ዳንኤል ዘነበ
የደም ማነስ በደምዎ ውስጥ በቂ የሆነ ጤናማ ቀይ የደም ሴሎች ወይም ሄምግሎቢን ሲያንስ የሚከሰት በሽታ ነው። ሄሞግሎቢን ዋናው የደም ሴሎቻችን ክፍል ሲሆን ከኦክስጅን ጋር ይጣመራል። በጣም ጥቂት ወይም ጤናማ ያልሆኑ ቀይ የደም ሴሎች ካሉን ወይም ጤናማ ያልሆነ ጥቂት ሄሞግሎቢን ካለን በሰውነታችን ውስጥ ያሉት ሴሎች በቂ ኦክስጅን አይደርሳቸውም።
የደም ማነስ ምልክቶች
የደም ማነስ ምልክቶች ከሆኑት አንዱ የሆነው የድካም ስሜት የሚከሰተው የሰውነት አካሎቻችን በትክክል ለመስራት የሚፈልጉትን ያህል ኦክስጅን ስለማያገኙ ነው። ሴቶች፣ ህፃናት እና ከባድ በሽታ ያለባቸው ሰዎች ለደም ማነስ የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።
ስለ ደም ማነስ ልናስታውሳቸው የሚገቡ ጠቃሚ ነገሮች እነሆ፦
* አንዳንድ የደም ማነስ አይነቶች በዘር የሚተላለፉና በወሊድ ጊዜ ህፃናትን የሚያጠቁ ናቸው።
* ለአቅመ ሄዋን የደረሱ ሴቶች በብረት (አይረን) እጥረት ለሚከሰተው የደም ማነስ በተለየ ሁኔታ የተጋለጡ ናቸው። ምክንያቱም በወር አበባ ጊዜ የደም መፍሰስ እና በእርግዝና ወቅት የደም ፍላጎት ስለሚጨምር ነው።
* በእድሜ የገፉ ሰዎች በደም ማነስ የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው ምክንያቱም በምግብ እጥረት እና የተለያዩ የህክምና ችግሮች ስለሚኖሩባቸው ነው።
የደም ማነስ አይነቶች
የተለያዩ የደም ማነስ አይነቶች አሉ፤ ሁሉም የተለያዩ መነሻ እና የተለያየ ህክምና አላቸው። በብረት እጥረት የሚከሰተው የደም ማነስ በጣም የተለመደ በሽታ ነው። አመጋገባችንን በመቀየር እና የብረት ንጥረ ነገር በመውሰድ በቀላሉ መታከም እንችላለን። አንዳንድ የደም ማነስ አይነቶች ለምሳሌ:- በእርግዝና ወቅት የሚከሰተው ጤናማ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ እስከ እድሜ ልክ የሚዘልቁ ናቸው።
የደም ማነስ መነሻ ምክንያቶች
ከ400 የሚበልጡ የደም ማነስ አይነቶች አሉ እነሱም በሶስት መደቦች ይከፈላሉ፦
1. በደም መፍሰስ የሚከሰት፣
2. ቀይ የደም ሴሎች ምርት መቀነስ ወይም
የማምረት ችግር፣
3. በቀይ የደም ሴሎች ውድመት/ጥፋት የሚከሰት የደም ማነስ አይነቶች ናቸው።
በደም መፍሰስ የሚከሰት የደም ማነስ፡-
ደም በሚፈሰን ጊዜ ብዙ ቀይ የደም ሴሎችን እናጣለን፤ ይህም የሚከሰተው በትንሹ ለረጅም ሰዓት ደም ስለሚፈሰን ሲሆን ይህን ነገር ብዙ አናስተውለውም። እንደዚህ አይነቱ ከባድ የደም መፍሰስ በሚከተሉት መንገዶች ይከሰታል።
* ከጨጓራና አንጀት ጋር የተያያዙ በሽታዎች /ኪንታሮት፣ ቁስለት፣ የጨጓራ ህመም እና ካንሰር/
* የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶች /አስፕሪን ወይም አይቡፕሮፊን/
* የወር አበባ እና በወሊድ ጊዜ /በተለይ በወር አበባ ጊዜ የደም ፍሰት ከመጠን በላይ ከሆነ እና በተደጋጋሚ እርግዝና ከተከሰተ/
ቀይ የደም ሴሎች ምርት በመቀነስ የሚከሰት የደም ማነስ፡-
