አስመረት ብስራት
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሃያ ሁለተኛ ጊዜ የሚከበረውን የስጋ ደዌ ቀንን አስመልክቶ በአለርት ሆስፒታል ውስጥ ስጋ ደዌን የተመለከቱ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ የፓናል ውይይት ተደርጎ ነበር። በዚሁ መርሀ ግብር ላይ ያገኘናቸው የስጋ ደዌና የአባለዘር በሽታ እስፔሻሊስት ዶክተር ሽመልስ ንጉሴ ስለስጋ ደዌ በሽታ ህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ ኖሮት ራሱን መጠበቅ የሚገባው መሆኑን ይናገራሉ። የሰጡንን መረጃ በዚህ መልኩ አሰናድተነዋል። መልካም ንባብ።
የስጋ ደዌ ማይኮባክቴሪየም ሊፕሬ (mycobacterium lepra) በሚባል የባክቴሪያ ተህዋስ የሚመጣ ተላላፊ በሽታ ነው። በሽታው በዋናነት ቆዳን፣ ከአንጎል እና ከህብለ ሰረሰር ውጭ ያሉ ነርቮችን (peripheral nerve)፣ የላይኛው የመተንፈሻ አካል ሽፋኖችን (mucous membrane of upper respiratory tract) እና አይንን ያጠቃል።
የስጋ ደዌ በሽታ በሁሉም የእድሜ ክልል ያሉ ሰዎችን ያጠቃል። ይህ በሽታ መታከምና ሙሉ በሙሉ መዳን የሚችል ሲሆን ህመሙን በቶሎ መታከም አካል ጉዳተኛ ከመሆን ይከላከላል። የስጋ ደዌ ከአፍና አፍንጫ በሚወጡ ጠብታዎች እና ብናኞች ሲሆን በዚህም ምክንያት በበሽታው ከተጠቃና ህክምና ካላገኘ ሰው ጋር በሚደረግ ረዘም ያለ ንክኪ ይተላለፋል። ህመሙ ለአጭር ጊዜ በሚደረግ መጨባበጥ መተቃቀፍና አብሮ መኪና ውስጥ በመቀመጥ የመተላለፍ እድሉ አናሳ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሊረዳው የሚገባው የስጋ ደዌ በሽታ በዘር የማይተላለፍ መሆኑን ነው።
የበሽታው ምልክቶች
የዚህ በሽታ ምልክቶች በአብዛኛው አጠራጣሪ አይደለም። ከአካባቢው ቆዳ ነጣ ነጣ ያሉ እና ሲነኩ ምንም ስሜት የሌላቸው የቆዳ ምልክቶች፤ ህመም የሌለው የቆዳ እብጠት፤ ወፍራም እና ደረቅ የሰውነት ቆዳ፤ ህመም የሌለው የውስጥ እግር ቁስል፤ ህመም የሌላቸው የፊትና የጆሮ እብጠቶች፤ የአይን ጭራ እና የአይን ቆብ ፀጉር ማጣት፤ የእጅና የእግር ጡንቻ መድከም፤ የእጅና የእግር ነርቮች ማበጥ፤ የአፍንጫ መድማት እና በአፍንጫ ለመተንፈስ መቸገር ናቸው።
በዚህ ደረጃ ላይ ካልታከመ ደግሞ የእጅና እግር ሽባ መሆን፣ የአካል መጉደል፣ የእጅና የእግር ጣቶች ማጠር፣ በራሱ የማይድን የእግር ቁስል፣ አይነ ስውርነት፣ የአፍንጫ ቅርፅ መለወጥ፣ ህመም ያላቸው ነርቮች የሰውነት ቆዳ ማቃጠል ያስከትላል።
የሥጋ ደዌ በሽታ መኖር እንዴት ሊረጋገጥ ይችላል?
