ዋቅሹም ፍቃዱ
የአገራችን የፌዴራል ሥርዓት በአንድም ይሁን በሌላ ለብዙ ትችት የተዳረገ ነው ። በአንዳንዶች ዘንድ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ያደበዘዘ፣ አንድነትና አብሮነትን በእጅጉ ያቀጨጨ፣ከፋፋይ እና ለጽንፈኛ ብሔርተኞች ማቆጥቆጥ ጉልህ ድርሻ የተጫወተ አልፎ ተርፎም በየቦታው እየተስተዋለ ላለው ሞትና መፈናቀል መንስኤ እንደሆነም ይደመጣል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ህገመንግስቱ የተቀበረው ማንነት፣ የተደፈጠጠው ቋንቋ፣ ባህልና እሴቶች ከመቃብር ያወጣ ስለመሆኑም የሚከራከሩ ወገኖች አሉ ።ዛሬ የተፈጥሮ ማንነታቸው፣ባህልና ቋንቋቸውን ይዘው በትልቋ ኢትዮጵያ ውስጥ ራሳቸውን ሲያዩ ኢትዮጵያ ድርሻቸውና መገለጫቸው እንደሆነች በደንብ እንደሚረዱ የሚከራከሩ ወገኖችም አሉ።
የዛሬው እንግዳችን በ1950 ዎቹ በሚጀምረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ በጉልሕ ከሚነሱ የሀገሪቱ ፖለቲከኞች አንዱ የሆኑት አቶ ሌንጮ ለታ ናቸው ። ስለ ፌዴራሊዝም ፤ አሁን በሀገሪቱ ስራ ላይ ስላለው የብሔር ፌዴራሊዝም እና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ አነጋግረናቸው እንደሚከተለው አቅርበነዋል ፡፡
አዲስ ዘመን ፡ ፌዴራሊዝም በዓለም ተሞክሮ በአገራት ሁለንተናዊ ልማትና ዕድገት ያመጣው ለውጥ እንዴት ይገለጻል? ወደ ፌዴራል ስርዓት እየተቀላቀሉ ያሉ የዓለም አገራት እየጨመረ ነው ወይስ እየቀነሰ? ለምን ይመስልዎታል?
አቶ ሌንጮ፡ ፌዴራሊዝም በባህሪው በመተማመንና በመነጋገር ላይ የተመሰረተ የአስተዳደር ስርዓት በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ያለውን እውቀት፣ሀብት፣ልምድና ተሞክሮ በማዋጣት መብትና ግዴታውን በማክበር ለአገር ከልቡ እንዲሰራ ዕድል ይሰጣል። ያለ ህዝብ ተሳትፎ በተወሰኑ ሰዎች ፈላጭ ቆራጭነት የሚሰራ ልማት በህዝቡ ዘንድ የባለቤትነት ስሜት ስለማይኖረው የአገልግሎት ዕድሜ ላይኖር ይችላል።በህዝቡ በጎ ፍቃድ የሚሰራው የትኛውም የአገር ልማት ዋስትናው ህዝቡ ራሱ ስለሆነ የአገልግሎት ዘመኑም ረጅም በመሆኑ አገርን ከኪሳራ ያድናል።በአጭሩ በዴሞክራሲ ስርዓት ዉስጥ “የኔ ብቻ” የሚለው ሀሳብ ቦታ ስለሌለው የጋራ ሀብት በጋራ መጠቀም ለአገር ልማትና ዕድገት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በፌዴራል ስርዓት የሚተዳደሩ የዓለም አገራት ቁጥር እየጨመረ ነው።ይህ ደግሞ በአደጉ አገራት ብቻ ሳይሆን በአፍሪካን ጭምር እየታየ ነው።
አዲስ ዘመን፡ በአገራችን በተለይ ከብሔር ፌዴራሊዝም የአስተዳደር ስርዓት ጋር ተያይዘው ከፋፋይ፣የግጭት መንስኤና የኢትዮጵያዊነት ስሜት ሸርሻሪ አድርጎ የሚኮንኑ ወገኖች በብዛት ይደመጣሉ።እንዲያውም አንዳንዶቹ “የወያኔ ፈንጂ”ብለዉ ይጠሩታል።በእርስዎ እይታ ኢትዮጵያ ከፌዴራል ስርዓት ውጭ ሌላ ዕድል ነበራት ወይ?
