አንድ በሬ ስቦ፣ አንድ ሰው አስቦ፤ ድር ቢያብር፣ አንበሳ ያስር፤ ወዘተ የሚሉ የሃገራችን አባባሎች ትብብር ያለውን ፋይዳ አጉልተው የሚያሳዩ እሴቶቻችን ናቸው። ልክ እንደነዚህ ምሳሌያዊ አነጋገሮች ሁሉ መግባባትና መተባበር ከሌለ ሃገርን ወደፊት ማስኬድ ፈጽሞ አይቻልም።
በብልጽግና ማማ ላይ የደረሱ አገራት አሁን ላሉበት የእድገት ደረጃ የደረሱት አንድም እያንዳዱ ዜጋቸው በርትቶ በመስራቱ፣ በሌላም በኩል እጅ ለእጅ ተያይዘው በመስራታቸውና የመረዳዳትና የመደጋገፍን ስልት ተግባራዊ በማድረጋቸው እንደሆነ በርካታ ማሳያዎች አሉ። ለምሳሌ በአውሮፓ እና በአሜሪካ ትላልቅ ኩባያዎችና ድርጅቶች ከመሪነት ቁንጮ ላይ መድረስ የቻሉት አክሲዮን ገበያን መነሻ በማድረግና በዚህም የተቻላቸውን ጥሪት በማሰባሰብ እንዲሁም በመተማመንና በትብብር በመስራታቸው ነው።
መረዳዳት፣ መተባበርና በጋራ መስራት የተሻለ ስኬት ላይ ለመድረስ ከፍ ያለ ጠቀሜታ አለው። አንድ ሰው ብቻውን ከሚሰራው ሥራ ይልቅ የጋራ ራዕይ የሰነቁ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች የሚሰሩት ሥራ የበለጠ ስኬታማ ያደርጋቸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተጽፎ ለንባብ የበቃው የመደመር መፅሃፍም ይህንን ጉዳይ በአጽንኦት ያነሳዋል። የመደመር ፍልስፍና እንደሚለው ኢኮኖሚን ለማሳደግ ወረትን በማሰባሰብ የተወዳዳሪነት አቅምን ማሳደግ አስፈላጊ ነው። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በተበጣጠሰ ሁኔታ መስራት ግን ከእጅ ወደአፍ ከሆነ ኑሮ ሊያላቅቀን አይችልም።
ይህንን ታሳቢ በማድረግ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አነሳሽነት የተጀመረውና ውጤት ያመጣው የገበታ ለሸገር ፕሮግራምም የዚህ ትልቅ ማሳያ ነው። ከዓመት በፊት በተካሄደው በዚህ ገበታ ለሸገር ፕሮግራም በርካታ የሃገር ውስጥና የውጭ ሃገር ባለሃብቶችና በጎ ፈቃደኛ ሃገር ወዳዶች ተሳትፈው ስማቸውን ተክለዋል፤ በሃገራቸው ልማት ላይም የራሳቸውን አርማ አኑረዋል። እነሆ የሸገር ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለስኬት በቅተው ሲያዩ በወቅቱ በገበታ ለሸገር መርሐግብር ላይ የተሳተፉ ሁሉ አንገታቸውን ቀና አድርገው እንደሚሄዱ ጥርጥር የለውም። አሁን ደግሞ መልካም ዕድል ሆኖ የገበታ ለሃገር መርሐግብር ከፍ ባለ ሃገራዊ ጉዳይ መጥቷል።
ገበታ ለሃገር ፕሮጀክት በተለይ በሃገሪቱ ውስጥ ለዘመናት የተፈጥሮ ገፅታቸውን ብቻ ይዘው ተደብቀው የኖሩትን የተፈጥሮ ሃብቶች ለቱሪስት መስህብነት ለማብቃትና ሃብቶቹም ለሃገራቸው ህዝብ የልማት ምንጭ ይሆኑ ዘንድ እውን ለማድረግ ታስቦ የታቀደ ፕሮጀክት ነው። በዚህ ፕሮጀክትም የወንጪ፣ የኮይሻና የጎርጎራ የተፈጥሮ መስህቦች ለእጩነት ቀርበው ቀጣዮቹ የልማት ማዕከላት ሆነው ተመርጠዋል። በዚህም ገበታ ለሃገር ፕሮጀክት ተነድፎ አቅሙ፣ ቁርጠኝነቱና ፍላጎቱ ላላቸው ባለሃብቶች የገበታ ለሃገር ጥሪ ተላልፏል። በዚህም እስካሁን ድረስ ከሦስት ቢሊየን ብር በላይ ገንዘብ ቃል የተገባ ሲሆን ከዚህ ውስጥም ሁለት ሦስተኛው ገቢ ተደርጓል።
ይህ ፕሮጀክት ሃገራችን ወደ ብልጽግና ለምታደርገው ጉዞ ትልቅ የስኬት መንገድ ተደርጎ ይወሰዳል። ሃገር የሚያድገው በዜጎች ርብርብ ነውና በዚህ መርሐግብር ላይ በመሳተፍ እያንዳንዱ ባለሃብትና አቅሙ የፈቀደው ሁሉ በመረባረብ ለሃገሩ ልማት የበኩሉን ድርሻ ማበርከት ይጠበቅበታል።
በሃገራችን “ገበታ” ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ማህበራዊ እሴት ነው። ገበታ ክብር ነው። አባቶች እንደሚሉት ገበታ ከቀረበ በኋላ ትልቅ እንግዳ እንኳ ቢመጣ ባሉበት ሆነው ኖር ከማለት ውጭ ከገበታ ላይ መነሳት ነውር እንደሆነ እነዚሁ አባቶች ደጋግመው አስተምረውናል። ገበታ ከፍ ሳ ይል መነሳትም ነውር ነው።
ከዚህም በላይ ገበታ በተለይ ትልቅ ሰዎች ተሰባስበው ቁጭ ብለው የሚመገቡበት የአንድነት ተምሳሌት ነው። ገበታ የውይይትና የመግባባት ምልክትም ተደርጎ ይወሰዳል። በዚህና መሰል ባህላዊ እሴቶቻችን የተመሰለው ገበታ እነሆ ለሃገር ሃብት ሆኖ ቀርቦ ታላላቅ እንግዶች እየታደሙበት ይገኛሉ። በዚህ ገበታ ላይ መታደም አንድም ክብር ነው፤ አንድም ለሃገር ተገቢውን ክብር መስጠት ነው። ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ሃገራችንን የምናሳድግበትና ወደብልጽግና ለሚደረገው ጉዞ የበኩላችንን አስተዋፅኦ የምናበረክትበት ትልቅ ሃገራዊ እሴት ነው።
ገበታ መሰባሰቢያና ሃገራዊ ጉዳዮቻችንን ወደአንድ ማዕከል አምጥተን የምናጋራበት መድረክ ነው። በዚህ መድረክ መሳተፍ ደግሞ ሀገራዊ ክብሩ ከፍ ያለ ነው። እነዚህ ሦስት የሀገራችን ሃብቶች ዛሬ ከኪሳችን ጥቂት ጥሪት ቢጠይቁም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ራሳቸው ኪሳችንን የሚሞሉ ሃብቶቻችን ናቸውና ዛሬ ተንከባክበን ልናሳድጋቸው ይገባል። ዛሬ የተንከባከብነው ሥራ ነገ ብድሩ ከፍ ይላልና በገበታ ለሃገር ፕሮጀክት ላይ ያለንን ተሳትፎ እናሳድግ!
አዲስ ዘመን የካቲት 4/2013 ዓ.ም