ብዙ ጊዜ የተጠቃው ቆዳ እና ነርቭ ሀኪም በማየት ሊያውቀው ይችላል። ነገር ግን ለማረጋገጥ ከተጠቃው ቆዳ እና ነርቭ ናሙና በመውሰድ ባክቴሪያውን በአጉሊ መነፅር (microscope ) ማየት ይቻላል። በቆዳ ላይ ነጣ ነጣ ወይም ቀላ ብለው የሚታዩ ምልክቶች በጥጥ ሲነኩ ስሜት አልባ ከሆኑ ወይም ስሜት ከሌላቸው፤ በዳሰሳ ምርመራ የነርቭ እብጠት መኖር ያለምንም ጥርጥር ሲረጋገጥ በላቦራቶሪ ምርመራ የበሽታው አምጪ ጀርም መኖር ከተረጋገጠ የበሽታው ተጠቂዎች ሰው የሚከተሉትን እርምጃዎች መውሰድ ይኖርበታል።በቆዳ ላይ ነጣ ነጣ ወይም ቀላ ቀላ ያሉ ምልክቶች ሲታዩ በሽታው የሥጋ ደዌ ሊሆን ስለሚችል በፍጥነት ወደ ጤና ድርጅት ሄዶ ምርመራ በማድረግና በባለሙያ የሚታዘዘውን ህክምና ያለማቋረጥ በመውሰድ በሽታው እንዳለበት ከተረጋገጠ የጤና ባለሙያ በሚያዘው መሰረት መድኃኒቱን ሳያቋርጥ ሙሉ በሙሉ ወስዶ መጨረስ ከበሽታው ሙሉ በሙሉ እንዲድን ያደርገዋል።
ህክምና
የስጋ ደዌ በምርመራ ከተረጋገጠ በኋላ ከ2 እስከ 3 የሚደርሱ የተለያዩ ፀረ ተህዋስያን (multi drug) በመጠቀም ይታከማል። ይህም ባክቴሪያው መድሀኒቱን እንዳይላመድ ይረዳል። መድሀኒቶቹም Rifampicin፣ Clofazamine፣ Dapsone ናቸው። ህክምናው ከ6 ወር እስከ 2 ዓመት ሊፈጅ ይችላል። መድሃኒቱን በትክክል ከተወሰደ ሙሉ በሙሉ ይድናል። ለበሽታው የመጀመሪያውን መድሃኒት ከወሰደ ጀምሮ የማይተላለፍ ሲሆን ህክምናው የሚሰጠው በነፃ ነው።
የሥጋ ደዌ በሽታ ማንን ያጠቃል?
የሥጋ ደዌ በሽታ በሁሉም የኑሮ ደረጃና በየትኛውም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ወንዶችና ሴቶችን እኩል ያጠቃል። ይሁን እንጂ በአብዛኛው በይበልጥ የሚጠቁት በ15 እና በ45 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ወይም በአምራች የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው። የተመጣጠነ ምግብ ዕጦትና ለጤና ተስማሚ ባልሆነ ቤት ውስጥ ተፋፍጐ መኖር ለሥጋ ደዌ በሽታ የሚያጋልጡ ሁኔታዎች ናቸው።በአብዛኛው ህብረተሰብ ያለው የአኗኗር ሁኔታ ለስጋ ደዌ በሽታ ተገላጭነት የሚጨምር በመሆኑ ህመም የተገኘበት ሰው ጋር የሚኖሩ የቤተሰቡ አባላት በሙሉ ምርመራ ማድረግ ይገ ባቸዋል።
የሥጋ ደዌ በሽታ እንዴት ይተላለፋል?
አንድ ሰው በሥጋ ደዌ በሽታ ሊጠቃ የሚች ለው ሕክምና ካልጀመረ የበሽታው ተጠቂ ከሆነ ሰው ጋር ለረጅም ጊዜ አብሮ በመኖር የቅርብ ግንኙነት ሲኖረው ነው የሚተላለፈው።የሥጋ ደዌ ሕመምተኛ ሕክምና ከጀመረ ወይም ታክሞ ከዳነ በሽታውን በፍፁም ሊያስተላልፍ አይችልም።የሥጋ ደዌ በሽታ በዘር፣ በእርግማን ወይም በእርኩስ መን ፈስ የሚመጣ በሽታ አይደለም።የስጋ ደዌ በሽታ ሙሉ በሙሉ በህክምና የሚድን መሆኑን በመረዳት ህብረተሰቡ በቅድሚያ የህክምና ምርመራዎችን ማድረግ ይኖርበታል። አገልግ ሎቱም በሁሉም የመንግስት የጤና ድርጀቶች በነፃ የሚሰጥ ነው፡፡
መከላከያ
በስጋ ደዌ በሽታ ተጠርጣሪ ህመምተኞችን በሙሉ ወደ ህክምና በመውሰድ አስፈላጊውን የህክምና ክትትል እንዲያደርጉ ማስቻል አንዱ የመከላከያ መንገድ ነው። አድሎና መገለል ካለ የበሽታው ምልክቶች ያለባቸው በጊዜው እንዳይታከሙ ወይም ራሳቸውን እንዲደብቁ ያደርጋቸዋል፤ ስለሆነም በበሽታው የተጠቁ ሰዎችን ከማግለል መቆጠብ ተገቢ ነው። ሌላው የተፋፈገ አኗኗርን በተቻለ መጠን መቀነስም በሽታውን ይከላከላል።
አዲስ ዘመን የካቲተር 04/2013