አቶ ሌንጮ ፡ -እኔ የንጉሡንም የደርግንም ስርዓት ጠንቅቄ አውቃለሁ።እነዚህ ስርዓቶች ገፊ ስለ ነበሩ እንዳሉ ለማስወገድ ከእኔ ጭምር ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች በሁሉም አቅጣጫ በተለይ ደግሞ ተማሪዎች እልህ አስጨራሽ ትግል አድርገዋል።አንዱ መታረም ያለበት ስህተት የፌዴራል ስርዓት የህወሓት እጅ ስራ ወይ በጎ ስጦታ አለመሆኑ ነው። ከዚህ ይልቅ የአገሪቱ ህዝቦች የዘመናት ትግል ገፍቶ ያመጣው ስርዓት መሆኑ መታወቅ አለበት።ሰለዚህ ከፌዴራል ስርዓት ጋር ተያይዘው ህወሓትን ማመስገን ወይም መኮነን ፍጹም ስህተት ነው።ባይሆን እንኳ የትግራይ ህዝብ እንደሌሎቹ ወንድም ህዝቦች በስርዓቶቹ ደስተኛ ሰላልነበረ ወደ ትግል መግባቱ የማይካድ ሀቅ መሆኑ መታወቅ አለበት።
ከፌዴራል ውጭ ሌላ አማራጭ አለ የሚለው ሀሳብም ከምን እንደሚነሳ አይገባኝም። በአገራችን ምን ያልተሞከረ ስርዓት አለ? የንጉሱ አሀዳዊ ስርዓት ተሞክሯል፤ ውጤታማ አልነበረም።ብሶት ያንገሸገሻቸው የአገሪቱ ተማሪዎች፣አርሶ አደሮችና ሰርቶ አደሮች ስርዓቱን ለመገርሰስ በዓይነቱ ልዩ የሆነው አመጽ አቀጣጠሉ።ከእነሱ እኔም አንዱ ነኝ።ከአመጹ ተከትሎ አምባገነናዊ የደርግ ስርዓት ወደ ስልጣን መጣ።ደርግ በመጀመሪያዎቹ አካባቢ ዴሞክራሲያዊ በመምሰሉ የተቀጣጠለውን ረመጥ ለማርገብ ችሎ ነበር፣ከህዝቡም ከፍተኛ ተቀባይነትና አመኔታ ተጎናጽፎ ነበር።
ብዙም ሳይቆይ የዴሞክራሲን ጭላንጭል በማጥፋት ወደ ፍጹም አምባገነንነት ተቀየረ።ህዝቡም እንደገና ወደ ትገል ተመለሰ።ይህ ሁሉ ትግል የዴሞክራሲን፣የልማትንና የፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ፍለጋ ነበር።
አዲስ ዘመን፡ በተለይ ብሔር መሰረት ያደረገው ብቸኛው የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝምን አጥብቀው የሚቃወሙ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ስርዓቱን ተጠቅሞ ለመገንጠል የሚጥሩ ወገኖች አሉ።እንዴት ሆኖ አገሪቱን ማስቀጠል ይቻላል?
