ለማምረት የታሰበው 417 ነጥብ 72 ሚሊዮን ኩንታል ነበር። በአሁኑ ወቅት ከ90 በመቶ በላይ ምርት መሰብሰብ ተችሏል። ከተሰበሰበው ምርት ውስጥ 4 ነጥብ 5 በመቶ የሚደርሰው በኮምባይነር ነው የተሰበሰበው ። ቀሪው ደግሞ በሰው ኃይል ነው የተሰበሰበው። በትግራይ ክልል የተዘራ ማሣ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ነው። በአጠቃላይ እርጥበት በሚይዙ ደጋማ አካባቢዎች ግጭት በነበረባቸው ወደ ትግራይና መተከል አካባቢ ያልተሰበሰበና ያልተወቃ ሰብል አለ። ከነዚህ በስተቀር በአብዛኛው ምርት ተሰብስቦ ወደ ጎተራ ገብቷል። ግማሹም በክምር ደረጃ ነው ያለው። በተለይ ትግራይ ክልል ላይ ግጭት የተፈጠረው ምርት በሚሰበሰብበት ወቅት ነበር።
በዚህ ምክንያት እስከ አሁን ድረስ አርሶ አደሩ ወጥቶ የተመረተውን ምርቱን ሊሰበስብ አልቻለም። በቅርቡ ወደ ትግራይ ተዘልቆ በተደረገው የመስክ ምልከታ ምርት ስብሰባ አለመካሄዱ ታይቷል። አርሶ አደሩ በወቅቱ ምርት ካልሰበሰበ ወደ አስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ሊገባ ይችላል የሚል ግምትም አለ። መረጃው ተጠቃሎ ባይደርስም አርሶ አደሩና የአካባቢው ሕብረተሰብ ወደ አስቸኳይ ጊዜ እርዳታ እየገባ እንደሆነም ፍንጭ አለ። አካባቢው ተጨማሪም ምርት ይፈልጋል። በእርግጥ ትግራይ ላይ በአንበጣ የተጎዱ አካባቢዎች አብዛኛዎቹ ከፍተኛ የሰብል አምራች አይደሉም። ሆኖም የግብርና ሚኒስቴር ባለሙያዎች ወደ ትግራይ ባቀኑበት የመጀመሪያ ዙር የመስክ ምልከታ እነዚህ አካባቢዎችም ተጨማሪ የምግብ ሰብል እንደሚያስፈልግም ታይቷል። አስቀድሞ የሰው ህይወት መዳን ስላለበት የምግብ እጥረት ያለባቸው ወደ አስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ እንዲገቡ የተደረገበትም አለ። ሰላም የሰፈነበት የክልሉ አካባቢ የምርት ስብሰባው እንዲካሄድ ተሰርቷል። ሆኖም የምርት ግምገማ ለማካሄድ አሁንም በክልሉ ውስንነት ያለባቸው አካባቢዎች አሉ። ይሄን የቤት ሥራ አሁን ላይ ክልሉ ሰርቶ በቀጣይ ከፌዴራል ጋር በጋራ ለመሥራት ታቅዶም እየተሄደበት ይገኛል።
አዲስ ዘመን የካቲተር 04/2013