ይህ አይነት የደም ማነስ በሽታ በሚከሰትበት ጊዜ ሰውነታችን በጣም ጥቂት የደም ሴሎች ማምረት ወይም የደም ሴሎቻችን በትክክል ተግባራቸውን መወጣት ሲያቅታቸው ሲሆን በሁለቱም አጋጣሚዎች የደም ማነስ ይከሰታል። ቀይ የደም ሴሎች ችግር ይኖርባቸዋል ወይም በቁጥር ይቀንሳሉ የዚህ ምክንያት ጤናማ ያልሆኑ የደም ሴሎች ሲኖሩ ወይም ተግባራቸውን በብቃት ለመወጣት የሚያገለግሉ ሚኔራሎችና ቫይታሚኖች እጥረት ሲኖር ነው።
ለዚህ አይነቱ የደም ማነስ መነሻ ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፦
* ሲክል ሴል የደም ማነስ /አኒሚያ/፣
* በብረት እጥረት የሚመጣ የደም ማነስ፣
* በቫይታሚን እጥረት፣
* በመቅኒ እና አባት/መነሻ ሴል ችግር፣
* ሌላ የጤና ችግሮች ናቸው።
በሲክል ሴል የሚከሰት የደም ማነስ በዘር የሚተላለፍ ሲሆን ቀይ የደም ሴሎች የጨረቃ ቅርጽ እንዲኖራቸው ያደርጋል። ስለዚህ በቂ ኦክስጂን ወደ ተለያዩ አካሎች ማድረስ ያቅተዋል። የጨረቃ ቅርጽ ያላቸው የደም ሴሎች በጥቃቅን የደም ቧንቧዎች ውስጥ ይቀረቀራሉ፤ ይህም ህመም ያስከትላል።
በብረት እጥረት ምክንያት የሚከሰተው የደም ማነስ ብረት የተባለው ሚኔራል እጥረት ሲኖር ነው። በአጥንታችን ውስጥ ያለው መቅኒ ኦክስጂን ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍል የሚደርሰውን ሄሞግሎቢን ለመስራት ብረት ያስፈልገዋል። በቂ የሆነ የብረት ሜኔራል ከሌለ በቂ የሆነ ሄሞግሎቢን አይመረትም፤ የዚህ ውጤት በብረት እጥረት የሚከሰት የደም ማነስ ነው።
የዚህ አይነቱ የደም ማነስ መነሻ ምክንያቶች
የሚከተሉት ናቸው፦
• የብረት እጥረት ያለባቸው ምግቦችን
የመመገብ አባዜ፣
• እርግዝና እና ማጥባት የእናትን የብረት
ክምችት መጠን ይቀንሳል፤
• የወር አበባ፣
• በተደጋጋሚ የደም ልገሳ ማድረግ፣
•ከባድ ስፖርታዊ ልምምዶች፣
•የምግብ መፈጨት ችግሮች፣
•አንዳንድ መድሃኒቶች፣
•በቫይታሚን እጥረት፡- የደም ማነስ የሚከሰተው በቫይታሚን ቢ 12 እና ፎሌት እጥረት ነው። እነዚህ ሁለት ቫይታሚኖች ቀይ የደም ሴሎችን ለመስራት ያገለግላሉ።
ለዚህ ችግር መነሻ ምክንያቶች:-
•ሜጋሎብላስቲክ አኒሚያ፡ የቫይታሚን ቢ12 እና ፎሌት እጥረት፣
•ፐረንሸስ አኒሚያ፡ የቫይታሚን ቢ12 በጨጓራ የመጠጥ ችግር ነው፣
•የምግብ እጥረት፡ ትንሽ ስጋ ወይም ሙሉ ለሙሉ ስጋ አለመመገብ፣
•እርግዝና፣ አንዳንድ መድሃኒቶች፣ የአልኮል ሱሶች፣ የአንጀት በሽታዎች
በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰት የደም ማነስ መነሻቸው ለቀይ የደም ሴሎች ምርት የሚጠቅሙ ሆርሞኖች እጥረት ሲሆን በዚህ አይነት ምክንያት የሚከሰቱት የሚከተሉት ናቸው::
•ከባድ የኩላሊት በሽታ
•የተለያዩ በሽታዎች /ስኳር፣ ካንሰር፣
ሪህ፣ ኢንፌክሽን/
በቀይ የደም ሴሎች ውድመት/ጥፋት የሚከሰት የደም ማነስ:-
ቀይ የደም ሴሎች በሚሰባበሩበት ጊዜ እና የደም ዝውውር ውጥረት መቋቋም ሲያቅታቸው ያለ እድሜያቸው ይፈነዳሉ። ከዚያም ሄሞላይቲክ አኒሚያ ይከሰታል። ይህ ችግር ስንወለድ ወይም ካደግን በኋላ ሊከሰት ይችላል፤ አንዳንድ ጊዜ መነሻ ምክንያቱ አይታወቅም።
ምንጭ፦ የዶክተር አለአዲስ ዘመን የካቲተር 04/2013