አቶ ሌንጮ፡ ሁለቱም ዋልታ ረገጥ አደገኛ አካሄድ ናቸው ። የአገሪቱ ብሔሮች ቀለም ያልታተመባት ኢትዮጵያን ማስቀጠል ተሞክሮ ያልተሳካ ጉዳይ ነው።እኔም ወደ ትግል ሜዳ የገባሁት በነበረች ኢትዮጵያ ውስጥ ራሴን በማጣቴ ምክንያት ነው እንጂ ትግል ሱስ ሆኖብኝ አይደለም፣ ሌላውም እንደዛው ነው።ታዲያ ስርዓቱ የሚኮነንበት ምክንያት አይታየኝም ።በእርግጥ የሚስማማን ጉዳይ የተለየ የፌዴራል ስርዓት ተግባራዊ ከተደረገ የተለየ ፖሊቲካ ያስፈልግ በመሰረቱ የዓለም ነባራዊ ሁኔታም ስንመለከት አሁን ካሉበት የአስተዳደር ስርዓት ወደኋላ ያሉት የሉም፣ እናም ወደኋላ መመለስ አንችልም።
በሌላ በኩል ደግሞ ከኢትዮጵያ አፈንግጦ መውጣት የሚፈልጉ ኃይሎች ለአገርም ሆነ ለህዝባቸው እንደማይጠቅሙ ማወቅ ያስፈልጋል።ዓለም አንድ መንደር ለመሆን እየሰራችበት ባለችበት በአሁኑ ሰዓት የጎጠኝነት አስተሳሰብ የትም አያደርስም።ኦሮሞውን፣ አማራውን፣ትግሬውን፣ ጉራጌውንና የሌሎች ቀለም ያላት ኢትዮጵያን እብድ ካልሆነ በስተቀር የሚጠላ የለም።ስለዚህ ሁለቱንም ጫፎች ለማስታረቅ አሁን ያለውን የፌዴራል ስርዓት ለሁሉም በሚመች መልኩ በውይይት ማበጀት ትልቁ የቤት ሥራ አድርጎ መስራት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡ በተደረገው የህዝቦች የማንነት ትግል ዴሞክራሲ አሁን እጃችን ገብቷል።ነገር ግን ግጭቶች፣አለመግባባቶችና የዘመናት ጥያቄዎች አሁንም አልተቋጩም።በእርስዎ አመለካከት አገራችን ለምንስ የሰላም ረሃብተኛ ሆነች? የዓለም ተሞክሮስ ምን ያሳያል?
አቶ ሌንጮ፡ በዴሞክራሲ ውስጥ ያሉ ጥያቄዎች እንዲያው በአንድ ጀምበር የሚቋጩ ሳይሆን ጊዜ የሚጠይቁ ናቸው።በተለይ ብዝሃነትን በአግባቡ በማስተናገድ ጥያቄዎችን ለመመለስ ዴሞክራሲን ማሰለጥ ይቅር በአገራችን በዴሞክራሲ የተሻለ ተሞክሮ ካላቸው አገሮችም ዘንድ ትልቅ ፈተና ነው። ለምሳሌ እንግሊዝ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረች አገር ናት፤ የዴሞክራሲ ተሞክሮዋም የዳበረ ነው።ነገር ግን ዛሬም የስኮትላንድ፣የዌልስና የምዕራብ አየርላንድ ጥያቄ ይነሳል።ይህንን አጣጥመው የተሻለ ፌዴራል ስርዓት ለመፍጠር እየሰሩ ይገኛሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ የአንድ ብሔር የመንግሥት ስርዓት በአውሮፓ ለማስፋፋት ከፍተኛ ጥረት ስታደርግ የነበረችው ፈረንሳይ ናት።ነገር ግን ዛሬ የአንድ ብሔር ሀሳብ ስላልተካ በፈረንሳይ ኮርሲካ ፌዴራል ስርዓትን ተቀላቅላለች። ያም ሆኖ ግን እዚያም ጥያቄዎች አሉ። በተመሳሳይ መልኩ ጎረቤታችን ሱማሊያን ብንወስድ አንድ ብሔር፣ አንድ ሀይማኖትና አንድ ባህል በመኖራቸው ከግጭቶች፣ከአለመግባባቶችና ሌሎች ማህበራዊና ፖሊቲካዊ ቀውሶች ሊተርፉት አልቻሉም።
በአገራችንም የሚስተዋሉ ችግሮች በለውጡ ምክንያት ተገፍተው የወጡና ህዝቡ ከአፈና ስርዓት ከመላቀቁ ጋር የተያያዙ መሆናቸው መገንዘብ ያስፈልጋል።አንዳንድ ብሔሮች ያገኙት አንጻራዊ መብት ልንቀማ እንችላለን ብለው ጥርጣሬ ውስጥ በመሆን ሲወራጩ ግጭቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ። ችግሮቹንም እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ወደ መልካም መለወጥ እንጂ የዓለም ክስተት እንዳልሆነ አድርጎ መነታረክ ተገቢ አይመስለኝም።የሚነሱ ጥያቄዎችም ከኋላቀርነት የሚመነጭ ሳይሆን የዓለም ተሞክሮ ውጤትም ጭምር ናቸው ።
አዲስ ዘመን፡ የኢትዮጵያ ህዝብ በአመዛኙ አንድነቱን ይፈልጋል።የቀደሙት አባቶችም ቢሆን ለአገሪቱ አንድነት ብዙ ለፍተዋል ግን ደግሞ ሲወገዙ እንሰማለን።አሁን አንድነት የአክራሪ ብሔርተኞች መፈንጫ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ።እርስዎስ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ ሌንጮ፡ እኔ ለኢትዮጵያ አንድነት ሲሉ ላለፉት ሁሉ ክብር አለኝ።ሆኖም ግን የነበረው በጉልበት አንድ ለማድረግ የተሞከረው ነገር ስህተት መሆኑን አልሸሽግም። በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነት ቢሆን ኖሮ የት በደረስን ነበር።ብሔርተኝነትም ቢሆን የሚያቆጠቁጠው በአንድነት ውስጥ ኮታና ቦታ ሲጠፋ ነው።ሁሉን በእኩል የሚያይ ህገ መንግሥትና ሁሉንም የምትመስል ኢትዮጵያ ቢኖረን እርግጠኛ ነኝ የብሔተርኝነት አባዜ ያከትማል።
በተቃራኒው ከሆነ ግን ለወደፊት ወደለየለት ቀውስ ሊወስደን ይችላል።ለእኔ ኦሮሞነትህን ይዤ ወደ ኢትዮጵያዊነት እንድገባ ከተፈቀደልኝ ያለምንም ማቅማማት እቀበላለሁ።ነገር ግን ኦሮሞነቴን አውልቄ መግባት አልፈቅድም።እንዲሁም አክራሪ ብሔርተኛ መሆን አደጋ ስላለው መሆን አልፈልግም።በኢትዮጵያ ስም ማንነትን ከሌላ በተለየ መልኩ ማጎላትም ራሱ አክራሪ ብሔርተኝነት ስለሆነ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።በአጠቃላይ ማንነትን ይዘው ኢትዮጵያን መቀላቀል ለአገሪቱ ጥቅም እንጂ ቅንጣት ጉዳት የለውም።
አዲስ ዘመን፡ ሲታገሉለት የነበረው የአገሪቱ በተለይ ደግሞ የኦሮሞ ራስን በራስ የማስተዳደርና ሌሎች የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ስለ ተመለሰ ነው ከፖለቲካ ለመራቅ የወሰኑት?
አቶ ሌንጮ፡ ከፖለቲካው የራቅሁት የኦሮሞ ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ስለተመለስ ሳይሆን በዕድሜ ምክንያት ነው።ዕድሜዬ 75 ዓመት ሲሞላ ራሴን ከፖሊቲካ አመራርነት አገለልኩ።ግን መናገር የምፈልገው ነገር አለኝ።በዚህ አገር የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እጅግ ውስብስብና ፈታኝ ነው።ምክንያቱም የአገራችን ፖለቲካ በዴሞክራሲ ተቋማት ውስንነት የታጠረ፣ በባህላዊ ችግሮች የተበተበና በታሪካዊ ችግሮችም የታነቀ ነው።
ይህ ደግሞ ስር ከስር እልባት ካላገኙ አገራችን በምንም ተዓምር ወደ ዴሞክራሲ ስርዓት ልትሸጋገር አትችልም።ከሁሉም በላይ ደግሞ ዴሞክራት ባልሆኑ ሰዎች ዴሞክራሲን ማሰብ ራሱ ህልምና ቅዥት ነው። በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ዴሞክራቲክ ያልሆኑ ፖሊቲካ ፓርቲዎች ስለዴሞክራሲ ሲሰብኩ ታየዋለህ። ዴሞክራሲ በስብከት ሳይሆን በስራ ሰለሚመጣ ተግተው መስራትን ይጠይቃል።
አዲስ ዘመን፡ አቶ ሌንጮ ስለ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ጠንቅቀው እንደሚያውቁ ይነገራል።ማወቅ ብቻ ሳይሆን በህገ መንግሥቱ ረቂቅ ቻርተር ላይ ተሳትፈው እንደነበር ይነሳል።እስቲ ስለጉዳዩ ማብራሪያ ይስጡን፤
አቶ ሌንጮ፡ ሌንጮ በህገ መንግሥቱ አዘገጃጀት ላይ ድርሻ ነበረው የሚለው ጉዳይ ስህተት ነው፤ አልተሳተፍኩም።
አዲስ ዘመን፡ ከለውጡ ጋር ተያይዘው በአገራችን በተለይ በፖለቲካና በኢኮኖሚ ረገድ የተመዘገቡት ለውጦች እንዴት ይገለጻሉ? በዶክተር አብይ የሚመራ መንግሥትስ?
አቶ ሌንጮ፡ የአገራችን ፖለቲካ እጅግ ውስብስብ በመሆኑ አንዳንዴ ለውጥን ማስተናገድና መቀበል ራሱ አስቸጋሪ የሚሆን ይመስለኛል።ዳሩ ግን በሁለት ዓመት ወይም ከዚያ በላይ ወዲህ በአገራችን በተለይ በፖለቲካ ረገድ የተመዘገበው ለውጥ ይቅር እኔ ድፍን ዓለም የመሰከረ ጉዳይ ነው።በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ በእስር ቤት ተወርውረው ሲማቅቁ የነበሩ በርካታ ፖሊቲከኞች ከእስር ተፈትተዋል፣ እንደ ጠላት በአሸባሪነት ተፈርጀው ወደ ውጭ አገር የተሰደዱ ተፎካካሪ የፖሊቲካ ፓርቲዎች ወደ አገር ቤት ተመልሰዋል።እንዲሁም የሚዲያና የመናገር ነጻነት አዝማሚያም የታየበት ነበር።
በእድሜዬ ከንጉሡ ጀምሮ ዉስን የኢትዮጵያ መሪዎችን አይቻለሁ። ነገር ግን በእድሜ ታናሽ ግን ደግሞ እጅግ በሳል የሆነ እንደ ዶክተር አብይ ያለው መሪ አይቼ አላውቅም።ይሄ ማለት ዶክተር አብይ ፍጹም ነው ማለት ሳይሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ ካከናወናቸው ጉዳዮች አንጻር ምናልባት በዚህ ፍጥነት በርካታ ድሎችን ያስመዘገበ መሪ አልነበረም ማለቴ ነው።ያም ሆኖ ግን አማካሪዎቹ አንዳንዴ አያሳስቱም ማለት እንዳልሆነ መሰመር እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የሁሉም ማለትም የመንግሥት፣የህዝብና የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ይጠይቃል።ነገር ግን አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በአገራችን ብቁ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አፍርተናል ማለት ይቻላል?
አቶ ሌንጮ፡ ቀደም ሲል እንደ ገለጽኩት የአገራችን ህልውና ለማስቀጠል የዴሞክራሲ ስርዓት መከተል ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው።አሁንም እንደሚታየው ሁሉም በየቦታው የመብት ጥያቄ እያነሳ ይገኛል።ይህ አንዱ የለውጡ መገለጫ ነው።ይህ የመብት ጥያቄ በህግ አግባብ ምላሽ የሚያገኘው በዴሞክራሲ ብቻ ነው።በጉልበት ለማፈን ከተሞከረ ግን እንደ ሌሎቹ አገራት አገራችንም የመበታተን አደጋ ሊያጋጥማት ይችላል።
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በተመለከተ በእኔ እይታ በአገራችን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተፈጥረዋል ለማለት እቸገራለሁ። ለመፍጠርም ጊዜ የሚወስድ ይመስለኛል።ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ በተለይ ዴሞክራሲ ስርዓት የምትተዳደር አገር ውስጥ፣ መብቱና ግዴታውን ጠንቅቆ የሚያውቅ ከሁሉም በላይ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ማለት ነው።በእኛ አገር ግን ብዙውን ጊዜ ከመብት ጋር እንጂ ከግዴታ ጋር የሚነሳው ጥያቄ እጅግ ዉስን ነዉ።
አዲስ ዘመን፡ የተሳካ የፌዴራል ስርዓት በመርጋት የአገራችን ህልውና ለማስቀጠል ከማን ምን ይጠበቃል?
አቶ ሌንጮ፡ መልሱ ቀላል ነው።በመሰረታዊ ልዩነቶቻችን ሁሉም በጋራ ዴሞክራሲያዊ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል።በተጨማሪም ህዝብ ምን ዓይነት ኢትዮጵያን እንደሚፈልግ በውይይት ማዳበር የግድ ይላል።ውይይቱ በፖለቲካ ስርዓት ሳይሆን ምን ዓይነት የኢኮኖሚ ስርዓት እንደሚያስፈልግም ለውይይት ማቅረብ ጠቃሚ ይሆናል።ከሁሉም በላይ ደግሞ ለእርስ በእርሳችን ግንኙነትም እውቅና መስጠት ያስፈልጋል።ፖለቲከኞቻችንም ለስልጣናቸው ሳይሆን ሰላምና ልማት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለማረጋገጥ ተግተው መስራት ካልቻሉ ለሌላው ዕድል የመስጠት ባህል ማዳበር አለባቸው።አንድ ሳልጠቅስ የማላልፈው ነገር ባለፉት 27 ዓመታት በዋናነት ህወሓት በሰራው ስራ አገራችን አሁን ላይ በሁለት አጣብቂኝ ጉዳዮች መካከል ተወጥራለች።እነርሱም ፌዴራሊዝም ወይም መበተን።ይሄን ደግሞ አስቀድሜ በመጽሀፍ ጽፌዋለሁ ።
አዲስ ዘመን ፡ ቀሪ ዕድሜዎትን በተለይ አገሪቱን ከማረጋጋት አኳያ ምን ለመስራት አሰቡ?
አቶ ሌንጮ፡ በብሔር ብሔረሰቦች መካከል ፍቅር፣ሰላምና አንድነት እንዲመጣ እንደ ሽማግሌ የማስታረቅ ስራን መስራት እፈልጋለሁ ።ወጣት ፖለቲከኞች እመክራለሁ፣ ሲያጠፉም እንደ አባት እቆጣለሁ ።ምንም እንኳ ቤተሰቦቼ ውጭ አገር ቢኖሩም እኔ ግን ከዚህ በኋላ ወደ እዚያ ለመመለስ ፈጽሞ አላስብም።ባለችኝ ቀሪ ዕድሜዬ አገሬን እያገለገልኩ ህይወቴ እንድታልፍ እፈልጋለሁ።ወደ አገር የተመለስኩት ለዚህ ዓላማ ነው።
አዲስ ዘመን፡ በነበረን ቆይታ ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ሌንጮ፡ እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን የካቲተር 04/2013